የመልካሞች አለም፤ “ዮቶጵያ”

Wednesday, 25 November 2015 14:49

 

 

·         የፊልሙ ርዕስ - “ዮቶጵያ”

·         ደራሲና ዳይሬክተር - በሃይሉ ዋሴ

·         ፕሮዳክሽን - ማክዳ ፊልም ፕሮዳክሽን

·         ኤዲተር - ታምሩ ጥሩዓለምና ምትኩ በቀለ

·         ዳይሬክተር ኦፍ ፎቶግራፊ - አዲስ ምህረትና አብይ ፈንታ

·         ረዳት ዳይሬክተር - ምትኩ በቀለና አለማየሁ አድበው

·         ተዋንያን - ደሞዝ ጎሽሜ፣ መስፍን ሃ/የሱስ፣ ማክዳ አፈወርቅ፣ ህጻን ሚካኤል ሽመልስ፣ ሄኖክ ወንድሙ፣ ሚካኤል ኤፍሬምና ሌሎችም

የ“ዮቶጵያ” ፊልም ደራሲና ዳይሬክተር በኃይሉ ዋሴ (ዋጄ) ከዚህ ቀደም የተደመምንባቸው የ“አይራቅ” እና የ“ሰኔ 30” ፊልሞች ደራሲ ነው። በዚህ ፊልሙም “ገነታችሁን ልባችሁ ውስጥ ፈልጉት” ይለናል። በሚናገረው ንግግርና በሚያመነጨው ሃሳብ ምክንያት ጓደኞቹን ጨምሮ በዙሪያው ባሉ ሰዎች ዘንድ እንደ “ንክ” እና እንደ ፈላስፋ የሚቆጠረው ዘሪሁን (ደሞዝ ጎሽሜ) የፊልሙ ታሪክ መዘወሪያ ገጸ-ባህሪይ ነው።

“ዮቶጵያ” በሰው ልጆች ሃሳብ ውስጥ የተቀመጠችና የመልካምም መናኸሪያ የሆነች አምሳለ -ገነት የምትባል አይነት አገር ናት። እውነትን ሳይታክቱ የሚፈልጓት፤ ልቦናቸው በነገርና በተንኮል ያልተመረዘ፤ በደላቸውን ችለው ወይም ረስተው የሚኖሩባት ዓለም ናት፤ “ዮቶጵያ”።

ዘሪሁን ከምድረ እንግሊዝ ምሁርነቱን ይዞ ወደትውልድ ሀገሩ የመጣ እውነትን ፈላጊ ገፀ-ባሪይ  ነው። ነገሮችን አለመሸፋፈኑ እና በግልፅ የሚሰማውን መግለፅ መቻሉ ወዳጅም ስራም ሲያሳጣው በፊልሙ ውስጥ እንመለከታለን።

“ጣኦት አምልኮ ማለት ልቦናችን የሚወስድበት ነገርን ሁሉ የሚወክል ነው” የሚለው ዘሪሁን፤ እኛም የዘመኑ ሰዎች ሳናውቀው በገንዘብ ፍቅር ታውረን፤ በስውር ጣኦት አምላኪዎች ሆነናል ይለናል። ብዙዎች ባላሰቡትና በሚያስቡት መንገድ ሃሳቡን መግለፅ የዚህ ገፀ-ባህሪይ መለኪያ ነው።

ለምሳሌ ትወደው ከነበረ ሰው ስታረግዝ መከዳት የገጠማት አስተናጋጇ (ማክዳ አፈወርቅ) ባለትልቅ ህንፃ ባለቤት የሆነውን የቀድሞ ወዳጇን (የልጇን አባት) “ስለምን ከሰሽ ከፍርድ ቤት ብር አትቀበይም” የሚሉ ወትዋቾች ቢበዙም፤ ዘሪሁን ግን “ቀረሽበት” ሲል ውሳኔዋን ሲያደንቅ እንመለከታለን።

ፊልሙ በተለይም በግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ ያለውን የቋንቋ ፈተናና የታሪክ ክፍተት በሚገርም መንገድ አሳይቷል። ለህፃናት ፅኑ ፍቅር የሌለው መምህር፤ እንግሊዝኛ ዳገት ሆኖበት በትዕዛዝ የሚያስተምር መምህር በተቀጠረበት ትምህርት ቤት ውስጥ ህፃናትን መቅረፅ የቱን ያህል መሠረታዊ ስህተት እንደሚያመጣ “ዮቶጵያ” ጥሩ ማሳያ መሆን የሚችል ፊልም ነው።

“ሰው በልቡ የታቀፈው ሃሳብ ውጤት ነው” የምትለው አስተናጋጅ (ማክዳ አፈወርቅ) ሁሉም ሰው ባሰበው ልክ ይሰፈርለታልን አፅንታ አሳይታናለች። ገንዘብ ቢያስፈልጋትም እንኳን ከዳኝ ካለችው ባለሀብት ብር ከማግኘት ይልቅ ፊት ለፊቱ ካለ ካፍቴሪያ ውስጥ በአስተናጋጅነት እየሰራች ውላ መግባትን እርካታዋ ያደረገችው ይህቺ ወጣት፤ የልጇ ገነት ናት።

የዋሆችን ፍለጋ፤ በህፃንነት ፍቅር የወደቀው ዘሪሁን በወር 20ሺህ ብር ይከፈለው ከነበረ ድርጅት ከተባረረ በኋላ በ1200 ብር የህፃናት መምህር ሆኖ ሲቀጠር ማየት ገነትን (ሰላማዊ አለምን) ፍለጋ የሚያስከፍለውን ዋጋ ያሳየናል።

ሁለት ዓይነት ሀብታም አለ የሚለን “ዮቶጵያ” ፊልም፤ አንደኛው ሀብታም ገንዘቡ የበለጠው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ገንዘቡን የበለጠ እንደሆነ በስላቅ ይነግረናል።

ዘሪሁን የህጻናቱ መምህር ከሆነ በኋላ በብዙዎቹ ሲወደድና በቋንቋና በታሪክ ላይ ያላቸውን አስተሳሰብ ቢቀይር እንመለከታለን። በተለይም በፊልሙ ውስጥ በጨረፍታ የተነሳው ልጆች የወላጆች ግልባጭ መሆናቸው ነገር ነው። ለዚህም እንደማሳያ ስለሀገር በተነሳ ጉዳይ ላይ አንዲት ተማሪ “እኔ ሀገሬን አልወዳትም” ትላለች። የዚህ ሃሳብ መነሻው ደግሞ አባቷ ሁሌም ሀገሩን ሲያጥላላ መስማቷ ነበር። እናም መምህር ዘሪሁን ይናገራል። “አባትሽ ሀገሩን የጠላት ስለማያውቃት ነው” ይህ ለውጥ ማምጣት የቻለ አስተሳሰቡ ነበር።

“የእኔ ገነት እናንተ ናችሁ” በሚላቸው ልጆች መካከል የሚመላለሰው ዘሪሁን፤ እስቲ እናንተም ገነታችሁን በፅሁፍ፤ በቁስ፣ ወይም በስዕል አሳዩኝ ባለው መሠረት ህፃናቱ የየራሳቸውን ገነት ሲያመጡ እንመለከታለን።

“ዮቶጵያ” ፊልም በምስል ትርከት የሞላቸውን ሁለት ድንቅ ሃሳቦች አስታውሼ ልሰነባበት። የመጀመሪያው አስተናጋጇ ልጇን ትምህርት ቤት አድርሳው ስትመለስ፤ ዓይኗ ውስጥ የገባውን ነገር በማውጣት ትውውቅ መጀመራቸው ነው። ይህ ንግርት ያለው ክስተት (ትዕይንት) ይመስላል። የተሻለ እንድታይ ዘሪሁን የዓይኗን እክል ሲያፀዳው፤ ህይወትን በተሻለ እንድታይ ማድረጉን የሚያመለክት ነው፡ ከዚሁ ጋር መነሳት የሚገባው ሌላው ነገር የቤቱ ግማሽ ቀለም በመላቱ ነው። ዳይሬክተሩ ወጣቷን አስተናጋጅ ሲያስተዋውቀን ከልጇ ጋር የቤቷን ግድግዳ ቀለም ስትቀባ ነበር። የቀባችው ግድግዳም ግማሽ ድረስ ብቻ ሲሆን፤ የተቀረውን የሚችል ይቀባዋል ባለችው መሠረት ወደቤታቸው ጎራ ማለት የጀመረው ዘሪሁን ማስተካከሉ፤ የህይወታቸውን መጣመርና መሟላት የሚያሳይ ነው። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን የሁለቱን ተፈላላጊዎች በፍቅርና በትዳር መጣመር ዳይሬክተሩ የተናገረበት መንገድ ልዩ  ነው። ይኸውም ገና በመጀመሪያዎቹ ትዕይንቶች ውስጥ ለጓደኛው “ሽማግሌ” ሆኖ የሄደው ዘሪሁን በሙሽራው አንድ ቃል ሲገባ እናያለን። ሙሉ ሱፍና 10ሺህ ብር እያሳየ ከጓደኞቹ ቀድሞ ለሚያገባ እንደሚሸልም እንመለከታለን። በስተመጨረሻም ይሄንኑ ሱፍ በአስተናጋጁ ቤት ግድግዳ ላይ ተሰቅሎ እንድንመለከት በማድረግ የሁለቱን ጥምረት በውብ ቴክኒክ አሳይቶናል።

“ዮቶጵያ” ፊልም የመልካሞችን ዓለም እንድናልም፤ በገነትና በቅንነት እንድንቀና የሚያደርገን ስራ ነው። በፊልሙ ውስጥ የብርሃን፣ የድምጽና የኤዲቲንግ እንከኖች የሉም፤ ካሉም ሊሸፈኑ የሚችሉ ቀላል ስህተቶች ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። በተረፈ ግን መልካምነትን የሚመኝ፣ በቅኖች የሚተማመንና በነገ ተስፋ የሚያደርግ ሁሉ ሊመለከተው የሚገባው ፊልም ነው፤ “ዮቶጵያ!” መልካም የመዝናኛ ሳምንት።    

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
11423 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us