የማህበረሰባችን መስታወት፤ “50 ሎሚ”

Wednesday, 16 March 2016 13:17

 

·         የፊልም ርዕስ - “50 ሎሚ”

·         ደራሲና ዳይሬክተር - ረዲ በረካ

·         ፕሮዳክሽን ማኔጀር - የኔነህ እንግዳወርቅ

·         ኤዲተር - ብሩክ አረጋዊ

·         ፕሮዲዩሰር - ስፖትስ ፊልም ፕሮዳክሽን

·         ሳውንድ ትራክ - ሳሙኤል ወርቁ

·         ተዋንያን - ተዘራ ለማ፣ የትናየት ታምራት፣ ፋሪስ ብሩ፣ ሱራፌል

ፀጋዬ፣ መስፍን አያሌው፣ ቅድስት አበባው፣ ክርስቲና ሲሳይ እና ሌሎችም

  

“በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርም” ይሉትን የአበው ተረት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ፊልም ነው። የስነ-ልቦና ባለሙያዎች አንድን ሰው የሚቀርፁት ሶስት ወገኖች ናቸው ይሉናል። ቤተሰቡ፣ ህብረተሰቡና ትምህርት ቤቶቹ። . . . የ“50 ሎሚ” ፊልም ዋና ገፀ-ባህሪይ በፍቅር ያሳደገች እናቱን በድህነት ክፉ ጉልበት ሲነጠቅ፣ በንፍገት የሚገፋውን ህብረተሰብና በቸርነት የሚያበረታውን ሽማግሌ ተደግፎ የሚያሳየውን ውጣ ውረድ ይተርካል።

“50 ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው ደግሞ ጌጡ፤” መሆኑንም ይነግረናል። በስፖትስ ፊልም ፕሮዳክሽን ፕሮዲዩስ የተደረገው፤ የደራሲና ዳይሬክተር ረዲ በረካ “50 ሎሚ” የተሰኘው ልብ አንጠልጣይ ፊልም።  . . . በእነሰላምና ፍቅር ቤት የችግር ጉልበት ሲፈረጥም ገና በልጅነት ዕድሜው የእህቶቹ መመኪያ የሆነው ዮሴፍ (ፋሪስ ብሩ)  . . . በወሳኙ ሰዓት የፈለጋትን አንድ እንጀራ ተነፍጎ፤ ባለፈ ጊዜ 300 እንጀራ ቢቀርብላትም “አሻፈረኝ” ሲል ከማህበረሰቡ (ከጎረቤቶቹ) ጋር ፊትና ጀርባ ሆኖ ይጀምራል። (መሸተኛው ከሞተ በኋላ የመጣ መድሐኒት ምን ዋጋ አለው?)

“የሚሰጥ ልብ ካለ ሁሉም ሰው የሚሰጠው ነገር አያጣም” የሚሉት ጋሽ ሞገስ (ተዘራ ለማ) ተስፋ በቆረጠበት ዘመን የእርሱና የእህቱ መከታ ሲሆኑ እንመለከታለን። በአንጻሩ ደግሞ እንጀራ ሞልቶት፤ ስጋ እየቆረጠ፤ አብሮ ኗሪ ነው የተባለው ጎረቤት በአንድ እንጀራ ስስት ታስሮ በህፃን ዮሴፍ ልብ ውስጥ ቂም ሲዘራ፤ ለእዝን በሚሆን 300 እንጀራ ውስጥ የኛን ሰው አስመሳይነት እያጎላ፤ የህጻኑን የበቀል ስለት እየጠረበ እንደሆነ እንኳን አይረዳም። የንፍገት፣ የመገፋትና አለው ባይ የማጣት ስንጥቁን እያሰፋ፤ የህብረተሰባችን መስታወት ሆኖ በጉልህ የሚያሳየን “50 ሎሚ” ፊልም ያልዘራነው አይበቅልምና የነፈግነውን የሚነጥቅ፤ ያበደርነውን የሚመልስ ገፀ-ባህሪይ ፈጥሮ ያሳየናል።

“50 ሎሚ የጥበብ ፈጠራ መብቱን ተጠቅሞ ማህበረሰቡ የዘነጋቸውን ጥቃቅን የሚመስሉ ጉዳዮች በገፀ- ባህሪያቱ ህይወትና በተረት እያላወሰ እንካችሁ ይለናል። . . . “ሁሉም ሰው የተቦካ ግን ያልተጋገረ ታሪክ አለው” የሚለው ዮሴፍ (ፋሪስ ብሩ) ለእህቶቹ ሲል ከፍ ዝቅ በሚልበት ህይወት ውስጥ ለአሳዳጆቹ ፈተና የሚሆን ወንጀል ቢፈፅምም፤ የኋላ- ኋላ ግን ይባስ ብሎ አሳዳጁን የሚያሳድድ ”ነገር የገባው ነው” ተደርጎ ተስሏል። በሌላም በኩል “ከወንጀሉ ይልቅ የወንጀሉ መንስኤ ቢታወቅ” የሚመርጡ የፖሊስ አዛዡን በፊልሙ ውስጥ ማግኘት ጥበቡ ያለውን ብሩህ ተስፋ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

በፊልሙ ውስጥ በተሰወረ ማንነት የወንጀል ዱካ የምታነፈንፈው ፊያሜታ (የትናየት ታምራት) በምታሳድደው ሰው መረብ ውስጥ መውደቋን ዘግይታም ቢሆን ተረድታለች። እናም ወንጀልና ፍቅር በፊልም ውስጥ ግብግብ ሲገጥሙ ያስመለክተናል።

መስጠትን ለዋናው ገፀ-ባህሪይ (ዮሴፍ) በማሳየት በህይወት ሚዛን እንዲኖረው የሚያደርጉት የጎዳና ተዳዳሪው ጋሽ ሞገስ (ተዘራ ለማ) ከሚተርኳቸው ማራኪ ታሪኮች መካከል በተለይም አንዱ ማህበረሰብ ግለሰብን ብሎም ሀገርን እንዴት እንደሚሰራ ማሳያ በመሆኑ ሊጠቀስ ይገባዋል። ታሪኩ ከሞላ ጎደል እንዲህ ነው። . . .

ኢትዮጵያውያን አምላክን መልካም መሪ እንደሾመላቸው ይጠይቃሉ። አምላክም ከተለያዩ የወጪ ሀገራት ሰው መርጦ በመሪነት ቢሾምላቸው ይስማሙ እንደሆነ ቢጠይቅ ህዝቡ፣ “እኛ ቀኝ ያልተገዛን ህዝቦች ሆነን እንዴት ከሌላ ሀገር መልካም መሪ ይሾምብናል፤ ይልቅስ ከመካከላችን አንዱን መርጠህ መሪ አድርግልን” ይሉታል። ፈጣሪ ግን መልካም መሪ መሆን የሚችል ሰው ከናንተ ህብረተሰብ አልተፈጠረምና አዝናለሁ፤ እኔ ሰው ፈጥሬያለሁ እናንተ ደግሞ መሪያችሁን ፍጠሩ!” ይላል።. . . እናም “50 ሎሚ” ፊልም ፈጣሪ ሰውን ፈጠረ ህዝብ ደግሞ መሪውን ይፍጠር ይሉትን ማህበራዊ ፍልስፍና ያመለክተናል። . . . “ሰው ልቡ ከጠቆረ ሀገሩ ሁሉ ይጠቁራል” የሚለው ይህ ፊልም ማህበረሰብ የሚጠቅመውንም ሆነ የሚጎዳውን ነገር ከዛሬ ይልቅ ለነገ የማቆየት ምርጫ እንዳለው ይሰብካል። እናም በፊልሙ ፖስተር ላይ “ከነገ ይልቅ ትናንት ሩቅ ነው” ሲል ነገን በተሻለ ተስፋ እንድናይ ያዘጋጀናል።

በመጨረሻም በፊልሙ ውስጥ ከተነሳው ማህበራዊ ስላቅ መካከል አንዱን ልጥቀስ፤ በባንክ ዘረፋ የተጠረጠረውን ሰው ለማጥመድ የተላኩት ገፀ- ባህሪያት በቡና ቤት ውስጥ የሚለዋወጡት ንግግር (ዲያሎግ) እንዲህ ይላል። ወንዱ “ከፈለግሽ 100 ሴት አሰልፋለሁ” ሴቷ በንቀት ስትመልስ፣ “አንተ ማነህና ነው 100 ሴት የምታሰልፈው? ውሃ ነህ? ዳቦ ነህ? ታክሲ ነህ? ወይስ ስንዴ ነህ?” “50 ሎሚ” በስግብግቦች የተነጠቅነውን ሃምሳ ጌጥ አንድ ሰው ሲያስመልስ የሚያሳይ የህብረተሰብ መስታወት ነውና በፊልሙ ውስጥ ራሳችንን እንመልከት። መልካም የመዝናኛ ሳምንት!!! 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
10737 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us