በ12 ቋንቋዎች ምሥጋናን በበገና “ሳንታ ማሪያ”

Friday, 22 January 2016 12:32

 

 

ቋንቋን ከመናገር ባለፈ የሕግ አቅሙን የፈተንበትና የምሥጋና ዝማሬውን ያቀነቀነበት ባለተሰጥኦ ነው። የዛሬው እንግዳችን ሃያ ሁለት ቋንቋዎችን መናገር የሚችል ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል በቅርቡ “ሳንታ ማሪያ” በሚል በአስራ ሁለት የዓለማችን ቋንቋዎች ያዘጋጀውን የበገና መዝሙር እነሆ ሊለን ተቃርቧል። ይህ የብዙ ቋንቋዎች ተናጋሪ፣ አስተርጓሚ፣ አስጎብኚ፣ መምህርና ሼፍ እንግዳችን ካሱ ሰቦቃ ይባላል።

“የልጅነት ዘመኔ በፈተና የተቃኘ ነው” የሚለው ካሱ፤ እናቱ ገና የስድስት ወር ጨቅላ እያለ ትታው መሄዷን ይናገራል። ከአባቱ ጋር በአሰብና በምፅዋ የቆየ ሲሆን፤ ገና በለጋ የወጣትነት እድሜው ካስጠጉት ሰዎች ሳይርቅ በጅማና ጊቤ በረሃ አካባቢ ከአውራ ጎዳና ባለሙያዎች ጋር በመሆን የመንገድ ስራን ይሰራም እንደነበር ይናገራል።

ካሱ በትምህርት አለሙ የታሪክ ትምህርትን በእጅጉ ይወድ እንደነበር ይናገራል። በተለይም አንጋፋው የታሪክ ፀሐፊ ተክለፃድቅ መኩሪያ የፃፏቸውን መፅሐፍት ደጋግሞ በማንበብ የታሪክን ጠዓም ያጣጥም እንደነበር አይረሳም። “ታሪክ ማንበብ ይመስጠኛል” ባይ ነው።

የልጅነት መሠረቱን የጣለለት የህንድ ኮሚኒቲ መምህሩ ኮነ ለቋንቋ ያለውን ልዩ አቅም ተረድቶ ይረዳው እንደነበር የሚናገረው እንግዳችን፤ እንግሊዝኛ ከማንበብ፣ ከመፃፍና ከመናገር ባለፈ ለአራት ዓመታት የፈረንሳይኛ ቋንቋን እንዲማር ከአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ ጋር እንዲገናኝ በማድረግ የነበረውን ውለታውን አስታውሶ ያመሰግናል።

የቋንቋ ችሎታውን ለማዳበር ከማንበብና የተለያዩ የሰዋሰው መፅሐፍትን ከማጥናት በዘለለ የኤምባሲዎችን ደጃፍ ያንኳኳም እንደነበር ያስታውሳል። በዚህ ሂደት ውስጥ በተለይም የአረብኛ ቋንቋ ለመማር ቁርአንን ከማጥናት ባለፈ መስጂድ ድረስ በመዝለቅ ትምህርቱን ይከታተል እንደነበር ይናገራል። ከሁሉም በላይ ግን አቀላጥፎ የሚናገራቸው ሃያ ሁለት ቋንቋዎች ለመልመድ አዘውትሮ ከሚጠቀምባቸው ቴክኒኮች መካከል በአፅንኦት የሚናገረው፣ በቀን ውስጥ ሶስት በወር ደግሞ 90 ቃላትን ማጥናቱ እንደነበር ይናገራል። ካሱ ከቃላት ጥናቱ በተጨማሪ የቋንቋውን ሰዋሰው በሚገባ እንደሚጠቀም ይህም በእጅጉ እንደረዳው ይናገራል።

የዩኒቨርስቲ ደጃፍ አልረገጥኩም የሚለው ካሱ፤ በአሁኑ ወቅት በርካታ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ቋንቋቸውን ለማሻሻል ወደእርሱ ዘንድ እንደሚመጡ ይናገራል። ከዚያም ውስጥ አብዛኛዎቹ ቻይንኛን ለመማር እንደሚመጡ አስታውቋል። ከኮሌጅና ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በተጨማሪም አትሌቶች፤ ባለሥልጣናትና ዝነኛ ሰዎችም ለግል ደንበኞቹ እንደሆኑ ይገልፃል።

ቋንቋን ከማስተማርና ከማስተርጎምም ባለፈ፤ ከፌዴራል ፖሊስና ከፍርድ ቤቶች የምስጋና ደብዳቤ እየጎረፈለት የሚገኘው ካሱ፤ በአዲስ አበባ የተለያዩ አገራት ዜጎች የመኖራቸውን ያህል የፍትህ ስርዓቱን ለማቀላጠፍ በትርጉም እያደረገ ያለው እገዛ ከፍ ያለ ነው። ቋንቋን መናገር ብቻውን ሕግንና መንፈሳዊ ሀሳቦችን ለመረዳት በቂ ነው ወይ በሚል ለቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ፤ “ስለኔ የቋንቋ ችሎታ ለማውራት ብዙ ቀናት አይበቁንም። እኔ ወደዚህች ምድር ስመጣ ያለምክንያት እንዳልመጣሁ አምናለሁ። ተሰጥኦ በትምህርት ከምታገኘው ዕውቀት በላይ ነው። አንዳንድ ጊዜ በፍርድ ቤት ጉዳያቸውን የማስተረጉምላቸውን የቻይና ወይም የስፓኒሽ ዜጎች እናንተ ቋንቋችሁን በደንብ አትችሉም የምልበት አጋጣሚ አለ። ለሁሉም ቦታ የሚሆን የቋንቋ አገባብ የሚያሳይ መፅሐፍ አለኝ። ለፍርድ ቤት፣ ለአስጎብኝነት፣ ለስብከት የሚሆኑ የቃላት አጠቃቀሞችን ለይቼ አጥንቼ ነው የምቀርበው” ሲል የቋንቋ አጠቃቀሙ እንደቦታውና እንደሁኔታው እንደሚሆን ያስረዳል።

በተለይ የምታስታውሰው ቋንቋ የቱ ነው? ስንል ላነሳንለት ጥያቄም ሲመልስ ፖርቹጊዝ እንጀራዬን መጋገር የጀመርኩበት ቋንቋ በመሆኑ በተለይ አልረሳውም ይላል። ለዚህም ከዓመት በፊት ጋዜጠኛ ነቢል መሀመድ በሸገር ኤፍ ኤም አንድ ፕሮግራም ሰርቶልኝ ነበር። የፖርቹጊዝ መፅሐፍና ሲዲ እያጠናሁ መሆኔን ስናገር የሰሙ የአየር መንገድ ሰዎች ስልኬን አፈላልገው አገኙኝ።” የሚለው ካሱ በተለይም በፖርቹጊዝና በስፓኒሽ ቅልቅል ተናጋሪዎች ምክንያት የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ሁነኛ ሰው ሆኖ መቅረብ እንዳስቻለው ይናገራል።” በወቅቱ በአየር መንገድ በኩል ወንጀለኞች ተይዘው ማዕከላዊ ቀርበው በፍርድ ቤት ቃላቸውን ሲሰጡ ለመጀመሪያ ጊዜ በችሎት ማስተርጎምን የጀመርኩት ያኔ ነው” ይላል። የቋንቋ ጠቀሜታ የትየለሌ ቢሆንም በማህበረሰባችን ዘንድ ግን ቋንቋን ለማወቅ ያለው ፍላጎት በጣም በራድ ነውም ሲል ይተቻል።

በቅርቡ “ሳንታ ማሪያ” በሚል ለአድማጭ ጆሮ የሚያደርሰውና በአስራ ሁለት ቋንቋዎች የተዘጋጀው የበገና መዝሙር የኢትዮጵያን የበገና ዜማ ለውጪው ዓለም ለማስተዋወቅ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል ተብሎለታል። በግዕዝ፣ በኦሮምኛ፣ በአማርኛ፣ በጀርመንኛ፣ በፈረንሳይኛ፣ በእብራይስጥ፣ በአረብኛ፣ በግሪክኛ፣ በስፓኒሽ፣ በቻይንኛ፣ በጣሊያንኛ እና በምልክት ቋንቋ ተዘጋጅቶ የቀረበው ይህ ቪሲዲ የፊታችን ጥር 21 ቀን 2008 ዓ.ም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ይመረቃል።

“በገናን በ12 ቋንቋ እንደምጫወተው ዛሬ እውን ይሁን እንጂ ቀደም የተፃፈልኝ ነው ብዬ አምናለሁ። በገናን በተለየ ያስመረጠኝ ህይወቴ በራሱ የተመስጦ እና የፅሞና መሆኑ ነው። በገና የፅሞናና የተመስጦ መሳሪያ ነው። እኔ ፀጥ ያለ ህይወት ነው የምኖረው። ነገር ግን አንድ ወቅት በነቢል ፕሮግራም ላይ የተላለፈውን መልዕክት የሰሙ ሰው ወደኔ ስልክ ደወሉልኝ። “ ሲል በገና የመማር አጋጣሚው እንዴት እንደተፈጠረ ያስረዳል “እኔ ቋንቋ የማስተምረው በግል ለሚመጡ ሰዎች ነው። ያኔ ታዲያ መምህር ሲሳይ ደምሴ የተባሉ ከያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ደውለው ቋንቋ በግል እንዳስተምራቸው ጠየቁኝ” ሲል በገናን ለመማር ሰበብ የሆነለትን አጋጣሚ ያስታውሳል።” እርሳቸው    ቋንቋ ሊማሩ ሲመጡ፤ እኔ ደግሞ በገና እንዲያስተምሩኝ ጠየኩ” ይላል። በገና ከባድ መንፈሳዊ መሳሪያ መሆኑን ያወኩበት አንድ አጋጣሚ በመጀመሪያው ቀን ተከስቷል የሚለው ካሱ፤ በኢንፎኔት ኮሌጅ አንድ ክፍል ውስጥ በገናውን ይዤ ስልጠናውን ስጀምር ያላሰብነው እሳት ከጣሪያ ላይ ተከሰተ ሲል ያስታውሳል። ይህን ተዓምር ባየበት በዚያን ቀን አንድ ቃል ስለመግባቱም ይናገራል፤ ይህውም በበገና የተዜመና በ12 ቋንቋዎች የተዘጋጀ የምስጋና ዝማሬን መስራት እንደነበር አሁን ላይ ያስታውሳል።

በሶስት ወር ስልጠና የበገና ችሎታውን የገነባው ካሱ፤ በገናን ከመቃኘት ባለፈ የበገናን አሰራርና የክሩን አይነት መመርመር ጀመርኩ ይላል። “በገናን በተመለከተ ሙሉ ሰው ለመሆን ብዙ ለፍቻለሁ። እውነቱን ለመናገር አንድ ቋንቋ ከመልመድ ይልቅ የበገናን ክሮችን ቅኝት ማስተካከል በእጅጉ ፈትኖኛል” ሲልም የነበረውን ተግዳሮት ይናገራል።

“በባህሪዬ ፈጣንና ላደርግ ያሰብኩን ነገር ካልፈፀምኩ እንቅልፍ አይወስደኝም” የሚለው ካሱ፤ ጥንታዊውን የበገና ያሬዳዊ ዝማሬ በ12 ቋንቋዎች ተርጉሞ ለመስራት ሲነሳ ከመምህራኖቹ ጭምር “ይቅርብህ” የሚል ሃሳብ ቀርቦለት እንደነበር ይናገራል። በተለያዩ ቤተክርስቲያኖችና አዋቂዎች (አባቶች) በሚቀርብለት ግብዣ ስራውን ለመስራት ሲነሳ በየቋንቋዎቹ መንፈሳዊና ልከኛ ቃትን በመፈለግ ብዙ ስለመድከሙ ይናገራል። “የያሬድ ዝማሬን በበገና የሚያቀርቡ በርካታ ሊቃውንት በታሪክ ቢኖሩም ለዚህ ትውልድ ቅርብ ናቸው የምላቸው መምህር ግን አለሙ አጋ ናቸው” የሚለው ካሱ፤ “እርሳቸው በበገና የምስጋና ዝማሬን ለፈረንጆች ሲያቀርቡ በእንግሊዝኛ ስለዝማሬው ይዘት ከተናገሩ በኋላ በአማርኛ/ በግዕዝ መዘመራቸውን በዓለም ሚዲያዎች በኩል ስመለከት ለምን እኔ ለውጪዎች ሰዎች በራሳቸው ቋንቋ ዝማሬውን ሰርቼ አላቀርብም የሚል ጉጉት አድሮብኛል” ሲል መነሻ ስለሆነው ነገር ይናገራል።

በ“ሳንታ ማሪያ” የበገና ዝማሬ ስራው ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ የተባበረውን ዘማሪ ይልማን በእጅጉ አመስግኗል። በስራዎቹ ውስጥ የቋንቋ ልዩነት እንጂ የአገራቱን ስም በቋንቋቸው በራሳቸው እንዲሆን ተደርጎ ተሰርቷል። ለምሳሌ እስራኤላዊያን የንሰሐ መዝሙርን፤ ፈረንሳዊያን ጌቴ ሰማኔን በመዝሙራቸው ውስጥ ስለሚወዱ እንደነሱ ፍላጎት አድርጌ ሰርቼዋለሁ ሲልም ስለዝመሬው ይዘት ይተነትናል።

ይህ “ሳንታ ማሪያ” የተሰኘው የዝማሬ አልበም፤ በምስልና በድምፅ ተሰርቶ ከመቅረቡ አንጻር፤ በቅዱስ ያሬድ በገና ፈጣሪን ከማመስገኛነቱ ባለፈ ሀገሬን ለማስተዋወቅና ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቦታዎችን በማስተዋወቅ ቱሪስቶችን ለመሳብ እንገለገልበታለን ሲል ስለአልበሙ ጠቀሜታ ያብራራል።

በቋንቋ ማስተማር፤ ማስተርጎም፣ በበገና ዝማሬና በምግብ ዝግጅት ስራው በበርካቶች ዘንድ አድናቆት የተቸረው ይህ ባለሙያ፤ አለኝ በሚለው ትርፍ ሰዓት መዝናኛውን የሚያደርገው ከዕውቀት ጋር ነው። ብዙ ጊዜ ገድላትን በማንበብ የመንፈስ መሞላትና የአባቶችን ታሪክ ማንበብ በጣም የምደሰትበት ነው ይላል።

“ራሴን መገደብ በተፈጥሮዬ አልወድም” የሚለው ካሱ፤ ወደፊትም በተመሳሳይ የቅዱስ እዝራ ዝማሬን ሰርቼ በተለያዩ የዓለማችን ቋንቋዎች አቀርባለሁ። ይህንንም ለዓለም በማስተዋወቅ የድርሻዬን ለሀገሬና ለአለም አበረክታሁ” ሲል የበርካታ ችሎታዎች ባለቤት የሆነው ካሱ ሰቦቃ ተስፋውን ይገልፃል።        

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
10519 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us