ገፀ-ባህሪያቱ ያበዱበት “ማበዴ ነው”

Wednesday, 23 March 2016 12:10

 

·         የቴአትሩ ርዕስ - “ማበዴ ነው”

·         ድርሰትና ዝግጅት - ቢኒያም ወርቁ

·         ዝግጅት አስተባባሪዎች - ያሬድ ኤጉ፣ ሲራክ ጥበቡና ዮናስ አለማየሁ

·         ተዋንያን - ፍቃዱ ከበደ፣ ቅድስት ገ/ስላሴ፣ ራሔል ተሾመ እና ሔኖክ ብርሃኑ

   ናቸው።

·         ፕሮዲዩሰር - ለታሪክ አድቨርታይዚንግ

ይህ ቴአትር ከዓመት በላይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በመድረክ ላይ ቆይቷል። በታሪኩ እርስ በእርሳቸው ቀርቶ፤ ራስ ለራሳቸው መግባባት የተሳናቸውን ጥንዶች ሳይጀመር ያለቀ የትዳር ህይወት በአስቂኝ መልኩ ይተርካል።

“ማበዴ ነው” በልመና የተጀመረ የፍርቅ ግንኙነት፣ በይሉኝታ የተጠነሰሰ ወዳጅነት፤ በንቀት የተሞላን ጥምረት የሚያሳይ የሳታየር ኮሜዲ ዘውግ ያለው ቴአትር ነው። በቀላል የመድረክ ግንባታ፣ ስሜት በሚታይበት አተዋወንና በማይጎረብጥ ዝግጅት ቀርቦ ተመልካችን ጭምር የሚያጫውት አይነት ስራ ነው። ቴአትሩ ዘወትር ቅዳሜ በ11 ሰዓት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በመታየት ላይ ይገኛል።

የማይግባቡ ጥንዶች ለሚገነቡት ትዳር የጋብቻ ስነስርዓታቸውን ለመፈፀም በቀራቸው ቀናት ውስጥ ልምምድ ቢያደርጉም፣ ትዳር በልምምድ አይመጣምና ነገራቸው ሁሉ፤ “ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ” አይነት መሆኑ ለቴአትሩ ሳታየርነት የደምስሩ ሆኗል።

“ማበዴ ነው” ቴአትር በአራት ትዕይንቶች ተከፍሎ፤ በአራት ወጣት ተዋንያን የሚተወን እና ስነ-ልቦናዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን የሚዳስስ ስራ ነው። በገራገርነትና በጅላጅል ባህሪው የሚስቱን ጫና መቋቋም የተሳነው ፋርማሲስቱ ጌታቸው (ፍቃዱ ከበደ) በሚስቱ የበላይነት ሲደቆስ ማየት፤ በአትክልትና በአበባ እንክብካቤ መስህብና ፍቅር የተለከፈችው ማርታ (ቅድስት ገ/ስላሴ) ከማትወደው ሰው ጋር የጀመረችው የጋብቻ ጉዞ አታካችነት ከገፅታዋ መመልከት ቀላል ነው። እናም ነገራቸው ሁሉ “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” ይሉት አይነት የማይሳካ ጥምረትን ፍለጋ የሚደርግ ከንቱ ልፋት እናያለን።

በሁለቱ ጥንዶች የጋብቻ ስነሥርዓት ላይ በሚዜነት ለመታደም ከጀርመን የሚመጣው አርቲስቱ ቴሪ (ሔኖክ ብርሃኔ) እና የገጠር መምህሯ ጄሪ (ራሔል ተሾመ) በቴአትሩ ውስጥ የታሪክ ለውጥ መንስኤ ሲሆኑ እናያለን።

“በጣም ሰለቸኸኝ” ስትል እጮኛዋን በግልፅ የምትናገር ሚስት እና “የፍቅሬን ሩቡን ያህል እንኳን አልገለፅኩልሽም” በሚል አፍቃሪ መካከል በእንግድነት የተገኙት ሁለቱ ሚዜዎች፤ ታሪክ ብቻ ሳይሆን ልብ ነጣቂም ሆነው ቀርበዋል። በፎቶ እንኳን የማይተዋወቁት ሚዜዎቹ ካላቸው የትዳር ጉጉት የተነሳ በየፊናቸው አንዳቸው ሌላኛቸውን ለማግባት ወስነው የተገኙ ቢሆንም፤ ዳሩ  ግን ነገር ተቀይሮ ሙሽሮቹ የሚዜዎቹ ግጣም ሆነው እናገኛቸዋለን።

ዱላን እንደጦር የምትፈራውና አጋጣሚዎች ሁሉ ድብድብ የሚመስሏት መምህር ጄሪ፣ ከገጠር ወጥታ ውጪ ሀገር ለመሄድ ካላት ጉጉት የተነሳ፣ ከጀርመን የመጣውን ሚዜ ለማግባት መወሰኗን ለወዳጇ ስታዋያት፣ “መቼም የጀርመን ዱላ እንደሀበሻው አይሆንም” ስትል ራሷን ስታፅናና ማየት የቴአትሩን ሳታየርነት ያጎላዋል።

ከሚዜዋ ጋር በስካር መንፈስ ከመግባባት ባለፈ፤ ማውራት የሌለባቸውን ነገር እስከማውራት የደረሱት ጌታቸውና ጄሪ፣ የፍቅር ስበታቸው ሲጨምር እናያለን። እናም በጄሪ እንክብካቤ አክብሮትና ሰላማዊነት ልቡ የሚሸበርበት ጌታቸው፤ የእስካሁኑን የትዳር መጀመሪ ጉዞውን ሁሉ ሽሮ ሚዜዋን ሲመርጣት፤ “በህይወቴ ትልቁን ስህተት እንደሰራሁ የገባኝ አሁን ነው” ይለናል።

“ተጋብቶ ከመፋታት ሳይጋቡ መፋታት የምትለዋን ለጥቅስ የምትበቃ ንግግር ተናግረሻል የሚለው ሙሽራው ጌታቸው፤ እጮኛው ማርታን እንደማይወዳትና ጋብቻው ቢቀር ደስ እንደሚለው ጭምር ለጄሪ ሲነግራት መስማቱ፤ “ይህቺ ጠጋ -ጠጋ እቃ ለማንሳት ነው” ይሉትን ተረት ለተመልካች ያስታውሰዋል። ይባስ ብሎም ግትርነቷንና ጨቋኝነቷን ታግሶ የኖረው ጌታቸው ማርታን የሚገልፃት “ማርታ ማለት ከግራ የሚጀምር የአማርኛ መፅሐፍ ናት” በሚል ነው።

“ማበዴ ነው” ባለታሪኮቹ ሁሉ ሊያብዱ ተቃርበው፤ ነገር ግን ከእብደት መልስ ፈውስ የሚሆን የፍቅር መፍትሄን የሚያገኙበት ቴአትር ነው።

በቴአትሩ ውስጥ ጥያቄ የሚያጭረው (የሚፈጥረው) አንድ ነገር አለ፤ ይህውም በዚህ ዘመን ላይ ተንቀሳቃሽ ስልክ (ሞባይል) እያለ ለጭፈራ በወጡበት ምሽት ተጠፋፍተው መመለሳቸው ነው። አንድም ጊዜ ስለስልክ ካለመነሳቱም በላይ ሆን ብለው ተጠፋፍተው ነው እንድንል እንኳን ምክንያት ያልተሰጠበት መሆኑ ከአመክንዮ አንጻር በጣም ልል ነው። የ“ማበዴ ነው” ገፀ-ባህሪያት ግጣማቸውን አግኝተው በፍቅር እስከሚከንፉ ድረስ ሁሉም የሚያብዱበት አዝናኝ ቴአትር ነው። መልካም የመዝናኛ ሳምንት!

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
14926 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us