ወጣቶች ላይ ያተኮረው “አቢሲኒያ አርት ፌስቲቫል”

Wednesday, 24 February 2016 14:17

 

የተማረው ቴክኖሎጂ (በተለይም ኮምፒውተር) ቀመስ በሆኑ የስነ-ጥበብ ስራዎች ዙሪያ አተኩሮ ነው። የዘርፉ ባለሙያዎች “Digital Media art” በሚሉት በዚህ ዘርፍ ውስጥ የሚከናወኑትን ጥባበዊ ዕውቀቶች ለሀገራችን ወጣቶችም እድሉን በመስጠት፣ በመስራትና ራሣቸውን ለዓለም እንዲያስተዋውቁ በማመቻቸት አዲስ ፕሮግራም ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። የዛሬው የመዝናኛ እንግዳችን የአንጓ ግሩፕ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ዳይሬክተር የሆነው ወጣት ናትናኤል አለማየሁ ይባላል።

በግሉ ያለውን የጥበብ አድናቆት በወጣቶች አቅም ውስጥ ለማየት ይረዳው ዘንድ ከተለያዩ ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች የተውጣጡ ተማሪዎች የተሳተፉበትን “የአቢሲኒያዊው ሥነጥበብ ፌስቲቫል” ከየካቲት 5 እና 6 ቀን 2008 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ለመጀመሪያ ጊዜ አካሂዷል። “ወጣቶች የሚሰሯቸውን የጥበብ ውጤቶች ለተመልካች አቅርበው ትችትም ይህን ሙገሳ ማግኘታቸው ትልቅ ውጤት ነው” የሚለው ናትናኤል፤ የፌስቲቫሉ ዋነኛ አላማም ዕድል ያላገኙ ወጣቶች ስራቸውን ለተመልካች እንዲያደርሱ ዕድሉ ማመቻቸት ነው ይላል። ይህ የፌስቲቫሉ ቀዳሚ ዓላማ ቢሆንም በየዘርፉ አሸናፊ የሆኑ ወጣቶች ዓለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫሎች ላይ እንዲሳተፉ ዕድሉን ማመቻቸት ደግሞ ቀጣይ ዓላማቸው እንደሆነም ያስረዳል።

ለውድድር የቀረቡት 20 አጫጭር ፊልሞች፤ በስድስት ሰዓሊያን እያንዳንዳቸው 5 ስራዎችን (ይህም የፋሽን ምስሎችን ይጨምራል) እንዲሁም የፎቶግራፍ ኤግዚቪሽኖችን በድምር የያዘ ፌስቲቫል እንደነበር ወጣት ናትናኤል ይገልጻል።

ለውድድር የቀረቡት 20 አጫጭር ፊልሞች ከ10 እስከ 15 ደቂቃ የሚወስዱ ሲሆን፤ የፊልሞቹ አይነትም የኮሜዲ፤ የፍቅር፣ የሳይንስ ፊክሽን፣ የዘጋቢ ፊልም እና ድራማ ዘርፎች ተሰርተው ቀርበዋል። በፊልሞችም ውስጥ ወጣቶቹ ያነሷቸው ሃሳቦች ህገወጥ ስደት፣ የፆታ ጥቃት፣ የሴተኛ አዳሪነት ህይወት፣ የወሊድ ጊዜ ክስተት፣ ባህል፣ ፍቅርና ጤና ተኮር ሃሳቦች ናቸው።

የእነዚህ ዘርፎች አሸናፊዎችም በሶስት አለምአቀፍ የፊልም ፌስቲቫሎች ላይ የመታየትን እድል እንዲያገኙ እንሰራለን ነው የሚለው አዘጋጁ፤ ወጣቶቹን ደግፈን ለተሻለ መድረክ ማብቃት ዓላማችን ነበር ፌስቲቫሉን ስንገመግመው ሂደቱ እንደመነሻ በመጠኑም ቢሆን ተሳክቶልናል ይላል።

ይህ “አቢሲኒያ አርት ፌስቲቫል” ሲዘጋጅ እንደመጀመሪያነቱ ተግዳሮቶች ነበሩት ሲል የሚያስታውሰው ናትናኤል፤ በተለይም በፋይናንስ ረገድ ደጋፊ አካላትን አለማግኘት የነበረውን ጫና አክብዶብናል ይላል። ስንጀምር ሶስት አይነት ዕቅድ ነበረን፤ የመጀመሪያው ያስፈልገናል የተባለውን ገንዘብ በበቂ ደረጃ አግኝቶ መመደብ፤ ሁለተኛው መጠነኛ የሆነ ገንዘብ ማዘጋጀት የሚለው ሲሆን ሶስተኛውና ተግባራዊ የሆነው ደግሞ በራሳችን ገንዘብ ማውጣት ቢኖርብን እንኳን እንዴት እናደርጋለን? የሚሉ ነበር። በተለይም በፌስቲቫሉ ላይ የቀረቡትን ስራዎች በአንጋፋ ባለሙያዎች እንዲዳኙ ብንፈልግም የተጠየቅነው ገንዘብ ብዙ ስለነበር ወደራሳችን ሰዎች ዞረናል ሲልም ተግዳሮቶቹን ተከትሎ ስለመጣው ክፍተት ያስረዳል።

ይህን ፌስቲቫል የተለየ የሚያደርገው ነገር አልጠፋም። ወጣት ናትናኤል ከተመልካቹም አገኘነው ባለው ምላሽ ላይ ተመስርቶ ስለፌስቲቫሉ ልዩ-ባህሪያት ሲናገር፤ “በሁለት ቀን ውስጥ ፌስቲቫሉ ስዕልንም፣ ፋሽንንም፣ አጫጭር ፊልሞችንም በጥምረት ማሳየቱ ለየት ያደርገዋል” ሲል ይጀምራል። በመቀጠልም ወጣት ሰዓሊያን በየስዕሎቻቸው አጠገብ በመገኘት ስለስራዎቻቸው በቅርበት ትንታኔ ለተመልካች መስጠት መቻላቸው እና ስራዎቻቸው ከፌስቲቫሉ በኋላ ለሽያጭ እንዲውሉ ማመቻቸታችን ፌስቲቫሉ የተለየ ያደርገዋል ይላል። ይህም ሆኖ ግን የቀረበው በሁለት ቀናት ውስጥ መሆኑ ስለማጠሩ ከተመልካቹ አስተያየት ተሰጥቶበታል።

የጥበብ ስራዎችን በፌስቲቫል ደረጃ በማዘጋጀት ስትነሱ የኮሌጅና የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ ብቻ ማተኮራችሁ ሌሎች የመልካም ፈጠራ ባለቤት የሆኑና ኮሌጅ ያልረገጡ ወጣቶችን ማግለል አይሆንባችሁም? በሚል ለቀረበው ጥያቄ ወጣት ናትናኤል ሲመልስ፤ “ዓላማችን የኮሌጅ ወጣቶችን ብቻ አሳይተን ሌሎቹን ወጣቶች ለማግለል አይደለም” ያለ ሲሆን፤ በኮሌጆች አካባቢ ያሉ ወጣቶች የሚያነሱት ሃሳቦች ለማየትና የተማረውን ህብረተሰባዊ አመለካከት ለመፈተሸም በማሰብ ነው ሲል ያስረዳል።

በካናዳ ቶሮንቶ ትምህርቱን እንደተከታተለ የሚናገረው ናትናኤል፤ በቆይታውም የኮሌጅ ተማሪዎች የጥበብ አቅማቸውን አውጥተው እንዲያሳዩ ምቹ አካባቢ ይፈጠርላቸው እንደነበር ይናገራል። ይህንን ዓይነት ዕድል የአገራችን ወጣቶች ቢያገኙ በሚል መንፈስ ተነሳስቶ “አንጓ ግሩፕ” በሚል ባቋቋመው ድርጅት ስር “አቢሲኒያ አርት ፌስቲቫልን” ከዚህ ዓመት ጀምሮ በቀጣይነት ሊሰራበት ስለመነሳቱም ያስታውሳል። ፌስቲቫሉ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደመካሄዱ የተሰጡትን ትችቶችንም ሆነ ገንቢ አስተያየቶች ተቀብሎ አመታዊነቱን ይዞ ለመዝለቅ እየሰሩ መሆናቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ አስረግጦ ይናገራል።

“አቢሲኒያ አርት ፌስቲቫል” ላይ የቀረቡት ስዕሎች በአብዛኛው “አብስትራክት” እና “ሪያሊስቲክ” ስራዎችን አንፀባርቀዋል። በአጫጭር ፊልሞችም ዘርፍ ቢሆን፤ በከተሜ ህይወታችን ውስጥ ልብ ሳንላቸው በቀላሉ ያለፍናቸውን ጉዳዮች በጉልህ ያሳየበት ነው ሲል ስለስራዎቹ አስረድቷል። እነዚህም ፊልሞች በቀጣይነት በተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገፆች አማካኝነት በማሰራጨት ለብዙሃኑ ተመልካች ለማሳየት ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውንም ነግሮናል።

አማተር ወጣት የኮሌጅና የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ስራዎቻቸውን የሚያሳዩበት መድረክ ማመቻቸታቸውን እንደሚቀጥሉ ዳይሬክተሩ የተናገሩ ሲሆን፤ አሸናፊ ስራዎችም በቀጣይ ዓለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫሎች ላይ ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል። በሂደት ግን ሁለተኛው “አቢሲኒያ አርት ፌስቲቫል” ለወጣቶቹ የሚሰጠውን ሽልማት ለማሳደግ ማሰቡን ወጣት ናትናኤል የተናገረ ሲሆን፤ ለዚህም ድጋፍ የሚደርጉ አካላት ትብብራቸውን እንዲያሳዩም ጠይቋል።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
14726 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us