የቀዘቀዘው “የፍቅር ማዕበል

Wednesday, 04 November 2015 13:56

 

  • - የቴአትሩ ርዕስ - “የፍቅር ማዕበል”
  • - ደራሲ - ዣን አኑዊ
  • - ዝግጅትና ውርስ ትርጉም - ማንያዘዋል እንዳሻው
  • - ድራማተርጅ - ሳሙኤል ተስፋዬ
  • - ዝግጅት አስተባባሪ - ሰለሞን ተካ
  • - አልባሳት ዲዛይን - መሠረት ህይወት

 

  • ተዋንያን -ዋስይሁን በላይ፣ ስናፍቅሽ ተስፋዬ፣ ትዕግስት ባዩ፣ መሰረት ህይወት፣ ሱራፌል ተካ፣ ዳንኤል ተገኝ እና ደስታ አስረስ

የድህነት ሽሽትና የወጣትነት ግብዝነት በፍቅር ማዕበል በጉልህ የሚንተገተጉበት ቴአትር ነው “የፍቅር ማዕበል” የተሰኘውና ዘወትር እሁድ በ11፡30 ሰዓት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በመታየት ላይ ያለው ተውኔት።

የሚወዳትን ወጣት ከችግር አርቆ ለማግባትና የተሻለ ህይወትን በሚያልም ሰው የስሜት ከፍና ዝቅ ላይ ተመስርቶ የተሰራው “የፍቅር ማዕበል” ቴአትር፤ “በወጣትነት ደሃ መሆን ህይወትን ጎምዛዛ ያደርጋታል” ይለናል። አንቱ የምንላቸው፣ የምናከብራቸውና አሉን የምንላቸው ሰዎች ያላቸው ገንዘብ ለኛ ችግር ጊዜ ካልደረሰልን፤ እኛ መልሰን ችግር እንሆንባቸዋለን በሚል ግራ በተጋባ የፍቅር ስሜት ውስጥ የሚሽከረከረው ሃሳብ፤ ፍቅርን ተንተርሶ በማዕበል ውስጥ እምነት፣ ፍቅርና ሰብዓዊነት አንዴ ሲበረታ፣ አንዴ ሲረታ እንመለከትበታለን።

“አንተን የመሰለ ሸጋ በገንዘብ ጉዳይ መጨነቅ የለበትም” የምትለው የነጋዴው ሚስት (መሰረተ ህይወት) በፍቅር ሰንሰለት ታስሮ በዕዳ የሚንከራተተውን አብርሃም (ዋስይሁን በላይ) በ25ሺህ ብር ቼክ ልትገዛው ድርድር ትገጥማለች። የዚህችን ሴት አደገኝነት በባሏ አሰግድ (ሱራፌል ተካ) አንደበት “ሰይጣን አቅም ሲያጣ የሚልካት ሴት” እንደሆነች ይነገረናል። ይሁን እንጂ በ25ሺህ ብር ስጦታ ሳቢያ የፍቅሩን እምነት ለመጠበቅ የሚተጋው አብርሃም የኋላ - ኋላ ከማይወጣና ፍቅሩን ከሚያሳጣው የሃጢያትና የወንጀል ማቅ ውስጥ ሲገባ እንመለከትበታለን።

በመጀመሪያው ትዕይንት እንደቴአትር ህጋዊ ፍሰት ሁሉ አዘጋጁ ሁሉንም ገፀ -ባህሪያት ሊያስተዋውቀን ይሞክራል። በመጀመሪያ ሁለቱን ፍቅረኛሞች፤ ቀጥሎ ስግብግቡን ነጋዴ፣ ለጥቆ ደግሞ የነጋዴውን ሚስትና የአፍቃሪውን ወጣት ጓደኛ (ዳንኤል ተገኝ) በአካል እያመጣ እነሆ ብሎናል። ከነዚህ ሁሉ በፊት ግን የቤቱን ባለቤት ወ/ሮ መንበረን (የትዕግስት ባዩ) በፎቶና በስልክ ንግግር እንድናውቅ የተደረገበት ቴክኒክ ይታወሳል።

የነፍሳት ሞት እጅግ ዘግንኖት ሲሰቀጥጠው የምናየው አብርሃም፤ ለፍቅሩ ለምላሜ የመጨረሻ መፍትሄ ሆኖ የሚሰማው የወ/ሮ መንበረ ሞት መሆኑን መስማት “ማዕከሉ ወዴት እንደሚጥለን አናውቅም” በሚል ስነ አመክንዮ ካላለፍነው በቀር የሚዋጥ የገፀ-ባህሪው ሃሳብ አይመስልም። . . . ቁጭት፣ በቀልና ቅጣት በልቡ የሚመላለሰው አብርሃም ፍቅሩ ስትንገላታበት ማየት አልፈለገምና ሀብት ባላቸውና ባሳደጉት ወ/ሮ መንበረ ላይ እጁን ሲያነሳ ያስቀመጠው ምክንያት፤ “የገደልኳት ለገንዘቧ ብዬ ሳይሆን ገንዘቧ የደስታችን ዋጋ ስለሆነ ነው” የሚል ነው።

አዲሱን ትውልድ (ልጁን) ለማኖርና ለማስቀጠል አሮጌውን ማጥፋት የሚዋጥ ባይሆንም፤ ምናልባት ቴአትሩ ትርጉም መሆኑን ማሰብ በራሱ ትንፋሽ እንድንሰበስብ ሳያደርገን አይቀርም።

“ድህነት ከጠላቶቻችን ጋር ያብራል። እናም ፍቅራችንን አቅም ያሳጣዋል” የሚል እምነቱን ደጋግሞ የሚያስታውሰን አፍቃሪው አብርሃም፤ በአንፃሩ ግን ውሃ የሚያነሳ መልስ ባላትና በታናሹ ሃሳብ ስር ሲወድቅ በስተመጨረሻ እናያለን። ተፈቃሪዋ ሜሮን (ስናፍቅሽ ተስፋዬ) የአብርሃምን የድህነት ፍርሃትና የወንጀል ጉዞ የምትደመድምበት ዐረፍተ ነገር ጥልቅ መልዕክትን ያዘለ ነው። “ከልብህ ብትወደኝ ኖሮ ድህነት አያስፈራህም ነበር” እውነትም በፍቅር ማዕበል ውስጥ የሚጋልብ ሰው እንዴት ድህነት ሊያስፈራው ይችላል? አጥጋቢ ምላሽ ላገኘ ጥያቄ ነው። ያውም ኑሮን አብረው ለመታገል የቆረጠች ሴት አብረው እንዳለች እያወቀ።

በአራት ትዕይንቶች ተከፋፍሎ፣ በአንድ ሰዓት ተኩል ጊዜ ውስጥ በመድረክ ላይ የሚፀናው “የፍቅር ማዕበል” ቴአትር፤ በፍቅር ማዕበል የሚንሳፈፍን ወጣት ሌሎች ሲደርጉት የሚጠላውን ድርጊት ራሱ በባሰ መንገድ ሲያደርገው የሚገጥመውን ምስቅልቅል ስሜትና ፀፀት ያሳየናል።

በቁጭት፣ በእጦት፣ በፍቅርና በወጣትነት ባህር ላይ የተዘረጋችው የፍቅረኛሞቹ ህይወት “በፍቅር ማዕበል” ሳትናጥ ምን እንደምትመስል ማየት፤ ለፍርድም ለትንቢትም አስቸጋሪ እንደሆነ ተመልካችን ይዞ ይጓዛል።

በስተመጨረሻም አንዳንድ ነገሮች

“የፍቅር ማዕበል” ተጣድፏል። በስውር የጋለ ፍቅር፤ በወንጀል ሰንሰለት ሲቀዘቅዝ እናያለን። የእህትና ወንድም ተደርጎ ይታሰብ የነበረው ፍቅር፤ በምን የጊዜ ፍጥነት እንደሆነ ሳይታወቅ ሁለቱ ወጣቶች ይጸንሳሉ። ይህ ነገሩ እንዴት ነው የሚያስብል ፍጥነት ነው።

ሌላው በቴአትር የሚፈልገው የትወና ብቃት ማለትም የአካል የድምፅን የእንቅስቃሴን ስርዓቶች በጉልህን በግልፅ ተመልካች ጋር መድረሳቸው ምንም እንኳን ልምድ ያላቸው ተዋንያኖች ቢሆኑም መልካም እንደሆነ መግለፁ ተገቢ ነው። ነገር ግን ቴአትሩን የሚመለከት ደንበኛ (አዘውትሮ ቴአትሮችን የሚመለከት) ካለ ከዚህ ቀደም ባያቸው ቴአትሮች ውስጥ የነበሩ ገፀ-ባህሪያት በድጋሚ ብቅ ያሉት ሊመስለው ይችላል። ለምሳሌ የስናፍቅሽ ተስፋዬ ትወና በቀጥታ “ደመነፍስ” የተሰኘውን ተውኔት ላይ ያሳየችንን ገፀ-ባህሪይ ያስታውሰናል። በአንጻሩ ደግሞ የዳንኤል ተገኝ ትወና በጨረፍታም ቢሆን “ባቢሎን በሳሎን” የተሰኘ ቴአትሩን ማስታወሱ አይቀርም። ሁለቱ ተዋናዮች በሁለቱ ተውኔቶች ውስጥ ሁለቱን ገፀ-ባህሪያት የደገሟቸው አስመስሎባቸዋል።

በመጨረሻም “የፍቅር ማዕከል” ቴአትር በማንያዘዋል እንዳሻው ተተርጉሞ የተዘጋጀ መሆኑ የሚያስመሰግነው ሲሆን፤ በተለይም ኢትዮጵያዊ ለዛ ሰጥቶ ተመልካቹን ለታሪኩ የቀረበ ሰው ሊያደርግ መሞከሩ ይበል የሚያሰኝ ነው ማለትን እንወዳለን። መልካም የመዝናኛ ሳምንት ይሁንላችሁ!!!n

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
9282 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us