“ከፊልም ውጪ የሚያዝናናኝ ነገር የለም”

Wednesday, 20 April 2016 13:06

 

የ“በዝምታ” ፊልም ፕሮዲዩሰር አቤል ጋሻው

 

ባሳለፍነው ሳምንት “በዝምታ” የተሰኘ የቤተሰብ ድራማ ዘውግ ያለው ፊልም ወደሀገራችን ሲኒማ ተቀላቅሏል። በአቤል ሲኒማ በተካሄደው የፊልም ምረቃ ፕሮግራም ላይ በርካታ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን፤ ወጣቱ ፕሮዲዩሰር አቤል ጋሻውም አብረውት ለሰሩት ባለሙያዎችና ድጋፍ ላደረጉለት ሰዎች ሁሉ ምስጋናውን አቅርቧል። የፎቶግራፍ ባለሙያ የሆነውና በብሉናይል የፊልም ትምህርት ቤት “ዳይሬክቲንግ” ያጠናው አቤል፤ “በዝምታ” ፊልምን ለመጀመሪያ ጊዜ ፕሮዲዩስ በማድረግ ለተመልካች አቅርቧል። በፊልሙና በስራው ዙሪያ አጠር ያለ ቆይታን አድርገናል።

ሰንደቅ፡- ከዚህ ቀደም ምን ምን ስራዎችን ሰርተሃል?

አቤል፡- የራሴ ፎቶ ስቱዲዮ አለኝ። በሙያዬ ፕሮፌሽናል ካሜራ ማን ስሆን፤ የተለያዩ የቁንጅና ውድድሮችን በማዘጋትም ተሳትፌያለሁ። በብሉናይል ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ ከተለያዩ ፕሮዳክሽኖች ጋር በመሆን የሰራኋቸው ስራዎችም አሉ። በተጨማሪ ደግሞ ከተለያዩ አርቲስቶች ጋር የተለያዩ የሙዚቃ ክሊፖችን ሰርቻለሁ።

ሰንደቅ፡- “በዝምታ” ፊልም እንደመጀመሪያ የፕሮዲዩሰርነት ውጤቱን እንዴት አገኘኸው? ፊልሙ እንዴት ተመረጠ?

አቤል፡- ሲጀመር ለመስራት ያሰብኩት ፊልም በዝምታን አልነበረም። ደራሲና ዳይሬክተር አንተነህ አስረስ ጋር የሄድኩት ጀምሬው በነበረው የፊልም ፅሁፍ ውስጥ በአንዳንድ ነገር እንዲያግዘኝ ለመጠየቅ ነበር። በወቅቱ ግን አንተነህ ፊልም ለመስራት በዝግጅት ላይ መሆኑንና ጊዜ እንደሌለው ሲነግረኝ ፊልሙን አየሁት፡ በጣም የሚወደድ ታሪክ አለው። ኢትዮጵያዊነትን የሚያሳይ ፊልም ስለሆነ ስሜቴን ነክቶኝና ወድጄ ፕሮዲዩስ ለማድረግ የመረጥኩት ፊልም ነው ማለት እችላለሁ። ከኃላፊነት አንጻር ፕሮዲዩሰርነት የመጀመሪያዬ እንደመሆኑ በጣም ብዙ ፈተናዎች ነበሩት። ሲጀመር የፊልሙ ቀረፃ ቦታ ሀዋሳ በመሆኑ ሙሉ የፊልሙን አባላት ይዤ መሄድ ነበረብኝ። ያው እንደሚታወቀው የብዙ ሰውን ባህሪይ ችለህ መስራት በራሱ ትልቅ ፈተና ነው። በዚህ ላይ “አክተሮቹ” በልምድም በዕወቅናም ከኔ የተሻሉ የሚባሉ ናቸው። እነሱን መምራት ትንሽ ይከብድ ነበር።

ሰንደቅ፡- ፊልሙ ተሰርቶ ለመጠናቀቅ ምን ያህል ጊዜ ፈጀ? በሀዋሳ ቆይታችሁስ ምን የማትረሳው አጋጣሚ አለ?

አቤል፡- ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረፃ ቦታ ለመምረጥ 10 ቀናት ወስዶብናል። ከዚያም ቀረፃው ተጀምሮ ለ1 ወር ከ3 ቀናት ያህል ሰርተን ነበር። በመካከል ግን አንድ ተዋናይ ሚስቱ ትወልድ ነበርና ቀረፃው ተቋርጦ ቆየ። ከዚያም ለሁለተኛው ጊዜ ድጋሚ ሄደን ሳምንት ቆየን። በአጠቃላይ ሀዋሳ ውስጥ የነበረን ቀረፃ 1 ወር ከ13 ቀን ይሆናል። ይህ የቀረፃ ሂደት ኤዲት ተደርጎ ነው የ1 ሰዓት ከ35 ደቂቃ ፊልም የወጣው። በሂደቱ የማልረሳው ገጠመኝ የሆነ ቀን ቀረፃ ደርሰን፤ እቃችንን ሰብስበው ወደተከራየንበት ቤት ስንገባ ዕቃችንን ስናየው “ሳውንድ ሪከርደሩ” አልነበረም። በምን ፍጥነት ከመኪናችን ውስጥ እንደተሰረቀ አላወቅም። ያ አጋጣሚ በጣም አስደንጋጭ ነበር።

ሰንደቅ፡- “በዝምታ” ፊልም እንደመጀመሪያ መነሳሻ ሆኖሃል ማለት ይቻላል?

አቤል፡- ፊልሙ ከገበያ አንፃር መነሳሻ ይሆነኛል ብዬ አላምንም። ነገር ግን የልጅነት ህልሜን ከማሳካት አንጻር ፊልሙ ለኔ በጣም አሪፍ ነው። ብዙ ሰው ተዋውቄበታለሁ በፊልሙ ምረቃት ወቅትም ኩራት ተሰምቶኛል። ነገር ግን ደግሜ የምነግርህ ከገበያ አንጻር ብዙ ፊልሞች እየወጡ ስለሆነ አንዱ አንዱን መዋጡ ስለማይቀር አዋጭ ነው ማለት አልችልም። አሁን የሲኒማ ቤት ቁጥርና የፊልሙ ብዛት አልተመጣጠነም። ስለዚህ ከገበያ አንፃር አያዋጣም።

ሰንደቅ፡- “በዝምታ” ፊልምን እደተመልካች እንዴት አየኸው?

አቤል፡- በጣም ነው የሚገርምህ በአጋጣሚ “በዝምታ” የሚለው ርዕስ እኔ ነኝ የሰጠሁት። አንተነህ ሲጀምር የሰጠው ርዕስ ሌላ ነበር። ፊልሙ ጥሩ ታሪክ አለው። አባት የሴት ልጁን የፍቅር ህይወት በጥንቃቄ ሲመለከትና ሥነልቦናዊ ድጋፍ ሲያደርግላት ማየት በእኛ አኗኗር ያልተለመደ ነው፤ ምናልባት ሰውዬው ውጪ ሀገር ቆይቶ ከመምጣቱ አንጻር ነው ታሪኩ የሚነግረን። በተቃራኒው የራሱን ሃጢያት ሸፍኖ በልጁ ላይ የሚጮኽ አባት አለ። በዚህ ላይ የአባቱን ገመና ለመሸፈን የቻለ ልጅ በዝምታ ውስጥ ሲታመም ማየት ይገርማል። በነገራችን ላይ የአባትና ልጅ ከጥላቻ እስከፍቅር ያሳዩትን ትወና ተመልክቶ ግሩም ኤርሚያስ ደውሎልኝ ነበር። ምን ያህል እንደተደሰተበትና እንደወደደውም ነግሮኛል። ለኔም እንደተመልካች የትወናና የታሪክ ፍሰቱ በጣም አሪፍ እንደሆነ ይሰማኛል።

ሰንደቅ፡- በቀጣይ ከእነማን ጋር የመስራት ሃሳብ አለህ?

አቤል፡- በቀጣይ ሁለት ፕሮጀክቶች አሉኝ። አንደኛው ቀደም ብዬ የጠቆምኩህ ፊልም ነው። በቅርቡ ቀረፃው ይጀምራል። በመቀጠል ደግሞ ለየት ያለ ሃሳብ የያዘ የቲቪ ተከታታይ ድራማ እሰራለሁ ብዬ ዕቅድ ይዣለሁ። ምናልባት በድራማው አዳዲስና የአማተር ተዋንያንን ይዤ እመጣለሁ። ከፊልም አንጻር ከአለምሰገድ ጋር መስራት እፈልጋለሁ።

ሰንደቅ፡- በምን ትዝናናለህ?

አቤል፡- ከፊልም ውጪ የሚያዝናናኝ ነገር የለም። እንግዳ እንኳን ቤት ሲመጣ ፊልም እያየሁ ከሆነ ከሰላምታ ውጪ ሳልጨርስ መነሳት አልወድም። ሌላው ግን እንደመዝናኛ የምሰራው ስራዬ ፎቶ ማንሳት ነው ማለት ይቻላል።

ሰንደቅ፡- በስተመጨረሻ ደግሞ እስቲ ስለሰሞነኛ ጉዳይ እናውራ። የቃና ቲቪ መምጣት ለፊልሞቻችን ፈተና ነው ብለህ ታስባለህ?

አቤል፡- እንደኔ አስተሳሰብ የተመልካቾችን ምርጫ ማግኘት የዕይታ አድማሱ የበለጠ እንዲያድግ ያደርገዋል ባይ ነኝ። ተመልካቹ የተሻለ የማነፃፀሪያ መነፅር ያገኛል የሚል እምነት አለኝ። ነገር ግን ከባህል አንፃር ትንሽ መሸርሸሩ አይቀርም። እኔ ልጅ እያለሁ ብዙ የህንድ ፊልም እመለከት ስለነበር ከትምህርት በላይ ትኩረቴን ይወስደው ነበር። ለምን ብትል በትርጉም ስለሚታይ። አሁንም በቃና ቲቪ የሚቀርቡ ፊልሞች በትርጉም ስለሚሰሩ እና በየሰዓቱ እቤታችን ድረስ ስለሚመጡ፤ በተለይ ለልጆች ጊዜን የሚሻማ ይመስለኛል።. . . በተረፈ ግን በፊልም ስራዎች ጥሩ ዱላም ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ የእግር ኳስ ተመልካቹን ውሰድ፤ የውጪ ኳስ እያየ ከአሰልጣኙ በላይ ተንተኝ ሆኗል፤ የፊልሙም አካሄድ ወደዚያው ነው። ይበልጥ ተጠንቅቀን እንድንሰራ ግፊት ይሆነናል ማለት እችላለሁ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
8220 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us