“ጥበብ ኗሪ፤ ጠቢብ ኃላፊ” የሥዕል ትርዒት በጋለሪያ ቶሞካ

Wednesday, 17 February 2016 14:00

 

“ሥነ-ስዕል ዝም ብሎ ሌላ ሀሳብ አይደለም። በመለኮታዊው እና በሳይንሱ ዓለማት የሚንሳፈፉበትና የሚዋኙበት የተለየ ጥበባዊ እውነት እንጂ! የእኔም ስራዎች የዘመኔና የዘመናዊውም መላ ዓለም እውነት ነፀብራቅ ናቸው።” ይህ ስነ-ጥበባዊ ምልከታ ገና በጐልማሳነት እድሜው በአስደንጋጭ ሁኔታ ህይወቱ የተቀጨው ሰዓሊ ኤርሚያስ ማዘንጊያ ሀሳብ ነው።

ባሳለፍነው አርብ የካቲት 4 ቀን 2008 ዓ.ም ጋለሪያ ቶሞካ ለ19ኛ ጊዜ ባዘጋጀው የስዕል ትርዒት የሰዓሊውን ምርጥ ስራዎች “ጥበብ ኗሪ፤ ጠቢብ ኃላፊ” በሚል መሪ-ርዕስ ስር ይፋ አድርጓል። በዝግጅቱም ላይ የጋለሪያ ቶሞካ አዘጋጆች፣ የሰዓሊ ኤርሚያስ ቤተሠቦችና ጓደኞች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመው ነበር። ይህ የስዕል ትርዒት ለሁለት ወራት ዕይታ ክፍት የሚሆን ሲሆን፤ ማንም ሰው በነፃ መታደም እንደሚችልና በሰዓሊው ስራዎች ላይ የሚሰማውን ሀሳብ በግልፅ ማንፀባረቅ እንዲችል ስለመመቻቸቱም ተገልጿል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት የስዕል ትምህርቱን የተከታተለው ሰዓሊ ኤርሚያስ፤ ጳጉሜ 5 ቀን 2005 ዓ.ም በ36 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ሳይለይ በፊት የሰራቸውና ትርጉም አዘል የሆኑት ስራዎቹ ተመርጠው ለስዕል ትርኢቱ ዕይታ መብቃታቸውን የጋለሪያ ቶሞካ አርት ዳይሬክተር ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ይናገራሉ። ይህም ስራ እንዲታይና ለህዝብ እንዲቀርብ በማድረግ ረገድ የሰዓሊው እህት ትዕይንት ማዘንጊያ ድርሻ ከፍተኛ እንደነበር ትርዒቱ በተከፈተበት ወቅት ተገልጿል።

በትርዒቱ መክፈቻ ወቅት የጋለሪያ ቶሞካ አርት ዳይሬክተር የሆኑት ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ፤ “አርቲስቱ በህይወት ባይኖርም ከስራዎቹ ጋር ግን ሁሌ አብሮን ይኖራል” ብለዋል። ሰዓሊ ኤርሚያስ ማዘንጊያን በሚያስታውሰው ጽሁፋቸውም የሚከተለውን ሀሳብ አስፍረው በጋለሪው ስር በሚታተመው “ካታሎግ” ላይ እናገኛለን።

“በማለዳው የጎልማሳነት ዕድሜው ላይ ይገኝ የነበረው ሠዓሊ ኤርሚያስ ማዘንጊያ፤ በሀገረ ታንዛኒያ-ዳሬሰላም ከተማ ለስዕል ትርዒት ከርመው የመጡትን ኪነ-ቅቦቹን “የሞቱትን ነፍስ ልዝራባቸው” በማለት በቤተ ስዕል ማዘጋጃው የሰዓሊ ስልጣኑንና የፈጠራ መብቱን ተጠቅሞ፤ ቀኑን ሙሉ እየቆረጠና በሌላ ስራ ላይ እየለጠፈ ሲሰራና ሲጠበብ ዋለ። በእውነትም ኪነ-ቅቦቹ አዲስ ጥበባዊ ይዘትና ቅርፅ አግኝተው ተከሰቱ። ኪነ-ቅቦቹን ደጋግሞ ተመለከታቸው፤ ደስ አሉት። ነገም እንዲሁ እቀጥላለሁ ብሎ የፈጠራ ውጥኑን በልቡ አሰረፀ። ምሽቱ ለአይን ያዝ ሲያደርግ፣ ቀዝቃዛ አየር ለማግኘትና ለመዝናናት ወደውጪ ወጣ። እንደወጣ ግን አልተመለሰም። በዚያው አደረ። ነገረ-ጉዳዩ ይህ ነው ተብሎ እስከዛሬም ባልታወቀ ምክንያት፤ ሞቶ ንጋት ላይ አስከሬኑ ድልድይ ስር ተገኘ። በሰዓሊነቱ “የሞቱትን ስዕሎች ነፍስ ሲዘራባቸው” የዋለው ኤርሚያስ ማዘንጊያ፤ የራሱን ነፍስ ከደረሰበት አደጋ ለመታደግ ግን አልቻለም፣ እንደወጣ ቀረ። በህይወት የለም። ኪነ-ጥበቦቹ ግን ይኸው እስከዛሬ አሉ ነዋሪና ህያው ናቸው” ይላሉ።

ሰዓሊ ባይሆን ምን ይሆን እንደነበር ሲያስብ የሚጨንቀው ይህ ወጣት፤ የልጅነት ህልሙን በትምህርት ደግፎ ማሳየት የቻለ እንደነበር የሚያውቁት ይመሰክሩለታል። በጋለሪያ ቶሞካ የሰዓሊውን ዘመን፤ የዕውቀትና ምልከታ ላይ ተመስርተው በህብረ-ቀለማት እና “አብስትራክት” የሆኑ ስራዎች ለዕይታ ቀርበዋል።

“ስራዎቹ ለጥናት የሚጋብዙ ናቸው” ያሉት ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ፤ ዘመኑንና የዘመኑን ዕይታ በቀለማትና በመስመሮች አስቀምጦልናል ይላሉ። ፍፁም ነፃ በሆነ ስሜት ቀለማቱን ይጫወትባቸው ነበር የተባለው አርቲስቱ፤ ቢያልፍም ህያው መሆኑን አሳይቷል፤ ይህንንም በቤቱ የነበሩት ስዕል አፍቃሪያን መስክረውለታል።

በዕለቱ ሰዓሊና መምህር እሸቱ ጥሩነህ በቀጭኑ ባስተላለፉት ማስታወሻ ውስጥ የሚከተለውንም ብለዋል። “በርካታ ሰዓሊያን ስራዎቻቸውን ትተው አልፈዋል። ነገር ግን የመታየት ዕድል አላገኙም። ቶሞካ ይህን ዕድል ያመቻቸ በመሆኑ ቤተሠቦቻቸው አስፈላጊውን ሂደት አሟልተው ለዕይታ እንዲያቀርቡ ጋብዘዋል።” ሲሉ በህይወት የሌሉ ሰዓሊያንን ስራዎች ለዕይታ እንደሚቀርቡ ጠቁመዋል።

የሰዓሊው ቤተሠቦች በቦታው የተገኙ ሲሆን፤ በተለይም ለዚህ ትርዒት እንዲበቃ የለፋችው ታናሽ እህቱ ትዕይንት ማዘንጊያ፤ “የወንድሜ ስራ በዚህ ጋለሪ እንዲታይ በማድረጋችሁ ሁላችሁንም አመሠግናለሁ። የወንድሜ ስራ አሪፍና ኃይል ያለው ስራ ነው፤ አይታችሁ ተዝናኑበት” ብላለች።

በቀጣዩ መጋቢት 4 ቀን 2008 ዓ.ም በሰዓሊው ስራዎች ላይ ውይይት እንደሚደረግና በዚያም ላይ ወዳጆቹና ጓደኞቹን ጨምሮ የስዕል ባለሙያዎችም በስራዎቹና በግል ህይወቱ ዙሪያ ይጨዋወታሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ጋለሪያ ቶሞካ ለ19ኛ ጊዜ ባቀረበውና “ጥበብ ኗሪ፤ ጠቢብ ኃላፊ” የተሠኘው ትርዒት ላይ የሰዓሊ ኤርሚያስ ማዘንጊያ ከ20 በላይ ስራዎች ለዕይታ ቀርበዋል። እኛም ሰዓሊው በስራዎቹ ህያው ነውና በጋለሪያ ቶሞካ በመገኘት በስራዎቹ እንድትዝናኑ እንጋብዛለን።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
10783 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us