“የኢትዮጵያ ባህልና ሙዚቃ በሚገባው ደረጃ አልተዋወቀም”

Wednesday, 30 December 2015 13:43

 

 

ፕሮሞተር - ይስሃቅ ጌቱ

 

በሙያው አንጋፋ ፕሮሞተር ነው። ከ10 ዓመታት ላላነሰ ጊዜ የኢትዮጵያን ባህልና ሙዚቃ በተለያዩ የዓለም አገራት በማስተዋወቅና ለሙዚቀኞችም ምቹ አጋጣሚን በመፍጠር ይታወቃል፤ አቶ ይስሃቅ ጌቱ።

ተወልዶ ያደገው በደቡብ ክልል ውስጥ ሲሆን፤ ሐዋሳና ይርጋለም እድገቱንና ትምህርቱን አጠንክሮ የቆየባቸው አካባቢዎች ናቸው። “በሥርዓት በሚያምን ጀግና ቤተሰብ ውስጥ ነው ያደኩት” የሚለው አቶ ይስሐቅ፤ የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ በባህር ኃይል ውስጥ ሰልጥኖና ተቀጥሮ ስራ መጀመሩን ይናገራል። ይህ የባህር ጉዞ በህይወቱ የተለየን አጋጣሚ ስለመፍጠሩ የሚናገረው አቶ ይስሃቅ፤ ሆላንድ አገር በነበረው ቆይታ አንዲት ሆላንዳዊት አፍቅሮ በትዳር መኖሩንና ሁለት ልጆችም መውለዱን ይናገራል።

ጠቅልሎ ወደ ፕሮሞተርነት በመግባት የኢትዮጵያን ባህልና ሙዚቃን ማስተዋወቅ የጀመረውም ያን ጊዜ እንደሆነ የሚናገረው ይስሃቅ፣ “በወቅቱ በሆላንድ ቆይታዬ ለአራት ዓመታት በተማርኩበት (Public Administration) የህዝብ አስተዳደር ዘርፍ በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ስሰራ ቆይቼ፤ ባለቤቴ የደህና ቤተሰብ ልጅ ስለነበረችና እኔም ትንሽ ሳንቲም ስለያዝኩ ሁለት ሬስቶራንቶችን መክፈት ቻልኩ” ይላል። “ኒው ላይት” እና “ላይት ኦፍ አፍሪካ” በተሰኙት ሁለት ሬስቶራንቶች ውስጥ በሚጫወቱት ሙዚቃዎች ኢትዮጵያን ማስተዋወቅ “ሀ” ብሎ የጀመረ ስለመሆኑ የሚናገረው ፕሮሞተር ይስሃቅ፤ ከሬስቶራንቶቹ ታዳሚዎች በመነጨ ሀሳብ የተለያዩ እውቅ የሀገራችንን ድምፃዊያን ወደሆላንድ በማስመጣት ማጫወት መጀመሩን ያስታውሳል።

በወቅቱ አንጋፋና ዝነኛ ከነበሩት ድምፃዊያን መካከል አስቴር አወቀ፣ ጥላሁን ገሠሠ፣ መሐመድ አህመድ፣ ፀሐዬ ዮሐንስ፣ ሐመልማል አባተና ነዋይ ደበበን ጨምሮ በርካቶች መድረክ አግኝተው በውጪ ያለውን ኢትዮጵያዊና ቋንቋውን የሚያውቅ ፈረንጅ ሁሉ የሚያስደስት ስራ ስለመስራታቸው ይናገራል። ከሁሉም ግን “የህዝብ ለህዝብ” ስራ የሆላንድ ቆይታቸው የማይረሳ እንደነበር ሲያስታውስ፣ “በሆላንድ ቆይታቸው የህዝብ ለህዝብ ዝግጅትን በተመለከተ የኤርትራ ሰዎች የደርግ መራሽ ፕሮግራም እዚህ ሀገር አይካሄድም ባሉበት ወቅት ይህ የሀገር እንጂ የደርግ ጉዳይ አይደለም በማለት አግባብቼ ፕሮግራሙ በሆላንድ ሀገር በሰላም እንዲፈፀም የተቻለኝን አድርጌያለሁ” ይላል።

የአስቴር አወቀን አቅም ያየበትንና ሼህ መሐመድ ሁሴን ዓሊ አል አሙዲንን የተዋወቀበትን አጋጣሚ አስመልክቶ ሲናገርም፤ “በሆላንድ ከአስቴር ጋር እየሰራን ባለበት አጋጣሚ ሼህ አልአሙዲ ከእንግሊዝ በግል አውሮፕላን መጥተው በተለየ ጥበቃና መስተንግዶ ተስተናግደዋል። ያ አጋጣሚ ሼህ አልአሙዲንን ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወኩበት ከመሆኑም አልፎ ብዙዎች እኔን ያወቁበት ሁኔታን ፈጥሮልኛል። በወቅቱ ሼህ አልአሙዲ እንግዳችን ሆነው በመስተናገዳቸው ደስ ይለኛል” ሲልም የነበረውን ክስተት ያስታውሰዋል። ያን ዕለት አስቴር አወቀ ባልተለመደ መልኩ ወደ 20 የሚደርሱ ዘፈኖቿን ከመጫወቷም በላይ ታዳሚው በሙሉ የተዝናናበት ደማቅ ዝግጅት እንደነበርም ያስታውሳል።

በፕሮሞተርነት ከበርካታ አንጋፋ ድምፃዊያን ጋር ስለመስራቱ የሚናገረው አቶ ይስሃቅ ጌቱ፤ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስም በሌላው ዓለም አይቶ የወደደውንና የኢትዮጵያን ሙዚቃ ያሳድጋል ሲል ያሰበውን “የኢትዮጵያ አይዶል” ኀሳብ ማምጣቱን ይናገራል። በአሁኑ ወቅትም ከኮካ-ኮላ ሱፐር ስታር ጋር በመሆን ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣቶች ለማውጣት እየሰራሁ ነው ቢልም ያሰበውን ያህል እንዳልሄደለት አልሸሸገም።

የኢትዮጵያን ሙዚቃ እንደተቀሩት የአፍሪካ አገራት በመላው ዓለም በሚገባ ማስተዋወቅ አለብን የሚለው አቶ ይስሃቅ፤ በሙዚቃና በውዝዋዜ ዘርፍ በርካታ ወጣቶች ከፖሊስ ኦርኬሰትራ እስከ ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ድረስ ተቀጥረው የስራ ዕድል እንዲያገኙ ስለማስቻሉም ይናገራል። በአሁኑ ወቅት በጋራ እየሰራው የሚገኘው “የኮካ-ኮላ ሱፐር ስታር” ዝግጅት አመታትን ለምን አስቆጠረ ስንል ላነሳንለት ጥያቄ ፕሮሞተር ይስሃቅ ሲመልስ፤ “የበጀት እጥረት ነው” ይላል።

በቀጣይም የኢትዮጵያን ባህልና ሙዚቃ ለማስተዋወቅ እየሰራ ስለመሆኑ የሚገልፀው አቶ ይስሃቅ፤ “የኢትዮጵያ ባህልና ሙዚቃ በሚገባው ደረጃ አልተዋወቀም” ባይ ነው። “ከውጪ ስመጣ እሰራዋለሁ ብዬ ያቀድኩትን ፕሮጀክት በመነጠቄ በወሰደው ሰው ሳይሆን ፕሮጀክቴን አሳልፎ በሰጠው ሰው ላይ በጣም አዝኛለሁ” ሲልም ስላጋጠመው መሰናክል ይናገራል። በሙዚቃው አካባቢ አሁንም ድረስ አንዱ አንዱን ለመጣል የሚሄድበት አጉል አካሄድ መኖሩን በሐዘኔታ የሚናገረው አቶ ይስሃቅ፤ ቢሆንም የተቻለኝን አድርጌ የሀገሬን ባህልና ሙዚቃ አስተዋውቃለሁ ባይ ነው።

“ኢትዮጵያ ከችግሯ ባሻገር ሊታወቅላት የሚገባ ብዙ ሃብት አላት” የሚለው አቶ ይስሃቅ፤ በቅርቡ የኢትዮጵያን ባህልና ሙዚቃ ጨምሮ ምርቶች፣ ቅርሶችና እሴቶቻችንን ለማስተዋወቅ ከ20 ያላነሱ አገራትን የሚዞር “የሉሲ ዓለም አቀፍ ጉዞ ለኢትዮጵያ ንግድና ባህል ኤግዚቢሽን” የተሰኘ ዝግጅት ሊያካሂድ እንደሆነ ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል። “አንድን ሰው ከችግር ማውጣት ታላቅ የመንፈስ እርካታ ይሰጠኛል” የሚለው አቶ ይስሃቅ፤ አገራችን ብዙ ሃብት ያላት ሆና ባለመተዋወቋ ብቻ ሳንጠቀምበት መቅረታችን ሁሌም እንደሚያስቆጨው ደጋግሞ ይገልፃል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
11114 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us