የጉማ ሽልማት የመጨረሻ ዕጩዎች ታወቁ

Wednesday, 27 January 2016 12:29

 

ሁለት ሽልማት ዓመታትን ያሳለፈው ጉማ የፊልም ሽልማት ፕሮግራም ዘንድሮም ለ3ኛ ጊዜ የካቲት 21 ቀን 2008 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በድምቀት እንደሚካሄድ አዘጋጆቹ ተናግረዋል። በአስራ ሰባት ዘርፎች የመጨረሻ ሆነው የቀረቡትን ዕጩዎች ባሳለፍነው ሰኞ ጥር 16 ቀን 2008 ዓ.ም በጎልደን ቱሊፕ ሆቴል በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ ሆነዋል።

እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በጉማ ፊልም ሽልማት የዘንድሮ የህይወት ዘመን ተሸላሚ ሆነው የተመረጡት አንጋፋዋ ተዋናይት ክብርት ወ/ሮ አስካለ አመነሸዋ ናቸው። ወ/ሮ አስካለ አመንሸዋ በመድረክ ቴአትሮች፣ በቲቪ ድራማና በመጀመሪያው ልቦለድ ፊልም “ሂሩት አባቷ ማነው?” ላይ በመተወን ይታወቃሉ።

 

የጉማ ፊልም ሽልማት የዘንድሮ የመጨረሻ ዕጩዎች

ለ3ኛው ዙር የጉማ ፊልም ሽልማት በዕጩነት ከቀረቡት 26 ፊልሞች መካከል በ17 ዘርፎች በዳኞች ዕይታ የተመረጡት 22 ፊልሞች ሲሆኑ አራት ፊልሞች ግን በየትኛውም ዘርፍ ለመጨረሻ ዕጩነት መቅረብ ሳይችሉ ቀርተዋል። ለዕጩነት ተወዳድረው የመጨረሻውን የዕጩነት ዕድል ያላገኙት ፊልሞች ደግሞ “ጥለፈኝ”፣ “የሐምሌ ሙሽራ”፣ “ፍቅር በአዲስ አበባ” እና “የበኩር ልጅ” የተሰኙት ስራዎች ናቸው።

በ120 ዳኞች ተገምግመው በመጨረሻው ዙር የዕጩ ድልድል ውስጥ ገብተዋል የተባሉትን የካቲት 21 ቀን ይፋ በሚደረገው መድረክ ላይ ለአሸናፊነት የሚጠበቁት ስራዎች ደግሞ የሚከተሉት ሆነዋል።

በተለያዩ ዘርፎች በብዛት ዕጩ ሆኖ በመቅረብ ቀዳሚነቱን የያዘው የዳይሬክተር አንተነህ ኃይሌ ፊልም የሆነው “ላምባ” ሲሆን፤ በምርጥ ፊልም፣ በምርጥ ዳይሬክተር፣  በምርጥ የተመልካች ምርጫ፣ በምርጥ የፊልም ፅሑፍ፣ በምርጥ ሙዚቃ፣ በምርጥ ረዳት ተዋናይት፣ ተስፋ በሚጣልበት ተዋናይት፣ እንዲሁም በወንድና ሴት ምርጥ ዋና ተዋንያን ዘርፍ ታጭቷል።

በመቀጠል በስምንት ዘርፎች የመጨረሻ ዕጩዎችን ምድብ የተቀላቀለው ፊልም “ዓለሜ” ሲሆን፤ በምርጥ ፊልም፣ በምርጥ ዳይሬክተር፣ በምርጥ ሲኒማቶግራፊ፣ በምርጥ የፊልም ፅሑፍ፣ በምርጥ ድምፅ፣ በምርጥ ወንድ ተዋናይ፣ በምርጥ ረዳት ወንድ ተዋናይና ተስፋ በሚጣልባት ተዋናይት ዘርፎች ይወዳደራል።

በሰባት ዘርፎች በመታጨት ተከታዩን ስፍራ የያዘው ፊልም “ከዕለታት” ሲሆን፤ በምርጥ ፊልም፣ በምርጥ የተመልካች ምርጫ፣ በምርጥ ዳይሬክተር፣ በምርጥ ኤዲቲንግ፣ በምርጥ የፊልም ፅሑፍ፣ በምርጥ ዋና ተዋናይት እና በምርጥ ተስፋ የተጣለበት ተዋናይ ዘርፍ ተወዳዳሪ ሆኖ ቀርቧል።

“ኀርየት”፣ “አንድ ጀግና” እና “የፍቅር ዋጋው” የተሰኙት ፊልሞች እያንዳንዳቸው በአምስት ዘርፎች ዕጩ ሆነው ለመጨረሻው ዙር የሚወዳደሩ ሲሆን፤ በተለይም ሶስቱም በምርጥ ድምፅ ዘርፍ ይፎካከራሉ። “ኀርየት” ፊልም በምርጥ የፊልም ፅሑፍ፣ በምርጥ ስኮር፣ በምርጥ ድምፅ፣ በምርጥ ገፅ ቅብና በምርጥ ወንድ ተዋናይ ዘርፎ ታጭቷል። “አንድ ጀግና” ፊልም ደግሞ ለምርጥ ሲኒማቶግራፊ፣ በምርጥ ድምፅ፣ በምርጥ ገፅቅብ፣ በምርጥ መሪተዋናይ እና በምርጥ ረዳት ወንድ ተዋናይ ዘርፎች ታጭቷል። “የፍቅር ዋጋው” ፊልም በበኩሉ በምርጥ ፊልም፣ በምርጥ ዳይሬክተር፣ በምርጥ ሲኒማቶግራፊ፣ በምርጥ ኤዲቲንግ እና በምርጥ ድምፅ ዘርፎች መታጨቱ ተገልጿል።  

“ብላቴና”፣ “የመሀን ምጥ”፣ “የአራዳ ልጅ” እና “ሚስቴን ቀሙኝ” ፊልሞች በተለያዩ አራት ዘርፎች ለመጨረሻ የዕጩ ውድድር የቀረቡ ሲሆን፤ በምርጥ ስኮር፣ በምርጥ ሲኒማቶግራፊ፣ በምርጥ የተመልካች ምርጫ፣ በምርጥ ወንድ ተዋናይና በምርጥ ተስፋ የተጣባት ተዋናይት ዘርፎች ዕጩዎች ሆነው ቀርበዋል።

በሶስት ዘርፎች በመመረጥ የመጨረሻዎቹ ዕጩ ተወዳዳሪዎችን የተቀላቀሉት ፊልሞች “የፍቅር ቃል” በምርጥ ተስፋ የተጣለባት ሴት ተዋናይት፣ በምርጥ ኤዲቲንግ እና በምርጥ ዳይሬክተር ዘርፎች ተካቷል። “እናፋታለን” ፊልም ደግሞ በምርጥ ገፅ ቅብ፣ በምርጥ ድምፅ እና በምርጥ የፊልም ጽሑፍ ዘርፎች በዕጩነት ቀርቧል። ሌላው “ፍቅሬን ላድን” ፊልም ሲሆን፤ በምርጥ ዋና ሴት ተዋናይት፣ በምርጥ የፊልም ሙዚቃ እና በምርጥ የፊልም ፅሑፍ ዘርፎች ተወዳዳሪ ሆኖ በመጨረሻው የዕጩዎች ዝርዝር መካተቱን አዘጋጆቹ ተናግረዋል።

በሁለት ዘርፎች ዕጩ ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡት ፊልሞች አራት ሲሆኑ፤ “ፍቅርና ገንዘብ-2” በምርጥ ተስፋ የተጣለበት ተዋናይ እና በምርጥ የፊልም ሙዚቃ ታጭቷል። “እስከትመጪ ልበድ” ፊልም በምርጥ ሙዚቃና በምርጥ ስኮር የታጨ ሲሆን፤ “በመንገዴ ላይ” ፊልም ደግሞ በምርጥ ረዳት ተዋናይትና በምርጥ የተመልካች ምርጫ ዘርፎች የመጨረሻ ዕጩዎችን ተቀላቅሏል። ሌላው በሁለት ዘርፎች የታጨው ፊልም “የገጠር ልጅ” ነው፤ በምርጥ ስኮር እና በምርጥ ረዳት ተዋናይ ዘርፎች ይወዳደራል።

በአንድ ዘርፍ ብቻ በመታጨት የመጨረሻውን ዙር የተቀላቀሉት ዕጩ ፊልሞች “ሰኮ” በምርጥ ገፅ ቅብ፣ “ወንድሜ ያዕቆብ” በምርጥ ወንድ ተዋናይ፣ “አይገባንም” በምርጥ ተስፋ የተጣለበት ተዋናይ ዘርፍ፣ “ፍቅር ተራ” በምርጥ ረዳት ተዋናይ ዘርፍ እና “የወደዱ ሰሞን” በምርጥ ረዳት ተዋናይት ዘርፍ ዕጩዎች አቅርበዋል።

የካቲት 21 ቀን 2008 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ በሚካሄደው የሽልማት ዝግጅት ላይ በአስራ ሰባቱም ዘርፎች አሸናፊ የሆኑ ስራዎች በህዝብ ፊት የሚሸለሙ መሆኑንም አዘጋጁ ኢትዮ ፊልም ለሚዲያ ሰዎች ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ ከአምናና ከካቻምናው በተሻለ የሰዓትና የፕሮቶኮል ዝግጅት የደመቀ እንደሚሆንም ከወዲሁ ቃል ገብቷል

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
12050 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us