በመዝናኛ “ቃና” - ግራና ቀኝ

Wednesday, 13 April 2016 11:53

መጋቢት 26 ቀን 2008 ዓ.ም በይፋ የመዝናኛ መንደሩን የተቀላቀለው ቃና ቴሌቭዥን ጣቢያ በበርካቶ ዘንድ መነጋገሪያና ትኩረት ሳቢ ሆኗል። “ቃና” ቲቪን በተለየ መልኩ ትኩረት እንዲያገኝ ካደረጉት ሰበቦች መካከል አንደኛው በመዝናኛው ዓለም ላይ ሙሉ ትኩረቱን አድርጎ 70 በመቶ የወጪ፤ 30 በመቶ ደግሞ የሀገር ውስጥ ስራዎችን ለተመልካች ሊያቀርብ መሰናዳቱ ነው። ይህንንም ተከትሎ በርካታ የውጪ ሀገር ፊልሞች (በተለይም የላቲን አሜሪካ፣ የኮሪያ፣ የቱርክና የህንድ ፊልሞች) ባለሙያዎቹ “ዳቢንግ” በሚሉት ስልት ወደአማርኛ ቋንቋ በመቀየር “ፍለጋ”፣ “ወጥመድ”፣ “የጠፋ ስም”፣ “የውበት እስረኞች”፣ “ጥቁር ፍቅር”፣ “ዛራና ቻንድራ”፣ ፊልሞችን እነሆ በረከት እያለ ይገኛል።

ይህንን የቃና ቴሌቭዥን አካሄድ የስንፍና ስራ ነው፤ የሀገርን ባህል የሚመርዝ ነው፤ በዳዴ ላይ ያለውን የሀገራችንን የፊልምና የድራማ ጥበብ ገዳይ ነው ሲሉ የሚሞግቱ ተቋማትና ግለሰቦችም ተከስተዋል። ይህንንም ተከትሎ በጋዜጣዊ መግለጫና በማህበራዊ ድረ-ገፆች የተሰሙ በርካታ ድምፆች የመኖራቸውን ያህል ለዛሬ በመዝናኛ አምዳችን የግራ ቀኝ አስተያየቶችንና የምሁራንን አተያይ በቃና ቲቪ አካሄድ ላይ እንጠይቃለን። ለመሆኑ “ቃና” ይዞልን የመጣው የመዝናኛ አካሄድ ለኢትዮጵያ ፊልሞችና የቴሌቭዥን ድራማዎች ምን ጠቀሜታ እና ጉዳት አለው?

“የቃና ቲቪ አመጣጥ የፊልም ኢንዱስትሪዎችን ሊያበረክተው ከሚችለው አስተዋፅኦ አንጻር በበጎም በጎ ባልሆነም መንገድ ተጽዕኖ ይኖረዋል” ይህን የሚሉት የኢትዮጵያ ፊልም ሰሪዎች ማህበር ፀሐፊ አቶ አክሊሉ ማቴዎስ ናቸው። ቃና ቲቪ ስራውን ከመጀመሩ በፊት የመወያየት አጋጣሚ ማህበራችን ነበረው የሚሉት ፀሐፊው፤ ጣቢያው እንደቴክኒክ ይዞት የመጣው ነገር አለማቀፋዊ አሰራር ነው ይላሉ። በተለይም እንደኛ ብዙ ቋንቋ ባለበት ሀገር “ዳቢንግ” (ድምፅን በመቅዳትና አስመስሎ በመለጠፍ  የሚከናወን የትርጉም ስልት) ማስተዋወቁ ትልቅ ነገር ነው። ይህም ከፍ ሲል ትልቅ የመወዳደሪያ ምክንያት ይሆናል የሚሉት አቶ አክሊሉ፤ “ተመልካቹ ከአመታት በፊት ከውጪ ፊልሞች ወደሀገር ውስጥ ፊልሞች ትኩረቱን መልሶ የማየቱን ያህል፤ አሁን በቲቪ የመጣለት የፊልም አቀራረብ ትኩረቱን ሊወስድብን ይችላል ብንል ብንሰጋ እንኳን የተሻለ ለመስራት እንድንጥር መቆስቆሻ ጭምር ሊሆነን እንደሚችል ከግምት መግባት አለበት” ባይናቸው።

ይህንን የአቶ አክሊሉን ሃሳብ ደራሲና ዳይሬክተሩ ዮናስ ብርሃነመዋ ይጋራዋል። “በሀገር ውስጥ ለሚሰሩት የቲቪ ተከታታይ ድራማዎችና ፊልሞች ማሳያ መሆን የሚችሉ ቴክኒኮችን እንማርባቸዋለን። ከሁሉም በላይ ደግሞ ለተመልካቹ አማራጭ ለወጣት ምሩቃንም የስራ ዕድል በመፍጠሩ መልካም ነው ብዬ አስባለሁ” ይላል።

በተለይም በፊልሞቹ ጥራትና ታሪክ፤ የሴራ አጎናጎንና የአተዋወን ብቃት፤ የዳይሬክቲንግ አቅምና የካሜራ ልቀት የበርካታ ወጣቶችን ትኩረት እየሳበ ከመሆኑ አንጻር የባህል ወረራ እየተፈፀመብን ነው የሚሉ ሰዎች አልጠፉም።

የኢትዮጵያ ቴአትር ባለሙያዎች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ቢኒያም ወርቁ፤ የቃና ቲቪ አካሄድ እንደግለሰብም እንደማህበርም ያሳስበናል ባይ ነው። “የቃና ቲቪ አካሄድ ባህል ላይ የመጣ ወረራ ነው። አንዳንድ ሰዎች የጣቢያውን አሰራር አማራጭ ነው ይላሉ፤ ግን አይደለም። ዘመኑ የግሎላይዜሽን ነው ቢባልም በደንብ መረዳት ያለብን ነገር አለ። አሰራሩ የኢትዮጵያ ፊልሞች ላይ ጫና ይፈጥራል፤ ከዚያም በተጨማሪ የሰነፍ ስራ ነው ብለን እናስባን” ሲል ይተቻል። ወጣቱን ሳምንቱን ሙሉ ተከታታይ በሆኑ የውጪ ሀገር ፊልሞች መወጠር ውሎ ሲያድር ቀላል የማይባል ቀውስ መፍጠሩ  አይቀርም ሲልም ነገሩ ልብ ሊባል እንደሚገባ በአፅንኦት ያሳስባል።

ይህንን የደራሲና ዳይሬክተር ቢኒያም ወርቁን ሀሳብ የሚቃወሙ ሰዎች ደግሞ የሀገር ውስጥ ፊልሞችስ በየትኛው ስራቸው ነው ኢትዮጵያዊ ፊልም አሳይተው ባህላችንን የጠበቁት? ሲሉ ይጠይቃሉ።፡ እዚህም መልስ የሚሰጠው ቢኒያም፤ “ይህን ለመናገር ከባድ ቢሆንም አንድ ነገር ግን ግልጽ ነው። እኛ እዚሁ በምንሰራው ስራ መወቃቀስና መነጋገር እንችላለን። ከውጪ የሚመጡ ፊልሞች ግን ይጫኑብናል እንጂ ለመነጋገር አንችልም። ከኛ ቁጥጥር ውጪ ናቸው” ባይ ነው

የኢትዮጵያ ፊልም ሰሪዎች ማህበር ፀሐፊው ግን የተለየ ሃሳብ አላቸው፤ “እንደማህበር ከወዲሁ በጣቢያው የሚታዩ ፊልሞች የባህል ወረራ ያስከትላሉ ብለን በደፈናው አናምንም። ነገር ግን ተመርጠው መቅረባቸውን ፊልሞቹን በማየት በይዞታቸው ላይ መነጋገር ይቻላል” ይላሉ። ይህም ሆኖ ሙሉ በሙሉ ከተፅዕኖ ነፃ ነው ማለት እንዳልሆነም ይጠቁማሉ።

“ኮሜርሻል ፊልሞች ከሞራል ይልቅ በቀላሉ መሳብ የሚችል ነገር ላይ ነው የሚያተኩሩት” የሚለው ቢኒያም፤ የቃና ቲቪ የሚያሳያቸው ፊልሞችም የሞራል ግንባታን አይወክሉም ይላል። ከዚህም ውጪ 70 በመቶ የውጪ ሀገር ፊልሞችን ይዞ መምጣት የኛን ስራዎች ይጎዳል፤ የመመልከቻ ቦታንም ያሳጣል ሲል ይሞግታል። በዚህ የቢኒያም ሃሳብ በፍፁም የማይስማማው የፊልሙ ባለሙያው ዮናስ ብርሃኑ መዋ ደግሞ፤ “የባህል ወረራ ይካሄድብናል የሚለው አስተሳሰብ በጣም ሲበዛ የጠነከረ ነው። በዚህ ደረጃ ልንመለከተው የሚገባ አይመስለኝም፤ ምክንያቱም በአንፃራዊነት ልናነሳቸው የምንችላቸው ሙዚቃዎች፣ አለባበሶች፣ የቋንቋ አጠቃቀሞች፣ አኗኗራችን ከሌላው አለም የወረስናቸው ነገሮች አሉት። ስለዚህ ምንም አይነት የምዕራባውያንን ነገር መጠቀም በባህል ወረራ ነው ተብሎ መንፀባረቁ ተለጥጦ የታየና የሚከብድ ይመስለኛል” ይላል።

የግራቀኙን ሰሞነኛ ሀሳቦ ከተከታተሉ ባለሙያዎች መካከል ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቴአትር ጥበባት መምህር እንዲህ ይላሉ፤ “ኢትዮጵያ ውስጥ ሀገረኛ ፊልሞች ልንላቸው የሚገቡ በጣት የሚቆጠሩ ስራዎች ናቸው። የሃይሌ ገሪማ “ጤዛ” እና “አድዋ”፣ የጳውሎስ ረጋሳ “አሸንጌ” ከወጣት ባለሙያዎች ደግሞ “ስርየት”፣ “አልቦ”፣ “የወንዶች ጉዳይ 1” እና “ላቦረና” ሊጠቀሱ ይችላሉ። የተቀሩት ብዙ የሚቀራቸው ናቸው” ካሉ በኋላ የቃና ቲቪ አመጣጥ ለበርካታ ወጣት ምሩቃን የስራ ዕድል ከመፍጠሩ ባሻገር የተሻሉ ስራዎችን የምናይበት ዕድል ፈጥሮልናል ሲሉ ያክላሉ። ለዚህም የእጓለ ገ/ዮሐንስ አባባል ተውሰው፣ “ያለንን ይዘን የሌለንን ከሌለው ተውሰን እንሂድ” የሚለውን ቃና በሰፊው ተግብሮታል ባይ ናቸው።

ይህም ቢሆን ቃና ቴሌቭዥን ጣቢያ ተገቢውን ክፍያ ለባለሙያዎች በመክፈልና በማሰልጠን ከመስራቱ ባሻገር፤ የሚያቀርባቸውን ፊልሞች አስጠንቶና ለኛ ሀገር ተመልካች የሚመጥኑ ናቸው ያላቸውን ማቅረብ እንዳለበት ባለሙያዎቹ ያሳስባሉ። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው መምህር ከዚህም የመረረ ሃሳብ ለፊልም ባለሙያዎችን ያቀርባሉ። “የራሳችንን የቤት ስራ ሳንሰራ ተወዳዳሪ ስራዎች ሲመጡ መጮህ ዋጋ የለውም። ስንቶች ናቸው ፊልምን በዕውቀት የሚሰሩት?”ሲሉም ይጠይቃሉ። ከፍ ሲልም ቃና ቲቪ ለሃሳብ ስርቆት የተመቹ የነበሩ የውጪ ፊልሞችን ዕውቅና ሰጥቶ በቀጥታ ማቅረቡ ሊያስመሰግነው ይገባል ሲሉም ያሰምሩበታል።

በ“ቃና” ቲቪ አጀማመር ላይ በርካታ አከራካሪ ሃሳቦች ቢነሱም በቀጣይ ልብ ሊባሉ የሚገባቸው መሰረታዊ ጉዳዮች እንዳሉ ግን ሁሉም ሰው ይስማማል። ይኽውም በመጀመሪያ “ቃና” አማራጭ ጣቢያ ሆኖ እንደመምጣቱ ተመራጭም ይሆን ዘንድ፤ ፊልሞቹ ከሞራል ግንባታና ከታሪክ አወቃቀር አንጻር ለሀገራችን ተመልካቾች የማይጎረብጡ እንዲሆኑ በባለሙያዎች ጥናት መደገፉን በእጅጉ ይመክራሉ። ከባለሙያዎችም አንጻር የቲቪ ተከታታይ ድራማ ቴክኒኮችን ከመማሪያ ዕድል አኳያ ተመልክተው ለተሻለ ስራ ልባቸውን ቢከፍቱ ጣቢያውን መማሪያ ማድረግ ይችላሉ የሚሉ እንዳሉ ሁሉ የፊልሞቹ ሳቢነትና በተከታታይ ቀናት መቅረብ የበርካቶችን የጊዜ አጠቃቀም እየተፈታተነው ነው የሚሉም አልታጡም። በተለይም ጣቢያው ለሚያቀርባቸው ፊልሞች በይፋ የእድሜ ገደብ ቢያስቀምጥም የወላጆች ክትትል ግን በእጅጉ አስፈላጊ ስለመሆኑ የሚመክሩት እነዚህ ባለሙያዎች፤ በቃና የሚታዩት ፊልሞች ለኢትዮጵያዊ የፊልም ባለሙያዎችም ሆነ ለተመልካቹ የሚያቀርቡት ነገር በጥንቃቄ መታየት ያለበት ነው ይላሉ። በመጨረሻም እንዲህ እንላለን፤ “ቃና” ይዞልን ከመጣው የመዝናኛ ብፌ በአስተውሎት በማንሳት የተሻለ አተያይና የተሻለ ሕይወት እንዲኖረን እንመኛለን። አልያ ግን ትኩረትና ጥንቃቄ ካልተሰጠው በመዝናኛ ስም የሚቀርቡት ፊልሞች ከአዝናኝነታቸው በላይ መርዘኝነታቸው እንዳያይል ስጋት አለን። መልካም የመዝናኛ ሳምንት!!!

ይምረጡ
(8 ሰዎች መርጠዋል)
12230 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us