“በማለዳ ኮከቦች ዳኝነት ሂደት ብዙ ጊዜ እንጋጫለን”

Wednesday, 04 May 2016 12:41

 

“የማለዳ ኮከቦች” ፕሮግራም አዘጋጅ፣ ደራሲና ዳይሬክተር ፍፁም አስፋው

በቦጋስ ፊልም ፕሮዳክሽን ተዘጋጅቶ በኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቭዥን ጣቢያ የሚቀርበው “የማለዳ ኮከቦች” የሁለተኛ ዓመት ፕሮግራሙን ባሳለፍነው እሁድ ተጠናቋል። ከአምናው በርካታ መሻሻሎችን አሳይቷል የተባለለት ይህ የተሰጥኦ አማጭና አዝናኝ ፕሮግራም የዚህ ዓመት ሂደቱ ምን ይመስላል? ምን አይነት ክስተቶችን አስተናግዷል? በቀጣይ ምን የታሰበ ነገር አለ? ስንል፤ የፕሮግራሙ ሃሳብ ባለቤት፣ ደራሲና ዳይሬክተር ፍጹም አስፋውን እንዲሁም ከዳኞቹ አንዱ የሆነው አንጋፋው ተዋናይ እና ደራሲና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ተስፋዬን አነጋግረናቸዋል።

ቦጋስ ፊልም ፕሮዳክሽን የዛሬ ሁለት ዓመት ይህን መሰሉን አዲስ የተዋንያን የተሰጥኦ መድረክ አመቻችቶ ሲጀምር በበርካቶች ዘንድ እሩቅ የማይጓዝ ተደርጎ ይታሰብ እንደነበር ሀሳብ አመንጪው ፍፁም አስፋው ይናገራል፤ “ሃሳቡ ለሁላችንም አዲስ ነው። ፕሮግራሙን በመጀመር ያነሳሳን ነገር ምንድነው በፊልም ስራ ሂደት ውስጥ በርካታ “ታለንቱ” ያላቸው ወጣቶችን እናይ ነበር። ሁሉም ወጣቶች አብረውን መስራት እንደሚፈልጉ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ይነግሩናል። ነገር ግን ሁሉንም በእኛ አቅም ማሰራት እንደማንችል ስላወቅን ለምን ተሰጥኦቸውን አደባባይ አውጥተን ለሌሎች ባለሙያዎች አይን ቅርብ አናደርጋቸውም በሚል ነው የጀመርነው፤ አሁን ላይ ተሳክቶልናል የሚያስብል ድፍረት ያለው ውጤት እያየን ነው” ይላል።  

የዚህ ፕሮግራም መጀመር ከወጣቶቹ በተጨማሪም ለፕሮዲዩሰሮቹና ለትወና ባለሙያዎች በጠቅላላ አማራጭ አምጥቷል የሚለው ደግሞ በፕሮግራሙ ላይ በዳኝነት የሚሳተፈው ተዋናይ እና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ተስፋዬ ነው። “ወጣቶቹ ያላቸው ብቃት እኛ ልምድ አለን ለምንለው ባለሙያዎች ጭምር የሚገርም ነው። እናም እነዚህን ባለተሰጥኦ ወጣቶች የሚጠቀምባቸው የትወና ፍላጎት (መድረክ) ይኖራል ብለን እናስባለን። እኛ በአደባባይ እያበጠርን ያመጣናቸውን ልጆች በርካታ ባለሙያዎች ደግሞ ለስክሪኑም ሆነ ለመድረኩ እንደሚያበቋቸውና የሚገባቸውን እንጀራ እንደሚሰጧቸው ተስፋ አለኝ” ባይነው።

በዳኝነት ሂደቱ በርካታ ውጣ ውረዶች እንደሚያልፉ የሚናገረው ቴዎድሮስ፤ “ለክፉ አንድረስ እንጂ ከመድረኩ ጀርባም ቢሆን ጭቅጭቅ አለብን” ይላል። ይህንን ሃሳብ የፕሮግራሙ ባለቤት ፍፁም አስፋውም ይጋራዋል። “የሰራው ባህሪይ ነው፤ በማለዳ ኮከቦች የዳኝነት ሂደት ብዙ ጊዜ እንጋጫለን፤ ነገር ግን አምሮ የሚሄድ አይደለም። በፕሮግራሙ ዕለት በቲቪ አልታየ ይሆናል እንጂ ከዳኞቹ መካከል አንዱ የሆነው ሚኪ (ሚካኤል ሚሊዮን) በግልጽ መድረክ ላይ ተናግሮታል። የመጨረሻውን ውጤት ከመስራታችን በፊት ማሂን (ማህሌት ሰለሞን) እና ቴዲን ጨምሮ በጣም ተጨቃጭቀን፤ ደግመን የማንነጋገር እስኪመስል ድረስ ተኮራርፈን ነበር” ሲል ያስታውሳል።

የማለዳ ኮከቦች እንደመዝናኛ ፕሮግራምነቱ አይረሴ የሚሏቸውን አጋጣሚዎች በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄም ምላሽ ሰጥተዋል። አርቲስት ቴዎድሮስ፣ “እንደዳኛ ስመለከተው የልጆቹ አቅም ያስደንቀኛል። እንደተመልካች ስሆን ደግሞ ፍፁም የምዝናናባቸው ትወናዎችም አጋጥመውኛል። ከሁሉም ግን በዚህ ስራ ሂደት ውስጥ መቼም የማልረሳው አጋጣሚ አለ የሚለው ቴዲ፤ ይኸውም አንዲት በእርሱ ቡድን ውስጥ ተወዳዳሪ የነበረች ወጣት በሰማችው ውጤት ራሷን ስታ ከመድረክ ጀርባ መውደቋ ትልቁና አስደንጋጩ ክስተት ነበር ይላል። ፍፁም በበኩሉ ስለፕሮግራሙ አዝናኝነት ሲናገር የጀመርነውም ከማዝናናት አንጻር ነው ይላል። “ፕሮግራሙ ለወደፊት ወጣቶችን ለማሰልጠን ይሰራ ይሆናል እንጂ አሁን ባለው ሁኔታ በመድረክ እንቅስቃሴያቸው ላይ ተመስጠን ከመሞከር፤ በውድድር ሂደቱ አንዳንድ እገዛዎችን ከማድረግ በዘለለ ዋነኛ ትኩረቱ ማዝናናት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል” ይላል።

እኔ እንደተመልካች ደጋግሞ በማየት አልዝናናም ሲል የግል ባህሪውን የሚናገረው ፍፁም፤ “ፕሮግራሙን ቤቴ ተቀምቼ ስመለከት ድክመቶችን ነው የማወጣው፤ ከዚህ የተሻለ መስራት አንችልም ነበር ወይ እያልኩ ከምዝናናው ይልቅ የምቆጭበት ጊዜ ይበልጣል” ሲል ስለፕሮግራሙ የስራ ሁኔታ በእጅጉ እንደሚጨነቅ ያስረዳል። ያም ሆኖ ይህ ፕሮግራም ክትትል የሚፈልግ መሆኑን የሚገልፀው ፍፁም፤ በኤዲቲንግ ሂደቱ ለቀጣይ ዙሮች መሻሻል የሚረዱ ግብአቶችን እንሰበስባለን ሲል ከቀጥታ ፕሮግራሙ ይልቅ የጀርባ ስራው ብዙ እንደሚያለፋና ስለመሻሻሉ ትኩረት እንደሚያደርግ ይጠቁማል።

በርካቶችን ማስደንገጥ የሚችሉ ወጣቶች ስለመኖራቸው የሚናገረው ፍፁም፤ በየዙሩ የተሻለ አቅም ያላቸውን ልጆች አይተናል ይላል። “ምሳሌ መጥቀስ ካስፈለገ ዘንድሮ በሴቶቹ ምድብ 3ኛ የወጣችው ሃና በቀለ እና 4ኛ የወጣችው እስከዳር እርስቱ የወንድ ገፀ-ባህሪይን ተላብሰው ያሳዩት ትወና ሴትነታቸውን የሚያስረሳና ፍፁም የተዋጣለት ነበር” ሲል ያስታውሳል።

የተመልካቹ አተያይ/አይን በእጅጉ ሰልጥኗል የሚሉት የፕሮግራሙ ዳኞች፤ በፅሁፍም ሆነ በስልክ በሚደርሳቸው መልዕክት የተመልካቹ ምክንያታዊ ዳኝነት የተመልካቹን አቅም የሚለኩበት እንደነበርም ይገልጻሉ። በዳኝነት ሂደቱ ተመልካች የኛን ስሜት ውጠን፤ ኮስተር ብለን እድንቀመጥ ይፈልጋል የሚለው ፍፁም፤ ይህ ግን ከፕሮግራሙ ባህሪይ ጋር አብሮ አይሄድም” ሲል ይመልሳል።

ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደው “የማለዳ ኮከቦች” የትወና የተሰጥኦ ፕሮግራም ከአምናው ምን ተማረ? ለመጪውስ ምን ያስባል ያልነው አዘጋጁ ፍፁም ሲመልስ፤ “ከመጀመሪያ ዓመት የተሻለ የሰራን ይመስለኛል። ከዳኝነት ቅርፅ አንፃር ካለፈው ዘንድሮ የተሻለ ሰርተናል የሚል እምነት አለኝ። በፈተና አሰጣጥም ላይ ዘንድሮ ከሰባት እስከስምንት የሚደርሱ የተለያዩ የማጣሪያ ፈተናዎችን መስጠት ችለናል። ከማዝናናትም አንፃር ይኸኛው የተሻለ አመት ነው ብዬ አስባለሁ” ሲል የሚያስረዳው ፍፁም፤ ለቀጣዮቹ ዙሮችም ካለበት የተሻለ ስራን ይዞ ለመቅረብ ዝግጅት መደረጉን ሳይጠቁም አላለፈም።

ቦጋስ ፊልም ፕሮዳክሽን የሁለተኛውን ዙር የተሰጥኦ ውድድር ሲጀምር የተመዘገቡት ተወዳዳሪዎች ከ2ሺህ በላይ ናቸው የሚለው አዘጋጁ፤ ከካሜራ ባሻገር በተደረገ ማጣራት ባለፉት ከ1050 ተወዳዳሪዎች መካከል 200 የሚሆኑት መድረክ አግኝተዋል። ከእነዚህ ተወዳዳሪዎችም አምስት ሴት እና አምስት ወንድ ተወዳዳሪዎች ለመጨረሻው ዙር የቀረቡ ሆነዋል። በዚህም በሴቶቹ ምድብ ቤተልሄም ኢሳያስ አሸናፊ ስትሆን፤ በወንዶቹ ምድብ ደግሞ ነጂብ መስኡድ ተሸላሚ ሆነው ለእያንዳንዳቸው የ100ሺህ ብር ሽልማትና የፊልም ስራ ዕድል እነሆ በረከት ተብለዋል።

የሁለተኛ ደረጃውን ከሴቶች ክርስቲ በቀለ ስታገኝ፤ ከወንዶች አለምሰገድ አሰፋ አሸናፊ በመሆን ለእያንዳንዳቸው የ60 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል የሶስተኛ ደረጃውን በሴቶች ሃና በቀለ ስታሸንፍ፣ በወንዶቹ ምናለ ያረጋል አሸናፊ ሆኖ በነፍስወከፍ የ40ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። አራተኛ የሆኑት በሴቶቹ እስከዳር እርስቱ እና በወንዶቹ ናሆም ሃ/መለኮት ሲሆኑ፤ አምስተኛ ደረጃውን ያገኙት ከሴቶቹ ማህሌት በላይ እና ከወንዶቹ መኮንን ንጉሴ (ምክትል ሳጅን) ሆነዋል። ሽልማቱን ለአሸናፊዎቹ የሰጡት ወጋገን ባንክ እና ዳሽን ቢራ ናቸው።

“ለእኛ ሁሉም የመጨረሻ ተወዳዳሪዎች አሸናፊዎች ናቸው” የሚሉት የፕሮግራሙ ዳኞች፣ ውጤቱ የተሰጠው ከአማካሪ ዳይሬክተሮች፣ ከተመልካች እና ከራሳቸው ከዳኞቹ ተወጣጥቶ እንደሆነም ጠቁመዋል። ቀጣዩ ዙር እስኪጀመር ምርጥ 20 ውስጥ የገቡት ተወዳዳሪዎች ተከታታይ ድራማ ሰርተው የሚያቀርቡበት እድል እንደሚኖር የተናገረው አዘጋጁ የ3ኛው ዙር ተመዝጋቢዎችንም ለማስተናገድ ዝግጅት እናደርጋለን ሲል ተናግሯል።     

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
10672 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us