የመብት ሙግት “የቃቄ ውርድወት”

Wednesday, 03 February 2016 14:31

 

     በአገራችን መድረኮች ለተመልካች ዕይታ ይፋ ከሆኑ ጥቂት ታሪክ ቀመስ ቴአትሮች መካከል አንዱ ነው። ዘወትር እሁድ በ8፡30 ሰዓት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በመታየት ላይ ያለው “የቃቄ ውርድወት” ቴአትር።

ይህ ትውፊታዊ ቴአትር ብሔራዊ ቴአትር ከጉራጌ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የቀረበ ሲሆን፤ ደራሲው ጫንያለው ወ/ጊዮርጊስ፤ ያዘጋጀው ደግሞ ዳግማዊ ፈይሳ ነው። አድካሚ የዝግጅት ሂደትን እንዳለፈና ምስጉን ጥበባዊ ጥምረት በታየበት በዚህ ቴአትር ላይ ፍቃዱ ተክለማርያም፣ አልጋነሽ ታሪኩ፣ አብራር አብዶ፣ ፋንቱ ማንዶዬ፣ መስከረም አበራ፣ ይታገሱ መለስ፣ ሚኪ ተስፋዬ፣ ሕንፀተ ታደሰ፣ ሳሙኤል አካሉ፣ ትዕግስት ባዩ፣ ሽታዬ አብርሃ፣ ዳንኤል ተገኝ፣ ደስታ አስረስ፣ ራሄል ተሾመ፣ ምትኩ በቀለ፣ ፀጋዬ ብርሃነ፣ ኑረዲን ነስሮን ጨምሮ አንጋፋና ወጣት ተዋንያን በዋናነት፤ በአጠቃላይም ወደ100 የሚጠጉ ከያኒያን በቴአትሩ ላይ ተሳትፈውበታል።

በ1855 ዓ.ም አካባቢ በጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ እንደክስተት ተነስታ ሴቶች መብትና ሰብዓዊ ክብራቸው እንዲጠበቅ የተሟገተችን እንስት ታሪክ የሚያሳይ ስራ ነው። ከዛሬ 150 ዓመታት በፊት በብሔሰቡ ዘንድ የነበረውን የሴቶች ጭቆና፤ ማህበራዊ ውለምታ፣ የመብትና የእኩልነት ጥያቄዎችን በማንሳት ባህላዊ፣ ማህበራዊና ልማዳዊ አካሄዶችን የሞገተችው “የቃቄ ውርድወት” የቴአትሩ ማዕከላዊ ጉዳይና ራስ ናት።

በዘመኑ ሴቶች ይደርስባቸዋል ያለችውን ጭቆና ራሷ ወደትዳር ዓለም ስትገባ መሞገት የጀመረችው የቃቄ ውርድወት (መስከረም አበራ) በአገሩ አለ የተባለውን ጀግና አጋዝ ቡልቼ (ዳንኤል ተገኝ) አግብታና የብቻዋ አድርጋ መኖር ስትጀምር የሚቆሰቆስ እሳት በቴአትሩ የግጭት ሙቀትን ሲፈጥር እናያለን።

በጉራጌ ባህል መሰረት እንደፈረንጆቹ ሁሉ የአባት ስም ቀድሞ የሚጠራ በመሆኑ አባቷ ዳሞ ቃቄ (ፍቃዱ ተ/ማርያም) የውርደወትን ነገር በነፃነት የሚመለከት ደግና ቸር ሰው ተደርገው ተስለዋል። የቴአትሩ ግጭት የሚጀምረው በሁለተኛው ገቢርና ትዕይነት ላይ ሲሆን፤ ይህውም ሁለት ሚስቶችና አምስት ልጆች ያለው ጀግና ባሏ አጋዝ ቡልቼን እኔ ያንተ እንደሆንኩ ሁሉ አንተም የኔ ብቻ መሆን አለብህ በሚለው መነሻነት ነው። ዳሩ ግን ሲወርድ ሲዋረድ እንደመጣው የማህበረሰቡ አኗኗር ሶስተኛ ሚስቴ አድርጌ ማግባቴ ጥፋቱ ምኑ ላይ ነው? የሚለው አጋዝ ቡልቼ፤ የአንቺም የነሱም ባል እሆናለው ማለቱን በሚቃወም የታሪኩ ግለት ወደተመልካቹ እንዲጋባ ተደርጓል። ይህ ትዕይንት ከመጠናቀቁ በፊት ቃቄ ውርድወት ያነሳቸው መሠረታዊ ጥያቄ እንዲህ የሚል ነበር፣ “ለኔ አንተ ብቸኛ ፀሐዬ ነህ፤ አንተ ግን ስንት ፀሐዮች አሉ?” በዚህ ወቅት የተሰማው የተመልካቹ የአድናቆት ጭብጨባ የጥያቄውን አግባብነት የሚያጎላ ነበር።

ቴአትሩ ወዝ ባለው የቋንቋ አጠቃቀም፣ ምቾት በሚሰጥ የአተዋወንና የአልባሳት ቅንጅት የተሰራ ከመሆኑም በላይ ተመልካች ሳይሰለች የምልሰት ታሪክ ያሳየበት መንገድ በእጅጉ የሚመስጥ ነበር። ይኸውም የቃቄ ውርድወት እና አጋዝ ቡልቼ ለመጀመሪያ ጊዜ የተያዩበት የተዋወቁበትን አጋጣሚ፤ ተሰምቷቸው የነበረውን ስሜትና የገለፁበትን መንገድ በሁለቱ ዲያሎ (ጭውውት) ውብ በሆነ መንገድ መቅረቡ ተመልካችን ዘና የሚያደርግ ነበር ለማለት ያስደፍራል።

ቃቄ ውርድወት ሚስት በሆነችበት ማግስት ባሏ የእርሷ ብቻ እንዳልሆነ ስትገነዘብ በሚጀምረው ግጭት የጉራጌ ሴቶች ሁሉ የመብት ጥያቄ ሆኖ በመቀጠል እስከስምንት የሚደርሱ የመብት ሙግቶች አደባባይ እንዲወጡ አድርጋለች። ሴቶቹ በወቅቱ ካነቋቸው ጥያቄዎች መካከል አንድ ባል ለአንድ ሚስት ሆኖ እንዲፀና፣ በትዳሯ ውስጥ እኩል የመወሰን መብት፣ ሴት ልጅ የወደደችውን የማግባት መብት፣ እንዲኖራት ያልመሰላትን ባል የመፍታትና ከእርግማን ነፃ የመሆን መብት እንዲሁም “ጀፎረ” (የሴቶች ሸንጎ የመጥራት መብት) እንዲከበር የሚሉት እና ሴት ልጅ ለጥሎሽ አትሸጥ የሚሉት ይገኝበታል።

የሴቶቹ ጥያቄ በመላው ጉራጌ ተቀጣጥሎ በወንዶች በሚመራው ባህላዊ ሸንጎ (ጆካ) ዘንድ የደረሰ ቢሆንም፤ “ለያዥ ለገናዥ” ያስቸገረ ነገር ሆኖ ሲቀጥል  እንመለከታለን። የሴቶቹን የመብት ጥያቄ መጠናከር “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” የሆነባቸው ሽማግሌዎቹ ነገሩን “የፈጣሪ ቁጣ ነው” እስከማለት ደርሰዋል። “ጆካው” ፊት የቀረቡት ሴቶች፤ ውሃ በሚያነሳ አመክኖአዊ ዝርዝር ጉዳዮች የተከራከሩ ቢሆንም የኋላ- ኋላ ግን የመብት ጥያቄው በዱላና በጉልበት ሲቀለበስ ያሳየናል።

“ቃቄ ውርድወት” የጀመረችውን የመብት ሙግት በመግፋት ጀግና ነው የተባለውንና የቱንም ያህል ቢወዳት ከሽማግሌዎቹ ቃል መውጣት የከበደውን አጋዝ ቡልቼን ፈትታ ነፃነቷን ስታውጅ እንመለከታለን። በዚያም ጀካው ትዳሯን በፈታችና ጥፋት ፈፅማለች ባላት ሴት ላይ የሚፈፅመውን “አንቂት” የተሰኘ እርግማን በመተው በነፃ ሲያሰናብታት በትግሉ ሜዳ ላይ ብቻዋን ስትቀር የሚሰማትን የስሜት ስብራት “እነዛ መብታቸውን የሚጠይቁና በየጓዳቸው የሚያለቅሱ ሴቶች የታሉ?” ስትል ትጠይቃለች።

“የቃቂ ውርድወት” ከሰፊውና ጥልቁ የጉራጌ ዘመን ተሻጋሪ ትውፊት መካከል ይህንን ሲያሳይ፤ በተራኪዋ (ትዕግስት ባዩ) ወቅታዊ ትርስት እና በባህላዊ ሙዚቃ አዋህዶ በመድረኩን፤ ለ2፡30 የሚቆየው ትርኢት ተመልካችን እያጫወተ በዚያን ዘመንም እንዲህ የሚያስብ ሰው ነበር የሚያስብል፤ አሁንም ድረስ ያልተመለሱ አንዳንድ የመብት ጥያቄዎችን ለሙግት ያቀርባል።

ይህ ቴአትር እጅግ የተደከመበትና ብዙ ወጪም የሚጠይቅ እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው። ነገር ግን ያለፈውን ዘመናችንን ብቻ ሳይሆን ጠንካራ ስብዕናንና አሁንም ድረስ ያልተመለሱ የሴቶችን ጥያቄ የሚያነሳ ከመሆኑ አንፃር ተደጋግሞ ለማህበረሰባዊ የጥበብ ገበታ በመቅረብ ሊታይ የሚገባው ቴአትር ነው እንላለን። የቃቄ ውርድወት ብቻዋን ሮጣ ብቻዋን ያሸነፈች ጀግና፤ መልካም የመዝናኛ ሳምንት ይሁንላችሁ!!!

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
15470 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us