የተሰረቀን ሰላም ፍለጋ

Wednesday, 01 June 2016 11:52

         የፊልሙ ርዕስ - “ሠላም ነው?”

ድርሰትና ዝግጅት - ቅድስት ይልማ

ፕሮዳክሽን - ኤልና ፊልም ፕሮዳክሽን

ኤክስኪዩቲቭ ፕሮዲዩሰር -ፀጋነሽ ኃይሉ

ማጀቢያ ሙዚቃ - ድምፃዊ ኤሊያስ ሁሴን

ምስል ቅንብር - ብስራት ጌታቸው እና ተካበ ታዲዮስ

ተዋንያን - ፀጋነሽ ሃይሉ፣ ኤርሚያስ ታደሰ፣ አስሚካ በቀለ፣ ቴዎድሮስ ወዳጄ፣ ፍፁም ጫኔ፣ ሙሉጌታ ጥላሁን፣ ራሄል ሃይሉ እና ሌሎችም

“መስረቅ ጥበብ ነው” የምትል ስርቆት ሱስ የሆነባት መሪ ገፀባህሪይ፤ ለስራውና ለእውነት በጽናት የቆመው የፖሊስ ምክትል ኢንስፔክተር የሚያሳዩትን ልብ አንጠልጣይ ትንቅንቅ ታሪክ የሚያሳይ ፊልም ነው። ባሳለፍነው ሳምንት በርካታ እንግዶች በተገኙበት የተመረቀው “ሠላም ነው?” የተሰኘው ፊልም።

“ሠላም ነው?” ፊልም ከዚህ ቀደም “ረቡኒ” እና “መባ” በተሰኙት ስራዎቿ የታወቀችው ቅድስት ይልማ ተፅፎ የተዘጋጀ ሲሆን፤ በ123 ስቱዲዮ ተዘጋጅቶ በኤልና ፊልም ፕሮዳክሽን ለተመልካች ቀርቧል።

በችግር የሚሰቃዩ ቤተሰቦቿን በመርዳት፤ ሴትነቷን በሚያስረሳ ስርቆት ተጠመደችው ፍቅር (ፀጋነሽ ኃይሉ) ምን ያህል የእጅ አመል እንዳለባት ዳይሬክተሯ ገና በፊልሙ ጅማሬ ለተመልካች ያሳየችበት መንገድ ግልፅ ነው። እናም ይህ ስርቆት ከቤተሰቦቿም ሆነ ከአካባቢው ማህበረሰብ ሲያስገልላት አክስቷን ብላ ከጅማ አዲስ አበባ ትመጣለች።

በሌላ በኩል ደግሞ ምክትል ኢንስፔክተር ታዲያስ (ኤርሚያስ ታደሰ) የፖሊስነትን ሙያ ወንጀለኞችን ስለመቅጣት በሚል ወዶትና አክብሮት የተቀላቀለ አካል ሲሆን፤ በወንጀለኞች እጅ ያጣውን የአባቱን ነፍስ መመለስ ባይችል እንኳን ወንጀለኞችን ለፍርድ የሚያመነታ ተደርጎ የቀረበ ገፀ-ባህሪይ ነው።

“አይጥ ቤት ድመት ገባ” እንዳሉት የፍቅር አክስት፤ የፖሊሱን ሞባይል ከመስረቋም ብሶ የተፈጠረውን ግርግር በመጠቀም ሞባይሌ ጠፍቷል ይሰጠኝ ስትል “የሌባ አይነደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ” አይነት ውዝግብ ውስጥ ስትገባ እንመለከታለን። ይህ የሌባና ፖሊስ ሽኩቻ ውሎ እያደር በሁለቱ ገፀባህሪያት በኩል ያልተሻለ የፍቅር ስበትን ሲፈጥር . . . “የፍቅር ነገር የቸገረ ነገር የጠፋለት መላ” ሆኖ እንመለከታለን። ገና ተማሪ እያለ የፍቅር ደብዳቤ ፅፈሃል በሚል የተገረፈው ታዲዮስ፤ ፍቅሩን መግለፅ አስጨንቆት፤ የጓደኛው አቋራጭ መንገድ ግራ አጋቢ ሲሆንበት እንመለከታለን። ሌባውን መያዝ ግድ ሆኖበት በመንታ መንገድ ላይ ሲወዛወዝ ድንገት ፍቅር የጠለፈው ምክትል ኢንስፔክተር ልቡም ኪሱም ሲፈተሽ “ሠላም ነው?” ፊልም ያሳየናል።

ያም ሆኖ “ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይቀርም” እንዲሉ፤ በፍቅሯ እፍ ክንፍ ያለላት ወጣት ኪስ አውላቂ መሆኗን በተረዳ ጊዜ ለራሱ የገባውን እውነተኛ ቃል በመጠበቅ ፍትህን ከፍ አድርጎ፤ ፍቅሩን በልቡ እንደያዘ ለፍርድ አሳልፎ ይሰጣል። የልቡንም የኪሱንም ሌባ ይጨክንበታል።

“ሰው የእጁን ፍሬ ነው የሚበላው” የሚለን ይህ ፊልም፤ የልጅቷን የድፍረት ምክንያት  የሚያስደግፈው የእናቴንና የእኔን ዕድሜ ሰርቋል” የሚል እምነት በከተማው አለ የተባለውን ሃብታም አባቷን በአክስቷ አማካኝነት አግኝታ ጊዜ የማይገዛውን ብዙ ገንዘብ ለመስረቅ ያደረገችው ሙከራ የገፀባህሪዋን እልህና ቁጭት በግል የሚያሳይ ነው።

· የፊልሙ ዝግጅት

“ሠላም ነው?” ፊልም ከዝግጅት አንጻር በተለይም የዋናዋና ገፀ-ባህሪይ የስርቆት አቅም እንደፊልም አዝናኝ በሆነ መልኩ አሳይቷል። በርግጥም የልጅቷ የእጅ አመል በሰዎች ዘንድ ያንን ያህል ሲፈራ ምን አይነት ሌባ ብትሆን ነው? ብሎ ተመልካቹ መጠየቁ አይቀርም። ለዚህም መልስ ይሆነው ዘንድ የአባቷን የወርቅ ሰዓት ከእጁ ላይ በምን ፍጥነት አደንዝዛ እንደወሰደችበት ብቻ ማየቱ በቂ ነው። የገፀ-ባህሪያቱ ማንነት በተግባራቸውና በድርጊታቸው በግልጽ ጎልቶ እንዲወጣ ተደርጓል።

·  የተዋንያኑ ትወና

“ሠላም ነው?” ፊልም ውስጥ ገፀ-ባህሪያቱ በልካቸው የተስፋ በሚመስል መልኩ ተዋንያኑ የትወና ድርሻቸውን ተወጥተዋል። ፖሊሳዊ ፅኑ አቋምና ገታራነት የሚታይበት ታዲዮስ፤ በተሰጠው ገፀ-ባህሪይ መሠረት የኔ ናቸው የሚላቸውን ሰዎች ሳይቀር በህግ ፊት ሲያቀርብ፤ በማጣትና በማግኘት መሃል የሚታየውን ስሜት በሚገባ ተጫውቶታል። ፍቅርም እንዲህ ብልጣብልጥነት ጣጣ ቢስነቷን፣ አዛኝነቷን ጭምር ስሜት በሚሰጥ አተዋወን አሳታናለች። እዚህ ላይ በግልጽ መነሳት ያለበት ትወና አለ። ይህውም የፍቅር አክስት እና የሃብታም አባቷ ልጅ (እህቷ) የተጫወቷቸው ገፀ- ባህሪያት ወደእውነት የተጠጉ፣ ምናልባትም ከትወና ይልቅ ወደህይወት በእጅጉ የቀረቡ ናቸው ሊባል ይችላል።

·  የገፀ-ባህሪያቱ የቋንቋ አጠቃቀም

ደራሲና ዳይሬክተሯ ቅድስት ይልማ እንደከዚህ ቀደም ስራዎቿ ሁሉ በዚህም አንድ አዲስ ነገር ለማሳየት ሞክራለች። ገፀ-ባህሪያቱ ያደጉበትን አካባቢና ውሏቸውን የሚያሳይ ቋንቋ ተጠቅመዋል። ለምሳሌ ፍቅር አንድ ነገር ሲገጥማትና ስትገረም በኦሮምኛ “አካሲ!” ማለቷ የጅማ ልጅነቷን እንድናስታውስ ያደርገናል። በሌላ በኩል ደግሞ በአካባቢያቸው በኪስ አውላቂነት የሚታወቁት ወጣት የሚጠቀሙበት የወፍ ወይም የአራዳ ቋንቋ ወይም መረጃ የሚሰጡት የሰፈሩ ህፃናትና የጠጅ ቤቱ አስተናጋጅ ከፖሊሱ ጋር የሚግባባው “ኮድ” አዘል ቋንቋ ማሳያ መሆን ይችላል። ይህንንም ለማሳየት በፊልሙ ውስጥ በ“Subtitle” የቀረበበት መንገድ አስመስጋኝና ተመልካችን ከግራ ማጋባት ያዳነ ነው። እዚህች ጋ ጠቆም አድርጎ ለማለፍ ያህል፤ በትወና ውስጥ እንስሳትም ያላቸው ድርሻ የሚናቅ ያለመሆንን ያህል አንድ ጉድለት በፊልሙ ውስጥ ታይቷል። ሃብታም አባቷን ፍለጋ ወደትልቁ ግቢ የገባችው ፍቅር ምንም እንኳን የግቢው ውሻ ቢገጥማትም ይነክሳታል ወይም ይጮህባታል ብለን ስጠብቅ ይባስ ብሎ ሲቅለሰለስ ማየት ልጅቷ ቤተኛ ናት እንዴ የሚያስብል ሆኖ ከታሪኩ ጋር አልገጥም ብሏል።

· ሙዚቃና ኤዲቲንግ

“መሀረቤን አይታችኋል? አላየንም” ይሉትን የልጅነት ጨዋታ በሙዚቃው ውስጥ የሚያስታውሰን “ሠላም ነው?” ፊልም የእኛን ፍለጋ ስንሄድ አንዱን ጥለን ሌላውን አንጠልጥለን የህይወትን መንገድ አዙሪት ያሳየናል። ምስሉ እና ድምፅ ፍሰቱን ለማቀናጀት በኩል ኤዲተሩ ልፋት የማይተካ ሚና እንደነበረው በፊልሙ ውስጥ በጉልህ ይታያል።

በአጠቃላይ “ሠላም ነው?” ፊልም የጠፋብንን ሞራል፤ የጠፋብንን ዕድሜ፤ የጠፋብንን ገንዘብ፤ የጠፋብንን ሰውነት፤ የጠፋብንን ፍቅር እና የጠፋብንን ሠላም በአደባባይ የሚያፈላልግ ፊልም ነው ማለት ይቻላል። የግለሰቦች ታሪክ በሲኒማ ስክሪን ላይ ከጅረትነት ወደ ወንዝነት ብሎም ግድብነት ተለውጦ ለፍቅር ለሠላምና ለሞራል ሲፈስ የምናይበት፤ የህብረተሰብን ትብብርና የአንድን ሰው ዋጋ የምናይበት ፊልም “ሠላም ነው?” ተሰኝቷል። መልካም የመዝናኛ ሳምንት!!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
10378 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us