ከጎዳና የተነሳው “አምባሳደር”

Wednesday, 16 December 2015 13:29

 

“መነሻዬ ከጎዳና ነው” የሚለው ወጣቱ የጉራጌኛ ድምጻዊ መላኩ ቢረዳ፤ በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ የሙዚቃ ስራዎቹን በማቅረብ ይታወቃል። በአሁኑ ወቅት በቋሚነት በዩድ አቢሲኒያ የባህል ምግብ አዳራሽ የምሽት ስራዎችን ያቀርባል። ከዚህ ቀደም “ትዊስት በጉራቄ” እና “አምባራኒ” የተሰኙ የጉራጌኛ አልበሞቹን ለህዝብ ያቀረበ ሲሆን፤ በዚህ ዓመት የሚወጣው ሶስተኛ አልበሙን ግን ከወዲሁ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ይውል ዘንድ ሰርቶ ጨርሶታል። ከዚህም ባለፈ ወጣቱ ለሚሰራው ስራ የበጎ አድራጎ አምባሳደር እየሆነ መጥቷል። ከወጣቱ የጉራጌኛ ድምጻዊ መላኩ ቢረዳ ጋር በስራዎቹና በበጎተግባር እንቅስቃሴው ዙሪያ ያደረግነውን አጭር ቆይታ እነሆ፡-

ሰንደቅ፡- ሶስተኛ አልበምህን ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ለመስጠት መዘጋጀትህን ሰምቻለሁ፤ ውሳኔህ ከምን የመነጨ ነው ከሚለው ብንጀምር?

መላኩ፡- የህይወቴን ፈታኝ ምዕራፍ በጎዳና ያሳለፍኩ ሰው ነኝ። ለአራት ዓመታት በጎዳና ሕይወት ውስጥ አሳልፌያለሁ። ለትምህርት ብዬ ብዙ መስዋትነት ከፍያለሁ። ደግሞም ስለችግር በደንብ የሚረዳ ሰው በችግር ውስጥ ያለፈ ሰው ይመስለኛል። እርቦኝ፣ በባዶ እግሬ ሄጄ፣ በቀዝቃዛ ሲሚንቶ ላይ ተኝቼ ያለፍኩ ሰው ነኝ። ስለዚህ ችግረኞችን መርዳት ደስ ይለኛል። እስካሁንም ከክብራን አረጋውያን መርጃ፣ ከመቄዶኒያ፣ ከሙዳይ፣ ከሜሪጆይ እና “ሰዓት ዕላፊ” ከተሰኘው የሬዲዮ ፕሮግራም ጋር በመተባበር ወገኖቼን ባለኝ አቅም ለመርዳት እየሰራሁ ነው። ይህንንም አልበም ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች የሰጠሁት በዚሁ መነሻ ነው። እዚህ ላይ በተለየ የማነሳው “ጉርዳ” (ቃል ኪዳን) የተሰኘና በጉራጌ ውስጥ የተቋቋመ የበጎ አድራጎት ድርጅት ነው። ድርጅቱ የአካል ጉዳት ያለባቸውን፣ ማየት፣ መስማትና መናገር የተሳናቸውን ወገኖች የሚረዳ ሲሆን፤ ተቋሙን ለማጠናከር ከተለያዩ ሰዎች ጋር በጋራ እየሰራን ነው። መጪውን አልበምም ለበጎ አድራጎት ተቋማት በመስጠት አጋርነቴን ማሳየት እፈልጋለሁ።

ሰንደቅ፡- እስቲ ወደአነሳስህ ልመልስህ ሙዚቃን መቼና እንዴት ጀመርክ?

መላኩ፡- ሙዚቃን በትምህርት ቤት ነው የጀመርኩት። እኔ ከገጠር የተነሳው ሰው ነኝ። ጉራጌ ውስጥ ቸሃ- ወረዳ እንደብር ከተማ ነበርኩ። የሚያስተምረኝ ስላልነበረ፤ ወደአዲስ አበባ መጣሁ። እዚህ የማውቀው ሰው ስላልነበረኝ፤ ጎዳና ወጣሁ። ለአራት ዓመታትም በጎዳና ላይ ኖሬያለሁ። አንዴ ከጎጃም በረንዳ እቃ ያሸከሙኝ ሴት ደብተር ገዝተውልኝ ስላም በር ት/ቤት ለመመዝገብ ስሄድ ጊዜው እንዳለፈ ነገሩኝ። ነገር ግን ተመላልሼ ስላስቸገኩ ርዕሰ መምህሩ አዝነውልኝ እንድማር ስለተፈቀደልኝ መማር ጀመርኩ። አንድነገር አምናለሁ፤ ብዙ ጊዜ የምንፈልገው ነገር የማንፈልገው ነገር ውስጥ ነው የሚኖረው። ከ5ኛ ክፍል በኋላ አማርኛ ዘፈኖችን ወደጉራጊኛ ስልት እየቀየርኩ መዝፈን ጀመርኩ። ለወላጆች ቀን ብዙ ተወዳጅ ዘፈኖችን አቀርብ ነበርኩ። ከዚያም እድሉን አግኝቼ ከፖሊስ ኦርኬስትራ ሙዚቃ ጋር ለ7 ዓመት አብሬ ሰርቻለሁ።

ሰንደቅ፡- ጉራጊኛን በተለየ ስልት ለመስራት የወሰንከው ከምን መነሻ ነው?

መላኩ፡- ከልጅነቴ ጀምሮ የጉራጌኛ ሙዚቃዎችን ስሰማ አልበሞቹ ሁሉ የሚያስጨፍሩ ናቸው። የኔ ቁጭት የነበረው የሙዚቃውን ባህላዊ ይዘት ሳይለቅ ከጭፈራ በዘለለ ለምን አልሰራም የሚል ሲሆን፤ በመጀመሪያው “ትዊስት በጉራጌ” አልበሜም ውስጥ ትውሲት፣ ትግርኛ፣ ሱዳን፣ ትዝታ፣ አንቺ ሆዬ፣ አምባሰልና ሬጌ እንዲካተትበት አድርገን ተወዳጅ ስራ ለመስራት ችለናል። ባይገርምህ ያ አልበም ፌስታል አዙሬ ከሸጥኩት ላይ ሳንቲም ቆጥቤ ያወጣሁት አልበም ነው።

ሰንደቅ፡- “ትዊስት በጉራጌ” የተሰኘው የመጀመሪያ አልበምህ ለህዝብ ጆሮ ሲደርስ የተሰማህ ስሜት እንዴት ይገለጻል?

መላኩ፡- በውስጤ የተለያዩ ስልቶችን በጉራጌ የሙዚቃ ስልት የሞከርኩበት በመሆኑ ብዙ ሙዚቃ ቤቶች አልተቀበሉኝም ነበር። በመጨረሻ “ስታር ሙዚቃ ቤት” ወስዶት አከፋፈለው በጣም ተወዳጅ ሆነ። በተለያዩ ሚዲዎች ስራዬን ስሰማው የተለየ ስሜት ነበር የሚሰማኝ። አንዳንዴም ሳስበው ለዚህች የምታልፍ ቀን ነው ያህ ሁሉ የተሰቃየሁት ብዬ ሁሉ አስብ ነበር። ደስታዬን እጥፍ ድርብ ያደረገው ደግሞ አልበሜ በወጣበት ሰሞን የ10ኛ ክፍል ትምህርት ውጤት 3 ነጥብ 8 አግኝቼ ያለፍኩበት ነበር። የሁለቱን ደስታ በጣም ነገር ያጣጣምኩት።

ሰንደቅ፡- ከዘፈኖችህ ውስጥ የራስህ ዜማና ግጥሞች አሉ? በተለየ የምታስታውሳቸው ስራዎችስ?

መላኩ፡- በስራዎቼ ውስጥ አብዛኞቹ ዜማና ግጥሞች የራሴ ናቸው። ለተለያዩ አርቲስቶችም ዜማና ግጥም እሰጣለሁ። በህይወቴ ከፍቅር ይልቅ ስለአብሮነትና መተጋገዝ ብዘፍን ደስ ይለኛል። ፍቅርን በተመለከተ “ኦምባራኒ” ሙዚቃዬ ፍቅርን የገለፅኩበት ዘፈን ነው። ስለሀገር ዘፍኛለሁ።

ሰንደቅ፡- በተለየ የምትወዳቸው እና ምሳሌ ያደረካቸው ድምጻዊያን አሉ?

መላኩ፡- ባይገርምህ የቴዲ ታደሰ፣ የማዲንጎ አፈወርቅ፣ የኤሊያስ ተባባል፣ የጋሽ ጥላሁንና የጋሽ ማህሙድን አማርኛ ስራዎች እያደመጥኩ ነው ያደኩት። እነዚህ አንጋፋ ድምፃውያን በኔ ስራ ላይ ተፅዕኖ የላቸውም ማለት አይቻልም።

ሰንደቅ፡- ግጥምና ዜማ ለመስራት የሚያነሳሳህ ምን አይነት ሁኔታ ነው?

መላኩ፡- ዜማና ግጥም ለመስራት ውስጤ ሊሰማኝ ይገባል። በጣም ሳዝን ግጥም መፃፍ ይሆንልኛል ብዬ አምናለሁ። ስለዚህ ስሜቴ በተጎዳ ጊዜ የመስራት አቅሜ ይጨምራል።

ሰንደቅ፡- እስቲ ደግሞ ስለአዲሱ አልበምህ ንገረኝ። ምን ያህል ስራዎችን አካተህበታ?

መላኩ፡- በቅርቡ የሚወጣው አዲሱ አልበሜ መጠሪያው “ዓለም” ነው። በውስጡ 13 ዘፈኖ ተካተውበታል። ዕወቅ አቀናባሪዎች ተሳትፈውበታል። ይህ አልበም በትዝታ ፣ በጉራጌኛ፣ ሱዳን በጉራጌኛ፣ አንቺ ሆና አምባሰለም በጉራጌኛ ተሰርቶበታል። ስለመተዛዘንና ስመረዳዳት በተለይ ማህበራዊ ህይወታችንን የሚዳስስ ስራ ነው ማለት እችላለሁ። ሙሉ ለሙሉም ለበጎ አድራጎት ተቋማት የሚውል አልበም ነው።

ሰንደቅ፡- ይህን አልበም ለመስራት ምን ያህል ወጪ አወጣህ?

መላኩ፡- ይህን አልበም ለመስራት አሉ የተባሉ አቀናባሪዎች ጋር ሄጃለሁ። ቢኒያም መስፍን (ቢኒ ባና)፣ ተሰማ፣ የኩኩን ያቀናበረው አማረ ታምሩ፣ ይትባረክ፣ መሀመድ ኑር ሁሴንና ዶክተሬመኮንን ለማ፣ ሰለሞን ሃ/ማርያም እና ሌሎችም ታዋቂ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ነው። በአጠቃላይ ወደ 150ሺህ ብር በትንሹ ወጥቶበታል።

ሰንደቅ፡- ይህ አልበምቢሸጥ ምን ያህል ያወጣል? ስጦታውንስ ያበረከትከው ለየትኞቹ ይሆናል?

መላኩ፡- ወጪው ከዚህም በላይ ነው። ነገር ግን ለጥያቄህ መልስ ለመስጠት ያህል ይሄን አልበም ብንሸጠው እስከ 250ሺህ ብር ማግኘት እንችላለን ብዬ አምናለሁ። ይሄ አልበም ለድርጅቶች ገቢ እንዲሆን ሳደርግ ከእግዜር ቀጥሎ ያለኝ ይሄ ህዝብ እንደሆነ ለመመስከርም ጭምር ነው። ለክብራን አረጋውያን መርጃ፣ ለሙዳይ እና ጉርዳ የተሰኙት ተቋማት በጋራ ይረዱበታል።

ሰንደቅ፡- በቅርቡ ታመህ ሆስፒታል ገብተህ ነበር፤ ምን ነበር ያጋጠመህ፤ አሁንስ ጤንነትህ እንዴት ነው?

መላኩ፡- አሁን ሙሉ በሙሉ ጤነኛ ነኝ። ህመሜ የኩላሊት ኢንፌክሽን ነው። ነገሩ ቀላል ቢመስልም የሃኪም ቤት ክትትልን ይፈልጋል። አሁን እነደምታየኝ በጣም ጤነኛ ነኝ ፈጣሪ ይመስገን።

ሰንደቅ፡- ብዙዎች በመታመምህ ደንግጠው ነበር፤ በቶሎ ወደስራህ ስትመለስ ምን አሉህ?

መላኩ፡- ባይገርምህ የሰው ፍቅር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ያየሁት ታምሜ በተኛሁበት ወቅት ነው። በዚህ አጋጣሚ ተመላልሰው የጠየቁኝን ሁሉ በጣም አመሰግናለሁሁ፤ በፍጥነት ወደስራ ከመመለሴ ጋር የማልረሳውን ገጠመኝ ልንገርህ። ከሆስፒታል እንደወጣሁ ቤት ከመቀመጥና አለሁም ለማለት ብዬ ወደ አቢሲኒያ የባህል ምግብ አዳራሽ ሄድኩ። እንደምንም ብዬ አንድ ዘፈን ዘፍኜ ከመድረክ ወረድኩ። ታዲያ አንዲት ልጅ ከወላጆቿ ጋር ልትዝናና መጥታ አይታኝ ኖሮ ለአባቷ “አባዬ ይሄ እኮ መላኩ ነው፤ ባለፈው ታሞ “ኮማ” ውስጥ ነበር።፡ ስትለው አባትዬው ምን ሲል ሰማሁት መሰለህ “ይሄማ ምን ኮማ ውስጥ ነው ኮባ ውስጥ ቆይቶ ነው” አላት ይሄን አባባል መቼም አልረሳውም። ያዝናናኛል፤ አጨፋፈሬ ታምሜ የተነሳሁ ስላልመሰለው ነው።

ሰንደቅ፡- ድምጻዊ ሆነህ በተለያዩ መዝናኛ ስፍራዎች ብዙ ሰዎችን ታዝናናለህ፤ አንተስ በምነድነው የምትዝናናው?

መላኩ፡- በጣም የሚገርምህ ነገር እኔ የመዝናናት ስሜት የሚሰማኝ ሰዎች በሙዚቃዬ ሲዝናኑ ሳይ ነው። መቼም ሰው የሰራውን ምግብ ሲበሉለት ደስ እንደሚለው ሁሉ እኔም ደስ የሚለኝ ሰዎች ሲዝናኑልኝ ነው።

ሰንደቅ፡- የበርካቶችን ሰርግ ማድመቅህን ሰምቻለሁ፤ ክፍያህ ውድነው የሚባለው እውነት ነው?

መላኩ፡- እውነት ነው ብዙዎችን ድሬያለሁ። ነገር ግን ክፍያዬን በተመለከተ ሰዎች ቢናገሩ ደስ ይለኛል። ብታምንም ባታምንም ግማሹን ሙሽራ በነፃ ነው የዳርኩት ማለት እችላለሁ። ከገንዘብ በላይ የሰው ፍቅር ይበልጥብኛል። አንዴ እንደውም ለታክሲ 70 ብር ብቻ የተቀበልኩበት ጊዜ እንደነበረ አስታውሳለሁ፡፤ ሙሽሮች መጀመሪያ በሞራል ያነጋገሩህና በኋላ ላይ ሲቸግራቸው እተዋቸዋለሁ።

ሰንደቅ፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።

መላኩ፡- እኔም ይህን እድል ስለሰጣችሁኝ በጣም አመሰግናለሁ። መጪው አልበሜን እያደመጡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶቹን እንዲደግፉም በዚሁ አጋጣሚ ለአድናቂዎቼ ጥሪ ማቅረብ እወዳለሁ፤ አመሰግናለሁ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15134 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 87 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us