“ፅኑ ቃል”ን በትንሿ ቀዳዳ በኩል

Wednesday, 05 March 2014 13:56

እነሆ በ“ስርየት” ፊልሙ ልባችንን ሰቅሎ፣ ቀልባችንን ነቅሎ በፍርሃታችን ልክ ፍቅርን ያሳየን ቶም ፊልም ፕሮዳክሽን በመቀጠል እንካችሁ ያለን “ፔንዱለም” የተሰኘ ስክነት የጠፋበትን የፍቅር ቅብብሎሽና ደርሶ መልስ እንደነበር ይታወሳል። በቅርቡ ደግሞ ልብ ማንጠልጠሉን በተካነበት መንገድ ፍቅርና አልሸነፍ ባይነት ሲተጋተጉ ያሳየበትን “ፅኑ ቃል” የተሰኘ አዲስ ፊልም ይዞልን መጥቷል።

በቶም ቪዲዮ ግራፍ መምህርነቱና በፕሮዲዩሰርነቱ የምናውቀው ቶማስ ጌታቸው በ “ፅኑ ቃል” ፊልም ፕሮዲዩሰር ብቻ ሳይሆን ደራሲም ሆኖ በመምጣቱ የደረጃ ከፍታውን ሳናደንቅለት አናልፍም። ዳይሬክተሩ ደግሞ በጥቂት ስራዎቹም ቢሆን ስሙ የሚነሳለት ዳንኤል በየነ ነው። ለዛሬው የመዝናኛ አምድ የፊልም ዳሰሳ ልናደርግበት የተመረጡው “ፅኑ ቃል” ፊልምን በመሪ ተዋናይነት የሚዘውሩት ግሩም ኤርሚያስ (ከቶም ጋር በስርየት ፊልሙ ይታወሳል)፣ ማህደር አሰፋ እና ኤሊያስ ወሰን የለህ ናቸው።

     “ፅኑ ቃል” የዋናዋ ገፀ-ባህሪይ ቤዛ (ማህደር አሰፋ) አባት ለወዳጃቸው የገቡትን ቃል ለመፈፀም በማሰብ ልጃቸውን ለትዳር ሲያግባቧት እርሷ ደግሞ ከትዳር ይልቅ ትምህርቷን በማስቀደም የዓላማ ፅናቷን፤ ብሎም ትምህርቷን ጨርሳ አዲስ አበባ ውስጥ በባንክ ቤት ተቀጥራ የምትሰራና ሁለት ወንድምና እህቷን ለመርዳት የምትታትርን ወጣት ውጣ ውረድ የሚያትት ልብ አንጠልጣይ የፍቅር ፊልም ነው።

በዚህ ላይ የልጃቸውን ፍላጎት ለማክበር ሲሉ የትዳር ጥያቄውን ውድቅ ያደረጉትን አባቷን በመግደልና ቤተሰቡን በማስፈራራት ጭምር በፈፀመው ወንጀል ጎጃም ውስጥ በሚገኝ እስር ቤት ተፈርዶበት የገባው በላይ (ኤሊያስ ወሰንየለህ) ከእስር አምልጦ ለኔ ተመርጣ ቤተሰብ የሰጠኝን ልጅ በእጄ አስገባለሁ ሲል የሚሄድበትን እና ዋጋ የሚያስከፍለውን ረጅም መንገድ የሚያሳይ ነው፤ “ፅኑ ቃል” ፊልም።

የፊልሙ አጀማመር ጡዘቱን ተጠግቶ እንደሆን ያደረገው ደግሞ ወንድምና እህቷን ጠይቃ ከጎጃም የተመለሰችው ቤዛን (ማህደር አሰፋ) ተከትሎ አዲስ አበባ የገባው በላይ (ኤሊያስ ወሰንየለህ) የምትሰራበት መስሪያ ቤት ድረስ ገብቶ ሲጎበኛት ፤ በፍቅሯ ተነድፎ ሲመላለስ እንደስነበተ የሚነገረን አቤል (ግሩም ኤርሚያስ) የስጦታ አበርክቶ እንዲያይ ማድረጉ የታሪኩ ሴራ እንዲጠበቅ መነሻ ሆኗል።

የማትወደውን ሴት የራሱ አድርጎ ለመኖር የወሰነ የሚመስለው በላይ (ኤሊያስ ወሰነየለህ) ከእስር ቤት ያመለጠበትን ጀብዱ በአድናቆትና በመገረም አይትን እንዳበቃን፤ በአቤል እና በቤዛ መካከል ያለውን የግንኙነት መረብ ለመበጣጠስ ሲል ያውጠነጠነውን ሴራ ለማሳካት ማንነቱን ሰውሮና አሳዝኖ አቤል (ግሩም ኤርሚያስ) በሚያስተዳድረው ድርጅት ቤት ውስጥ ጉዳይ አስፈፃሚ ሆኖ ለመቀጠር ሲሳካለት ስናይ ቀጣዩን ትዕይንት በጉጉት እንድንጠይቅ የሚያደርግ ነው።

የበላይን (ኤሊያስ ወሰንየለህ) ከእስር ቤት አምልጦ መውጣት ከታናሽ እህቷ የሰማችው ቤዛ (ማህደር አሰፋ) መረበሿ አይሎ የሰማችው እውነት መሆኑን በአይኗ እያየች እንኳን ለመጋፈጥ የምታደርገው ጥረት ወዳጅ ሲያሳጣትና እራሷንም ለአደጋ ሲዳርጋት እናያለን። ገፀ-ባህሪዋ የተሳለችበት መንገድ ለሌሎች ሴቶች አርአያ መሆን የምትችልን፤ ፅናት ካላት ያሰበችውን የተመኘችውን ለማድረግ የሚያግታት ነገር እንደሌለ ለማሳየት ችሏል።

በአንፃሩ ደግሞ አቤል (ግሩም ኤርሚያስ) የወደዳትን ልጅ የራሱ ለማድረግና ከፍርሃቷ ለመታደግ የመውተርተሩን ያህል፤ የሴራ ጎንጓኙን በቤቱ ማኖር አለመረዳት ትልቅ ችግር ሲፈጥርበት እናያለን። በፊልሙ ውስጥ ሶስቱ ዋና -ዋና ገፀ-ባህሪያት በራሳቸው ቃል የፀኑ መሆናቸውን እንመለከታለን። ቤዛ (ማህደር አሰፋ) የማትወደውን ነገር ንቃ በፅናት ህይወቷን የመራችና የቀየረች ሴት ስትሆን፤ አቤል (ግሩም ኤርምያስ) ደግሞ ለቃሉና ላመነው ነገር ሟች መሆኑም ያሳየናል። በሌላኛው ፅንፍ በኩል ደግሞ በላይ (ኤሊያስ ወሰንየለህ) የኔ ናት ብሎ ያመነባትን ሴት የራሱ ለማድረግ እስከጥግ ሲሄድ እናያለን። የሶስቱ ገፀ-ባህሪያት የፍላጎት አለመጣጣም የፊልሙን ታሪክ ልብ የሚያንጠለጥል መዘወሪያ ሆኖ ቀርቧል።

“ፅኑ ቃል” ፊልም እንደአብዛኞቹ የዘመናችን ፊልሞች የምስል፣ የድምፅና የኤዲቲንግ ችግር የለበትም። በትወናም ቢሆን ብቃታቸውን የገለፁ ወጣቶች ታይተውበታል። ከእነዚህም በተጨማሪ በተለየ መልኩ ሊጠቀስ የሚገባው የቪዥዋል ኢፌክት ስራው ነው። ይህ የፊልም ቴክኒክ በ “ፅኑ ቃል” በተለይም በመጀመሪያዎቹ ትዕይንቶች አካባቢ በላይ (ኤሊያስ ወሰንየለህ) ከእስር ቤት ባመለጠበትና በፖሊሶች ክትትል ውስጥ በነበረበት ሂደት የሚታየውን ትዕይንት ማስታወስ ይበቃለ። ሌላው ለፊልሙ ተብሎ የተሰራ የራሱ ሳውንድ ትራክ መደመጡ ይበል የሚያሰኝ ነው።

ዳሩ ግን ፊልሙ የቱን ያህል ትርጉም የሚሰጥ ተደርጎ ቢሰራ በታሪኩ ላይ ጥያቄ የሚነሳ ከሆነ አንካሳ ያደርገዋል። እንግሊዞች፣ ትንሿ ቀዳዳ ትልቁን መርከብ ታሰጥማለች” ይላሉ። በ“ፅኑ ቃል” ፊልም ውስጥም እንደትንሽ የታየ ነገር ግን ፊልሙን ሊያሰምጡ የሚችሉ ስህተቶችም ተሰርተዋል ማለት ተገቢ ሳይሆን አይቀርም።

የመጀመሪያውን ዋነኛው የታሪኩ ችግርና ለተመልካችም ጥያቄን የሚፈጥረው ነገር የበላይ (ኤሊያስ ወሰንየለህ) ኑሮ እና ተግባር አለመመጣጠን ነው። ይህ ገፀ- ባህሪይ የ15 አመታት እስር ተፈርዶበት ወህኒ ቤት ቆይቶ፤ አምልጦ የወጣ እንደሆነ እያወቅን የማያውቃት ድሬዳዋ ነዋሪ መሆኑን ስለመናገሩ ይሁን ብለን፤ ያሰራውን “ፎርጂድ” መታወቂያ ብንቀበልለትም ሰዎችን በብር ማማለሉንና ቅጥር ጋሻ ጃግሬዎችን ማፍራቱን ስንመለከት ከየት የመጣ ነው? ስንል ምንጩ ያልታወቀ ሀብት መኖሩን እንጠይቃለን። ይህ የፊልሙን ታሪክ የተዓማኒነት ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ነው።

በአንድ ትዕይንት ላይ አቤል (ግሩም ኤርሚያስ) እናቱን የሚወድና ለድንገትም በሞት ያጣቸው ሰው መሆኑን በማሳየት ገፀ-ባህሪው ለእናት ያለውን ጥልቅ ፍቅርና ርህራሄ አስደግፎ ድንገት ወደመስሪያ ቤቱ የመጣን ፀጉረ ልውጥ ሰው ያለምንም ፎርማሊቲ የድርጅቱ ጉዳይ አስፈፃሚ አድርጎ በአንዴ መቅጠር ሲያስቡት ይጎረብጣል። የመጣው ሰው እርዳታውን ፈልጎ ነው እንኳን ብንል፤ ለእናቱ ማሳከሚያ የሚሆን ገንዘብ ሰጥቶ ማሰናበት ሲቻል የታሪኩን ገመድ ለመወጠር ሲባል ብቻ እዛው እንዲቀር መደረጉ አሳማኝ አልሆነው።

ቤዛ (ማህደር አሰፋ) ከጓደኛዋ ከቤቲ (የኋላሸት በለጠ) ስለ በላይ (ኤሊያስ ወሰንየለህ) ያገኘችው መረጃ ወደፖለስ ሊያስኬዳት የሚችል ሆኖ ሳለ፤ ከአቤል ጋር አንድ ላይ ባይችለት አፍታም እንደገፀ-ባህሪዋ ጥንካሬ መጋፈጥ ሲኖርባትና እውነቱን ማውጣት እየቻለች ለታሪኩ ሌላ ቀዳዳና ዙሪያ ጥምጥም በሚያመች አኳን መሸሽን መምረጧ የፊልሙን መርከብ ሌላ ቦታ የሚበሳ ሆኗል።

በስተመጨረሻም ሊጠቀስ የሚገባው የመቼት ችግር ነው። ምንም እንኳን አንድ ጊዜ የታዩ ቢሆንም ወንድምና እህቷን ያገኘችበት ቦታና እርሷ ያደረገችበት የእናትና የአባቷ ቤት አይመሳስልም። ካልሆነ ያ ለምን እንደተፈጠረና ወላጆቻቸውን በሞት የተነጠቁት ልጆቹ የትና ከማን ጋር እንደሚኖሩ በግልፅ ሊቀመጥ ይገባው ነበር። በእነዚህ ጉዳዮች ፊልሙ ግልፅነት የጎደለው በመሆኑ ብቻ ጥቃቅን ተብለው የተዘነጉ ችግሮች በብዙ ልናየው ከሚገባውና ከምንጠብቀው ፊልም ውስጥ ተከስተው ጎርብጠውናል።

ይሁን እንጂ ቶም ፊልም ፕሮዳክሽን “ስርየት” እና “ፔንዱለም” ን ባሳየን አቅሙ “ፅኑ ቃል”ንም እንካችሁ ሲል ከፍታውን በጠበቀ መልኩ ቢሆን ይሻል ነበር። ያም ሆኖ ከቶም ገና ብዙ እንጠብቃለን። ይሰጠናልም የሚል ተስፋ አለን። “ፅኑቃል” ትልቅ መርከብን የሚወክል ፊልም ቢሆንም በትናንሽ ቀዳዳዎች ግን ሊሰምጡጠት የሚችል ሆኖ ተገንብቷል።

ይምረጡ
(8 ሰዎች መርጠዋል)
12065 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us