“እልባት” በሕግ እና በይሉኝታ መካከል

Wednesday, 13 January 2016 14:23

 

 

የቴአትሩ ርዕስ - “እልባት

ድርሰት - ዳንኤል ሙሉነህ

ዝግጅት - አለአዛር ሳሙኤል

ረ/አዘጋጅ - ኤልያስ ደጀኔ

ተዋንያን - ኤፍሬም ልሳኑ፣ ህሊና ሲሳይ፣ ኤልያስ ደጀኔ እና ጌትነት

መድረክ ግንባታ- ዘሪሁን ተረፈ እና አየለ እሸቴ

መብራት - ብስራት ከበደና አካለ ገብሬ

ድምፅ - ቦጋለ ታደሰ

አልባሳት - ፋናዬ ወርቁ

ድንገት ባጋጠመው አደጋ ለመትረፍ ምክንያት ከሆነችው ሴት ቤተልሄም (ህሊና ሲሳይ) ጋር በይሉኝታ ፍቅር የጀመረው ሳሙኤል (ኤፍሬም ልሳኑ) ከዓመታት በኋላ የልጅነት ፍቅረኛውን ሲያገኝና ፍቅር ሲያገረሽ የሚያሳይ ቴአትር ነው፤ በአንጋፋዎቹ ባለሙያዎች ዳንኤል ሙሉነህ ተፅፎ፤ በአልአዛር ሳሙኤል የተዘጋጀው “እልባት”።

ከአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ መዘጋት ጋር ቆይቶ በድጋሚ ለመድረክ የበቃው ይህ ቴአትር፤ በአራት ትዕይንቶች ተከፋፍሎ በአራት ተዋንያን ለ1 ሰዓት ከ40 ደቂቃ ዘወትር አርብ አመሻሽ ላይ ለዕይታ የሚበቃ ትርጉም አዘል ስራ ነው።

ሳሙኤልን (ኤፍሬም ልሳኑ) አግብታ ለመኖር ህልሟ የነበረውና በሆስተስነት የምትተዳደረው ቤተልሄም (ህሊና ሲሳይ) በድንገቴ ደስታ ቤቱን አጥለቀልቀዋለው ብላ በማሰብ ከሄደችበት የመመለሻዋን ቀን አሳስታ በመናገር፤ ሳሚን በልደቱ ቀን ደስታ ልትፈጥርበት የያዘችው ውጥን ድንገት ሲሰበር ይታያል። ሳሙኤል በቀድሞ ፍቅረኛው ቤዛ (ሃና ጌትነት) ጋር በአንድ ቤት ሰክረው ማግኘቷ ቴአትሩን በጡዘት እንዲጀምር አድርጎታል።

“በዚህ ዘመን ደስተኛ ሰው ማየት በራሱ ያስደስታል” የሚለው ሳሙኤል፤ የራሱን ደስታና ፍቅር በይሉኝታ ገብሮ ሲሰቃይ ማየት የቴአትሩ ውጥረት ቋጠሮ ነው። “ፍቅር በፍቅር እንጂ በይሉኝታ አይሆንም” የምትለው ቤተልሄም፤ ሳሙኤልን ታግሳ የራሷ ለማድረግ ብትሞክርም ፈተናዋ በዝቶ የምትከፍለው መስዋትነት የተውኔቱ መጨረሻ አስደሳች “እልባት” እንዲያገኝ አስችሎታል። ያም ሆኖ እጮኛዋ እንደሚለው ጊዜው “ዘመነ እኔ ነው” የሚባል ቢሆንም አንዳድ “ሰው” አለ እንድንል ተስፋን አሳይቶናል።

በድሮ ፍቅረኛው ተከድቻለሁ ብሎ በማሰብና በአሁኗ እጮኛው ውለታ መካከል የሚዋልለው ሳሙኤል፤ መልህቋ እንደተበጠሰ መርከብ ሲንገለታ ማየቱ፤ የቤዛና የቤተልሄም ግብግብ፤ የልዑል (ኤልያስ ደጀኔ) ሰግብግብነትና የወሬ ወንፊትነት የተውነቴ ውበት ሆኖ ተመልካችን ያጫውታል።

ሳትፈልግ ባለሀብት እንደተዳረለት የምትናገረው ቤዛ (ሃና ጌትነት) ከውጪ ሀገር ቆይታው በኋላ የድሮ ፍቅረኛዋን ፈልጋ መልሳ የራሷ ለማድረግ ስትሞክርና እርሱም በአዲሷ እጮኛው አስቦ ሊርቃት ሲጥር ማየት የታሪኩን ንዳድ ማረገቢያ ይመስላል። አሁን ድረስ እንደሚወዳት እርግጠኛ የሆነች የምትመስለው ቤዛ፤ የሳሙኤልንና የእጮኛውን ቤተልሄምን ግንኙነት፤ የምትገልፀው “ፍቅር በይሉኝታ አይመሰረትም። . . . አንተ ለእሷ (ለቤተልሄም) ያለህን ክብር እንጂ ፍቅር አላየሁም” ስትል የስሜቱን ምሽግ ልታፈርሰው ስትታገል እናያለን።

በሌላ በኩል ደግሞ አግብቷት ወደውጪ የወሰዳት የቤዛ ባል ልዑል (ኤልያስ ደጀኔ)፤ ፍቅር እያቃዣት አእምሯዋን ቢፈታተነው ጊዜ ለፀበል በሚል ወደሀገር ቤት ይዟ ቢመጣም ያልጠበቀው ነገር ገጥሞት ሲፈተን እናያለን። ክብር ካለው ቤተሰብ ተገኝቻለሁ፤ ተምሬያለሁና የተሸለ ሀብት አለኝ ብሎ የሚያምነው ልዑል (አልያስ ደጀኔ) ቤዛ ልቧ መሸፈቱን ቀድሞ ቢረዳም የሚያጣው ፍቅርና ትዳር ሳይሆን ከፍቺ በኋላ የሚያካፍላትን ሀብት ሲያስበው ጭንቁ መሆኑን ማየት ብዙ ስላቅ ያለው ነው። የሁለቱ ባለትዳሮች ዕድሜም ሆነ ባህሪ አለመጣጣሙ የፍቺውን ሩጫ ዙር እያከረረ ሲሄድ እንመለከታለን። “መግባባት ሳይኖር መጋባት ግራመጋባት ነው” ሲል የሚሳለቀው ልዑል፤ ደራሲውና አዘጋጁ የቴአትሩ ማዋዣ አድርገው ያስቀመጡት ገፀ-ባህሪይም ጭምር ነው።

በ“እልባት” ቴአትር ውስጥ ከፍታ የስሜት ጣራን ማሳያ ሆኖ ቀርቧል። ለምሳሌም የቀድሞ ፍቅረኞቹ ሳሚ እና ቤዛ በተገናኙበት ቀዳሚ ትዕይንት ሁለቱን ሰዎች ጠረጴዛ ወለል ላይ አይተናቸዋል። (ይህ የፍቅር ስሜት ከፍታን የሚያሳይ ነው ሊባል ይችላል) ሁለተኛው ደግሞ የቤዛ ባለቤት ልዑል እና የቤዛ የልጅነት ፍቅረኛ ሳሚ በተገናኙበት ወቅት የቃላት ንትርኩ ወደአካል ንክኪ ከመለወጡ በፊት ሳሙኤል እንግዳው የተቀመጠበት ሶፋ ላይ በንዴት ዘሎ ሲወጣ እንመለከታለን። (ይህ ደግሞ የቁጣ ስሜትን ከፍታ ማሳያ አድርገን ልንወስደው እንችላለን) “እልባት” ቴአትር በቀላል ዝግጅትና በምርጥ አተዋወን የቀረበ ስራ ነው።

“እልባት” በመድረክ ቆይታው የስነልቦና ትርምስን፣ የፍቅር መጠማትን፣ የራስን መስጠትንና ራስን ላለማጣት የሚደረጉ የህይወት ትግሎችን ሁሉ ያሳየናል። “እልባት” ያነሳቸውን ጉዳዮች በመፍትሄ ለመቋጨት የሞከረ ቴአትር ነው።

ከባህሪዋ ውጪ ወጥታ በስካር የምታስመስለው ቤተልሄም፤ የሳሚንና የቤዛን ጥምረት ለማደስ ስትል የምትከፍለው መስዋዕትነት በትልቁ የሚታይበት “እልባት” አንዱ በይሉኝታ ሌላኛው በሕግ የታሰረበትን የፍቅርና የትዳር ህይወት መጨረሻ በወጉ ማሳየት የቻለ ቴአትር ነው። መልካም የመዝናኛ ሳምንት ይሁንላችሁ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15026 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us