ፍቅር “ከትዳር በላይ” ሲሆን. . .

Thursday, 24 December 2015 11:03

 

ቴአትር - “ከትዳር በላይ”

ደራሲ - ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ

አዘጋጅ - ካሌብ ዋለልኝ

ተዋንያን - ሰላማዊት በዛብህ፣ መስከረም አበራ፣ ታከለ ወንድሙ እና ካሌብ ዋለልኝ ናቸው።

የሚወዳትን ሴት ትመኘዋለች ለሚለው የሃብት ህይወት አሳልፎ በመስጠት፤ “የምትፈልጊውን ሳይሆን የሚያስፈልግሽን አድርጌያለሁ” የሚለው የ “ከትዳር በላይ” መሪ ገፀ-ባህሪይ ክብሬ (ካሌብ ዋለልኝ) ይወዳት የነበረችውን ምህረት (ሰላማዊት በዛብህ) በገዛ እጁ ካጣት በኋላ በህይወቱ የፈጠረችውን ክፍተት ለመሙላት የመሠረተው አዲስ ፍቅር በተመሳሳይ መንገድ ሲታመስ የሚያሳይ ዘመናዊ ኮሜዲ ቴአትር ነው።

“ከትዳር በላይ” ነፃነት ገደቡን ስቶ፤ የፍቅር ሃያልነት በዝቶ፤ የዋህነትና ጅላጅልነት የሚምታቱበት አዝናኝ ቴአትር ሆኖ ተመድርኳል።  ከቀድሞ ፍቅረኛው ጋር የአንድ ድርጅት ባለቤት ሆኖ የሚሠራው ክብሬ፤ በፍቅር መካከል መተማመን ካለ ቅናት ምን ያደርጋል” ሲል ውስጣዊ ቁጭቱንና ቅናቱን ሊደብቅ ቢውተረተርም፤ የቀድሞ ፍቅረኛዋ ምህረት ግን “በሚወዱት ሰው መቅናት ተፈጥሯዊ ነው” ስትል ትሞግተዋለች።  

በአራት ትዕይንቶች ተከፋፍሎ በአራት ተዋንያን ለ1ሰዓት ከ30 ደቂቃ በመድረክ የሚቆየውና ዘወትር ረቡዕ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በመታየት ላይ የሚገኘው “ከትዳር በላይ” ቴአትር በበርካታ ፍግ ክስተቶች የተዋቡ ትዕይንቶች የሚስተዋሉበት ነው።

“እሳት አመድ ወለደ” እንዲሉ ከአባቱ አቶ ሻረው (ታከለ ወንድሙ) ፍፁም ተቃራኒ የሆነ ባህርይ የሚያንፀባርቀው ክብሬ፤ “አብረን የኖርነው አስመሳይና ውሸታሞች ስለሆንን ነው” በምትለው የትዳር አጋሩ እሴተ (መስከረም አበራ) ተወጥሮ ይታያል።  . . . ከዕድሜያቸው በማይጠበቅ የቅምጥ ብዛት ጌጤነሽ፣ ፀሐይነሽ፣ ክብካብ ወዘተ እያሉ ሻንጣቸውን እንዳንጠለጠሉ በመሸበት የሚያድሩት የክብሬ አባት ጥሎባቸው የልጃቸውን የቀድሞ ፍቅረኛ ለልጃቸው ትዳር ቢመኟትም፤ ቤቱ ግን በተቃራኒው እጅ ላይ ወድቋል” ልጃቸው ከትናገር የማይሰሟትንና ሁኔታዋ የማይመቻቸውን እሴተን በመምረጡ ምክንያት የክብሬ ቤት በግጭት አውድማ ሲሆን ማየት ወይ የትዳር ነገር ያሰኛል።

መፍዘዙን አቁሞ፤ ምህረትን አግብቶ እንዲኖር አሊያም ደግሞ በቅናት ደም ፍላት ሚስቱን የት ገባሽ፣ የት ወጣሽ? ከማለት አልፎ በዱላ “ዠለጥ” እንዲያደርጋት የሚመክሩት አባቱን አልሰማ ያለው ክብሬ፤ “ውሃው ያልቃል እንጂ ድንጋዩ አይረጥብም” ተተርቶበታል።  የተዳፈነ ፍቅር በሚቀጣጠልበት በዚህ ቴአትር ሁለተኛ ትዕይንት ላይ በምህረት (በቀድሞ ፍቅረኛው) እና በእሴተ (በአሁኗ ሚስቱ) መካከል የቆመው ክብሬ በጥያቄ ጦር ሲጠቀጠቅ ማየት ተመልካችን በሳቅ መካከል የሚያሳቅቅ ትዕይንት ነው ማለት ይቻላል”።  

“ገፋፍተህ የማልፈልገው ትዳር ውስጥ አስገብተህኛል” የምትለው ምህረት፣ በትዳሯ ውስጥ ሆና አሁንም ድረስ እርሱን እንደምታስበው ትናገራለች፡፤ ይህም አልበቃ ብሏት “መሆን ያለበት ነገር ሆኗል” ለሚለው ክብሬ በሚስቱ ፊት “ወዳንተ እንድመለስ አትፈልግም ነበር?”ስትል ለጠየቀችው ጥያቄ ባልተረጋጋና በፍርሃት በተሞላ ስሜት ሆኖ “አዎ!” ሲላት የተመልካች መረዳት የሳቅ ፍንዳታ ይፈጥራል።  “የወደቀ ግንድ ምሳር ይበዛበታል” ይሉት ተረት ለክብሬ ፍቅር የሚሰራ ይመስላል።  ከምህረት ጥያቄ በመላ ሲያመልጥ እሴት በበኩሏ፤ “እሷ (ምህረት) ከኔ በላይ የምትወድህ ይመስልሃል?” ስትል ያቀረበችለትን ጥያቄ በጭንቀት ሆኖ ሲመልስ የተጠቀመው አነጋገር “እንደዚህ አይጠየቅም” የሚል ብቻ ነበር፡፤

“ከትዳር በላይ” ከፍቅርም በላይ በሚመስል፤ ከስግብግብነት የፀዳ፤ የራስን ሰው አሳልፎ በመስጠት የሚሰማን ፀፀትና ብስጭት በጉልህ ማሳየት የቻለ ሥነ-ልቦናዊ ትርጉሙ የበዛ ቴአትር ነው።  . . . ሰው ሚዛኑን አይሳት እንጂ የሚወደውን ነገር ማጣት የለበትም ወይም ላለማጣት ዋጋ ከመክፈል መሸሽ የለበትም።  ክብሬ ግን ፍርድ ከዚህ ተቃራኒ በሆነ ስሜት ሰዶ ማሳደድን የመረጠ ይመስል።  ለሁለተኛ ጊዜ በነፃነት ስም፤ በፍቅር መካከል ቅናት ምን ያደርጋል በሚል ከልቡ ባላመነበት ነገር ሲብሰለሰል ማየት የቴአትሩ ትልቅ ስላቅ ሆኗል።

እንደአባቱ የበዛ ጥንታዊ ወንዳወንድነት ቀርቶ እውነተኛ ስሜቱን መግለፅ ቢችል የሚያስብለን የክብሬ ነገር “ከትዳር በላይ” ነው።  የመጀመሪያ ፍቅረኛውን አንደርድሮ ለሀብታም ካደረ በኋላ፤ በእጁ ያለችውን እሴተን ደግሞ የቀድሞ ፍቅረኛዋ በሚገኝበት ድግስ ላይ ብቻዋን እንድትገኝ ፈቅዶ በስካር እብደት ውስጥ መብሰልሰል ምን ይሉት ተፈጥሮ ነው? ያስብላል።

እንደማጠቃለያ

“ከትዳር በላይ” ቴአትር በቀላል ታሪክ ውስጥ ጠንካራ ስነ-ልቦናዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን የምናይበት ነው።  ወዝ ባለው ቋንቋና በቀላል ዝግጅት የቀረበልን ይህ ቴአትር ብዙ ጥያቄና ብዙ መልስ የምናገኝበትም ነው።

በዚህ አጋጣሚ በቴአትሩ ውስጥ ቀላል የሚመስሉ ነገር ግን መሰረታዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ስህተቶችን መጠቆም ይኖርብናል።  የመጀመሪያው ስህተት ክብሬ (ካሌብ ዋለልኝ) ፍቅረኛው እሴተ ውጪ ልታድር በሄደችበት ምሽት በተሰራው ትዕይንት ላይ የተከሰተ ነው።  በወቅቱ ወደግሮሰሪ ለመስከር ስሄድ አድርጎት የነበረውና በቀጣዩ ትዕይነት ራሱን እስኪስት ጠጥቶና ሰክሮ ሲመጣ የለበሰው ልብስ ፍፁም የተለያዩ መሆኑ  ነገሩ እንዴት ነው? (ወይስ ሌላ ቀን ነው?) እንድንል ያስገድደናል።  ነገሩ የሆነው በዛው ምሽት ስለመሆኑ ግን የታሪክ ፍሰቱ ይነግረናል።  እናም በፊልሞቻችን የሰለቸነው “የኮንቲኒቱ” ችግር እንዳይደጋገም ትኩረት እንላለን።

ሁለተኛውና በትኩረት ለሚመለከት ተመልካች ግራ የሚያጋባው “የቀለበት” ነገር ነው።  ክብሬ (ካሌብ ዋለልኝ) ሙሉ ቴአትሩን የትዳር ልሙጥ ቀለበት አድርጎ ይታያል።  በአንጻሩ ደግሞ ሚስቴ ናት የሚላት እሴተ (መስከረም አበራ) ጌጥ እንጂ ቀለበት አናይባትም።  ተመልካችን ከማሳሳት በመሳሰሉ ምን ይላቸዋል? ጥያቄ የሚፈጥሩ ክስተቶች ሁሉ የቴአትር ተመልካችን መፈታተናቸው የበዛ ነውና አሁንም ትኩረት እንላለን። . . . መልካም የመዝናኛ ሳምንት !!!n

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
15504 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us