“ጤንነቴን አግኝቼ የምወደውን ሥዕል ይበልጥ መሥራት እፈልጋለሁ”

Wednesday, 09 March 2016 13:15

ወጣቱ ሰዓሊ ፍቃዱ አያሌው

 

የልጅነት ህልሙን እውን ማድረግ የቻለ ሰዓሊ ነው። ተወልዶ ያደገው ከከተማ ግርግር በራቀ ለምለም ስፍራ በመሆኑ ይመስላል በስራዎቹ ውስጥ ተፈጥሮ (landscape) ደምቆ ይታይበታል። የስዕል ትምህርቱን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስር በሚገኘው አለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት በ2001 ዓ.ም በማዕረግ አጠናቋል። ይህ ወጣት ሰዓሊ ፍቃዱ አያሌው ይባላል።

ሰዓሊው ከዚህ ቀደም ከወዳጆቹ ጋር አራት ጊዜ በቡድን የስዕል አውደ ርዕይ ያቀረበ ሲሆን፤ በዚህ ሳምንት የተጠናቀቀውንና ለአንድ ሳምንት ያህል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም አዳራሽ ይታይ የነበረውን ትርኢት ጨምሮ ሶስት ጊዜ በግሉ እነሆ ብሏል። ይህ ባሳለፍነው ሳምንት ያሳየው ሶስተኛው አውደ ርዕይ ከሌሎቹ በተለየ ትርጉም የሚሰጠው እንደሆነ ፍቃዱ ይናገራል። ከዓመት በፊት ድንገት የተከሰተው የቀኝ እጁ አለመታዘዝ ቀስ በቀስ ቀላል የማይባል መዘዝ ይዞበት መጥቷል።. . . 2002 ዓ.ም አካባቢ ቀበና በሚገኘው ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን ውስጥ እየሰራ ነበር፤ የእጁ ዝለትና አለመታዘዝ የታወቀው። እንደቀላል ቦታ ያልተሰጠው ይህ ክስተት በ2004 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ የቀኝ እጁ መታዘዝ ሲያቆም ከባድ ድንጋጤን መፍጠሩ አልቀረም። ህክምናው በውጪ ሀገር ቀላል እንደሆነ ቢነገረውም የሀገር ውስጥ ተስፋውን ለመሞከር ወደተጠቆመበት ኮሪያ ሆስፒታል መሄዱን የሚያስታውሰው ወጣቱ ሰዓሊ ፍቃዱ፤ በህክምናው ሂደት የበለጠ አደጋ እንዳጋጠመው ይናገራል። “በሶስት ቀንህ ድነህ ትወጣለህ ተብዬ የጀመርኩት ህክምና በሁለት ሳምንት ውስጥ ብሶብኝ ወጣሁ” ሲል የችግሩን አስከፊነት ይገልፃል።

የጤና እክሉ መባባሱ የታወቀለት ፍቃዱ፤ ለበለጠ ህክምና ወደታይላንድ ማምራቱንና በዚያም ህክምናው ጥሩ እንደነበር ይናገራል። “ቀደም ብዬ ትኩረት ሰጥቼው ወደውጪ ለህክምና አለመሄዴ ብዙ ነገሮችን አበላሽቶብኛል” ይህን በቁጭት የሚናገረው ፍቃዱ፤ “አሁንም ቢሆን ግን ገንዘብ ካገኘው ጤንነቴ ወደነበረበት እንደሚመለስ አምናለሁ፤ ሐኪሞቼም ተስፋ እንዳለኝ ነግረውኛል” ባይ ነው። ለዚህም ወገኖቼ እንደሚደርስልኝ ተስፋ አደርጋለሁ ሲል ተስፋውን ለዕይታ ባበቃቸው የስዕል አውደ-ርዕይ በኩል አሳይቷል።

ወደውጪ ሀገር ሄጄ በአግባቡ ብታከም በሁለት ወር ውስጥ መዳን እንደምችል ዶክተሮች ተስፋ ሰጥተውኛል የሚለው ሰዓሊ ፍቃዱ፤ ቀደም ሲል ወደታይላንድ ለህክምና ሲሄድ 500ሺህ ብር ይዞ መሄዱንና ያም ሳይበቃው ቀርቶ፤ ሰዓሊ መሆኑን የተረዱ ሐኪሞች ተባብረውት እንደነበር ያስታውሳል።

በአሁኑ ወቅት የወገኖቹን ድጋፍ ከመጠየቅ ባሻገር የስዕል ስራዎቹን በመሸጥና “በፖስት ካርድ” መልክ በማሳተም ለህክምና የሚሆነውን ገቢ ለመሰብሰብ እየሞከረ የሚገኝ ሲሆን፤ ከህመሜ ድኜ የተሻለ ስራና ምስጋና የማቀርብበትን ቀን እናፍቃለሁ፤ ከሁሉም በላይ ጤንነቴን አግኝቼ የምወደውን ስዕል ይበልጥ መስራት እፈልጋለሁ” ሲል ተስፋውን ይናገራል።

“ሰው የሚወደውን ነገር ሲሰራ ከስራነቱ ይልቅ መዝናኛነቱ ያይላል” የሚለው ሰዓሊ ፍቃዱ፤ ከጤንነቱ መጓደል በፊት በነበሩት ጊዜያት ስዕል መዝናኛው እንጂ ስራው እንደማይመስለው ይናገራል። . . . “ስዕል ፈጣሪ የሚሰጥህ በቃላት የማትተረጉመው፤ ነገር ግን የምትኖረው (feel) የምታደርገው ረቂቅ ነገር ነው” ይለዋል የስዕልን ትርጉም ሲገልፀው። ስዕል እንደሰምና ወርቅ አይፈታም።ዝም ብለህ ስሜቱን ታጣጥመዋለህ እንጂ የሚለው ፍቃዱ፤ ብዙ ጊዜ ተመልካቹ የስዕል ስራዎችን ሲመለከት ስዕሉን የሚገልፅ “ፅሑፍ” ይጠብቃል። ይህ ማለት ተመልካቹ በነፃነት ከማስብ ይልቅ የሰዓሊውን መንገድ ብቻ እንዲከተል የሚያስገድድ ነው” ሲል ስዕል በተመልካች እይታ ልክ መተርጎም ያለበት ጥበብ እንደሆነ ይከራከራል።

በስራዎቹ ውስጥ ብርሃንና የፈካ የተፈጥሮ ገፅታ የሚያጎላው ሰዓሊ ፍቃዱ፤ “በተለይ ሞቅና ደመቀ ያሉ ቀለማትን እወዳለሁ” ባይ ነው።  ነገር ግን ደማቅ ቀለማት ጎልተው ይታዩ ዘንድ ፍዝ ቀለማት አብረው መኖራቸው መዘንጋት እንደሌለበትም ያስተውሳል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ለዕይታ ከቀረቡት 42 ስዕሎች መካከል አብዛኞቹ Landscape (መልካምድር) እና The way (መንገዱ) የተሰኙት ስራዎች በስፋት ይስተዋላሉ። ይህ በተለየ የጎላበትን ምክንያት አስመልክቶ ሰዓሊው ሲናገር፤ “ተፈጥሯዊ የመልካምድር አቀማመጥ ማንንም ሰው እንደሚማርክ ሁሉ እኔንም ይማርከኛል። የኛ (የኢትዮጵያ) ዋናው ሀብታችንም ይህ ተፈጥሮ ነው ብዬ አምናለሁ። . . . ሌላው “መንገድ” የተሰኙት ስራዎቼ ደግሞ ያለፈውን የአሁኑን እና የወደፊቱን ጊዜ የሚያስተሳስር የህይወታችንን መንገድ ማሳያዬ ነው” ሲል ይገልፃል።

“ገና ብዙ መስራት በምችልበት ጊዜ ላይ የደረሰብኝ ድንገተኛ አደጋ እንቅፋት ሆኖብኛል የሚለው ወጣቱ ሰዓሊ ፍቃዱ አያሌው፤ አሁንም ቢሆን ከሁኔታዎች ጋር ተስማምቶና በፋሻ በተጠቀለለ ብሩሽ የስዕል ስራዎቹን መስራት እንዳላቆመ ለብቻው ባቀረበው ሶስተኛው አውደ-ርይ ላይ አሳይቷል። “ረጅም ጊዜ ወስጄ አንድን ስዕል ከሰራሁ ይበላሽብኛል” የሚለው ሰዓሊው፤ ጥሩ ስራ ለመስራት ሲዘጋጅ ስለሚሰራው ስዕል ሶስትና አራት ሰዓታትን በፅሞና ማሰላሰል እንደሚፈልግ፤ በተወጠረው ሸራ ላይ ግን በዛ ቢባል ከአንድ ሰዓት ተኩል በላይ ጊዜን እንደማያጠፋ ይናገራል።

አሁን ላይ ያጋጠመው ችግር ረቂቅ የሆኑና ጥልቀት የሚፈልጉ ስራዎችን ለመስራት እንደማያስችለው እንዲሁም ከመጠንም አንፃር በፊት ላይ በትላልቅ ሸራዎች የሚሰራቸው ስዕሎች ቀርተው ከ90 ሳንቲሜትር ቁመት እና ከ50 ሳ.ሜ ስፋት በላይ በሆነ ሸራ መሳል ተግዳሮት እንደሆነበትም ይገልጻል።

የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ከገባ በኋላ በተለይ ባስተማሩት መምህራን እንደሚኮራና ይበልጥ እንደሚያከብራቸው የሚናገረው ፍቃዱ፤ ከዚህ ውጪ በትምህርት ዓለም ከተዋወቃቸው ዓለምአቀፍ ሰዓሊያን መካከል ቫንጎግ በተለየ እንደሚገርመው ይገልጻል። ለዚህም መገረሙ እንደምክንያት የሚጠቅሰው በርካታ ስራዎችን በዚያን ዘመን መስራቱ ጉድ ሲያሰኘው፤ በዚህ ተርታ ውስጥ ሚካኤል አንጀሎም ይጠቀሳል ባይ ነው። በህይወቱ ምን እንደሚያዝናናው ሲጠየቅ፤ አንድ ነገር ለመስራት የሚጥር ሰው ሁሉ ደስታን እንደሚፈጥርለት የሚናገረው ፍቃዱ፤ “ሰው በክፉም ይሁን በደጉ መኖሩን ማሳየት አለበት” ብዬ አምናለሁ ይላል።

የህክምና ክትትሉን እንዲያደርግ ከመነሻው ጀምሮ የሰዓሊያን ማህበር ሙሉ ድጋፍ አድርጎለት እንደነበር በምስጋና የሚያስታውሰው ፍቃዱ፤ እነርሱ ተሯሩጠው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመነጋገር የቀበሌ ቤት እንዳገኝ ባያመቻቹልኝ  ኖሮ ችግሬ አሁን ካለሁበት ይብስ ነበር፤ ሲልም ማህበሩንና አስተዳደሩን ከልቡ ያመሰግናል። ከዚህ በተጨማሪ ተማሪዎቼና ቤተሰቦቻቸው፤ ወዳጆቼና ቤተሰቦቼ እንዲሁም የሚያውቁኝና የማያውቁኝ ሁሉ ስለረዱኝ እጅግ አመሰግናለሁ ይላል። ከስራ ባደረቦቼ በተጨማሪ ብሔራዊ ሙዚየም ቦታውን በነፃ በመፍቀድ ስለተባበሩት ማመስገኑ አልቀረም። ከሁሉም በላይ ግን እዚህ ቦታ እንድቆም የረዳችኝን ባለቤቴ ርብቃን በጣም አመሰግናለሁ ይህም ይድረስልኝ ሲል ምስጋናውን ለአደባባይ አብቅቶታል።   

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
8179 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us