ብዙ የሚጠበቅበት “የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል”

Wednesday, 11 November 2015 13:14

 

ዘንድሮ 10ኛ ዓመቱን በተለያዩ ክንውኖችና የፊልም ፌስቲቫልች እያከበረ ያለው “የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል” በሀገራችን ተጀምረው በጥንካሬ ረጅም ዕድሜን ካስቆጠሩ ፌስቲቫሎች ግንባር ቀደሙ ነው። እነሆ በዚህ ሳምንት ሰኞ ጥቅምት 29 ቀን 2008 ዓ.ም መከፈቻውን በ“ላምብ” (Lamb) ፊልም ያደረገው ፌስቲቫሉ በርካታ ዝግጅቶችን ያቀፈ ስለመሆኑ የፌስቲቫሉ ዳይሬክተር አቶ ይርጋሸዋ ተሾመ ይናገራል።

ከ70 በላይ አለምአቀፍና የሀገር ውስጥ ፊልሞች ለዕይታ በሚበቁበት በዚህ የፊልም ፌስቲቫል ላይ 20 ሀገረኛ ፊቸር ፊልሞችን እንዲሁም 50 የሚሆኑ አጫጭርና ረጃጅም ከተለያዩ አለማት የተመረጡ ፊልሞች ለዕይታ እንደሚበቁ ይጠበቃል። ከጥቅምት 29 እስከ ህዳር 6 ቀን 2008 ዓም ለአንድ ሳምንት የሚቆየው ይህ ፌስቲቫል፤ በኦሮሚያ ባህል ማዕከል አደራሽ፣ በፑሽኪንና በአሊያንስ ኢትዮ- ፍራንሲስ አዳራሾች በተለያዩ ፊልሞችና የውይይት መድረኮች ይከበራል።

በሊንኬጅ አርት ሪሶርስ ሴንተር አዘጋጅነት በሚካሄደው የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል ላይ ለዕይታ ከሚቀርቡ ፊልሞች በተጨማሪ ከአሜሪካ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ከውጪ በመጡ የፊልም ባለሙያዎች የአንድ ቀን ስልጠናና ውይይቶችም እንደሚኖሩ ዳይሬክተሩ ይናገራል። በኮንፈረንሱም ላይ የኢትዮጵያ ፊልምና ባህል በሚል ርዕስ ስር ውይይት የሚደረግ ሲሆን፤ በእስራኤላዊው የፊልም ባለሙያ ዳን ኦልማን የተሰራው ፊልም ለዕይታ ከመብቃቱ በተጨማሪ ለወጣት የፊልም ባለሙያዎች በዝቅተኛ በጀት ፊልም እንዴት ይሰራል በሚል ሃሳብ ላይ የግማሽ ቀን ስልጠና እንደሚሰጥም ተጠቁሟል።

ከዚህም በተጨማሪ ከህንድ ኤምባሲ ጋር በመተባበር የህንድን ፊልሞች በአማርኛ የግርጌ ትርጉም (Subtitle) ለተመልካች በማቅረብ ለውይይት እንዲቀርቡ ይደረጋል ያለው የፌስቲቫሉ ዳይሬክተር፤ የፌስቲቫሉ ተሳታፊ ፊልሞች በሶስቱ አዳራሾች ለዕይታ ሲቀርቡ በ5 ብር እና በነፃ ተብለው የተከፈሉ ሲሆን፤ የሀገር ውስጥ ፊቸር ፊልሞችን በ5 ብር የምናሳየው ፌስቲቫሉ ንግድ ባለመሆኑ ነው የሚለው የፌስቲቫሉ ዳይሬክተር አቶ ይርጋሸዋ ተሾመ፤ ሰፊውን ተመልካች ለመድረስ ሲባል 40 እና 50 ብር ይታዩ የነበሩ ፊልሞችን በ5 ብር ለማሳየት ተዘጋጅተናል ይላል። በአንፃሩ ግን ከተለያዩ አለማት የመጡትን ፊልሞች ተመልካቹ በነፃ እንዲታደም ክፍት ሆኗል ሲል ይጋብዛል።

“ለመሆኑ የኢትዮጵይ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል ለ10ኛ ጊዜ ሲዘጋጅ እየተንከባለሉ የሚከተሉት ተግዳሮቶች ምን ይመስላሉ?” ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ የፌስቲቫሉን ዳይሬክተር ሲመልሱ፤ “በግንባር ቀደምነት ሳይቋረጥ ይህን ያህል ርቀት ብንሄድም በፊልም ባለሙያው፣ በመንግሥት አካላትና በሚዲያው የሚገባውን ያህል ትኩረት አለማግኘቱና የተዛባ ግንዛቤ የታየ መሆኑ ትልቁ ፈተና ነው ይላል። ከዚህም ባሻገር ስንፖሰሮችን አሳምኖ አጋር ማግኘት እና ፌስቲቫሉን የማካሄጃ አዳራሾች አለመመቻቸት የበረቱ ፈተናዎች እንደነበሩ አልሸሸጉም።

በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ ያለፈው ይህ የፊልም ፌስቲቫል 10ኛ ዓመቱን ማስቆጠሩ በራሱ የበለጠ ኃላፊነትና የተቀባይነትን እየጨመረለት ስለመሆኑም ዳይሬክተሩ ይናገራል። እንደመልካም ጎን የሚታይለት ከፌስቲቫሉ አንጻር በርካታ የፊልም ውድድሮች እንዲነሳሱ መሆኑ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሀገራችን ፊልሞች በሙሉ ልብ እንዲወዳደሩ ዕድል መክፈቱንና ታዋቂ የፊልም ባለሙያዎች ለሀገራችን ወጣትና አንጋፋ ባለሙያዎች ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ መሆኑ የተሻለ ስኬት ነው ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል ሲል ዳይሬክተሩ ያስረዳል።

በርካታቶች ዘንድ የኮሪደር ወሬ ተደርጎ የሚነሳው የፊልም አመራረጡ ሂደት ሲሆን ይህንንም በተመለከተ የፌስቲቫሉ ዳይሬክተር በሰጡት ምላሽ፤ “እኛ እንደፊልም ፌስቲቫል አዘጋጅነታችን የተሳትፎ ጥሪ ለሁሉም አቅርበናል። ይህ ጥሪ ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ የፊልም ባለሙያዎች የሚቀርብ ነው። ይህን ጥሪ መሠረት አድርጎ ማንኛውም ፊልም መመዝገብ ይችላል። ነገር ግን የሀገርኛ ፊልሞችን በተመለከተ ሁለት መስፈርቶች አሉን። ተወዳዳሪና ተሳታፊ ልንላቸው እንችላለን። ለምሳሌ በ2007 ዓ.ም የተሰሩ ፊልሞች ለውድድር መቅረብ ይችላሉ። ከዚህ ዓመት በፊት የቆየ ፊልም ከሆነ ግን ለውድድር ሳይሆን ለሰርተፊኬት መሳተፍ ይችላል” ሲሉ ገልጸዋል።

$1·        የፌስቲቫሉ ሽልማቶች

እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል በስተመጨረሻ በተለያዩ ዘርፎች ሽልማቶችን እንደሚያበረክት ዳይሬክተሩ ይናገራል። በዋናነት ከሚጠቀሱት አስር የሽልማት ዘርፎች መካከል ምርጥ ተዋናይና ተዋናይት፣ ምርጥ ረዳት ተዋናይና ተዋናይት ተጠቃሾቹ ሲሆኑ፣ ምርጥ ዳይሬክተር፣ ምርጥ ፊልም ፅሁፍ፣ ምርጥ ፊልምና ምርጥ ሲኒማቶግራፊ፣ እንዲሁም አዳዲስ ተስፋ የተጣለባቸውን ተዋንያን የሚሸልም ዘርፍ እንዳለ ለማወቅ ችለናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ተመልካቹ “የኔ ምርጥ ነው ያለውን ፊልም “የሚመርጥበትና ድምጽ የሚሰጥበት ሁኔታ በአጭር ጽሁፍና በድረ-ገፅ እንዲሁም በሸገር ኤፍ ኤም በኩል የሚጣራ መሆኑንም ነግሮናል። በተለያዩ ዘርፎች ለሽልማት የሚበቁትን ፊልሞች የሚመርጡት ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ከደራሲያን ማህበርና ከፊልም ሙያ ማህበራት የተውጣጡ የዳኞች ስብስብ ስለመኖሩም ዳይሬክተሩ አቶ ይርጋሸዋ ተሾመ ይናገራል።

ከተለያዩ አጋጣሚዎች ሊመለከታቸው ያልቻላቸውን ዓለም አቀፍ ፊልሞች የኢትዮጵያ ተመልካች በጥራት እንዲያገኝ ማስቻሉ በራሱ ትልቅ ነገር ስለመሆኑ የሚናገረው የፌስቲቫሉ ዳይሬክተር፤ ሰው በነፃ ተገኝቶ መታደም እንደሚችል ይጋብዛል። ከዚህም ባሻገር ከፊልም ባለሙያዎች ጋር በቀጥታ ተገናኝቶ የመወያየት ዕድል ይኖራል ይህም ትልቅ መማማሪያ መድረክ ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን ባይ ነው። በአንጻሩ ግን በዓመት ውስጥ የወጡና በሲኒማ ቤት በመታየት ላይ የሚገኙትን 20 ሀገረኛ ፊልም ለመመልከት አምስት ብር እንደሚያስፈልግ የተጠቆመ ሲሆን፤ ፊልሞቹ ሳምንቱን ሙሉ ከጠዋቱ አራት ሰዓት ጀምሮ በተጠቀሱት መመልከቻ ስፍራዎች እስከ ምሽት ለዕይታ እንሚበቁ ይጠበቃል። ከ20ዎቹ ኢትዮጵያዊ ፊልሞች መካከል ለመጥቀስ ያክልም የፍቅር መንገድ፣ ላምባ፣ ፍቅር ተራ፣ እስክትመጪ ልበድ፣ ከዕለታት፣ አዱኛ፣ ብላቴና፣ እንቆጳ፣ አንድጀግና፣ እምነት፣ የገጠርልጅ፣ አለም በቃኝ፣ ሀርየት፣ ዡልየት፣ የፍቅር ቃል፣ የነገን አልወድም ይገኙበታል። “ለመሆኑ ያለፉትን ዓመታት ጨምሮ በኢትዮጵያ ፊልም ፌስቲቫል ላይ እየቀረቡ ያሉ ፊልሞቻችን ለውጣቸው እንዴት ይገመገማል? ስንል በቅርብ የሚከታተሏቸውን የፌስቲቫሉን ዳይሬክተር ጠይቀነው፣ “እውነቱን ለመናገር ኢትዮጵያ ውስጥ ፊልም በብዛት ይመረታል። በቅርቡ ከአፍሪካ ብዙ ፊልሞችን በማምረት ከናይጄሪያ ቀጥለን የምንጠራ ይመስለኛል። ይህ ተስፋ ሰጪ ነገር ነው። ነገር ግን እንደፊልም ባለሙያ ኢትዮጵያዊ ፊልም የሚባለው ነገር በሆሊውድ ተፅዕኖ ስር የወደቀ ይመስለኛል። በትወናና በዳይሬክቲንግ በጣም ጥሩ ለውጥ አለ። ቴክኒካል በሆኑት የኤዲቲንግ፣ ላይቲንግና ሳውንድም በሆኑ አሁን በጣም የተሻለ ጊዜ ላይ ደርሰናል። ነገር ግን ታሪክ ላይ ጥልቀት ያለውና መሳጭ ሀገረኛ ታሪክ መስራት አልተቻለም። ጥቂቶች ብቻ ይሰራሉ፤ እነሱን እናበረታታለን” ሲል የፊልም ፌስቲቫል ዳይሬክተሩ ጉድለትና ሙላቱን አጣምሮ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል ለተመልካቹ የመዝናኛ ለባሙያው የመማማሪያ ሳምንት ሆኖ እንደሚያልፍ በብላች ተስፋ ተጥሎበታል።  

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
11319 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us