“አድማጭ የሚያውቀኝ በሱዳንኛ ዜማዎቼ ነው”

Wednesday, 11 May 2016 12:14

 

ድምፃዊ አብርሃም ንጉሴ (አለል ጀማል)

 

“አለል ጀማል” በተሰኘው ዝነኛ የሱዳን ሙዚቃው ይታወቃል። በቅርብም በሙዚቃ ቅንብሩ ሚካኤል ኃይሉ፣ አብይ አርካና አሌክስ ይለፍ የተሳተፉበትን፤ በግጥምና ዜማው መላኩ ጥላሁንና ቢኒያም አህመድ የለፉበትን “ያኑርልኝ” የተሰኘ የበኩር አልበሙን ለአድማጭ አድርሷል። ሙገር ተወልዶ ሾላ አካባቢ ያደገው ወጣቱ ድምፃዊ አብርሃም ንጉሴ። በድምጻዊው ህይወትና ስራ ዙሪያ አተኩረን አጠር ያለ ቆይታ እንደሚከተለው አድርገናል።

ሰንደቅ፡- ሙዚቃን እንዴት ጀመርከው?

አብርሃም፡- ሙዚቃን እንደማንኛውም ሰው ከልጅነቴ ነው የጀመርኩት። ገና የ6 ዓመት ህጻን ሳለሁ ራሱ አያቴ እንግዳ ሲመጣ የኔን መዝፈን ነበር (እንደመዝናኛ) የሚጋብዙት። እናም ቤተሰቦቼ የመጀመሪያዎቹ አድማጮች ናቸው።

ሰንደቅ፡- ከቤተሰብ ወጥተህ የመጀመሪያ  መድረክ ያገኘህበት አጋጣሚ ታስታውሰዋለህ?

አብርሃም፡- እኔ እድለኛ ነኝ። በፊት ላይ ታዋቂ የነበረች አርቲስት አልማዝ ከበደ የምትባል ዘመድ ነበረችኝ። በተለያዩ ቦታዎች ትዘፍን ነበር። አንድ ቀን “ኮረብታማ” የሚባል ቤት ወስደችኝ። አንድ ዘፈን ባይሆን እንኳን “ጃም” እንዲዳረግ ከሌሎች አርቲስቶች ጋር አስተዋወቀችኝ። ያኔ ታምራት ደስታና ጥበቡ ወርቅዬም ነበሩ። ከሌሎቹ አነስ ያልኩ ስለነበርኩ ነው መሰለኝ አንድ ዘፈን በዘፈንኩ ቁጥር ጥሩ ተመልካች ነበረኝ።

ሰንደቅ፡- ለመጀመሪያ ጊዜ በሙሉ ባንድ መድረክ ላይ ስትወጣ የማንን ዘፈን ነበር የዘፈንከው?

አብርሃም፡- በጣም የምወደውን የቴዎድሮስ ታደሰን ዘፈን ነበር። በሙሉ ባንድ መጫወት ትንሽ ያስፈራ ነበር፤ ነገር ግን ልጅነቴን አይተው ሁሉም የባንዱ አባላት ይረዱኝ ስለነበር መሻሻል እያሳየሁ እዚህ ደርሻለሁ ማለት ነው።

ሰንደቅ፡- ከሙሉ ባንድ ጋር ተላምደህ ወደሙሉ ድምጻዊነት ስትመጣ ከበርካታ አድማጭ ጋር ያስተዋወቀህ “አለል ጀማል” የተሰኘ ነጠላ ዜማህ ነው። እስቲ ስለዚህ ስራ ትንሽ አጫውተኝ?

አብርሃም፡- ከነጠላ ዜማው በፊት ባይገርም ከጥበቡ ወርቅዬ ጋር ብዙ አመት የኖርን ጓደኛሞች ነን። እሱ ሲዘፍን እኔ የምሰማ ይመስለኛል። ጥበቡ ወርቅዬ ዘፈን ሲያወጣ እኔ ደቡብ ሱዳን ነበርኩ፡፤ ነጠላ ዜማውንም እዛ ሆኜ አንድ ቀን ነው የሰማሁት። ስራው የሰኢድ ካሊፋ ነው፡፡ እዚህ እንደመጣሁ ግጥሙን ወደአማርኛ በመመለስ ያለምንም መደጋገም በአንድ ቀን ነው ስቱዲዮ ገብቼ የተቀረፅኩት። ብዙ ድምጻዊ ጓደኞቼም እንደወደዱት ጭምር ነግረውኛል። ያን ያህል ያልደከምኩበት ቢሆንም የዘፈኑ እንደዚህ መወደድ በጣም ይገርመኛል።

ሰንደቅ፡- በነጠላ ዜማህ ጥላ በአልበምህ ላይ እንዴት ነው?

አብርሃም፡- ሰው ብዙ አያውቀኝም። ሱዳንኛውን በአልበሙ ውስጥ በማካተቴ ልክ ያቺ “ትራክ” (ዘፈን) ስትመጣ ብዙ አድማጭ “እንዴ ይሄ ልጅ ነው እንዴ ሱዳንኛ የሚዘፍነው?” እንደሚሉ ሰዎች ይነግሩኛል። “የኔ አላለሽማ” የተባለው ሙዚቃዬም ሙሉ በሙሉ በሱዳንኛ ዜማ ነው የተሰራው፤ ነገር ግን ገና አልተሰማም። ካለኝ ልምድ በመነሳት ቀስ -በቀስ ጆሮ ያገኛል ብዬ ተስፋ አድርጋለሁ። አሁንም ቢሆን ግን በርካታ አድማጭ የሚያውቀኝ በሱዳንኛ ዜማዎቼ ነው ማለት ይቻላል።

ሰንደቅ፡- ከዜማና ከግጥም በዘፈኖችህ በየትኛው ላይ ታተኩራለህ?

አብርሃም፡- ለሁለቱም ትኩረት እሰጣለሁ። ግጥሙ በጣም ቀላል ባይሆን ደስ ይለኛል። ነገር ግን ለዘፈን ይበልጥ መተኮር ያለበት ዜማው ላይ ነው ብዬ አምናለሁ። ከሁለቱ ምረጥ ካልከኝ ለዜማ አደላለሁ።

ሰንደቅ፡- “ያኑርልኝ” በተሰኘው አልበምህ ውስጥ ከተካተቱት ዘፈኖች መካከል ላንተ የተለየ ትርጉም የሚሰጥህ የቱ ነው? ለምን?

አብርሃም፡- እውነት ለመናገር ሁሉንም ዘፈኖቼን እወዳቸዋለሁ። አንድ ምርጥ ካልከኝ ግን “ያኑርልኝ” የሚለው ስራ ብዙ ነገር መግለፅ የሚችል በመሆኑና የአልበሙም መጠሪያ ስለሆነ በጣም እወደዋለሁ። አንተ በህይወት ለመቆየት ብዙ መኖር ያለበት ነገር አለ ብዬ አምናለሁ።

ሰንደቅ፡- ምናልባት ካንተ ህይወት ጋር በቀጥታ የተገናኘ ስራ በአልበሙ ውስጥ አለ ማለት ይችላል? ወይም ፃፉልኝ ብለህ ያሰራኸው ዘፈን አለ?

አብርሃም፡- አዎ “አምላኬ” የተሰኘው ዜማ በቀጥታ ከህይወቴ ጋር ይገናኛል። የኔን ህይወት የሚገልፅ ነው። በዜማው ውስጥ ባለቤቴን የሚገልጽ ሃሳብ አለ። እንዲህ አድርጋችሁ ስሩልኝ ብዬ ያሰራሁት ዘፈንም ነው። ለባለቤቴ ትዕግስት በላቸው በተለይ ለእሷ የተዜመ ስራ ነው። በነገራችን ላይ ከባለቤቴ ጋር ከተዋወቅን ወደ አስር አመት ይሆነናል። በስራዋ ተወዛዋዥ ሆና ነው የተገኘችው። ይህን ዘፈን ከዘፈንኩላት በኋላ “ክሊፑን” ያለእሷ መስራት ስላልፈለግን አቆይተነዋል፡፡ በነገራችን ላይ አሁን ልጃችንን በሆዷ ይዛለች፡፡ ከወለደች በኋላ የዚህን ዘፈን ክሊፕ እኛው እንሰራዋለን ብለን እየጠበቀርን ነው፡፡ (ሳቅ)

ሰንደቅ፡- በድምፃዊነት የት የት አገሮች ዞረሃል?

አብርሃም፡- በመዞር ደረጃ ሱዳን ዞርክ ከምትለኝ ኖርክ ብትለኝ ይቀላል። ምክንያቱም ብዙ እድሜዬን ያሳለፍኩት ሱዳን ነው፤ እንደሀገሬ የማስባት ሀገር ናት ከ10 ዓመት ላላነሰ ጊዜ ኖሬባታሁ። ሌሎች ጥቂት አረብ አገራት ሄድ መለስ ብዬም ሰርቻለሁ።

ሰንደቅ፡- እስቲ ከማትረሳው የመድረክ ስራ አንዱን አስታውሰኝ?

አቤል፡- ለኔ የማልረሳው መድረክ የአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ መድረክ ነው። የሱዳናዊው እውቅ ድምጻዊ መሀመድ ወርዲ ሙት አመት ለማክበር በተሰናዳ ፕሮግራም ላይ ከአንጋፋዎቹ መሀሙድ አህመድና “በአለማየሁ እሸቴ ጋር የመዝፈን እድሉን አግኝቼ ነበር። የነበረው ሰው ብዙ ነው። ሱዳንኛውን ስዘፍን የህዝቡ ምላሽ የተለየ ነበር። ከጨረስኩ በኋላ እንደውም ጋሽ መሀሙድ ሀበሻ ነህ እንዴ? ብሎ ሁሉ ጠይቆኛል (ሳቅ)።

ሰንደቅ፡- አብርሃም በምን ይዝናናል?

አብርሃም፡- እውነት ለመናገር ሲከፋኝም ሆነ ስድስት ሙዚቃ መስማት ነው የሚያዝናናኝ። ሙዚቃ መዝናኛዬ ነው።

ሰንደቅ፡- እስቲ ደግሞ ከአንጋፋና ወጣት የአገራችን አርቲስቶች (ድምጻዊያን) ማንን ታደንቃለህ?

አብርሃም፡- ሁሉም ዘፋኝ የራሱ የሆነ ብቃት አለው፤ አንዱን ከአንዱ ማበላለጥ ይከብደኛል። ነገር ግን በተለየ አጨዋወቱና ቅላጼው የሚገርመኝ አርቲስት ምኒልክ ወስናቸው ነው። እውነቱን ተናገር ካልከኝ ካለው ድምፅ አንፃር ብዙም አልተጠቀመበትም ብዬ ሁሉ አስባለሁ። የሰራቸው ስራዎች በተለየ አዘፋፈን፤ ነፃ ሆኖ የሚጫወትበት ሁሉ ነው የሚመስልህ።

ሰንደቅ፡- መድረክ ላይ አስመስለህ የዘፈንከው የጋሽ ምኒልክ ስራ አለ?

አብርሃም፡- በመድረክ የለም ነገር ግን አሁን “አይዶል” ላይ አንደኛ ከወጣው ዳዊት ጽጌ ጋር አብረን ዱባይ እንሰራ ነበር። እርሱ በምኒልክ ስራዎች ይታወቃል። ታዲያ አንድ ቀን ምን አደረግን እሱ የምኒልክ ወስናቸው “ትዝታ አያረጅም”ን በአማርኛ ሲዘፍን እኔ በሱዳንኛ ተቀበልኩት ተመልካቹ በጣም ነበር የተዝናናበት። . . . ከወጣቶቹ ካልከኝ ደግሞ በጣም ደስ የሚለኝ ማዲንጎ አፈወርቅ ነው። ድምጽና ጉልበቱ የተለየ ነው።

ሰንደቅ፡- እንደው ሌላ ዘፋኝ ተጫውቶት ስምተኸው፤ እኔ በዘፈንኩት ኖሮ ብለህ የሚያስቆጭህ ዘፈን አለ?

አብርሃም፡- ብዙ የለም። አሁን በቅርብ አበበ ተካ የለቀቃት “አሞኛል” የምትለው ዘፈን መልዕክቱም ሆነ ዜማው የሚያሳዝን ስለሆነ ብሰራው ብዬ ተመኝቻለሁ። ይሄን ስልህ ግን አበበ ተካ አልሰራውም ማለቴ አይደለም። ነገር ግን ከኔ ድምጽ አንጻር ብሰራው ይመቸኛል ከሚል ነው።. . . ያም ሆኖ ግን ዘፈኑ በጣም እንደተመቸኝ በዚህ አጋጣሚ መናገር ፈልጋለሁ፡፡

ሰንደቅ፡- ከመሰነባበታችን በፊት በቅርቡ የለቀከውን “ያኑርልኝ” አልበምን በተመለከተ የሰሙ ሰዎች ምን አሉህ? በቀጣይስ የሙዚቃ ዝግጅት ለማቅረብ ምን ዝግጅት እያደረክ ነው?

አብርሃም፡- ከአድማጮቼ የምሰማው ምላሽ በጣም ጥሩ ነው። እንደውም ከጠበኩት አንፃር አንሶብኛል ማለት እችላለሁ፡፤ ከሌሎች አርቲስት ጓደኞቼ ጋር ስናወራ ቀስ -በቀስ ይደመጣል ያንተ ስራ ይሉኛል። እንግዲህ እያየነው ነው። በቅርቡ በተለያዩ አለማት በመዞር የሙዚቃ ዝግጅት ለማቅረብ እየተዘጋጀን ነው። በመጨረሻም ለአልበሜ መሳካት አብረውኝ የነበሩትን ሰዎች በጠቅላላ ለዚህ አጋጣሚ አመሰግናለሁ ማለት እወዳለሁ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
10769 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us