“እውቀት ያላቸው የፊልም ባለሙያዎች አሉን”

Wednesday, 19 February 2014 13:08

ተዋናይ ኤልያስ ጌታቸው

 

ሰው ለሰው” በተሰኘው የኢቲቪ ተከታታይ ድራማ ለ20 ክልሎች ታምራት የተሰኘ ገፀ-ባህሪን ተላብሶ ከተጫወተ በኋላ ገፀ-ባህሪው በመሞቱ ምክንያት ከተመልካች ዕይታ ርቋል። የዛሬው እንግዳችን ከ“ሰው ለሰው” ድራማ ውጪ ጥቂትም ቢሆኑ የሚታወስባቸው ፊልሞችን ሰርቷል። ከነዚያም ውስጥ “ቢንጎ”፣ “ቁንጮ”፣ “ኢንጂነሮቹ”፣ “ከመጠን በላይ” እና በቅርቡም ከግሩም ኤርሚያስና ከማህደር አሰፋ ጋር የተጣመረበትን “ፅኑ ቃል” ልንጠቅስለት እንችላለን። እንግዳችን በብዙዎቹ ዘንድ በቁጥብነቱና በዝምተኛነቱ የሚታወስ ነው። ከተዋናይ ኤሊያስ ጌታቸው ጋር እንዲህ ተጨዋውተናል፤. . .

ሰንደቅ፡- ትወናን እንዴት ጀመርከው?

ኤሊያስ፡- አጀማመሬ እንደማንኛውም አማተር ተዋናይ በትምህርት ቤት ውስጥ ነው። የተማርኩት ኮከብ ጽባህ ት/ቤት ሲሆን፤ በድራማ ክበብ ውስጥ ጥሩ እንቅስቃሴ ነበረኝ። ከዚያም 12ኛ ክፍል ጨርሼ ስወጣ ሉሲ የቴአትር ክበብ ውስጥ ተሳትፎ አደርግ ነበር። ከዚያም እየጠነከርኩ ስመጣ ወደመከላከያ የቴአትርና የሙዚቃ ዝግጅት ክፍል ተቀላቀልኩ። ያም ሆኖ መከላከያ ውስጥ እየሰራሁም ቢሆን በግሌ አንዳንድ የሚዲያ ስራዎችን እሰራ ነበር። ለምሳሌ “ከሀሌታ” ጋር የተስፋ ጎህን ስራ ሰርተናል። ኢቲቪ ላይም አዝናኝና አስተማሪ አጫጭር ስራዎችን እንሰራ ነበር።

ሰንደቅ፡- እስቲ ሰሞኑን ለተመልካች ስለቀረበው “ፅኑ ቃል” ፊልም እናውራ፤ እንዴት ተመረጥክ?

ኤሊያስ፡- “ፅኑ ቃል” ላይ እንግዲህ የተመረጥኩት ፕሮዲዩሰሩ እንደነገረኝ ከሆነ አስቀድሞ ሰዎችን አናግሯል። “ከሰው ለሰው” ድራማ ሰለሞን አለሙን፣ ከ“መካኒኩ ላይ ዮናስ ብርሃነ መዋን እና ማህደር አሰፋን ከጠየቃቸውና ስለኔ አቅም ከነገሩት በኋላ ነው ወደኔ የመጣው። ዳይሬክተሩ ዳንኤልም ያውቀኝ ስለነበር እድሉን ሰጥተውኛል። ደስ ብሎኝ ሰርቻለሁ። ብዙም ሰው የዚህን አይነት ገፀ-ባህሪይ ይጫወታል ብሎ አይጠብቅም፤ እኔ ግን መጫወት እንደምችል አስብ ነበር። ይህን አቅሜን ለማሳየት በ“ፅኑ ቃል” ፊልም ተሳክቶልኛል። ነገር ግን ከዚህም በላይ ሆኜ መስራት እችላለሁ።

ሰንደቅ፡- ይህ ገፀ-ባህሪይ በጣም ጨካኝ ነው። ነገር ግን እስካሁን ከሰራኋቸው ገፀ-ባህሪያት ለየትኛው ታደላለህ?

ኤሊያስ፡- እውነቱን ለመናገር ከዚህ ቀደም የሰራሁት “ከመጠን በላይ” ፊልም ላይ ያለው ገፀ-ባህሪይ በጣም ደስ ይለኛል። ምክንያቱም ገፀ-ባህሪው ከአካላዊ ገፅታው ይልቅ ሥነ-ልቦናዊ ላይ የተሰራ በመሆኑ በጣም ነው የሚያሳዝነኝ። አይተኸው ከሆነ ሚስቱን ለዝነኛ ሰው እንዲፈትንለት ሲል አሳልፎ እስከመስጠት የሚደርስ ነው። ለወደደው ሰው ራሱን የሰጠ አይነት ሰው ነው። እዚህ “ፅኑ ቃል” ላይ ስትመጣ ደግሞ ገፀ-ባህሪው በማህበረሰቡ የተዛባ አስተሳሰብ ምክንያት ተገፍቶ፤ ያንተ ናት ተብሎ ቤተሰቦቹ የሰጡትን ሴት እስከመጨረሻ ድረስ ያለፍላጎቷ የኔ ናት ብሎ ድንጋይ ሲፈነቅል የሚኖር ሰው ነው። ራስ ወዳድነቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከመድረስም አልፎ በሽተኛ የሆነ ሰው ይመስለኛል ሳስበው።

ሰንደቅ፡- በ“ፅኑ ቃል” ፊልም ውስጥ ያለው ገፀ-ባህሪይ ካንተ ባህሪይ ፍፁም ተቃራኒ ይመስለኛል። ወደባህሪው ለመግባትም ሆነ ለመውጣት የተለየ የምታደርገው ነገር አለ?

ኤሊያስ፡- እንደአንድ ተዋናይ ይህን ባህሪይ ልጫወት ስዘጋጅ ጥቂት የፅሞና ደቂቃዎችን ብቻዬን መሆን እፈልጋለሁ። ሀሳቤን ሰብስቤ ፊልሙ መቀረፅ ከተጀመረ በኋላ ግን ሌላውን ነገር ሁሉ አላስታውሰውም። ለምሳሌ “ፅኑ ቃል” ላይ ያለው ገፀ-ባህሪይ ምን ያህል ጨካኝ እንደነበረ የተሰማኝ አሁን በሲኒማ ሳየው ነው። እንጂ ስሰራው የገፀ-ባህሪየው ጉዳት ይሰማኝ ስለነበር መጥፎ ሰው አይመስለኝም ነበር። ገፀ-ባህሪይ ይህን የሚያደርግበት የራሱ እውነታ እንዳለው ይሰማኝ ነበር ማለት ነው። አሁን እንደተመልካች ሲኒማ ላይ ሳየው ግን የወሰደው እርምጃ ለካ ከባድ ነው እንድል አድርጎኛል።

ሰንደቅ፡- ይህን ፊልም ስትሰራ አደጋ ደርሶብህ እንደነበር ሰምቻለሁ፤ ምን ነበር?

ኤሊያስ፡- እውነት ነው፤ በፊልሙ ውስጥ እንዳየኸው ከእስር ቤት የማመልጥበትን “ሲን” እየሰራን ስሮጥ ሚዛኔን ስቼ በመውደቄ የሾለ ድንጋይ ላይ ወደኩ፤ መተንፈስም መናገርም አልቻልኩኝም ነበር። ቤቴል ሆስፒታል ሄጄ ህክምና ተደረገልኝ “ራጅ” ተነሳሁ፤ ደህና ሆንኩኝ። ግን ለ15 ቀን የቆየ ህመም ነበረው። አሁን ግን ይመስገነው ደህና ነን። ሌላው ችግር ሆኖብኝ የነበረው ገፀ-ባህሪይ ሲጃራ በጣም የሚያጨስ ነበር እና ለመተንፈስ ሁሉ ተቸግሬ እንደነበር አስታውሳለሁ።

ሰንደቅ፡- ከመከላከያ ከወጣህ በኋላ የነበረህ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

ኤሊያስ፡- ለተወሰኑ ጊዜያት ከኢትዮጵያ ወጥቼ ነበር። በዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ፤ ዱባይ ነበር የቆየሁት። “ዞል” የተሰኘ የአማርኛ መዝናኛ ፕሮግራም በሱዳኖች ቻናል በኩል ለይላ ከምትባል ልጅ ጋር የጀመርኩት እኔ ነኝ። ያኔ ኢቲቪ በሳተላይት አይሰራጭም ነበርና እኛ ተመራጭና ብቸኛ የኢትዮጵያውያን መዝናኛ ፕሮግራሞችን እንሰራ ነበር። ነገር ግን ብዙ ልንገፋበት አልቻልንም። እኔ ካቆምኩት በኋላ ድምጻዊት ሃይማኖት ግርማ ጀምራው ነበር። ከዚያም ያንን ትቼ ወደሲኒማ ስራ ገባሁ። ከእስራኤሎች ካምፓኒ ጋር በመሆን ከሲኒማ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሰራዎችን ሰርቻለሁ። በዚህ ሁሉ መሀል ፊልም ለመስራት በማሰብ የፊልም ፅሁፍ አዘጋጅቴ ጨርሼም ነበር።

ሰንደቅ፡- በስደት እያለህ ለመስራት ያሰብከው የመጀመሪያ ፊልም በምን ምክንያት ሳይሳካ ቀረ?

ኤሊያስ፡- የመጀመሪያው ምክንያት ልንሰራ ባሰብንበት ጊዜ የበጀት ችግር አጋጠመን። እርሱን ለመፍታት ስንሯሯጥ ደግሞ ብረውኝ ሊሰሩ ያሰቡ ልጆች ታሰሩብን። ፊልሙን ለመስራት ብለን ሁሉ ቤት ተከራይተን ልምምድ እናደርግ ነበር። እውነቱን ለመናገር በሰው ሀገር ማቴሪያሎች ርካሽ ናቸው፤ ሰው ግን ውድ ነው። እንደፈለክ ተቀጣጥረህ አትገናኝም። ባይገርምህ ፈልሙን ፅፌ ጨርሼ እስካሁን አልሰራሁትም። ወደፊት እንግዲህ ይታሰብበታል።

ሰንደቅ፡- በኢቲቪ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰርተህ የታየኸው መቼ እና እንዴት ነበር?

ኤሊያስ፡- ስራዬ እንደተዋናይ ብቻ አልነበረም። እንደፀሐፊም እንደአዘጋጅም ሆኜ ሰርቻለሁ። ለመጀመሪያ ጊዜ ኢቲቪ ላይ የቀረብኩት አስታውሳለሁ በ1986 ዓ.ም ነው። ህክምና በሚል የበዓል ፕሮግራም ላይ ነው። ከዚያ በኋላ የተለያዩ ስራዎችን ሰርቻለሁ፤ ለምሳሌ አለማየሁ ታደሰ ያዘጋጀው “ነግ በኔ” የሚል በሙስና ላይ ያተኮረ ድራማ ሰርተናል። ከዚያም ከህዝብ ጋር በደንብ የተዋወኩበትን “የዓይኔ አበባ” የተሰኘ ተከታታይ የኢቲቪ ድራማ ሰርቻለሁ።

ሰንደቅ፡- በመከላከያ የቴአትርና የሙዚቃ ክፍል ቆይታህስ ምን ምን ስራዎችን ሰርተሃል?

ኤሊያስ፡- በመከላከያ ቆይታዬ በፊልምም በቴአርትም በጣም ብዙ ስራዎችን ሰርተናል። ወታደራዊና ሰራዊቱን የሚገነቡ ነገሮች ናቸው። ለህብረተሰቡም ገንቢ የሆነ መልዕክት ያላቸውን ስራዎች ሰርተናል። እኔ በግሌ አብዛኛውን ጊዜ አስተማሪ የሆኑ ስራዎችን መስራት ላይ አተኩራለሁ። ደስ የሚለኝም በዚህ ሙያ በኩል ለህብረተሰቡ የምሰጠው አንድ ቁም ነገር ቢኖር እንጂ ዝም ብሎ “አርቲስት ነው” ለመባል መስራት አልፈልግም። ከጭብጨባ በተለየ ጥበብ ለራሷ ታደላለችና ሙያው ለህብረተሰብ ፋይዳ መዋል አለበት ብዬ አስባለሁ። ብዙ ጊዜ የአርቲስቶች ስም ተደጋግሞ ይነሳል። ይህ የሆነው ሙያው የተለየ ስለሆነ ሳይሆን ለሚዲያ ቅርብ ስለሆነ ብቻ ነው የሚገን የሚመስለኝ። እንጂ ብዙዎች በራሳቸው ሙያ ለሀገራቸውና ለህብረተሰባቸው ትልልቅ ስራዎችን ይሰራሉ። እኛም በዚህ ሙያ አንዳች ማህበረሰባዊ ጥቅም ያለው ነገር ብንሰራ ደስ ይለኛል።

ሰንደቅ፡- ብሰራው ብለህ የምትመኘው እስካሁንም ያልሞከርከው ገፀ-ባህሪይ አለ?

ኤሊያስ፡- ብዙ ሰው የሚያውቀኝ በድራማና ልብ አንጠልጣይ ስራዎቼ ነው። ኮሜዲ የምችል የማይመስላቸው አሉ። ነገር ግን በገፀ-ባህሪያት ላይ የተገነባን ኮሜዲ ፊልም ብሰራ በጣም እመኛለሁ። ይህን ስልህ በቋንቋ እና በተረብ (በቀልድ) ላይ የተመረኮዘን ኮሜዲ ሳይሆን የባህሪይ ኮሜዲ ብሰራ የተሻለ ነገር ማሳየት እችላለሁ ብዬ አስባለሁ። ወጪዎቹ ፊልሞች ላይ ይታወቃሉ። ለምሳሌ ሮቢን ዊሊያምስ “missed that fire” ጨምሮ ሌሎችም አሉት። የሚታየው ውጣ ውረድ መራር ሆኖ የሰውዬው ገፀ-ባህሪይ ግን ልጆቹን ለማግኘት የሚያሳየው ነገር በጣም ያስቅሃል። እንደዚህ አይነት ለማሳቅ ተብሎ ሳይሆን የሰውዬው ባህሪይ በራሱ ሳቅ የሚፈጥር ስራ ባገኝ ደስ ይለኛል።

ሰንደቅ፡- “ሰው ለሰው” ድራማ ላይ ፈጥነህ በመሞትህ አሁን ስታስበው ቅር ይልሃል?

ኤሊያስ፡- የሚገርመው ነገር ገና ሰው ለሰው ድራማን ስጀምረው ከአዘጋጆቹ የተዋዋልነው ለ10 ክፍሎች ነበር። ነገር ግን የታምራትን ገፀ-ባህሪይ ፀሀፊውና ዳይሬክተሩ ስለወደዱት ወደሃያ ሁለት ሃያ ሶስት ክፍል ነው የሰሩት። እንደተዋናይ ደግሞ የተሰጠህን ገፀ-ባህሪይ ትጫወታለህ እንጂ የኔ እድሜ ይቀጥል ወይም ይጠር ማለት አትችልም። የፈጠረው (ደራሲው) በቃው ባለ ጊዜ ይበቃዋል።

ሰንደቅ፡- እስከዛሬ ከሰራሃቸው ገፀ-ባህሪያት ካንተ ጋር የሚመሳሰል ባህሪይ የነበረው አጋጥሞሃል?

ኤሊያስ፡- በፍፁም የለም። ነገር ግን አሁንም ድረስም ውስጤ ያለው ገፀ-ባህሪይ “ከመጠን በላይ “ፊልም ላይ ያው ነው። ስነ-ልቦናዊ አስተሳሰቡ ይገርመኛል። እኔ በተፈጥሮዬ ሰዎችን ሳውቅ ስማቸውን ብቻ ሳይሆን ባህሪያቸውንም ቢሆን ደስ ይለኛል። ለነገሮች ጠለቅ ያለ ትኩርት መስጠት እወዳለሁ ብዬ አስባለሁ።

ሰንደቅ፡- በፊልሙ ላይ ያየንህን ያህል በመድረክ ቴአትሮች አላየንህም አጋጣሚ ነው?

ኤሊያስ፡- ቴአትር አሁን እንኳን በቅርቡ ለሀገር ፍቅር ለመስራት ጀምረን ነበር። ነገር ግን ተገምግሞ አላለፈም፤ ቀረ። ስጀምር በተለይም መከላከያ ሳለሁ ግን ብዙ ቴአትሮችን ሰርቻለሁ። በፕሮፌሽናል መድረክ ላይ ከሰራሁት መካከል “የ13ወር ፀጋ” በብሔራዊ ቴአትር ተጋባዥ ተዋናይ ሆኜ የሰራሁት አንዱ ነው።

ሰንደቅ፡- አሪፍ ክፍያ ነው ወይስ አሪፍ ገፀ-ባህሪይ ነው የምታስቀድመው?

ኤሊያስ፡- የፊልሙ ጌታ ዳይሬክተሩ ነው። ዳይሬክተሩ አሪፍ አድርጌ እሰራዋለሁ ለሚለው ፊልም ራሴን እሰጣለሁ። ያም ሆኖ ጥሩ ክፍያ የምጠይቅ ነኝ። ነገር ግን ገፀ-ባህሪይውን ከወደድኩት ጥሩ ፊልም ነው ብዬ ካሰብኩ ደግሞ በትንሽም ዋጋ ቢሆን እሰራለሁ።

ሰንደቅ፡- እስካሁን ከሰራሃቸው ፊልሞች ውስጥ የተፀፀትክበት ስራ አለ?

ኤሊያስ፡- በፊልሞች አልፀፀትም። ነገር ግን ምናለ አብሬያቸው ባልሰራሁ ያልኳቸው ሰዎች ይኖራሉ። ምክንያቱም ሰዎቹ ናቸው አንድን ፊልም ጥሩም መጥፎም ሊያደርጉት የሚችሉት ብዬ ስለማስብ።

ሰንደቅ፡- ስለፊልሞቻችን በብዛት መሠራት ምን ትላለህ?

ኤሊያስ፡- እውነቱን ለመናገር ካለን የባለሙያ አቅምና እውቀት እንዲሁም ከበጀት አንፃር ያለውን ፈተና ሁሉ ተቋቁመው ብዙ ፊልሞች መሰራታቸው ፊልማችን አድጓል የሚያስብል ነው። አድጓል ስልህ ሁልጊዜ እኛ ራሳችንን ከሆሊውድና ከቦውሊድ ስራዎች ጋር ስለምናነፃፅር ነው እንጂ ከኛ አንጻር ከተለካ ያለበት ደረጃ ጥሩ ነው፤ ለወደፊትም ተስፋ አለው። የሚገርምህ አሁን በቅርብ ጊዜ በማንዴላ ህይወት ላይ ያተኮረው ፊልም ሲሰራ እንደአጋጣሚ የማንዴላ አሰልጣኝን ቦታ ካስት ተደርጌ ነበር። እዛ ላይ የሚያስደንቅ የፊልም እውቀት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች አይቻለሁ።

ሰንደቅ፡- ምን ያዝናናሃል?

ኤሊያስ፡- ከቤተሰቦቼ ጋር ስሆን ዘና እላለሁ። ዮሐንስ የሚባል ቆንጆ ልጅ አለኝ፤ ባለቤቴ ወሰኔ ትባላለች። ከስራ ውጪ ከነሱ ጋር መሆን ያስደስተኛል። በተረፈ ግን ፊልም ማየትና መፅሐፍትን በማንበብ ነው የምዝናናው።

ሰንደቅ፡- ለወደፊት ምን ለመስራት አስበሃል?

    ኤሊያስ፡- የራሴን ስራዎች መስራት እፈልጋለሁ። በቅርቡ ፅፌ የጨረስኳቸው ወደ አራት የሚደርሱ ፊልሞች አሉኝ። በተለይ አንደኛው ወቅታዊ ነው፤ ወቅቱ ስያልፍ ልሰራው እፈልጋሁ። ከዚያ ውጪ አንድ የቶክ ሾው የቲቪ ፕሮግራም በመጀመር ሀሳብ ማካፈል እፈልጋለሁ።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
11134 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us