“የብርሃን ሰበዞች” ብርሃናማ ምሽት

Wednesday, 18 May 2016 13:53

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ በታዳሚዎች ተሞልቷል። ሰኞ ግንቦት 8 ቀን 2008 ዓ.ም አመሻሽ ነው። በአብዛኛው ወጣቶች በታደሙበት በዚህ ዝግጅት ላይ የሀገር ልብስ በለበሱ አስተናባሪዎች የዕለቱ ተመራቂ መፅሐፍ እየተሸጠ ነው። አንጋፋና ዝነኛ የጥበብ ቤተሰቦችም በአዳራሹ ተገኝተዋል። ዝግጅቱ “የብርሃን ሰበዞች” የተሰኘውን የዮሐንስ ሞላ ሁለተኛ መፅሐፍ ለመመረቅ የተሰናዳ ነው። ዮሐንስ ሞላ የስታስቲክስና የዲሞግራፊ ባለሙያ ቢሆንም፤ በበርካቶች ዘንድ የሚታወቀው ግን በማኅበራዊ ድረ-ገጾች በሚፅፋቸው ገንቢ ሀሳቦቹና የግጥም ስራዎቹ ነው።

 

በፕሮግራሙ ላይ “ቅላፄ ባንድ” የኢትዮጵያን አይዶል አሸናፊ ከሆነው ዳዊት ፅጌና ከሌሎችም ወጣት ድምፃዊያን ጋር በመሆን ታዳሚውን ሲያዝናና አምሽቷል።… የዛሬ ሦስት ዓመት ማለትም ሐሙስ ግንቦት 6 ቀን 2006 ዓ.ም የዮሐንስ ቀዳሚ ስራ “የብርሃን ልክፍት” ሲመረቅ የክብር እንግዳ የነበሩት እናቱ ወ/ሮ ልጅዓለም ሲና ዘንድሮም ክብር ያለውን የክብር እንግድነት በአዳራሹ በድምቀት አግኝተውታል።

 

ለዝግጅቱ መዋዛት አቶ በኃይሉ ገ/መድህን በአዳራሹ የሳቅ ብርሃን የሚረጩ ጨዋታዎችን አስደምጧል። …. ከስነ-ግጥም አንፃር ደግሞ አቶ ነፃነት ተስፋዬ አጠር ያለ ዳሰሳ በመፅሐፉ ዙርያ አቅርበዋል። ይህን ዳሰሳም እንደሚከተለው ለአንባቢያን እንዲመች አድርገን አቅርበነዋል።

 

ገጣሚ ዮሐንስ ሞላ ከዚህ ቀደሞ ባሳተመውም ሆነ ዛሬ በሚመረቀው መፅሐፍ ርዕስ ላይ ብርሃንን ደጋግሞ ማንሳቱ በራሱ የብርሃን ፍቅር እንዳለበት ያስታውቃል በማለት የዕለቱን ዳሰሳ ማቅረብ የጀመሩት አቶ ነፃነት ተስፋዬ፤ ስለሁለቱም መፅሐፍት ብርሃን ገጣሚው ያበራበትን መንገድ ያስቀምጣሉ።

 

የመጀመሪያ ስራው የሆነው “የብርሃን ልክፍት” ርዕሱን ለምን እንደሰጠው ሲያስረዳ፤ ለሌሎች ብርሃን የመሆን ፀጋ ተሰጥቷቸው ብርሃን በመሆን፣ በሌሎች ፊት ብዙ የመከራ እሣት ውስጥ ላለፉ ትጉህና በጐ ሰዎች እንደነበር ያስታውሰናል። አሁን ደግሞ “የብርሃን ሰበዞች”ን ሲፅፍ በኑሮአችን መካከል ያለውን ልዩነት፤ ብዝሃነታችን በአንድነታችን ካልተሳሰረ ፋይዳ ቢስ መሆኑን ለመግለፅ ተጠቅሞበታል የሚሉት አቶ ነፃነት ሁለቱም መድብሎች ግን ጥልቅ የሆኑ ሀሳቦች ተነስተዋል ባይ ናቸው። የመፅሐፍቱ የሽፋን ስዕሎች በራሳቸው ትርጉም የሚሰጡ ድርሰቶች ይወጣቸዋልም ብለዋል።

 

“የብርሃን ሰበዞች” የተሰኘው የመፅሐፉን ርዕስ የያዘው ግጥም፣ በመፅሐፉ ውስጥ አለመካተቱ መልካም አለመሆኑን የገለፁት አቶ ነፃነት፤ ከዚህ በኋላ ይህ መፅሐፍ የህዝብ ሆኗልና በቀጣይ ህትመት እንዲያካትተው “በአንባቢው” ስም እጠይቃለሁ ብለዋል። ገጣሚው በዚህ መድብል ውስጥ 72 ግጥሞችን እንካችሁ ያለን ሲሆን፤ ጉዳያቸውም ሀገራዊ፣ ማኅበረሰባዊና፣ የዴሞክራሲ እጦት፣ የሀገር ፍቅር፣ የባለጊዜዎች የበላይነት፣ ስደትና ፍቅር ዋነኛ ማጠንጠኛዎቹ እንደሆኑም ያትታሉ።

 

“መሀረብ ያላችሁ” በሚለው ግጥሙ በጭንቀትና በእንባ ተሞልቶ “አገሬን ያያችሁ፣ መልሱ ‘ባካችሁ!” ሲል ሀገራችንን ያፋልገናል። በዘር፣ በሃይማኖት፣ በጐሳ እንዳንከፋፈልና ብሶት እንዳይነግስም “ደኔን አትነካኩት!” በተሰኘው ግጥሙ እንዲህ ይላል፡-

 

ቋሚ ግንዴን ስነጣጥር፣ ቅርንጫፌን ሰነጣጥቆ፣

ዘሬን ለቀማ ባከነ፣ ጀግናው ታጋይ ባ’ጭር ታጥቆ።

 

 

ውበትንና ፍቅርን የገለፀባቸው ግጥሞቹም እርሱ እንደሚለው እንደማር ይጣፍጣሉ የሚሉት አቶ ነፃነት፤ “በከንፈርሽ በራ’ፍ ሳልፍ” እና “ለጦቢኛ መልካት” የተሰኙት ግጥሞቹ ተጠቅሰዋል።

 

ታምር ነው ውጤቱ፣ ልብ የሚያመረቃ፣

ትውልድ የሚሻገር፣ ዘመን የሚያነቃ፣

ሲታሰብ ሲጣፍጥ፣ እንኳንስ ሲበላ!

ሀበሻኛ ውበት፣ ኢትዮጵኛ ገላ!

 

በግጥም አፃፃፉ ፈጠራ የታከለበት ከመሆኑም ባሻገር ውስጠ-ወይራ ይዘታቸው በብዙ መንገድ ሊተነተን የሚችል ነው የሚሉት ዳሰሳ አቅራቢው፤ የዘመናት የአገራችንን ኩነት የዘረዘረበትን “መስቀል አደባባይ፣ መንገዱ ሲቆፈር፣ የሸተተኝ አፈር” የተሰኘው ግጥሙ እያንዳንዱ መስመር ዘመንን የሚያሳይ ነው ይሉናል።

 

ሽንት ላቦት ብጥብጥ፣

ጩኸት፣ ብሶት ቅይጥ፣

የ“ነይ እርግብ አሞራ”፣ የ“ጉሮ ወሸባዬ”

የድግስ ጉድ ሆታ …

የ“ይውደም” ጋጋታ…

የ“ልማት” ሆይ ሆይታ..

የብሶት ኡኡታ…

የመፈክር መዓት፣

የደመራ አመድ፣ የደም እንባ ልንቁጥ

የጠያቂ ገላ በክፋት ሲወቀጥ

የምስኪን ሰውነት በተንኮል ሲረገጥ

‘ሚያሰሙትን አይነት

መንታ መንታ ድምጾች-የለውጥና የነውጥ፣

የተሸከመ አፈር!

ታሪክ ሲንፈራፈር

መስቀል አደባባይ መንገዱ ሲቆፈር።

 

 

ከአመት በፊት በሊቢያ በረሃ ውስጥ በግፍ አንገታቸውን ስለተቀሉ ወገኖቻችን የሚያያትተው ግጥምም የህዝቡን ሐዘን ብቻ ሳይሆን፤ ወጣቶቹ በወቅቱ ምን ሊሰማቸው እንደሚችል በምናቡ የሚያሳይበት ስራው ነው ይሉናል። “ምን ምን አለህ ያኔ?” የተሰኘው ይህ ግጥም በመፅሐፉ ካሉ ስራዎች ሁሉ ረጅሙና አምስት ገፅ የሚሸፍን ሲሆን፤ ከሁሉ የበለጠና የዮሐንስን የመፅሐፍ አቅም ያሳየበት ነው ተብሎለታል።

 

ከባህር ዳርቻው በግፍ ወደ ጸና፣ የጭካኔ ማማ፣

እንደበግ ሲነዱህ ወደ እረፍትህ መንደር፣ በሞቱ ጐዳና

ወደ ክብርህ መንበር፣ ወደ ጽድቅ ከተማ

ከወንድምህ ጋር፣ በመከንዳት ርቀት፣ በረድፍ ስታቀና

ምን ምን አለህ ሆድህ? ምን ተሰማህ ከቶ?

ምን ምን አሳሰበህ? ልብህን አመሰው ምን ከፊትህ መጥቶ?

 

የቃላት አመራረጡና አቀራረቡ እንጂ መሰል ግጥሞች ለሌሎችም ወጣት ገጣሚያን ይነሳሉ ያሉት ዳሰሳ አቅራቢው፤ በበርካታ ስራዎቹ ውስጥ ግን እንባ ተደጋግሞ ተነስቷል ሲሉ ይጠቁማሉ። በመፅሐፉ መጀመሪያ ስለ እናቱ ያቀረበውን “በረከት” የተለየና ስነ-ፅሁፋዊ አቅሙንም ያሳየ ነው ተብሎለታል።

 

የዕለቱ የመድረክ አጋፋሪ ሆና ያመሸችው መምህርት ብሌን ሳህሉ ስትሆን፤ ቀላል የሆነን አካሄድን መርጣ የተሳካ ምሽትን አስተናግዳለች ማለት ይቻላል። ምሽቱን ወጣት ገጣሚያን ከገጣሚው “የብርሃን ሰበዞች” እንደነበራቸው አይዘነጋም። መፅሐፍ እና ከራሳቸው ስራዎች ያቀረቧቸው ግጥሞችም ምሽቱን ብርሃናማ በማድረግ ልዩ ጣዕም እንደነበራቸው አይዘነጋም።n   

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
723 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us