“ተመስጋኙ” መምህርና ሰዓሊ

Wednesday, 28 October 2015 13:25

 

ሰኞ ጥቅምት 8 ቀን 2008 ዓ.ም የሰዓሊና መምህር ወርቁ ማሞን 81ኛ ዓመት የልደት በዓልና 50ኛ ዓመት የጥበብ ጉዞ የሚያስታውስ ደማቅ ዝግጅት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በድምቀት ተካሂዷል። ይህንን የምስጋና ፕሮግራም ያዘጋጁት ደግሞ የሰዓሊያን ማህበርና አቢሲኒያ የጥበብ ትምህርት ቤት ሲሆኑ፤ በዝግጅቱም ላይ የጋሽ ወርቁ ማሞ ተማሪዎች፣ የሙያ አጋሮች አድናቂዎችና ወዳጆች ተሳታፊዎች ነበሩ። ይህንኑ ፕሮግራም አስታከን የሰዓሊና መምህሩን የ50 ዓመት የጥበብ ጉዞ መለስ ብለን ለመቃኘት በሚል፤ በአሁኑ ወቅት በሚያስተምሩበት አቢሲኒያ አርት ስኪል በመገኘት የሚከተለውን አዘጋጅተናል።

በፕሮግራሙ መዘጋጀትና ያን ያህል ሰው ተገኝቶ ለእርሳቸው ያለውን ፍቅርና አድናቆት መግለፅ ለልባቸው ሃሴትና ኃላፊነት እንደሰጣቸው የሚናገሩት ሰዓሊና መምህር ጋሽ ወርቁ ማሞ፤ በድንገተኛ አደጋ ያጋጠማቸው አካል ጉዳትና እርጅና ሳይበግራቸው አሁንም ድረስ ከተማሪዎቸው ጋር ዕውቀትን እየተጋሩ ነበር ያገኘናቸው።

የማህበረሰባችን የኪነ-ጥበብ በተለይም የሥነ-ስዕል ዕይታ ደካማ በሆነበት መንገድ ላይ ሃምሳ ዓመታትን ራስን በጽናት አቁሞ ቤተሰብ እያስተዳደሩ ህይወትን መምራት ፈተና አይሆንም ወይ? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ሰዓሊና መምህሩ ሲመልሱ፤ “ለሁሉም ባይሆን መኖር የቻሉ ሰዎች (ሰዓሊያን) አሉ። በርግጥ አሁንም ድረስ ብዙ መሰናክሎች አሉ፤ በኃይለ ስላሴ ዘመን የስዕል ትምህርት ቤት በአቶ አለፈለገ ሰላም አማካኝነት ሲመሠረት ጥበብ እንዲያድግ ነበር። አሁን ውጪ ሀገር ድረስ ሄደው ስዕልን ተምረው ጥሩ የሚሰሩ ልጆች አሉ። ነገር ግን ኑሮን አሸንፈው ቤተሰብ መስርተው ተደላድለው መኖር የቻሉ ሰዎች በጣም ጥቂቶች ናቸው” ይላሉ።

ስዕልን ለመስራት የማሳያ ቦታ፣ የስነ-ስዕል ትምህርት አለመበራከት፣ የገቢ ዝቅተኝነት ሁሉ ተደራራቢ ተግዳሮቶች እንደሆኑ ሰዓሊና መምህሩ ይጠቅሳሉ። በ1950ዎቹ መጀመሪያ በአለፈለገ ሰላም በተመሠረተው የስዕል ትምህርት ቤት በተከታታይ የክረምት ተማሪ በመሆን ወደሙያው መግባታቸውን የሚያስታውሱት የ81 ዓመቱ አንጋፋ ሰዓሊና መምህር ጋሽ ወርቁ ማሞ፤ በዚህም በትምህርታቸው (በስዕል ችሎታቸው) ባሳዩት የላቀ ጥበብ በቀድሞዋ ራሽያ (የአሁኗ ሩሲያ) የትምህርት ስልጠናን ካገኙ ተማሪዎች መካከል በስዕል ከቀዳሚዎቹ አንዱ ናቸው።

በራሽያ በኪነ-ህንጻ አካዳሚነቱ “አንቱ” የተባለና ከ260 ዓመታት በላይ እድሜ እንዳለው በሚነገርለት “ሬፒን አርት አካዳሚ” አስር ዓመታትን ቆይተው ስዕልን ስለመማራቸው የሚናገሩት ጋሽ ወርቁ፤ “ይህን ዕድል ያገኘሁት በአለ የጥበብ ትምህርት ቤት ለመመረቂያ የሰራሁትን “አድዋ” የተሰኘ ስራዬን ተመልክተው ንጉሱ አድናቆታቸውን በመግለፃቸው ነው” ይላሉ። ይህም ስራ 3 ሜትር በ6 ሜትር ስፋትና ርዝመት ያለው ስለመሆኑም ይጠቀሳል። በራሽያ ቆይታቸው የመጀመሪያው ዓመት ለቋንቋ የተሰጠ ቢሆንም፤ ጋሽ ወርቁና ጓደኞቻቸው ግን በስድስት ወራት ውስጥ በሩሲያ ቋንቋ መግባባት ጀምረው እንደነበር ያስታውሳሉ።

በብርዳማዋ ሩሲያ የነበራቸው የትምህርት ቆይታ በተለይም በመጀመሪያዎቹ ዓመታት አካባቢ ቀላል እንዳልነበር የሚያስታውሱት ሰዓሊና መምህሩ፤ በተለይም በእጃቸው በኩል አጥንታቸው ድረስ ዘልቆ የሚሰማቸው ጠንካራ ብርድ የሚፈጥርባቸው መጠዝጠዝ ጥርሳቸውን ነክሰው ያሳለፉት ፈታኝ ጊዜ እንደነበር ይናገራሉ። “በትምህርቴ የቱንም ያህል ብርቱ ብሆን የራሽያን ቅዝቃዜ ባሰብኩ ቁጥር ከምኔው በጋ በመጣልኝ እያልኩ አስብ ነበር” ሲሉ የወቅቱን ህመምና ስቃይ ይገልፁታል።

የመድረክ ቅንብርና የቀለም ቅብን ምርጫቸው አድርገው ተምረዋል። በስተመጨረሻም በጥሩ ውጤት የተመረቁ ሲሆን፤ በመምህራኖቻቸውም ሆነ በክፍል ጓደኞቻቸው በኩል ምስጉን ተማሪም እንደነበሩ ያስታውሳሉ። ከዚህም ባሻገር ሰኞ ምሽት በብሔራዊ ቴአትር በነበረው ፕሮግራም ላይ ጋሽ ወርቁ ማሞ እንደመምህር መልካም አባትና ያወቁትን ለማሳወቅ ደከመኝ ሰለቸኝን የማያውቁ እንደሆኑ በተማሪዎቻቸው (አሁን አንጋፋ መምህራኖች ናቸው) ሲመሰክርላቸውም ሰምተናል።

ከአስር ዓመታት የትምህርት ቆይታ በኋላ ከራሺያ ወደኢትዮጵያ የተመለሱት ጋሽ ወርቁ፤ ለ22 ዓመታት የሥነ-ሥበባት ትምህርት ቤት ውስጥ አገልግለዋል። ይህም ሆኖ “በአርት ስኩል” ውስጥ የነበራቸው የመምህርነት ሚና በስተመጨረሻ ግን ጡረታ ሲወጡ ሊያስመርቋቸው 3 ወራት የቀራቸውን ተማሪዎች ትተው መውጣታቸው አሁን ድረስ ይቆጨኛል ይላሉ።

እዚህ ደረጃ ከመድረሳቸው ባለፈ በብርቱ የሚያደንቋቸው ኢትዮጵያውያን የስነ-ስዕል ባለሙያዎችን በተመለከተ ሲናገሩ፤ “የመጀመሪያው ሰው አለፈለገ ሰላም ናቸው። እርሳቸው ስዕል እንዲያድግ አስተዋፅኦቸው ከፍተኛ የነበረ ባለሙያ ናቸው። በመቀጠል ደግሞ ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌና ገ/ክርስቶስ ደስታ በሚያሳዩዋቸው ስራዎች ብዙ የተማርኩባቸው ጥበበኞች ናቸው” ሲሉ ይገልጿቸዋል።

“ሁሉም ሰው ጥሩ ስዕል ሊሰራ ይችላል። ነገር ግን ጥበብ መስራቱ ነው ከባዱ” የሚሉት ሰዓሊና መምህሩ ወርቁ ማሞ፤ ስዕል የተሻለ ዕይታን እንደሚፈልግም አፅንኦት ሰጥተው ይናገራሉ።

ሃምሳ ዓመታትን በስዕል ሙያ ውስጥ ያሳለፉት አንጋፋው ሰዓሊና መምህር፤ አሁን ድረስ የሚቆጫቸው ነገር እንዳለ በይፋ ተናግረዋል። በተለይም ለስዕል እድገት አስተዋፅኦቸው ከፍተኛ ነው የሚባልላቸው የሙዚየሞችና የጋለሪዎች አለመበራከት ትልቅ ችግር እንደሆነ ይናገራሉ። በዘመናቸው ይህ ተሻሽሎ አለማየታቸው ይቆጨኛል ባይም ናቸው። በቀጣይ የራሳቸው የስዕል ማሳያ ስፍራ ለመክፈት እንደሚፈልጉ የሚናገሩት ጋሽ ወርቁ፤ የቦታ ጉዳይ ምላሽ ያላገኘ ጥያቄ ሆኖባቸዋል።

ከኢትዮጵያ ወደራሽያ ለትምህርት ከመሄዳቸው በፊት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በጉልህ የሚነሳውን የአድዋ ጦርነት መሠረት ያደረገ “አድዋ” የተሰኘ ስዕል መስራታቸው የሚታወስ ሲሆን፤ የራሽያ ቆይታቸውን አጠናቀው ከመመለሳቸው በፊት ደግሞ የኢትዮ ሶማሌን ጦርነት የሚያስታውስ “እናቶች” የተሰኘ ስዕል ለመመረቂያቸው ስለመስራታቸው ሰምተናል።ለመሆኑ የእነዚህ ጦርነት ጠቀስ ስዕሎች ግጥሞጥሞሽ ምክንያቱ ምን ይሆን ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄ ሰዓሊና መምህሩ ሲመልሱ፤ “አድዋን ለመሳል ያነሳሳኝ ተማሪ እያለን በምናነባቸው የታሪክ መፅሐፍት ውስጥ የሌሎች ሀገራት ታሪክ በምስል (በስዕል) የተደገፈ ሆኖ ሳለ የእኛ ታሪክ ግን በፅሁፍ ብቻ መቅረቡ ያስቆጨኝ ስለነበር ነው። ስለ አድዋ ታሪክ ከቤተሰቦቼ የሰማሁትንና ከታሪክ መጽሐፍት ያነበብኩትን ተንተርሼ በቁጭት የሳልኩት ገላጭ ስራ ነው” ይላሉ። “እናቶች” የተሰኘውን የመመረቂያ ስራቸውን በተመለከተም “ኢትዮጵያ ከሶማሌ” ጋር የነበራትን ጦርነት ተከትሎ ራሽያ ውስጥ ሆነው የሚሰሙትን ዜና ተንተርሰው ወንዶች፣ ልጆች፣ ሌሎች ወደጦርነት ሲዘምቱ እናቶች (ሴቶች) ምን ይመስላሉ? በሚል ሃሳብ መነሻነት የሰሩት ትልቅ ስራቸው ሆኗል።

በርካቶች ስለመምህርና ሰዓሊ ጋሽ ወርቁ ማሞ ሲናገሩ፤ ስዕሎቻቸውን መሸጥ ግድ ካልሆነባቸው በስተቀር አይፈልጉም። ከዚህም ባሻገር አሁንም ድረስ “አልሸጣቸውም” ብለው ያስቀመጧቸው ስራዎች ስለመኖራቸው ይናገራሉ። ለመሆኑ ምክንያታቸው ምን ይሆን? ጋሽ ወርቁ ታሪክ አለው ይላሉ። የእናታቸው ቤት ወንዝ ዳር የተገነባ መሆኑን የሚያስታውሱት ሰዓሊና መምህሩ፤ በአንድ ወቅት አደገኛ ጎርፍ ይመጣና ለበርካታ ጊዜ ሰርተው ያስቀመጧቸውን የስዕል ስራዎችና ፎቶ ካሜራ በጎርፉ መወሰድ ተከትሎ አርክቴክት ተሾመ ደምሴ የተባለ ዘመዳቸው ወንዙን ተከትሎ በየጢሻውና በየጎድጓዳው ሁሉ ስዕሎቻቸውን ሰብስቦ በማምጣት የከፈለውን ዋጋ ታሳቢ በማድረግ፤ እነዚህ ስዕሎች ከወንዝ ከወጡ በኋላ ያፀዳቸውና ወደቀድሞ መልካቸው የመለሳቸው ሰዓሊ ዘሪሁን የትምጌታ መሆኑን እያሰቡ መታሰቢያዎች ስለሆኑ መሸጥ የለባቸውም በሚል እነዚህ ስዕሎች አውደ-ርዕይ ቢቀርቡም የገዢዎችን አቅም ለመፈታተን በከፍተኛ ዋጋ ስለሆነ የሚገዛ አልመጣም፤ ይህም ጥሩ ነገር ነው ይላሉ።

በሌላ በኩል ግን ስዕል መሸጥ የማይፈልጉበትን ዋነኛ ምክንያት ሲያብራሩ፣ “ስዕሎቼን ከመሸጥ የራሴ የማሳያ ስፍራ ኖሮኝ ባሳያቸው ይሻላል ከሚል ሃሳብ ነው” ይላሉ። ጥቂት ሙዚየሞችና ጋላሪዎች ብቻ ባሉበት ከተማ ውስጥ “የራሴን ስራዎች ማሳያ ስፍራ ባገኝ በጣም ደስተኛ ነኝ” ይላሉ። ይህንንም ለማድረግ በቅርቡ የእናታቸውን መኖሪያ ቤት በምቹ አካባቢ የመተካት አጋጣሚውን መንግስት ቢያመቻችላቸው የተሻለ እንደሚሆን የቀረበውን ሃሳብ ተግባራዊ እስከሚሆን እየጠበቀም እንደሆነ ነግረውናል።

የ81 ዓመቱ አንጋፋ ሰዓሊና መምህር ወርቁ ማሞ፤ አሁንም ብርቱ መምህርና ብርቱ ሰዓሊ እንደሆኑ አሉ። አለኝ በሚሉት ትርፍ ጊዜም ቢሆን ምን በማድረግ ይዝናናሉ ላልናቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ “ከድሮም ጀምሮ ተንቀሳቃሸ ፊልም የመስራት ፍላጎቱ አለኝ፤ አሁንም እየሞከርኩ ነው። እርሱን በመስራት እዝናናለሁ። ፎቶ በማንሳትና መፅሐፍትን በማንበብም እንዲሁ እዝናናለሁ። የመፅሐፍ ነገር ግን አሁን-አሁን ዓይኔ ሳይደክም አልቀረም። በህክምና ቀጠሮ ላይ ነኝ ሲስተካከል ማንበቤን እቀጥላለሁ” ይላሉ።

ለአንጋፋው ሰዓሊና መምህር ረጅም ዕድሜንና መልካም ጤንነትን የምንመኝላቸው ሲሆን፤ የተማሪዎቻቸውን ፍሬዎች እየተመለከቱ የሚደሰቱበት ጊዜ እንዲበዛም መልካም ምኞታችን ነው። “ሰዓሊ በርትቶ መስራትን የዕለት ተግባሩ ማድረግ አለበት። አንዳንድ ወጣቶች “ሙዴ” አልመጣም እያሉ የሚያቀርቡት ምክንያት መቅረት አለበት። ወረቀት ላይ ነው ሙዱን መፈለግ” ሲሉ የመጨረሻ ምክራቸውን ለወጣት ሰዓሊያን ያስተላልፋሉ።n  

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
15347 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us