የ“እንግዳ” ቴአትር እንግዳ ኀሳቦች

Wednesday, 02 March 2016 13:09

 

 

·         የቴአትሩ ርዕስ - “እንግዳ”

·         ድርሰትና ዝግጅት - ማንያዘዋል እንዳሻው

·         መነሻ ሃሳብ - ሎላ አናግናስቲ

·         ተዋንያን - ሽመልስ አበራ (ጆሮ)፣ ሐረገወይን አሰፋ እና አልአዛር

                ሳሙኤል    

አዳዲስ ሃሳቦች፣ አዳዲስ የዝግጅትና የትወና ደርዞች የታዩበት ዘመን አይሽሬ (Classical) ስራ ነው በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ ዘወትር እሁድ በመታየት ላይ የሚገኘው “እንግዳ” ቴአትር . . . የቴአትር ባለሙያዎች እንደሚሉት “እንግዳ” ቴአትር “አብስርድ” ሊሰኝ የሚችል ነው። ደራሲና አዘጋጁ ማንያዘዋል እንዳሻው በፌስ ቡክ ገጹ እንዳስቀመጠውና የቴአትር ባለሙያው ነብዩ ባዬ ስለ እንግዳ ቴአትር መነሻ ሃሳብ ባቀረበበት “የጥበብ መንገድ” የሬዲዮ ፕሮግራሙ ወቅት “ለ “አብሰርድ” ምንነት ሲያስረዳ እንዲኅ” ይገልጸዋል። “አብሰርድ ቴአትር የሰው ልጅ በኑሮ ውስጥ አምኖ የተቀበላቸውን እምነቶች የሚሞግትና የህይወትን መጨረሻ የሚጠይቅ ነው። የህይወት ኡደትና ሽክርክሮሽ መቆሚያው ሞት ስለሆነ የሰው ልጅ ሞቱን የሚጠብቅ ፍጡር ነው ማለት ነው። እነዚህን አስተሳሰቦች ፀሐፊዎቹ ተመካከረውና አንድ አይነት ስምምነት ላይ ደርሰው ሳይሆን፤ በራሳቸው የደረሱበት የህይወት ድምዳሜ ነው” ይለናል።

“እንግዳ” ከአስተሳሰብ አንጻር ብዙ የሚፈትሻቸውና የሚሳለቅባቸው ቁምነገሮች አሉት። በመድረኩ ላይ ባለትዳሮች አምሳል የምናያቸው ገፀ-ባህሪያት ሁለት ሲሆኑ፤ አንደኛው ህይወቱን በትወና ሙያ የሰጠው (ሽመልስ አበራ) እና ባለቤቱ (ሀረገወይን አሰፋ) እንዲሁም የዚህ ቤት እንግዳ ደግሞ የሥነ-ልቦና ባለሙያው (አልአዛር ሳሙኤል) ናቸው። . . . ቴአትሩ በስላቅ ከሚያነሳቸው ሀሳቦች መካከል ሁሉም ሰው አብሮ የሚኖረው ለፍቅር ሳይሆን ልማድ ሆኖበት ነው” ይሉናል። በትዳራቸው ውስጥ መሰላቸት የገጠማቸው ጥንዶች ትዳራቸውን ማደሻና ማጣፈጫ ያደረጉት መንገድ በርግጥም እንግዳ የሚባል አይነት እንደሆነ ጠቋሚ ነው።

በየሳምንቱ ወደቤታቸው በሚጋብዙት የተለያየ እንግዳ ላይ በተውኔቱ ውስጥ ሌላ ተውኔት የሚሰሩት እነዚህ ባለታሪኮች ስላቃቸው ብዙ ነው። የዛሬው እንግዳ ደግሞ የሥነ ልቦና ባለሙያ ነው። እናም አባወራው 24 ሰዓት የትውውቅ ጊዜ ሳይሞላው ሚስቱን ለመጠየቅ ቤቱ ድረስ የመጣውን ሰው “ውሽምነት ቀላል ስራ አይደለም” ሲል ይሳለቅበታል፡፡

ቴአትሩ በመንታ ሃሳቦችና ክስተቶች የተሞላ ነው። ይህም ከመጀመሪያው ዕይታ ጀምሮ የሚታይ ነው። በጭለማ ውስጥ ጥቁር መነፅር ማድረግ፤ በመድረክ ላይ ሌላ መድረክ ማቆም፤ በቴአትሩ ውስጥ ሌላ ቴአትር ለመስራት መፍቀድ፤ በመሰልቸትና አብሮ በመኖር፤ በማፍረስና በማደስ መካከል እንግዳውን ብቻ ሳይሆን ተመልካቹንም ጭምር የሚያታልል፤ የሚኮረኩርና የሚፈታተን ቴአትር ነው።

የራሳቸውን ትዳርና ህይወት እንደአዲስ በመስራት (በሞባይል ዘመን አነጋገር “ሪ-ስታርት” ለማድረግ ሲሉ) በእንግዶቻቸው ላይ ተውኔት እየሰሩ የሚጫወቱት እነዚህ ባለትዳሮች በሥነ-ልቦና ባለሙያው (አልአዛር ሳሙኤል) አገላለጽ “ለብቻችሁ መቀመጥ ስለማትችሉ ነው እንግዳ እየጋበዛችሁ የምትሰቃዩት” ተብለው ተገልፀዋል።

በውብ ቃለ-ተውኔት፣ በፈጣን ድርጊትና በቀልጣፋ አተዋወን የሚደምቀው ይህ ቴአትር፤ በሀገራችን እንደተለመዱት ታሪካዊ ተውነቴቶች ሁሉ የቴአትር ቤቱን ሙሉ አዳራሽ ለመጠቀም ሲሞክር እንመለከታለን። (እዚህ’ጋ ሐረገወይን አሰፋ እና አላአዛር ሳሙኤል የሚጫወቷቸው ገፀ-ባህሪይት ከመድረክ ርቀው በአዳራሽ ቀኝ ክንፍ በኩል የሚያሳዩን የምልሰት ታሪክ ማሳያ ተደርጎ ሊጠቀስ ይችላል)

በቴአትሩ ምረቃ ወቅት ከተበተነው ወረቀት ላይ እንዲህ የምትል መሳጭ ፅሁፍ ትነበባለች። “ምንም እንኳን በህይወት ውስጥ ተስፋ መቁረጥ፣ ፍርሃት፣ ግራ መጋባት፣ ብቸኝነትና መሰላቸት እንዲሁም ሞት ቢኖም፣ እያንዳንዱ ግለሰብ ህይወትን ማጣጣምና በጋለ ስሜት (Passionately) እና በሀቀኝነት (Sincerely) የመኖር ሃፊነት አለበት” ብለው የሚያምኑ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ፣ የ“እንግዳ” ቴአትርም ይህን ሃላፊነት ለመጠቆም ይሞክራል” ሲል ያትታል።

ሌላው በቴአትሩ ውስጥ የሚታየው አስመሳይነት ነው። ገፀ-ባሪያቱ ሁሉ ማስመሰል ይችሉበታል። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል የሚል ተመልካች የተውኔቱን ሂደት በሚገባ መገንዘብ መቻል አለበት። ሶስቱም ሻማ የሚበራላቸው ገጸ-ባህሪያት ማስመሰልን (በቴአትሩ ውስጥ ሆነው ሌላ ቴአትር መተወንን በሚያስደንቅ ብቃት ያሳዩናል።)

የ“እንግዳ” ቴአትር ባለታሪኮች በሙሉ ፀባያቸው እንግዳ የሚሆንበት ተመልካች ብዙ ነው። ያም ሆኖ አስቀድሞ እንደተባለው ታዳሚው ቴአትሩን የሚረዳው ለህይወት ባለው ግንዛቤ ልክ ነው። . . . በልመና የተጀመረ ፍቅር የተባለለት ትዳር፤ ላገባ የፈለኩት ሚስቴን አልነበረም የሚል ባል፤ ህይወትን መኝታ ሞገትን ደግሞ ከህልም እንደመንቃት አድርጋ የምታስብ ሚስት፤ ያመነውን የቀድሞ ፍቅር ያጣው የሥነ-ልቦና ባለሙያ በሚዘውሩት በዚህ ታሪክ ውስጥ “እንግዳ” ክስተቶችና “እንግዳ” ሃሳቦች የሚያስደምሙት የሚኮረኩሩት፣ የሚያስቁትና የሚሞግቱት ተመልካች ቢኖር አያስገርምም። መልካም የመዝናኛ ሳምንት።   

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
10103 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us