ፍቅር እስከ መቃብርን በሌላ መነጽር የቃኘው “ምናብ እና ገሃድ”

Wednesday, 06 April 2016 12:00

 

በይርጋ አበበ

·         የመጽሀፉ ርዕስ ምናብ እና ገሀድ የሩቅ ቅርብ ዝንቅ 

·         ደራሲ ዶክተር ዘካሪያስ ዓምደብርሃን

·         የገጽ ብዛት 265

·         ዘውግ ሀይማኖታዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሀሳቦች በቤተ ክርስቲያን እና በካህናት ውስጥ

·         መነሻ ሀሳብ የዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ “ፍቅር እስከ መቃብር መጽሀፍ”

·         ህትመት ሮኆቦት አታሚዎች

·         ዋጋ ሰባ ብር

በውጭ ዓለም ያሉ ደራሲያን የአገራቸውንና የዓለምን ፖለቲካ ቀጣይ እጣ ፈንታ የሚመለከቱ ጽሁፎችን ጽፈው ለንባብ ያበቃሉ። ለዚህ አባባል ምሳሌ ሆኖ በስፋት የሚነሳው ብሪቲሽ ህንዳዊው ጆርጅ ኦርዌል ነው። ኦርዌል በተለይ “Animal Farm” በሚለው መጽሀፉ “ኮምዩኒዝም የሚባለው ርዕዮተ ዓለም እንዴት እንደሚወድቅ ለዛ ባለው ቅኔያዊ ጽሁፉ አስነብቦ ነበር።

ልክ እንደ ኦርዌል ሁሉ በአገራችን በተለይም በፖለቲካው ላይ ምን ሊከሰት እንደሚችል በብዕራቸው የገለጹ ደራሲዎች አሉ። በርካቶች በቀይ ኮከብ ዘመቻ ወቅት በጻፈውና ለሞቱ ምክንያት የሆነው መጽሀፍ ተብሎ በሚታወቀው “ኦሮማይ” መጽሀፍ ደራሲ በዓሉ ግርማ የደርግን ስርዓት “ኦሮማይ” በሎ የገለጸበት አንዱ ሲሆን ዘውዳዊውን መንግስት መናገርም ሆነ መተቸት “ውግዝ ወ አርዮስ” በሚያስብልበት ዘመን “ፍቅር እስከ መቃብር” ብለው የጻፉት ክቡር ዶክተር ሀዲስ አለማየሁ ሌላው ናቸው።

ዲፕሎማቱ መምህሩ እና ደራሲው ክቡር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ ዘመን ተሻጋሪ በሆነው መጽሀፋቸው የዘውዳዊውን መንግስት አወዳደቅ የሚተነብይ መጽሃፋቸውን ሲጽፉ ለዘዳዊው መንግስት ውድቀት ተባባሪ የሆኑትን አካላት በተለይም የሀይማኖት ሊሂቃንን ስህተትም ጽፈውታል። ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ በፍቅር እስከ መቃብር መጽሀፋቸው “ፊታውራሪ መሸሻ” የተባሉት አምባገነን አገረ ገዥ “ጉዱ ካሳ” በተባለ አስተዋይ የቤተ ክርስቲያን ሰው መጻኢው ሁኔታ እንዲነገራቸው ቢያስደርጉም ፊታራሪ መሸሻ የጉዱ ካሳን ጦማር ከመስማት ይልቅ ውዳሴ ከንቱ እያበዙ የሚናገሩትን የቄስ ሞገሴን እና ሌሎች የቤተ ክህነት ሰዎች የሚነግሯቸውን ብቻ መስማትን መርጠው ነበር። በዚህም ምክንያት “አበጀ በለው” የተባለ የገበሬዎች አመጽ መሪ ተነስቶ ሲያስራቸው እንመለከታለን። ይህ ምክረ ሀሳብ ለልቦለዱ ማጣፈጫነት የቀረበ ሳይሆን በወቅቱ የአገሪቱ ንጉስ ለነበሩት ለአጼ ኃይለሥላሴም ጭምር መልዕክት ያዘለ ነበር። ዶክተር ዘካሪያስ ዓምደብርሃን “ምናብ እና ገሃድ” በሚል ርዕስ ባዘጋጁት ጥናታዊ መጽሃፍ ሊያስዳስሱን የሞከሩትም የዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁን ያልተሳካ ምክር ከእነ ስህተቶቹ እንዲሁም በዚህ መን ላሉት አጼዎች መልዕክት የሚያስተላለፍ መጽሀፍ ነው።

የዶክተር ዘካሪያስ ጥናታዊ መጽሃፍ መነሻውን በፍቅር እስከ መቃብር መጽሃፍ ላይ አድርጎ አሁን ባለንበት ዘመንም ሆነ ባለፍናቸው መንገዶች ሁሉ የተሰሩ እና አሁንም እየተሰሩ ያሉ ስህተቶችን ቁልጭ አድርገው አስቀምጠዋል። ጸሀፊው የተሰሩ ስህተቶች ያስከፈሉትን ዋጋም በሚገባ ያስቀመጡ ሲሆን አያይዘውም ለችግሮቹ መፍትሔም አስቀምጠዋል። ይህ ደግሞ ከአዘንድ የጥናት ጽሁፍ የሚጠበቅ ነው።

የምናብ እና ገሀድ ጸሀፊ ዶክተር ዘካሪያስ ዓምደብርሃን ለመጽሀፋቸው ዝግጅት መጽሃፍ ቅዱስን ጨምሮ ከ30 በላይ ሀይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ታሪካዊ መጽሃፎችን እንዲሁም የተለያዩ መዝገበ ቃላትን ተጠቅመዋል። መጽሁፉን የተመለከትንበት መጣጥፍ ሙሉ ክፍል ከዚህ በታች ቀርቧል።

የዶክተር ዘካሪያስ ዕይታ በፍቅር እስከ መቃብር መጽሀፍ

ዶክተር ዘካሪያስ በመጽሀፋቸው በዓለም ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ስለሚፈጥሩት ሁለት ተቋማት (ኃይማኖት እና መንግስት) ሰፋ ያለ ማብራሪያ ይሰጡና “በዓለማችን አንዱ አንጋሽ ሌላው ነጋሽ ሆነው የቆዩት እነዚህ ሁለት ተቋማት መለየት እስኪያቅተን ድረስ ጋብቻቸው ፍጹም ነበር” ሲሉ በመግቢያቸው ላይ መናገር ይጀምራሉ። ጸሀፊው ሁለቱ ተቋማት ጋብቻቸው የድሮ ሆኖ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ፍቺ የፈጸሙ አለመሆናቸውንም ይገልጻሉ። ለምሳሌ በገጽ “ምንም እንኳ ዛሬ ዛሬ የምናያቸው ገዥዎች መንግስት (ፖለቲካ) በሀይማኖት ጉዳዮች ጣልቃ አይገባም እያሉ ቢደሰኩሩም በተዘዋዋሪ መልኩ የኃይማኖት ሊሂቃንን ለማንበርከክ የማይምሱት ጉድጓድ የለም” ሲሉ የእምነት ተቋማቱ እና ሊሂቃኑ በእጅ አዙር የፖለቲካው ጥገኛ ሆነው መቀጠላቸውን ይናገራሉ።

የኃይማኖት ሊሂቃን በህዝብ እና በአገር አስተዳደር ላይ ሊጫወቱት የሚገባ ሚና ቢኖርም ሚናቸውን መወጣት አለመቻላቸውን የሚናገሩት ዶክተር ዘካሪያስ፤ በድሮ ዘመን የነበረው የኃይማኖት ተቋማት ሊሂቃን ተንበርካኪነትና ለሆዳቸው ማደር በዚህ ዘመንም አገሪቱን ዋጋ እያስከፈላት መሆኑን ሲገልጹ “ዛሬ የምናያቸው አምባገነን መሪዎች በማህበረሰቡ ላይ ያለማንም ከልካይ የሚፈነጩት ከኃይማኖተኛ ተቋማት በቅለው በወጡ ሊሂቃን ዝምታ እና ከዚህ የተነሳ በመጣ ዝምተኝነት ነው” ይላሉ።

 ዶክተር ዘካሪያስ የኃማኖት ተቋማት ሊሂቃኑ ሚናቸውን በአግባቡ እንዳይወጡ የፍርሀት ቆፈን ይዟቸዋል ሲሉ የጥናታቸውን ውጤት ይገልጻሉ። ለሊሂቃኑ በፍርሃት ቆፈን ውስጥ መዘፈቅ ሁለት ገፊ ምክንያቶችን የሚያቀርቡት ጸሀፊው የመጀመሪያው “ከእውቀት ማነስ የመጣ ነው” ይላሉ። በሁለተኛ ደረጃ ያስቀመጡት ደግሞ “የሀይል አሰላለፍ መለወጥ ነው” ብለዋል። ለሁለት መከራከሪያ ነጥባቸው ያቀረቡት አስረጂ ምክንያት ደግሞ “በጥንቱ ዘመን የነበረው የኃይማኖት ሊሂቃን የፖለቲካ ሀይል ቀንሶ በአምባገነን መሪዎች መዳፍ ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል ቁጥጥር ስር መዋሉ ስጋት ፈጥሯል” በማለት አቅርበዋል። ዶክተር ዘካሪያስ የኃይማኖት ሊሂቃንን የፍርሃት ቆፈን የወደቁበትን ምክንያት ሲያቀርቡ “በእውቀት ማነስ” ለሚለው መከራከሪያቸው አስረጂ ነጥብ ሳያቀርቡ አልፈውታል።

በዚያም ተባለ በዚህ ግን የኃይማኖት ሊሂቃን በፍርሃት ቆፈን መውደቅ የሚያሳድርባቸው ተንበርካኪነት በሊሂቃኑ ላይ አርፎ የሚቀር ሳይሆን ለለሚመሩት ምእመንም የሚተርፍ መሆኑን ዶክተር ዘካሪያስ ይናገራሉ። የኃይማኖት የፍርሃት ቆፈን ከማንኛውም አይነት ሊሂቃን የበለጠ ተላላፊ ነው የሚሉት ጸሃፊው “ዛሬ በአገራችን የሚታየውን ክስተትም ሆነ በዘመናት መካከል በታሪክ ጎልብቶ የሚታየውን የኃይማኖተኛ ሊሂቃን የፍርሃት ቆፈን ለሚመለከት ሰው ክስተቱ አሳዛኝ ሆኖ ይታየዋል። በቄሳር እግር ስር ያልወደቀ ሊሂቃን ከኃይማኖት ተቋማት መካከል ማግኘት ይከብዳል። የቄሳርን ትርፍራፊ ያልለመደ ካህን የለም ማለት ይቻላል። የኃይማኖት ሊሂቃን ከሁሉ የበለጠ ለቄሳር መስዋዕት በማቅረብ ተወዳዳሪ የላቸውም። የኃይማኖት ሊሂቃኑ የቄሳራዊያን ሊሂቃን ባሪያ ወደመሆን ደረጃ ከተሸጋገረ ሰነባብቷል” ሲሉ ገልጸዋል።  

ሌላው ሀዲስ ዓለማየሁ?

ዶክተር ዘካሪያስ ዓምደብርሃን ሃይማኖተኛ ሲሆኑ በሚከተሉት የሃይማኖት ተቋም ውስጥም “ፓስተር መሆናቸውንና በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ አገልግሎት” እንደሚሰጡ ተናግረዋል። ዶክተር ወይም ፓስተር ዘካሪያስ እሳቸውም እንደ ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ ኃይማኖተኛ ቢሆኑም የኃይማኖት ተቋማትን ሊሂቃን ሚና ለመተቸት ፍርሃት አልቆፈደዳቸውም። ክቡር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮት ተኮትኩተው ያደጉ ቢሆኑም በቤተ ክርስቲያኒቷ ውስጥ የሚያዩዋቸውን ያፈነገጡና አግባብ ያልሆኑ ድርጊቶችን በመጽሀፋቸው በግልጽ ተችተዋል። ለዚህ ደግሞ እንደ ጉዱ ካሳ (ካሳ ዳምጤ) አይነት ገጸ ባህሪ የቤተ ክርስቲያኒቷን ሊሂቃን ድክመት ሲያወግዝ ይታያል።

ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ በመጽሀፋቸው ካሰፈሯቸው ገጸ ባህሪያት መካከል በቤተ ክህነት ሰዎች እንደ ጤነኛ የሚታዩት ቄስ ሞገሴ የሚያቀርቡት ሀሳብ ጤነኝነት የሚጎድለው ሆኖ ሳለ በምትኩ እንደ ጉዱ ካሳ አይነት የተወገዘ ገጸ ባህሪን የተላበሰ ሰው ግን ሀሳቦቹ እውነት ሆኖ መቅረቡን አሳይተውናል።

ልክ እንደ ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ ሁሉ ዶክተር ዘካሪያስም በጥናታዊ መጽሀፋቸው ላይ የሃይማኖት ተቋማት ሊሂቃን (መሪዎች) በአገራዊ ጉዳዮች ላይ እያደረጉ ያሉትን አስተዋጽኦ ይኮንናሉ። ሀሳባቸውን ሲገልጹም “ዛሬ በምናየው ዓለም አቀፋዊም ሆነ አገራዊ ሁኔታ ውስጥ የኃይማኖት እና የፖለቲካ ተቋማት ጋብቻ ምክንያት ማህበረሰቡ የሚያልፍበትን ዋና ብዝበዛ የኃይማኖት ተቋማትም ሆኑ መሪዎቿ ከላይ የተሰጣቸውን መለኮታዊ ትዕዛዝ በመዘንጋት ከቄሳር ልጆች ጋር የሚያደርጉት ውስልትና እጅግ አስጸያፊ ነው” ሲሉ በግልጽ ይተቻሉ።

ዶክተር ዘካሪያስ ከላይ ላለው ሀሳባቸው የሰጡት ማጠናከሪያ ሀሳብ ደግሞ “በመጽሀፉ (ፍቅር እስከ መቃብር) የሚታዩት አድርባይ የኃይማኖት ሊሂቃን የፖለቲካው ምሰሶ እና ድጋፍ በመሆን ይጫወቱት የነበረውን አይነት ገጸ ባህሪ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ለማየት መብቃታችን ማህበረሰቡ፣ የፖለቲካ ሊሂቃን፣የኃይማኖት ሊሂቃንና የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ትንቢታዊ የሆነውን የፍቅር እሰከመቃብርን የማንቂያ ደወል አለመስማት ወይም ቸልታ ይመስለኛል” በማለት ገልጸዋል።  

ዶክተር ዘካሪያስ ስለ ፍቅር እስከ መቃብር እና ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ

ዶክተር ዘካሪያስ ዓምደብርሃን “ምናብ እና ገሀድ” የተሰኘውን የጥናት መጽሀፍ ያዘጋጁት የዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁን “ፍቅር እስከ መቃብር”ን መነሻ በማድረግ መሆኑን ቀደም ሲል ገልጸነዋል። ዶክተር ዘካሪያስ የፍቅር እሰከመቃብርን ደራሲ ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁን ጥቃት የማይወዱ እና ደፋር “ህያው ጉዱ ካሳ” ብሎ ይጠራቸዋል። የድፍረታቸውና ጥቃት የማይወዱ መሆናቸውን ሲገልጹም “ደራሲው መጽሀፉን በዚያን ጊዜ (ንጉሱ ስልጣን ላይ እያሉ) ማሳተማቸው ነው” ይላሉ። አያይዘውም “ደራሲው (ሀዲስ ዓለማየሁን) ማህበረሰቡ ለውጥ እንደሚሻ ግልጽ በሆነ ሁኔታ ተንትነዋል። ትንታኔው የሚያሳየው በሁለት መንገድ ሲሆን አንደኛው በባህሪያቱ ሁለተኛው ደግሞ በትረካቸው ውስጥ መሆኑን ተጢኗል” ሲሉ ገልጸዋል። በደራሲው ላይም “ጉዱ ካሳ” የሚባለው ገጸ ባህሪ የሚስተዋልባቸው እንደሆነ ዶክተር ዘካሪያስ ጽፈዋል።

 ፍቅር እስከ መቃብርን በተመለከተ ደግሞ “የኃይማኖት ተቋማትና የእምነቱ መሪዎች የሚጫወቱት ወላዋይ ገጸ ባህሪ ጉልህ ሆኖ እንዲወጣ ተደርጎ የተሰራው በዚሁ በፍቅር እስከ መቃብር መጽሀፍ ነው። መጽሀፉ ባህል ወግ እምነት ጽናት ፖለቲካ ታማኝነትና አገልጋይነት የተፈተሹበት ነው” ሲሉ ገልጸውታል።

ምናብ እና ገሀድ ታዋቂው የፖለቲካ ሳይንስ አስተማሪው ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማሪያም የመጽሀፉን መቅድም የጻፉ ሲሆን መጽሀፉንም በሀይማኖት አስተምህሮቶችና ስርዓት ላይ ዳሰሳ አድርጎ በአማርኛ ቋንቋ የተጻፈ የመጀመሪያው መጽሀፍ ነው ሲሉ ገልጸውታል።

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ ምናብ እና ገሀድ የሩቅ ቅርብ ዝንቅ በኢትዮጵያ ባህል ወግ ሀይማኖትና ፖለቲካ ላይ ትኩረቱን አድርጎ የተሰራ መጽሀፍ ሲሆን በውስጡም ዘጠኝ ምዕራፎች ይዟል። መጽሀፉ በይዘቱ ለየት ያለ እና ያልተለመደ ነው። የደራሲው የቋንቋ አጠቃቀም እና የዋቢ መጽሀፍትን አወሳሰዳቸው ዶክተር ዘካሪያስ ጥልቅ አንባቢነታቸውን የሚያሳይ ቢሆንም በስፋት በአገራችን የተለመደው የፊደላት ግድፈትና የስርዓተ ነጥብ አጠቃቀማቸው ሊስተካከል የሚገባ ሆኖ አግኝተነዋል። በተለይ የስርዓተ ነጥብ አጠቃቀማቸው የእሳቸውን ሀሳብ እና ከሌሎች ደራሲያን የወሰዷቸውን ሀሳቦች ለመለየት እስከሚያስቸግር ድረስ የተደበላለቁባቸው የመጽሀፉ ክፍሎች ታይተዋል።

ዋጋው 70 የኢትዮጵያ ብር እንደሆነ የተገለጸ ቢሆንም መጽሀፉ ማተሚያ ቤት ከመግባቱ በፊት ዋጋው የተገለጸ ስላልነበረ ተመሳሳይ የወረቀት ቀለም ተፈልጎ በፕላስተር የተለጠፈ መሆኑ ጥሩ አይደለም። ሁለተኛው ዕትም ሲዘጋጅ ታሳቢ ሊደረግባቸው የሚገቡትም እነዚህና ሌሎች ጥቃቅን ስህተቶች እንዲስተካከሉ ትኩረት መስጠት ይሆናል።  

ይምረጡ
(20 ሰዎች መርጠዋል)
12194 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us