በ“ቆንጆዎቹ” ሁሉም ያልፋል!

Wednesday, 10 February 2016 13:25

 

ቅዳሜ፤ ጥር 28 ቀን 2008 ዓ.ም የአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ በታዳሚዎቹ ተሞልቶ ነበር። ይህም የሆነበት ዋነኛ  ምክንያት አደይ የኪነ-ጥበባት ስራዎች ፕሮዲዩስ በማድረግ ለተመልካች ያደረሰውን “ቆንጆዎቹ” ቴአትር ለመመረቅ ነበር።

“ቆንጆዎቹ” በቪክቶር ሮዞቭ መነሻ ሃሳብ ላይ ተመርኩዞ ዘውዱ አበጋዝ የፃፈውና አንጋፋው የቴአትር ባለሙያና መምህሩ ተሻለ አሰፋ ያዘጋጀው ባለ ስድስት ትዕይንቶች ቴአትር ነው። በዚህ ቴአትር ላይ ይገረም ደጀኔ አስቴር፣ ተስፋለም ታምራት፣ ትዕግስት ግርማ፣ ሕሊና ሲሳይ፣ የምስራች ግርማ፣ ወለላ አሰፋ፣ ፍቅርተ ጌታሁን፣ ሰለሞን ሀጎስ፣ ሱራፌል ፀጋዬ እና ፍቃዱ ፋሲል በትወናው ረገድ ድንቅ ብቃታቸውን አሳይተዋል።

በዕለቱ በርካታ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በታደሙበት በዚህ የቴአትር ምሽት የክብር እንግዶች ሆነው የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ዴኤታ ወ/ሮ መዓዛ ገ/መድህን እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቴአትር ጥበባት ክፍለ ትምህርት ዲን የሆኑት አቶ ነብዩ ባዬ ናቸው። ቴአትሩን ፕሮዲዩስ በማድረግ ያቀረቡት የአደይ የኪነ-ጥበባት ስራዎችን የሚመሩት ወጣት ቢኒያም ከተማ እና ወጣት ኢየሩሳሌም ካሳ ቴአትር ድጋፍ የሚያስፈልገው ታላቅ የኪነ-ጥበብ ስራ ለመሆኑ ተናግረው፤ ፕሮዲዩስ ሲያደርጉ ያገዟቸውን ሰዎችና ተቋማት በማመስገን ተመልካቹ በቴአትሩ እንዲዝናና ጋብዘዋል።

“ቆንጆዎቹ” ቴአትር ስደትና ቁጭት፣ ፍቅርና ተስፋ የሚሰፈሩበት ቁና ነው። የራሱ ያልሆነ ቤት ለግል ጥቅሙ በማዋል ገንዘብ በመሰብሰብ ከሀገር የመኮብለል (ወደደቡብ አፍሪካ የመሰደድ) ፍላጎቱን ለማሟላት በጨከነ ወጣትና ስብዕናውን ከፍ አድርጎ በፍቅር ማሸነፍን በመረጠ ወንድም መካከል የሚደረገው ትግል በጉልህ ይታይበታል።

ክፋቱ ጣሪያ የነካው ታላቅ ወንድም ተመስገን (ይገረም ደጀኔ) የግራና ቀኝ ያሉ ጎረቤቶቹን በነገርና በቁጣ ሲያዋርዳቸውና ሲያራክሳቸው ቴአትሩ ያሳየናል። በአንፃሩ ደግሞ ከምስኪን ቤተሰቦቿ ጋር የምትኖረውን ወሰን (ህሊና ሲሳይ) እና ከፎቅ  ላይ ተወርውራ የአካል ጉዳት ደርሶባት ከአረብ አገር የተመለሰችውን ውብዬ (ትዕግስት ግርማ) በማፅናናትና ተስፋን በመስጠት የተጠመደው ተስፋዬ (ተስፋለም ታምራት) ከወንድሙ ጋር ያለው የአስተሳሰብ ልዩነት ለየቅል መሆኑ “የእናት ሆድ ዥንጉርጉር” የሚያስብል ነው።

“ቆንጆዎቹ” በተዋበ ቃል ተውኔትና በተቃና ዝግጅት የተቃኘ መሆኑ የአስሩን ተዋንያን ጥምረት ከማሳየቱም በተጨማሪ የተሸፋፈነን ሥነ-ልቦናዊ ጦርነት በግልፅ ማሳየት የቻለ ቴአትር ነው።

“በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ” እንዲሉ በድህነት ላይ  አእምሮ ህመምተኛ እናቱ እና በማህበረሰቡ ዘንድ ከተዋረዱ አባቱ ጋር የሚኖረው ህጻን ሲሳይ (ፍቃዱ ፋሲል) በሚደርስበት ጫና ብርቱ የነበረበትን ትምህርት በማቋረጥ፣ ራሱን ሲያገልና ከሰው ይልቅ የውሻ ፍቅርን ሲመርጥ እንመለከታለን። በአንፃሩ ደግሞ ቤተሰቧን ያዋረደውንና በእጅጉ የምትጠላውን ሰው በፍቅር ቃል የምታማልለው የታዳጊው እህት ወሰን (ህሊና ሲሳይ) ቅንና የተስፋ ሰው ሆና፤ “ሁሉም ያልፋል። ሁሉም ይቀራል” ስትል ታፅናናለች። “ጥሩና የምታረጋጋህ ሴት ታስፈልግሃለች” ስትል ተመስገንን የምትሞግተው ውስን የምታገኘው መልስ “አንቺ ማለት ተጎልተሽ ሁሉም ያልፋል ስትዬ ሁሉም የሚያልፍሽ ጅል ነሽ” የሚል ስላቅ ይሆናል።

“በሬ ካራጁ ይውላል” እንዲሉ፤ በክፉ ስብዕናው የገነነውን ሰው አጥብቃ የምትወደው ውብዬ ከአካላዊ ስብራቷ ባልተናነሰ ጎልቶ የሚታየውን ስነ-ልቦናዊ ስብራት በግቢው ውስጥ ከተተከሉት አበቦች ጋር ማዛመዷን እንመለከታለን። (እዚህ’ጋ በብዙዎቿችን ዘንድ የሚታወቀውን “የመጨረሻዋ ቀሚስ” የተሰኘ አጭር ልቦለድ ማስታወስ ግድ ይላል). . . ያም ሆኖ ፍቅሩን እና እንክብካቤውን ከባልነት ይልቅ የእናትነት አድርጋ የምትስለው ውብዬ፤ “ቅጥ ያጣ ሀዘንና እንክብካቤህ አንድ የጎደለኝ ነገር እንዳለ ያስታውሰኛል” ስትል ታጣጥለዋለች። ዳሩ ግን ተስፋዬ በፍቅሯ እንዲህ እፍ- ክንፍ ማለቱ ግራ ቢገባው፤ “ስለምወድሽ ነው የማዝንልሽ ወይስ ስለማዝንልሽ ነው የምወድሽ?” ሲል ግራ መጋባቱን ይገልፃል።

ሰው የቱንም ያህል በድህነት ውስጥ ቢኖር ሞራልን መጠበቅ እንደሚል የሚያሳዩን የድሃው ቤተሰብ አባወራ፤ አቶ አበጋዝ (ሰለሞን ሀጎስ) ሰዎች ክብራቸውን ለብርም ለነገርም እንዳይደፈር ሲያደርጉ እናያለን። “የሚያጠግበኝ ከሽንብራው ጋር የምበላው ኩራቴ ነው” የሚሉት እኚህ አባት፤ በቁጭትና በንዴት የሚንተከተክ ልጃቸውን ስለበቀል ፀያፍነት ሲያስረዱት፤ ውርደታቸውን ዋጥ አድርገው “መግደል ሀጢያት ነው” ይሉታል። የቤተሰባቸውን ፍላጎት እንዲያሟሉበት ከተስፋዬ የሚሰጣቸውን የገንዘብ በረከት ቀዳደው መሬት ሲጥሉ ስናይ የሞራል ፅናታቸውን በጉልህ እናይበታለን።

በ“ቆንጆዎቹ” ቴአትር ውስጥ ስግብግብነት፣ ቁጭት፣ ቅናትና ፀፀት፤ ትዕግስትና ፍቅር በመፈራረቅ በገፀ-ባህርያቱ ህይወት ውስጥ ከመታየታቸው ባሻገር ተምሳሌታዊነትም በጉልህ የተገለፀበት ቴአትር ነው ማለት ይቻላል።

ከተዋንያኑ ባልተናነሰ በቴአትሩ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የሚሰጣቸው ሦስት ክስተቶች የስነ-ልቦናዊ ጦርነቱ ማቀጣጠያ ሆነው ቀርበዋል። የቆንጆዎቹን ከፍታና ዝቅታ ተመልካች እንዲታዘብና ተምሳሌታዊነታቸውንም እንዲረዳ የአዘጋጁ ልፋትም በጉልህ ይታይባቸዋል። እነዚህ ተምሳሌታዊ (ገፀ ባህሪያት) አንደኛው ውሻ ሁለተኛው “ዊልቼር” ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ ቀድመን የጠቀስነው “አበባ” ነው።

በውሻው ውስጥ መገፋትን፣ መታመንን፣ መፅናትንና መስዋትነትን ስንመለከት በዊልቼሩ ውስጥ ደግሞ የስደትን አስከፊ ውጤት አሳይቷል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ በአበቦቹ መነቀልና መተከል፤ በጠወለገና መፅደቅ ውስጥ ተስፋና በቀልን ፍቅርና መስጠትን እንድናይ ሆኖ ቀርቧል። “ቆንጆዎቹ” በቃለ-ተውኔቱ ፣ በትወናው፣ በዝግጅቱና በታሪክ ፍሰቱ ቆንጆ ተደርጎ የተሰራ ተውኔት ነው። መልካም የመዝናኛ ሳምንት ይሁንላችሁ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
10641 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us