“የኢትዮጵያው ኦስካር” ተሸላሚዎች

Wednesday, 18 November 2015 13:48

 

 

ለበርካቶች መልካም የመዝናኛና የመማማሪያ ሳምንትን የፈጠረው “የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል” ከትናንት በስቲያ ሰኞ ሕዳር 6 ቀን 2008 ዓ.ም በደማቅ የሽልማት ፕሮግራም ተጠናቋል። በኦሮሞ ባህል ማዕከል አዳራሽ በተከናወነው የምሽቱ የሽልማት ፕሮግራም ላይ በርካታ እንግዶችና ተሸላሚዎች የታደሙ ሲሆን፤ በ10ኛ የፊልም ፌስቲቫል (አንዳንዶች እንደሚሉት ደግሞ የኢትዮጵያው ኦስካር) በ10 የተለያዩ ዘርፎች የተመረጡ እጩዎች የመጨረሻ አሸናፊዎቻቸው በተመልካች እና አድናቂዎቻቸው ፊት ሽልማታቸውን ተቀብለዋል።

በምሽቱ “ላምባ” ፊልም በአራት ዘርፎች አሸናፊ በመሆን አውራ ሆኗል። ይህ ፊልም በምርጥ መሪ ተዋናይ፣ በምርጥ ፊልም ጽሁፍ፣ በምርጥ ዳይሬክተር እና የዓመቱ ምርጥ ፊልም በሚሉ ዘርፎች ተሸልሟል። በተከታይ የአስሩን ዘርፍ የመጨረሻ ዕጩዎችና ተሸላሚዎች እናስታውሳለን።

·        የዓመቱ ምርጥ ረዳት ተዋናይ

በዚህ ዘርፍ አምስት የመጨረሻ ዕጩዎች የተመረጡ ሲሆን፤ አስናቀ ደሞዜ (ከዕለታት)፣ ካሳሁን ፍሰሃ (ከአንድ ጀግና)፣ አለማየሁ በላይነህ (ከገጠር ልጅ)፣ ሙሉጌታ ጌታቸው (ከዓለም በቃኝ)፣ ታምሩ ብርሃኑ (ከእምነት) እና ተሻለ ወርቁ (ከዓለም በቃኝ) ናቸው። በዚህ ዘርፍ የዘንድሮ ምርጥ ረዳት ተዋናይ ተብሎ ሽልማቱን ያገኘው ካሳሁን ፍሰሃ “ከአንድ ጀግና” ሆኗል።

·        የዓመቱ ምርጥ ረዳት ተዋናይት

በዓመቱ ከታዩ ፊልሞች ውስጥ በኢትዮጵያ ፊልም ፌስቲቫል ተሳታፊ ከሆኑት  መካከል የምርጥ ረዳት ተዋናይት እጩ ውስጥ የገቡት፤ ቲና ገ/አምላክ (ከእስከትመጪ ልበድ)፣ ሉሊት ካሳዬ (ከፍቅር ተራ)፣ ፍቅርተ ደሳለኝ (ከብላቴና)፣ መሰረት ባጫ (ከአዱኛ) እና መክሊት (ከእምነት) ፊልም ናቸው። በምሽቱ የሽልማቱን ካባ የደረበችው ምርጥ ረዳት ተዋናይትም ቲና ገ/አምላክ “ከእስክትመጪ ልበድ” ፊልም ሆናለች።

·        የዓመቱ ምርጥ መሪ ተዋናይ

በዚህ ዘርፍ በመጨረሻ ዕጩነት የቀረቡት ተዋንያን ደረጄ ደመቀ (ከአንድ ጀግና)፣ ግሩም ዘነበ (ከጎረየት)፣ ግሩም ኤርሚያስ (ከላምባ)፣ ሔኖክ ወንድሙ (ከፍቅር ተራ) እና ፍሬው አበበ (ከአማሪያ) ፊልሞች ሲሆኑ፤ የምሽቱ ተሸላሚ ሆኖ የተመረጠው ደግሞ  ግሩም ኤርሚያስ “ከላምባ” ፊልም ሆኗል።

·        የዓመቱ ምርጥ መሪ ተዋናይት

በዘርፉ ከሌላው ከተለየ መልኩ ስድስት የመጨረሻ ዕጩዎች የተዘረዘሩ ሲሆን፤ እነሱም አርሴማ ወርቁ (ከእምነት)፣ ገነት ንጋቱ (ከአማሪያ)፣ እድለወርቅ ጣሰው (ከፍቅሬን ላድን)፣ እፀህይወት አበበ (ከዕለታት) ሜላት ሰለሞን (ከገጠር ልጅ) ሊዲያ ሞገስ (ከላምባ) ፊልም ቀርበዋል። አሸናፊ ሆና በምሽቱ የነገሰችው ተዋናይት ደግሞ እፀህይወት አበበ “ከዕለታት” ፊልም ሆናለች።

·        የዓመቱ ምርጥ ተስፋ የተጣለበት ተዋናይ

ይህ ዘርፍ ጀማሪ የፊልም የትወና ባለሙያዎችን ለማበረታታት የተሰናዳ ሲሆን፤ ዘርፉ በሁለቱም ፆታ የመጨረሻ ዕጩ ሆነው የቀረቡ አራት ተስፈኞችን በመድረኩ አስተዋውቋል። እዮብ ዳዊት (ከብላቴና)፣ እዮብ አኑዋር (ከአዱኛ)፣ ኖሚን ሳሙኤል (ከአዱኛ)፣ አማኑኤል ክሪስ (ከከዕለታት) ፊልም ናቸው። የዘርፉ የዘንድሮ ተስፋ የተጣለበት ተዋናይ ደግሞ ህፃን አማኑኤል ክሪስ “ከዕለታት” ፊልም ሆኗል።

·        የዓመቱ ምርጥ የፊልም ፅሁፍ

ከታሪክ አንጻር በእጅጉ ፈተና እየገጠመው የሚገኘው የሀገራችን የፊልም ኢንዱስትሪ ለዘንድሮ የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል አምስት ምርጥ የፊልም ጽሁፎችን በዕጩነት ያቀረበ ሲሆን፤ አርሴማ ወርቁ (ከእምነት)፣ አንተነህ ሃይሌ (ከላምባ)፣ ብሩክ ሞላ (ከአንድ ጀግና)፣ ወንደሰን ይሁብ (ከገጠር ልጅ) እና ዮዲት ጌታቸው (ከእንቆጳ) ፊልም ታጭተው በምሽቱ አሸናፊ መሆን የቻለው ፅሁፍ ግን “ላምባ” ፊልም ሆኗል።

·        የዓመቱ ምርጥ የሲኒማቶግራፊ

በዚህ ዘርፍ ሙያዊና ቴክኒካል ብቃታቸውን ያሳዩ ወጣት ባለሙያዎች በእጩነት መቅረባቸው ተገልጿል። በዚህም ብስራት ጌታቸው (ከእምነት)፣ ተስፋዬ አፈወርቅ (ከዡሊየት)፣ ቢሊመኮንን (ከአንድ ጀግና)፣ አላዛር ሽፈራው (ከፍቅር ተራ) እንዲሁም አብርሃም ደምሴ (ከእንቆጳ) ፊልም ተመርጠዋል። አሸናፊ መሆን የቻለው ግን ቢሊመኮንን “ከአንድ ጀግና” ፊልም ተሸላሚ ሆኗል።

·        የዓመቱ ምርጥ ዳይሬክተር

የፊልሞቻችንን ጉልበትና ጥንካሬ አውጥተው ያሳዩልናል የምንላቸው ባለአራት አይን ሙያተኞች የተዘረዘሩበትና ጠንካራ ፉክክር የነበረበት ዘርፍ ነው ተብሎለታል። በዚህ የዓመቱ ምርጥ ዳይሬክተር ዘርፍ እጩ የሆኑት፤ አቤል ሀጎስ (ከአንድ ጀግና)፣ አርሴማ ወርቁ (ከእምነት)፣ አለምፀሐይ በቀለ (ከእንቆጳ)፣ አንተነህ ሃይሌ (ከላምባ) እና ወንደሰን ይሁብ (ከገጠር ልጅ) መሆናቸው የታወቀ ሲሆን፤ የምሽቱ አሸናፊ አንተነህ ሃይሌ “ከላምባ” ፊልም ተሸላሚ ሆኗል።

·        የዓመቱ ምርጥ ፊልም

በዘንድሮ ዓመት በበርካታ ተመልካቾች ታይተው፤ በፊልም ባለሙያዎች ትንተና መሠረት ከፍታ ተበጅቶላቸው በ10ኛው የኢትዮጵያ ፊልም ፌስቲቫል የመጨረሻ ዕጩ ውስጥ የተዘረዘሩት ፊልሞች፤ የገጠር ልጅ፣ እንቆጳ፣ እምነት፣ ላምባ እና አንድ ጀግና ናቸው። እነዚህ አምስት ፊልሞች በእያንዳንዳቸው በተለያዩ ዘርፎ ዕጩዎችን ያበዙ ሲሆን፤ የአመቱ ምርጥ ፊልም የተባለው “ላምባ” ሆኗል፡፡

·        በተመልካች ምርጫ የዓመት ምርጥ ፊልም

በዚህ ዘርፍ ተወዳዳሪ የመጨረሻ ዕጩዎች ሆነው የቀረቡት ስራዎች አማሪያ፣ ብላቴና፣ የነገርኩሽ ዕለት፣ አንድ ጀግና እና ዓለም በቃኝ ፊልሞች ሲሆኑ፤ የዓመቱ ምርጥ የተመልካች ምርጫ ሆኖ የምሽቱን ሽልማት ያገኘው ደግሞ “ዓለም በቃኝ” ፊልም ሆኗል።

በ10ኛው የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል በምርጥ ፊልሞች የመጨረሻ ዕጩ ሆነው በመቅረብ እና “ከሶስት ዘርፎች በላይ በመታጨት የሚጠቀሱት፤ “ላምባ” ፊልም በአራት ዘርፎች፣ “አንድ ጀግና” ፊልም በአምስት ዘርፎች፣ “እምነት” ፊልም በስድስት ዘርፎች፣ “እንቆጳ” ፊልም በሶስት ዘርፎች እና “የገጠር ልጅ” ፊልም በአራት ዘርፎች ተመርጠዋል። ፌስቲቫሉ ከአመት አመት መሻሻልን እያሳየ ቢመጣም መታረም ያለባቸውን አርሞ የበለጠ ሆኖ በቀጣዩ ዓመት እንደምናገኘው የብዙዎቻችን ተስፋና እምነት ነው።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
11413 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us