የኪሩቤል ዓለሞች “የማይታየውን በሚታይ”

Wednesday, 09 December 2015 13:48

ስዕልን መሞነጫጨር የጀመረው ገና በልጅነቱ ነበር። የማስመሰል ሙከራዎቹ በዙሪያው ባሉ ሰዎች በመወደዳቸው የተበረታታው ይህ ሰዓሊ፤ በስተመጨረሻ አምስት ኪሎ ካስገባው የሲቪል ኢንጂነሪንግ ትምህርቱ ኮብልሎ የአርት ስኩል አባል እንዲሆን አድርጐታል። “አብዛኞቹ ስራዎቼ ምስላዊ ናቸው። ከትናንት እስከዛሬ፤ የሰው ልጅ፤ የሥነ-ጥበብ ስራዎች የፈጠራ ምንጭ እንደመሆኑ የኔም ተመሳሳይ ነው። የሰው ልጅ ተክለ ቁመና፣ ስሜቱ፣ ባህሪው፣ እኔነቱ፣ የእርስ በርስ ግንኙነቱና ሌሎችም በእኔ ውስጥ ትልቅ ቦታ አላቸው። እነዚህን ምንነቶች እና ልዩነቶች መፈለግ ይመስጠኛል። የተለያዩ ቁሶችን፣ የአሳሳል ስልቶችን፣ ፎቶግራፍና ቪዲዮን ጨምሮ የተለያዩ የመገናኛ አማራጮችን እጠቀማለሁ። በእነዚህ ውስጥ አለሁና ህይወትን ለመመርመር እተጋለሁ። ጀማሪ ብሆንም እነዚህ ሁሉ አማራጮች ጠቃሚ እንደሆኑ የገባኝ ይመስለኛል። ለገዛ ራሴ የሚገርመኝን ውጤትና እርካታም እየሰጡኝ ነው።” ይህን የሚለው ወጣቱ ሰዓሊ ኪሩቤል አበበ ነው።

እድል ቀንቶትና ተራው ደርሶ 18ኛውን የጋለሪያ ቶሞካ የሥዕል ትርኢት የሚያሳየው ይህ ወጣት፤ በአንጋፋው ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ብዕር “የሁለት ዓለም ሰዓሊ ነው” ተብሏል። ለዚህም ምክንያቱ የተዘረዘረው እንደሚከተለው ነው። “… በኪነ ቅቦቹ ምንነት እንደምናየው የሁለት ዓለም ሰዓሊ ነው። የድብቅና የግልፅ፣ የነፍስና የአካል፣ የህሊናዊና የነባራዊ ዓለም ሰዓሊ ነው። በማይታየው የሰው ልጅ ነፍስ የሚታየውን የሰው ልጅ አካል፤ በሚታየው የሰው ልጅ አካል የማይታየውን የሰው ለጅ ነፍስ፤ በስሜት ገላጭ እውነታዊ የጥበብ ዘይቤ በመልአከ ምስልና በሥነ-እርቃን ገላ ገፅታ አመሳጥሮና አዋህዶ እየሳለ ያለ ሰዓሊ ነው” ሲል ስለወጣቱ ሰዓሊ የተሰማውን በጋለሪያ ቶሞካ ባዘጋጀው ካታሎግ ላይ አስፍሯል።

“የሙሉ ጊዜ ሰዓሊ የመሆን ህልሙ አልነበረኝም” የሚለው ኪሩቤል፤ አርክቴክቸር የመማር ፍላጐቱ ሲጐድል እጁ ላይ የወደቀው ሲቪል ኢንጂነሪንግ ቢሆንም፤ በስዕል ፍቅር ምክንያት አቋርጦ ወደ ሥነ-ጥበብ ት/ቤት ማቅናቱን ይናገራል።

ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ የስዕል ተሰጥኦውን ለመግለፅ ያመቸኛል ወዳለው “Painting” (ሥነ ስዕል) ላይ ወደሚያተኩረው ትምህርት ክፍል ገብቶ ተምሯል። “አርት ስኩል መግባት ማለት ከሌሎች ትምህርት ቤቶች በጣም ይለያል። ለእኔ እንደ አዲስ ተሰርቶ እንደመውጣት ነው” የሚለው ኪሩቤል፤ ትምህርቱ ለሥነ-ጥበብ ብቻ ሳይሆን ለህይወት እና ለሰው ልጅ ያለህን አተያይ ይቀይረዋል ባይ ነው።

ሰዓሊያን ሁሉ እንደሚስማሙበት “ስዕል ምስላዊ ቋንቋ ነው”፤ ለወጣቱ ኪሩቤል ግን ስዕል ማለት፤ ወደግል ህይወቱ አስገብቶ ከራስ ጋር መነጋገሪያ፣ መቆዘሚያና መታደሻም ጭምር ነው። ከሁሉ በላይ ግን ስዕል ለኪሩቤል አዲስ ሀሳብ መፍጠሪያም ነው።

ቀድሜ የተዋወኩት መሳልን (መሞነጫጨርን) ነው የሚለው ወጣቱ ሰዓሊ ኪሩቤል አበበ፤ ገና ከመነሻው አርአያ (ተምሳሌት) የማደርገው ሰው አልነበረኝም ባይ ነው። ነገር ግን በሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት ቆይታው ታሪካቸውን ካነበበላቸው ጥበበኞች መካከል ለሩሲያዊው ሰዓሊ ሚካኤል ሩቭል የተለየ ተመስጦ እንደነበረው ይናገራል። በተለየ በዚህ ሰው ላይ እንዲመሰጥ ስላደረገው ነገር ሲገልፅም፤ “ሩብል ‘Symbolist’ ነው። ከዚህም በላይ በስራዎቹ ላይ እኔ የምፈልጋቸውን ስሜቶች አገኝበታለሁ። ብዙ ጊዜ ስለነፍሱ ነው የሚስለው፤ በተለይም ነፍሱን በሁለት መንገድ ለመግለጽ የሚሞክርበት ዘይቤው በጣም ደስ ይለኛል” ሲል ይገልፀዋል።

“በእኔ ስራዎች ውስጥ ከቀለምና ከመስመር በላይ ቅርፅ ይጐላል” የሚለው ሰዓሊ ኪሩቤል፤ በልጅነቱ ነገሮችን ደግሞና አስመስሎ መሳል ላይ ያተኩር እንደነበር የሚገልፅ ሲሆን፤ አሁን ላይ ግን የሰው ሰውነትና ስብዕና ላይ አተኩሮ በስዕሎቹ እንደሚገልፅ ይናገራል። ይህም በተለየ ይመስጠው የነበረው የሩሲያዊው ሰዓሊ መንገድ እንደሆነ ያስታውሳል።

በስዕል ስራዎቹ ውስጥ በትኩረት የሚሰራው የውስጥን ስሜት ወደውጭ፤ የውጪን ስሜት ደግሞ ወደ ውስጥ በማስቀመጥ እንደሆነ የሚናገረው ኪሩቤል፤ “የሚታየውን የሰው ገፅታ እንደ ቋንቋ ተጠቅሜ የውስጡን ሀሳብ (ስሜት) ለማሳየት እተጋለሁ” ባይ ነው።

በጋለሪያ ቶሞካ ያቀረባቸው ከ30 በላይ ስራዎች ሲሆኑ፤ በ2003 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አርት ስኩል ከተመረቀ በኋላ ያቀረበው የመጀመሪያው የብቻ የስዕል ትርኢት እንደሆነም ይገልፃል። ለትርኢቱ ርዕስነት የተሰጠው “የማይታየውን በሚታይ” የሚል ሲሆን፤ ማዕከላዊ ሀሳባቸው (ጭብጣቸው) ደግሞ ቅድም እንደገለፀው አካላዊ ገፅታን እንደመግለጫ መሳሪያ በመጠቀም ውስጣዊ ሀሳብ ማጋለጥ እንደሆነ ያሰምርበታል።

የስዕል ትርኢቱ ለዕይታ ከበቃ በኋላ ተመልካችህ ያንተን ሀሳብ አግኝቶታል ወይ? በሚል ላቀረብንለት ጥያቄ ሲመልስ፤ “ያልጠበኩትን ምላሽ አግኝቻለሁ። ብዙዎቹ ራሳቸው የተሰማቸውን ነው በስራዎቼ ላይ ተመርኩዘው መግለፅ የሚሞክሩት፤ ሁሉም ከእኔ ሀሳብ ጋር ገጥሟል ባልልም የተመልካቹ እይታ ግን ለእኔ በጣም የሚያስደስት ነበር” ሲል ይገልፀዋል።

ወጣቱ ሰዓሊ ኪሩቤል አበበ ህይወቴ ስዕል ነው። የሙሉ ጊዜ ስራዬም ሆነ መኖሪያዬ ስዕል እንዲሆን እሻለሁ ቢልም፤ ፈተናው የማይቀር እንደሆነ ያስታውሰናል። “ከእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ አንፃር በስዕል ብቻ ኑሮን መግፋት ሊከብድ ይችላል። ነገር ግን አልሞት ባይ ተጋዳይነት ሳያዋጣ አይቀርም” ይላል።

ከስዕል ስራዎቹ ውጪ ለመዝናናትና ራሱን ለማደስ የእግር ጉዞን እንደሚመርጥ የሚናገረው ኪሩቤል፤ ከዚያም ባሻገር ሙዚቃን ማድመጥና ተፈጥሮአዊ አካባቢዎችን መጐብኘት እንደሚዝናናባቸው ይገልፃል።

ከተከፈተ አንድ ሳምንት ያለፈው የሰዓሊ ኪሩቤል አበበ የጋለሪ ቶሞካ የስዕል ትርኢት ለሁለት ወራት የሚቆይ ሲሆን፤ የጥበብ አፍቃሪያን ስራዎቹን በነፃ ታድመው እንዱዝናኑትና ሀሳብ እንዲለዋወጡበት ይጋብዛል። በስተመጨረሻም ድጋፍ ላደረጉለት፣ ላበረታቱትና የስዕል ስራዎቹን እንዲያቀርብ መልካም ፍቃዳቸውን ለሰጡት የጋለሪያ ቶሞካ ሰዎች ምስጋናዬ እነሆ ብሏል። መልካም የመዝናኛ ሳምንት እንዲሆን እኛም ተመኘን።¾ 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
14874 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 151 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us