“ጥቁር ሰው ወድጄው የሰራሁት ክሊፕ ነው”

Wednesday, 26 February 2014 12:35

አርቲስት ሳሙኤል ተስፋዬ

በድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) የ “ጥቁር ሰው “ሙዚቃ ክሊፕ ላይ አፄ ምኒልክን ወክሎ በመስራቱ ይታወቃል፤ የዛሬው እንግዳችን አርቲስት ሳሙኤል ተስፋዬ። ተወልዶ ያደገው መርካቶ አካባቢ ሲሆን ከሚታወቅበት የትወና ችሎታው በተጨማሪ ፀሐፊና ሰዓሊም ነው። ቴአትርን ከክበባት ጀምሮ ይሰራ የነበረው የዛሬው እንግዳችን በትምህርትም ቢሆን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል የዲግሪ ምሩቅ ነው። ከሚታወስባቸው በርካታ ስራዎቹ መካከል “ሶስተኛው ችሎት” ፣ “ዋናው ተቆጣጣሪ” እና “ደመ ነፍስ” ቴአትሮቹ ሲጠቀሱ፤ በፊልም የመጀመሪያው የሆነው “ትግስት” ጨምሮ “ይሉኝታ” እና “ሎሚ ሽታ” ይታወሱለታል። መልካም ቆይታ

ሰንደቅ፡- ወደትወናው አለም እንዴት ገባህ?

ሳሙኤል፡- የመርካቶ ልጅ በመሆኔ ብዙ ባህሪያቶችን የማየት አጋጣሚው ነበረኝ። በዚህ ላይ እናቴ እና አያቴ ለንባብ የነበራቸው ፍቅር በኔም ላይ ተፅእኖ ማሳደር የሚችል ነበር። እናቴ ወ/ሮ ፍቅረማርያም አበበ የመጀመሪያ መምህሬ ነበረች። ባይገርምህ ንባብን ገና ትምህርት ቤት ሳልገባ ከቤቴ ነው ጨርሼ የወጣሁት፡፤ “አርሙኝ”፣ “ወዳጄ ልቤን” እና “አንድ ሺ አንድ ሌሊት” የተሰኙትን መፅሀፍት ወደት/ቤት ሳልገባ አንብቤያቸዋለሁ። እናቴ መምህሬ ብቻ ሳትሆን የመጀመሪያዋ አድናቂዬም ነበረች። የሆነ ነገር ሳነብ፣ የሆነ ነገር ስሰራ በጣም ነበር የምታበረታታኝ። እኔ ስተርክ እናቴ ስታደምጠኝ ያኔ ነው ትወናን የጀመርኩት የሚመስለኝ። እኔ ለናቴ ብቸኛ ልጅ አይደለሁም ግን የስለት ልጇ ነኝ። ለዛም ነው “ሳሙኤል” (ስለቴ ሰመረ) የተባልኩት። ከኔ በፊት ሁለት ልጆች የሞተባት እናቴ ከኔ በኋላ ግን አምስት ሴቶችን አግኝታለች። ስለዚህ ለኔ ልዩ ትኩረት ነበራት። ተመልካችና አድማጭ ኖሮኝ ስላደኩ ይመስለኛል ትወናን ከልጅነቴ ሳላውቀው ያዳበርኩት።

ሰንደቅ፡- በትምህርት ቤትና በክበባትስ እንቅስቃሴህ ምን እንደሚመስል ታስታውሰዋለህ?

ሳሙኤል፡- ከክበባት በፊት እናቴ ወደቤተክርስቲን ስትወስደኝ እዛ ደግሞ ሌላ አለም ነበር የሆነብኝ። ፍልስፍናው ኪነ-ጥበቡ፣ ስዕሉ፣ ዝማሬው ከሃማኖታዊ ቦታነቱ ባሻገር በአማኑኤል ደብር የነበረኝ ቆይታ ልዩ ነበር። የሚገርም ደግሞ እኔ በባህሪዬ ከአንደኛ ክፍል እስከ ስምንተኛ ክፍል በጣም ፈሪ የምባል፤ አይናፋር ተማሪ ነበርኩ። ለኔ ጓደኛዬ፣ እናቴ ነበረች። ከዚያ ውጪ ደግሞ የማነባቸው መፅሐፍት ናቸው። ባይገርም ሳላውቀው የማነባቸው መፅሀፍት ከእኩዮቼ ጋር የሚለያዩኝ አይነት ሆኑ። ተራ የልጆች ጨዋታ አይመስጠኝም ነበር። ሳላስበው እየተገለልኩ መጣሁ። አንድ ቀን ግን ድንገት አንዲት “ጠብታ ማር” የምትሰኝ የዴልካርኒጌ መፅሀፍ እጄ ገባችና አነበብኳት። የሚገርም የሥነ-ልቦና መፅሐፍ ነበር። ለኔ የተፃፈ ሁሉ ይመስለኛል። ህይወትን ተነጥሎ መምራት አስቸጋሪ መሆኑን፤ ከሰዎች ጋር እንዴት መግባባት እንደምችል ሁሉ ያትታል። በዚህ ላይ እኔ ወደፊት መሆን የምመኘው ወደ የኪነ-ጥበብ ሰው ነው አሊያም ደግሞ ዲፕሎማት መሆን ነበር። እነዚህ ሙያዎች ደግሞ ከሰው ጋር የሚያገናኙና መግባባትን የሚጠይቁ ናቸው። ልክ ዘጠነኝ ክፍል ስገባ ከአንደኛ ክፍል እስከ 8ኛ ክፍል የነበረችን ለማካካስ በሚመስል መልኩ ያልገባሁበት ክበብ የለም። ሚኒ-ሚዲያ፣ ሀገርህን እወቅ፣ ሙዚቃና ቴአትር ብቻ ሁሉም ክበባት ውስጥ ስሜ ነበር። የከሰዓትም የጠዋትም ተማሪ ያውቀኝ ነበር ማለት ትችላለህ። ከዚያም በክረምትም ጭምር የቴአትር ክበቡን አቋቁመን በኮልፌ ኮምፕሬሲፍ ት/ቤት አዳራሽ ውስጥ መስራት ቀጠልን ማለት ነው። እዚህ’ጋ ሳልጠቅሰው የማላልፈው በአማኑኤል የሰንበት ት/ቤት አዳራሽ ውስጥ በሳምንት አንድ ቴአትር ማሳየት ቋሚ ስራችን ሆኖ እንደነበረ ነው። እንዲያውም ቴአትር በ10 ብር ማሳየት የቻልነው በወቅቱ እኛ ነበርን። የእንዳልካቸው መኮንን “አርሙኝ” ከተሰኘው መፅሀፍ ውስጥ “የቃየን ድንጋይ” የሚል ስራ ወደተውኔት ቀየርነው። ብዙ ተመልካች እንዳገኘን አስታውሳለሁ።

ሰንደቅ፡- ወደፕሮፌሽናል መድረኮችስ እንዴት መጣህ?

ሳሙኤል፡- በክበባት ውስጥ እየሰራሁ የምድር ጦር የኪነት ቡድን ማስታወቂያ አወጣ። ተወዳድሬ አለፍኩ። ፈታኞቻችን እነአለማየሁ ታደሰ እነበሃይሉ መንገሻ ነበሩ። ደሞዝተኛ ሆነን ስልጠና ወስደን ወታደር ቤት ስራ ጀመርን ማለት ነው። ባይገርምህ ሁለት አመት በባድመ ግንባር ተሳትፌ ነበር።

ሰንደቅ፡- አካሄድህ ለውጊያ ነው ወይስ የኪነ-ጥበብ ዝግጅት ለማቅረብ?

ሳሙኤል፡- ለውጊያ ነው! በዛላ አንበሳ ውጊያ ላይ ተሳትፌያለሁ። ከዚያም ወደሰሜን እዝ ኦርኬስትራ ተመደብኩኝ። ከዚያም ወደምድር ጦር ተመድቤ አዲስ አበባ ተመለስኩ። በዚህ ጊዜ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለመጀመሪያ ጊዜ በማታው ፐሮግራሙ በዲፕሎማ በቴአትር ትምህርት ማስታወቂያ አወጣ። አመልክቼ ስለተቀበሉኝ ዲፕሎማዬን መማር ጀመርኩ። ልክ ዲፕሎማዬን ስጨርስ ባህርዳር ምዕራብ ዕዝ ኦርኬስትራ ተመደብኩኝ። እዛ ስመደብ አለቃዬ የነበረው ኮሎኔል ጌትነት ይባላል (እርሱም በቴአትር ተመርቋል፤ በቅርቡም “ገዳይ ሲያረፋፍድ” ፊልም ላይ የሽፍታውን ገፀ-ባህሪይ ተላብሶ ተጫውቷል) በትምህርቴ መቀጠል እንደምፈልግ ሳማክረው አለቆቼን አሳምኖ አዲስ አበባ ተመልሼ ደሞዝ እየተላከልኝ ዲግሪዬን እንድማር አደረጉኝ። ይህ እንግዲህ የመከላከያ ውለታ ነው። ተምሬ እንደጨረስኩ ወደመከላከያ የሬዲዮ ክፍል ገብቼ የኪነ-ጥበብ አዘጋጅ ሆንኩኝ። ሁለት አመት ከሰራሁ በኋላ በ2001 ዓ.ም ከዚያ ለቀቅኩ።

ሰንደቅ፡- ወደብሄራዊ ቴአትር እንዴት ነበር የመጣኸው?

ሳሙኤል፡- ባይገርምህ፤ ከመቀጠሬም በፊት በተጋባዥ ተዋናይነት እሰራ ነበር፡፤ ለምሳሌ “ዋናው ተቆጣጣሪ”፣ “ደመ-ነፍስ” (በዚህ ቴአትር ውስጥ የሽመልስ አበራን ቦታ ተጫወቻለሁ)፣ ከዚያም በሀገር ፍቅር በረዳት አዘጋጅነትና በተዋናይነት “ሩብ ጉዳይ” ቴአትርን ሰርቻለሁ። ከቴአትር ቤቶች ጋር ገና ዩኒቨርስቲ እያለሁ ነው ግንኙነት የፈጠርኩት። ከዚያ ማስታወቂያ ሲወጣ ተወዳድሬ አለፍኩ። ከዚያ አሁን የቴአርት ምዘና እነፃና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ ሆኜ እየሰራሁ ነው።

ሰንደቅ፡- ቀደም ሲል ስናወራ ለዩኒቨርስቲ መመረቂያ በሰራኸው “ወጫሌ 17” የተሰኘ ቴአትር ላይ የምኒልክ ገፀ-ባህሪይ ተጫውተህ ነበር። ንግስና ደጋግመሃል የሚባል ነገር ሰምቻለሁ፤ “ጥቁር ሰው” ላይ ደግሞ የባሰ ጎልተህ ወጥተሃል እንዴት ተገጣጠመ?

ሳሙኤል፡- ንግስና ሳይደጋገምብኝ አልቀረም (ሳቅ) . . . የዲፕሎማ ተማሪ ሳለሁ የመመረቂያ ስራችን “ካሊጉላ” ነበር በዚህ ላይ የሮሚውን ንጉስ ካለጉላን ገፀ-ባህሪይ ነው የተጫወትኩት። ወደዲግሪው ስንመጣ ደግሞ የመመረቂያ ስራችን “ውጫሌ 17” የሚል ሲሆን እዚህም ላይ የንጉስ ምኒልክን ገፀ-ባህሪይ ወክዬ ነው የተጫወትኩት። ነፍሷን ይማረውና ህይወቴ አበበ ነበረች ጣይቱን ሆና የምትጫወተው። ብዙ ሰዎችም አንተ ምኒልክን ትመስላለህ ይለኝ ነበር። ያንን ስራ ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን አይቶት ነበር። በሚካፒስት ተስፋዬ ወንድማገኝ ዙሪያ ዶክመንተሪ ፊልም ሊሰራ አስቦ ስለሚካፕ አርት ከማውራቴ በፊት ለምን ስለፊልም አጀማመር አላውራም ብሎ ያስባል። ኢትዮጵያ ውስጥ ፊልም የተጀመረው በአፄ ምኒልክ ጊዜ መሆኑ ሲታወስ ጌጡ የምኒልክን ገጽ እኔ እንድሰራ ጋበዘኝ። ሚካፔን ተስፋዬ ወ/አገኘ ነበር የሰራኝ። እንዲውም ያን ዘጋቢ ፊልም ያየ ብዙ ሰው ምስሉ “አርካይቫ” ወይም ተቀርፃ የተቀመጠ የቆየ ምስል መስሎት ነበር። ድንገት ግን ጌጡ ተመስገን ሲገባ ነው ድራማ መሆኑ የታወቀው። ያኔ ብዙ ሰው በማህበራዊ ድረ-ገፆች አማካኝነት ወዶት ነበር። ከዚያም “ጥቁር ሰው” ሲሰራ ዳይሬክተሩ ታምራት ከተስፋዬ ጋር አብረው ይሰሩ ስለነበር ተጠርቼ ሄድኩኝ በታየው መልኩ ሰራነው ማለት ነው። የሚገርምህ ነገር ምኒልክን ከልቤ ነው የምወዳቸው፤ ገፀ-ባህሪያቸውን ስለተጫወትኩት ብቻ ሳይሆን ታሪካቸውን ሳነብ በራሱ የሚመስጡኝ መሪ ናቸው።

ሰንደቅ፡- “ጥቁር ሰው” አልበም እየተደመጠ ባለበት ወቅት ያን ክሊፕ መስራቱ ላንተ ምን ፈጠረብህ?

ሳሙኤል፡- እውነቱን ለመናገር ስራውን የጀመርነው ዘፈኑ ከመውጣቱ በፊት ነው። ለኔ ደስ ያለኝ ምኒልክን ትሰራዋለህ መባሌ ነው። ለኔ ምኒልክ ንጉስ ብቻ አይደለም፤ መንፈሳዊም የሞራልም ሰው ነው። ምኒልክን ትሰራለህ ሲሉኝ ለምን እንደምሰራ ሁሉ አልጠየኩም ነበር። ከዚያ በኋላ ነው ለቴዲ የዘፈን ክሊፕ መሆኑን የሰማሁት፤ ዘፈኑም አሪፍ ነበር። በፕሮዳክሽንም የልጆቹ አቅም የሚገርም እንደነበር በስራው ውስጥ ታይቷል። ባይገርምህ ለስድስት ደቂቃ ስራ ወደስድስት ቀን ነበር የቀረፅነው።

ሰንደቅ፡- በቀረፃው ወቅት የማትረሳው ነገር ምንድነበር? ከቴዲስ ጋር ተገናኝታችኋል ምን ምላሽ ነበረው?

ሳሙኤል፡- ከቴዲ ጋር የተገናኘነው በአልበሙ ምረቃት ምሽት በሂልተን ነው። “ስንገናኝ በጣም ደስ ብሎኛል፤ አሪፍ ስራ ነው” ብሎኛል። ከዚያም ትዝ ይልህ ከሆነ ሂልተን መድረኩ ላይ የሰራነው ስራም ብዙ ሰው ወዶታል። ከዚያም ከቴዲ ጋር የምስጋና ፕሮግራሙ ላይ በድጋሚ ተገናኝተናል። ስራውን ስሰራ ከነወንድምአገኘ ጋር ስለምንተዋወቅ በፍቅር ነው የሰራነው እንጂ ሳንቲም ተደራድሬ አልነበረም። የማልረሳው እና ደስ ያለኝ ነገር ቢኖር እኔ ከዚያ በፊት ፈረስ ጋልቤ አላውቅም ነበር። በቀረፃው ወቅት ነው ለምጄ የጋለብኩት። ደግነቱ የሰለጠኑ ፈረሶች ነበሩ አልተቸገርኩም።

ሰንደቅ፡- በርከት ያሉ የመድረክ ስራዎች ላይ ተውነሃል፤ ከሬዲዮ ድራማዎች ውጪ ወደፅሁፍስ ያለህ ነገር እንዴት ነው?

ሳሙኤል፡- ፅሁፍ ጀመርኩ ከተባለ የጀመርኩት በግጥም ነው። ብዙ ግጥሞች ቤቴ አሉኝ። ግን የምፅፋቸው ለማሳተም ብየ ሳይሆን በጊዜው የሚሰማኝን አንድ ስሜት ለመተንፈስ ብዬ ነው፤ ለማስታወስ ግን የመጀመሪያ የግጥም ስራዬን ለፖሊስ ፕሮግራም ነበር “ሰላም” ትላለች ርዕሷ፤ በሬዲዮ የተነበበልኝ ጊዜ የተሰማኝ ስሜት ልዩ ነበር። ከዚያ ውጪ የሬዲዮና የቲቪ ድራማዎችን ፅፌያለሁ። ለመጀመሪያ ጊዜ በቲቪ የሰራሁት ድራማ ለወጣቶች በተሰኘው ፕሮግራም ላይ ነው። ያኔ ሰለሞን አስመላሽ የተባለ ጋዜጠኛ ነበር የሚሰራው። የሰራነው ድራማ ለዓመት በዓል ተወዳድሮ ሲወድቅ ሰለሞን ወጣቶች ፕሮግራም ላይ ትሰሩታላችሁ አለን። ተስማምተን ተቀረፀ። ነገር ግን ፕሮግራሙ ይተላለፍ የነበረው በምሽት በመሆኑ ቲቪ ቤታችን ባለመኖሩ ለማየት ያየነውፍዳ ቀላል አልነበረም። አሁን ግን በብዛት በተለይም በሸገር ሬዲዮ የቅዳሜ ጨዋታ ፕሮግራም ላይ ከ10 ያላነሱ ድራማዎችን ፅፌ ተውኛለሁ።

ሰንደቅ፡- በሬዲዮ ድራማዎችና በቴአትር ስራዎች ብዙ የመታየትህንና የመደመጥህ ያህል ብዙም ፊልሞች ላይ አልታየህም ለምንድነው?

ሳሙኤል፡- እውነቱን ለመናገር ከፊልም መቶ ሺ ጊዜ ቴአትር ነው የሚሻለኝ። 20 እና 30 ፊልሞችን ከምሰራ አንድ ቴአትር ብሰራ ይሻለኛል። ይህን ስልህ ፊልምን አልወድም እያልኩህ አይደለም። የሰራኋቸው ፊልሞች አሉ። ለምሳሌ የመጀመሪያ የፊልም ስራዬ “ትግዕስት” ይሰኛል። በዝግጅትም በትወናም ተሳትፌበታለሁ። ከዚያም የ “ሎሚ ሽታ” እና “ይሉኝታ” ላይ ተጫውቻለሁ፤ ሌሎችም አሉ። ያም ሆኖ የኔ ትኩረት የመድረክ ስራዎች ናቸው። በገንዘብ የማይገናኙ እንኳን ቢሆን ለኔ ከፊልምና ከቴአትር ምርጫ ቢቀርብልኝ አይኔን ሳላሽ ቴአትርን ነው የምመርጠው።

ሰንደቅ፡- በዚህ ሳምንት (እሁድ) “ቅጥልጥል ኮከቦች” የተሰኘ አዲስ ቴአትር ይዛችሁ መጥታችኋል፡፤ ምን አዲስ ነገር አለው?

ሳሙኤል፡- “ቅጥልጥል ኮከቦች” አዲስ እይታን ይዞ የመጣ የውድነህ ክፍሌ ድርሰት ነው። አዘጋጁ ደግሞ ተሻለ አሰፋ ነው። ተሻለ ዩኒቨርስቲ እያለን መምህሬ ነበ። አሁን ደግሞ አዘጋጄ ሆኗል። በጣም የሚገርምህ እስካሁን ከሰራኋቸው ቴአትሮች ብዙ ክርክር የተደረገበት ቴአትር ይህ ስራ ነው። ይዞት የተነሳው ሀሳብ የተለየ ስለሆነ ተመልካችም እንደሚወደው እርግጠኛ ነኝ። በህክምና ጉዳዮች ላይ ነው የሚያጠነጥነው፤ ወደዘጠኝ ወር ነው ልምምድ የሰራነው። ለኔ የተሰጠኝ ገፀ-ባህሪይ ጥሩ ስብዕና ያለው አይደለም። ሽመልስ አበራ፣ መሰረተ ህይወት፣ ሜሮን ጌትነት፣ ስናፍቅሽ ተስፋዬ፣ ሱራፌልና ዳንኤልን የመሳሰሉ ጥሩ-ጥሩ አክተሮች ተሳትፈውበታል።

ሰንደቅ፡- በልምምድ ወቅት የማትረሳውን አጋጣሚ አጫውተኝ?

ሳሙኤል፡- ቴአትርን በጣም የምወደው ሁሌ ተግዳሮቶች ያሉት ስራ በመሆኑ ነው። አሰልቺ ስራ አይደለም። በየዕለቱ አዳዲስ ገጠመኞች ይኖሩሃል። ተመልካች አያውቀውም እንጂ መድረክ ላይ አንድ ነገር ይፈጠራል። እርሱን ለመሸፈን ፈጣን መሆን አለብህ። ለምሳሌ አንድ ጊዜ የሚልረሳው በህይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ “ሶስተኛው ችሎት”ን ስንሰራ መድረክ ላይ ቃለ-ተውኔት ጠፋኝ። እኔ ደግሞ እንደጠፋብኝ አላወኩም። የመሰለኝ አብሮኝ የሚሰራው ሰው የጠፋበት ነው። የምር ተናድጄ ሌሎች ነገሮችን እየጨማመርኩኝ እጠብቀዋለሁ። ከዚያ እርሱ ቀስ ብሎ ጠቆም አደገኝ። ለካ እኔ ነኝ የጠፋብኝ፤ በጣም ከመደንገጤ የተነሳ ጭልም ሁሉ አለብኝ። ከመድረክ ስወጣ የለበስኩት ልስ ላብ-በላብ ሆኖ ነበር። ሌላም ጊዜ እንዲሁ ገና ቴአትሩ የተጀመረ አካባቢ ነው። ቀድሜ ሶፋ ላይ ቁጭ ብዬ ነበር መብራት የሚበራው። ገና በጭለማ ውስጥ የምቀመጥበትን ሶፋ በእግሬ ቀስ እያልኩ በመፈለግ ላይ ሳለሁ መብራቱ በራብኝ ሳላስፎግር ስፖር እንደሚሰራ ሰው ሆንኩኝና አልፍኩት( ሳቅ)

ሰንደቅ፡- ቆይታችን መዝናኛ ላይ ነውና አርቲስት ሳሙኤል ምን ያዝናናዋል?

    ሳሙኤል፡- እኔ በጣም የምዝናናው መፅሀፍትን በማንበብና ስእል በመሳል ነው። ትንሽ የሚደብር ስሜት ከተጫጫነኝ ስዕል መሳልን እመርጣለሁ ያኔ ነው ዘና የምለው። አብዛኛውን ጊዜ የምስላቸው ስዕሎች መንፈሳዊ በመሆናቸው ለደብሮች (ለቤተክርስቲያኖች) እሰጣለሁ። አሁን በቅቡ አለማዊ ስራዎቼን በኤግዚቭሽን መልክ የማሳየት ሀሳብ አለኝ። እየሰበሰብኩ ነው።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
9449 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us