የአባት ዕዳ፤ “አትውደድ አትውለድ”

Wednesday, 30 March 2016 11:54

 

·         የፊልሙ ርዕስ - “አትውደድ አትውለድ”

·         ፕሮዳክሽን - ግዕዝ ፊልም ፕሮዳክሽን

·         ፕሮዲዩሰር - ብሩክ አየለ

·         ኤዲተር - ናኦድ ጋሻውና አቤኔዘር ፍቃዱ

·         ድርሰትና ዝግጅት - ናኦድ ጋሻው

·         ተዋንያን -ፍቅር አለማየሁ፣ አለማየሁ ታደሰ፣ ሽመልስ በቀለ፣ ደረጃ ሃይሌ፣ ጀንበር አሰፋ፣ ቤተልሄም ሰለሞን፣ ሰላም ይሁን አስራትና ሌሎችም

 

“የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም” ይሉትን ብሂል ተንተርሶ፤ ተዳፍኖ በዘገየ በቀል እና በቤተሰብ ፍቅር ተጎንጉኖ የሚታይ በፍግ የተሞላ ልብ አንጠልጣይ የቤተሰብ ፊልም ነው “አትውደድ፣ አትወለድ”

 

ወላጅ ለልጁ የማይሆነው የለም የሚለን ይህ ፊልም፤ የአባት እዳ ለልጅ፤ የልጅም ዕዳ ለወላጅ ሲሆን ያሳየናል። ከአስር ዓመታት በፊት በተከሰተ የህግ ስህተት ምክንያት የሚወደውን ልጁንና ሚስቱን የተነጠቀው አባወራ የበቀል ስልቱን ሲመዠርጥ፤ የተንኮል ድሩን ሲያደራ ያሳየናል። እናም የበቀል ጥምን ለማርካት፤ የክፋት ፅዋው እስኪሞላ የሚቀጣውን ሰው እስኪወድና እስኪወልድ ይጠብቃል።

 

የተወሳሰበ የወንጀል ሴራ፤ ያልተቋጨ የትዳር ጥያቄ፤ ያልተመለሰ የወላጅ ጉጉት፤ ዱካ የሚያነፈንፍ የምርምር ቡድን ሁሉ የሚታየው በዚሁ “አትውደድ አትውለድ” ፊልም ውስጥ ነው።

 

በሙያው ጠንካራ የሕግ ባለሙያ የሆነው ተስፋዬ (አለማየሁ ታደሰ) ከቀድሞ ፍቅረኛው የወለዳትን ልጅ ስጦታ (ፍቅር አለማየሁ) በድንገት ዱብ ዕዳ ያውቃታል። ይህም እናቷ ታማ በሆስፒታል ጣር ላይ ሳለች በእህቱ በኩል ቤቱ ድረስ የመጣችውን አምኖ በመቀበልና በአዲሲቷ ፍቅረኛው (ቤቴልሄም ሰለሞን) የአግባኝ ጥያቄ መካከል ሲወጠር እንመለከታለን።

በአንፃሩ ደግሞ የህክምና ትምህርቱን በውጪ ሀገር ተከታትሎ የመጣውና በበቀል ሰይፉን ከአፎቱ ለመሳብ ጊዜ እየጠበቀ የነበረው ዶክተር ሰለሞን (ሽመልስ በቀለ) ባልተጠበቀ አጋጣሚ ግዳዩን እጁ ላይ ወድቆ ያገኘዋል።

 

በፊልሙ ውስጥ ግራ የሆነ ባህሪይ የሚታይባቸው የተስፋዬ ወላጆች ሮማን (ጀንበር አሰፋ) እና መብራቱ (ደረጄ ሃይሌ) በአንዲትም ሃሳብ መስማማት እንደተሳናቸው፤ ባለመግባባታቸው ውስጥ ለተመልካች ሳቅ ያጭራሉ። ያም ሆኖ አንድ የሚስማሙበትም ሆነ የሚሰውበት ሰው ቢኖር ልጃቸው ተስፋዬ ብቻ ነው። ይህም በግልጽ የሚታየው በስተመጨረሻ የሰራውን ጀብዱ ተመልክተው አባት፣ “የእናቱ ልጅ!” ሲሉ እናት በበኩላቸው፣ “የአባቱ ልጅ” ይሉናል። ከሁሉም በላይ ግን ጡረተኛ ደህንነቶች መሆናቸው ለሰሩት ስራ ሽፋን ሆኖ ቀርቧል።

 

በሌላ በኩል የልጅ አዋቂ አይነት ባህሪን የተላበሰችው ስጦታ (ፍቅር አለማየሁ) . . . ዳይሬክተሩ በመጀመሪያው ትዕይትን (ሲን) ላይ ያስመረኮዛት ዣንጠላ ብዙ ትርጉም የነበረው ነው ለማለት ያስደፍራል።

 

ልጅቷ ብርቱና ጠንካራ፤ ብልህና በራሷ የምትተማመን ተደርጋ ከመሳሏም በላይ የእናቷን ሞት ጭምር ለመቀበል መቁረጧን ሊያሳየን ይፈልጋል። አባቷንም ቢሆን ለራሷ በጠዋት ትምህርት ቤት ሲያደርሳት ለራሷ ከተዘጋጀ ምግብ ላይ ቁርስ እንዲበላ ስትጋብዘው፣ “ወንድልጅ መዋያው ስለማይታወቅ ቁርስ ሳይበላ ከቤት አይወጣም” ስትል ትገስፀዋለች። እናም የቋጠረችውን ምሳ ለአባቷ ትታለት ወደትምህርት ቤት ትገባለች። አባትም በልጁ ድርጊት ተገርሞ ስለልጁ ሲያሥብ ይውላል። እናም ይህቺ የልጅ አዋቂ የፊልሙ ማዕከላዊ መዘወር ሆና ተስላለች።

 

በኢንተርፖል የወንጀል ምርመራ ውስጥ መስራት የቻለው አብይ (ሰላምይሁን አስራት) በክስተቶቹ ሁሉ ጨዋታን መፍጠር የሚወድ ገፀ-ባህሪይ ከመሆኑ የተነሳ ሽጉጥ ተነጣጥሮበት ሳይቀር መቀለድ መቻሉ የፊልሙን ዘውግ የሚፈታተን ነው ማለት ይቻላል። ይህ ገፀ-ባህሪይ ለእጮኛው የትዳር ቀለበት ያስረበት ትዕይንትም በጣም ዋዘኛ ጨዋታ የታከለበት እንደነበር ታይቷል።

 

ከወንጀል ክትትል ቢሮ ውጪ በሆነ መንገድ የተደረገው የስልክ ጠለፋና የአድራሻ አሰራር፤ የህፃኗ ተተርጓሚ ንግግሮችን መናገር መቻሏ፤ ከዋናው ወንጀል አድራጊ የተነጠቀ ወንጀል መኖሩ ፊልሙን ውስብስብ አድርጎታል ማለት ይቻላል። ግን በፊልሙ ውስጥ የማይዋጥ ትዕይንት (ሲን) ሆኖ የቀረበው እናትና ልጅ ተደብድቦ ቱቦ ውስጥ የወደቀውን ሰው ማንሳታቸውን ተከትሎ እናት የመኪና አደጋ ሲደርስባት አጠገቧ የነበረችው ልጅ ድርጊቱን የተረዳችው እጅግ ዘግይታ ነበር።

 

አትውደድ አትውለድ ፊልም በተለይ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም እሳቤ /Imaginative/ እና በግራፊክ ዲዛየን አዲስ ፈጠራን ይዞ ቀርቧል።

 

“አትውደድ አትውለድ” በካሜራ አንጻር፤ በኤዲቲንግ፣ በሙዚቃና በብርሃን አጠቃቀም የተሻለ አቅም የታየበት ቢሆንም ያነሳውን ታሪክ ያቀረበበት ውስብስብ መንገድ ከማዝናናቱ ባለፈ የሚያወናብድ ነው ሊባል ይችላል። ያም ሆኖ የፈጠራና የሀሳብ ነፃነት ጥግ የለውም በሚል የተደራጁና የታጠቁ “ወንጀለኞች” በአንድ በኩል፤ በሌላ በኩል ደግሞ በአንድ መኖሪያ ቤት ጣሪያ ስር ሆነው የወንጀለኞችን ዱካ የሚከተሉ ባለቴክኖሎጂ የምርመራ ቢሮ ሠራተኞች በፊልሙ ውስጥ “ምዕራባዊነት” አጉልተው የሚያሳዩ/ የሚያስታውሱ ቀረፃዎች ሆነው ቀርተዋል። እናም በፊልሙ ውስጥ “ጎሽ ለልጇ ስትል. . .” ይሉት ታሪክ የሚታይ ሲሆን፤ “አትውደድ አትውለድ” ነገር ግን ከወደድክና ከወለድክ ደግሞ በወደድከውና በወለድከው የመጣውን ለመቀበል ተዘጋጅ ይለናል። መልካም የመዝናኛ ሳምንት!!!  

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
14988 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us