“ፍቅር አለቃ” መስዋዕትነት እና ይቅር ባይነት

Monday, 02 May 2016 15:57

 

የፊልሙ ርዕስ      “ፍቅር አለቃ”

ፕሮዳክሽን    በሚ ፒክቸርስ ተዘጋጅቶ፤ በቢኒያም ፊልም ፕሮዳክሽን የቀረበ

ደራሲ       ኤርሚያስ ክብሮም        

ዳይሬክተር   ሰለሞን ሙሄ

ተዋንያን     ሰለሞን ሙሄ፣ ተዘራ ለማ፣ መኮንን ላዕከ፣ ኃይሉ ጭንቢ፣ ፌቨን ከተማ፣ ምግባር ተሾመ እና ሌሎችም።

 

በተማረበት ሙያ የገጠሩን ኅብረተሰብ ለመርዳት የሚውተረተረው ዘካሪያስ (ሰለሞን ሙሄ) የቤቱን በር ለመዝጋት በሚያደርገው ትግል ውስጥ ከብረት ይልቅ ለሰብዓዊነት ያለውን ክብር የሚገልፅበት መንገድ የገፀ-ባህሪውን ስብዕና እና የታሪኩን አብይ ፍንጭ የሚያመላክት ይመስላል። “ሰው በእምነት እንጂ በብረት ብቻ በሩን አይቆልፍም”

አንዱ ከሚወደው ነገር በላይ ክብሩንና ማንነቱን ሲያስቀድም፤ ሌላው ሀብትና ንብረቱን ሲቆጥር የተገነባ ፍቅር እየፈረሰ፤ የፈረሰ ፍቅር ደግሞ ቀስ በቀስ ሲገነባ የሚያሳየው “ፍቅር አለቃ” ፊልም በኤርሚያስ ክብሮም ተፅፎ በሰለሞን ሙሄ ዳይሬክት ተደርጐ ቀርቧል። 

 

በአባቱ በሻምበል (መኮንን ላዕከ) ግትር አቋም ምክንያት የቤተሰቡ ትዳር የተበተነበት ዘካሪያስ፤ አንድም ቤተሰቡን ለማስታረቅ አንድም የእርሱን አዲስ ህይወት ለመጀመር ከሄደበት ገጠር ወደ አዲስ አበባ ይመለሳል።

በሌላ በኩል በድብብቆሽ የተሞላው፤ በሱስ ልክፍትና በሀብት ንብረት ሰንሰለት የታሠረው የዮዲት (ምግባር ተሾመ) እና የመስፍን (ኃይሉ ጭንቢ) ፍቅር ከአመታት በኋላም እንኳን ትዳር ደጃፍ መድረስ አቅቶት ሲንገዳገድ እንመለከታለን። ከዚህ ሁሉ በላይ በአባቷ ድርጅት ውስጥ አዲስ ሠራተኛ ሆኖ የመጣው የልጅነት ጓደኛዋን በቅንነት መቅረብ የተሳናት ፍቅር (ፌቨን ከተማ) እንከን ፈላጊ ሆኖ ተስላለች። ለዚህም ገና በልጅነት በተከሰተ ቀላለ ፀብ የግንባር ጠባሳዋ ሁሌም ስለዘካሪያስ ያላት ክፉ መንፈስ እንዳይለወጥ ማሕተሙን ያስቀመጠባት አስመስሏታል። ዳሩ ግን ዘካሪያስ “በይቅርታ መታረቅ እስካለ ድረስ በደንብ መጋጨት ነው እንጂ” ሲል፤ በቀልድ አስመስሎ ሊናገራት ቢሞክርም ፍቅር ግን፤ “ይቅርታን ተማምኖ ማጥፋት በጣም ያስጠላል” ትላለች።

 

እናም የቤተሰቡን የቀድሞ ፍቅር፤ የወዳጆቹን የትዳር ነገር የእርሷን አዲስ ግንኙነት ለማደስ የሚውተረተረው ዘካሪያስ የሰዎችን ጥፋት የራሱ እያስመሰለ፤ ቅጣታቸውን ሲቀበል ፍቅር በይቅርታ እና በግልፅነት እንጂ በእልህና በግትርነት እንደማይፀና ከቃል በላይ በተግባር የሚያሳይ ገፀ-ባህሪይ ሆኖ ተስሏል። የአባቱ የሻምበል ብቸኝነትና የወዳጁ የመስፍን ሆደ-ባሻነት ተዳምሮ በዕድሜ ተራርቀውም ቢሆን በፍቅር አለቅነት መሀል የሚዋትቱት ሁለቱ ገፀ-ባህሪያት የሚያሳዩት ትዕይንት በእጅጉ አዝናኝ ነው ማለት ይቻላል። በሌላ በኩል ደግሞ የፍቅረኛዋን የሲጃራ ሱስ የራሷ አድርጋ “እሾህን በእሾህ” ለማውጣት የምትታትረው ዮዲት፤ ጥበቃዋና ፍቅሯ ያስከፈላት መስዋዕትነት በእጥፍና በይቅርታ ሲመለስላት ወይም ሲክሳት እንመለከታለን።

 

በስተመጨረሻም በከፈለው መስዋዕትነትና በዘረጋው የፍቅር ድልድይ ላይ ቤተሰቡን አስማምቶ፤ ጓደኞቹን አጋብቶ፤ እርሱም የተመኘውን ፍቅር አግኝቶ ሲኖር እንመለከታለን። ለዚህ ሁሉ ታዲያ “ፍቅር አለቃ” የሆነው ራስን ለሌሎች አሳልፎ መስጠትና ይቅር ባይነት መሆኑን በገፀ-ባህሪያቱ ታሪክ ውስጥ ፍንትው አድርጐ የሚያሳይ ፊልም ነው።

 

በመጨረሻም ቢስተዋል

በወጣትና አንጋፋ ተዋንያን ድምር የቆመው “ፍቅር አለቃ” ፊልም ያነሳውን ሀሳብ ለተመልካች በቀላል መንገድ ያሳየ ነው ማለት ይቻላል። ነገር ግን ሁለት መሰረታዊ ድክመቶችን በጉልህ አሳይቷል። የመጀመሪያው የካሜራ አንግልና ምስል አወሳሰድ ነው። የተቆረጡና ተመልካች ጋር ያልደረሱ የገፀ-ባህሪይ ስሜቶች ብርክት ብለው ታይተውበታል። ለዚህም የካሜራ ባለሙያው፣ የኤዲተሩና የዳይሬክተሩ ኃላፊነት ጥያቄ ውስጥ የወድቃል።

በሌላ በኩል በበርካታ ፊልሞች ውስጥ እንደቋሚ ችግር ከመጠቀሱ የተነሳ፤ እንደተራ ስህተት እንዲታለፍ የሚፈለገው የኮንቲኒቲ (የቦታ፣ የምስል፣ የአልባሳትና የገፅ-ቅብ ተከታታይነት) ጉዳይ ነው። በዚህ ፊልም ውስጥ በተለይም በዘካሪያስና በፍቅር መካከል ቂም አስረግዞ፤ የግጭት መንስኤ (Source of Conflict) ነው የሚባልለት የግንባር ጠባሳ በሦስት የተለያዩ ትዕይንቶች (ሲኖች) ውስጥ ቦታውን ስቶ እንድናይ ተደርገናል። በስንብት ጊዜ፣ በመኪና ሰው በሚሸኙበት ጊዜና በጋራ በቆዩበት ጊዜ የምናየው የጠባሳ አቀማመጥ ቦታው የተዛነፈ ነው።

በአጠቃላይ ግን “ፍቅር አለቃ” ፊልም ለታሪክ ወዳድ ተመልካቾች ቁም ነገር ያለውና በቀላል አተዋወን የቀረበ የቤተሰብ ድራማ ዘውግ ያለው ስራ ነው ማለት ይቻላል። እናም ስስ ስህተቶቹን በይቅርታ ሸፍነን የምንመለከተው አይነት ፊልም ነው። መልካም የመዝናኛ ሳምንት!!!n   

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
10467 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us