“አልበም መስራት ትልቅ ፕሮጀክት ነው”

Wednesday, 08 June 2016 12:09

 

ድምፃዊ ፀጋልዑል ሃ/ማርያም (ማንታ ፀሐይ)

የዛሬው የመዝናኛ እንግዳችን የመጀመሪያ አልበሙን ባሳለፍነው ሳምንት ግንቦት 24 ቀን 2008 ዓ.ም በሰሰን ባርና ሬስቶራንት አስመርቋል። ድምጻዊው “ማንታ ፀሐይ” የተሰኘ የበኩር በአልበሙን እንካችሁ ይበል እንጂ ከዚህ ቀደም በሰራቸው በጣት የሚቆጠሩ የትግርኛ ነጠላ ዜማዎቹም ይታወቃል። ድምጻዊ ፀጋልዑል ኃ/ማርያም የኪሮስ አለማየሁና የአብርሃም ገ/መድህን አድናቂ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ከ6 ዓመታት በኋላ ያወጣው ይህ አልበሙ በበርካታ አድማጮቹ ዘንድ የዜማ ቅላጼው ከአብርሃም ገ/መድህን ጋር ይመሳሰላል እስከመባል ደርሷል። ከድምፃዊው ጋር ስለአልበሙና የግል ህይወቱ ጥቂት ቆይታ አድርገናል።

ሰንደቅ፡- ሙዚቃን መቼና እንዴት ጀመርክ በሚለው ብንጀምርስ?

ፀጋልዑል ፡- ሙዚቃን የጀመርኩት በመቀሌ ነው። መጀመሪያ ስጀምር “ኦርጋኒስት” ሆኜ ነበር የምስራው፤ ከስምንት ዓመት በፊት ወደአዲስ አበባ ስመጣም በሜጋ የራሚ ባንድ ጋር እሰራ ነበር። ያም ሆኖ ጎን-ለጎንም የድምፅ ስራዎችን ነጠላ ዜማ ደረጃ ሰርቻለሁ። ይህ የመጀመሪያ አልበሜ ከ6 ዓመታት በላይ ጊዜ ወስጄ የሰራሁት ስራ ነው ማለት ይችላል።

ሰንደቅ፡- ውልደትህና እድገትህ የት አካባቢ ነው?

ፀጋልዑል፡- የተወለድኩት አስመራ ከተማ ነው፤ ገና ህጻን እያለሁ ወደመቀሌ መጥቼ አደኩ። በሙዚቃ ህይወት ውስጥ መኖርን የጀመርኩት በመቀሌ ነው። ገና “ሃይስኩል” እንደገባሁ በክበብ ውስጥ ድራማ መስራትን ነበር የምፈልገው። አንተ ላታውቀው ትችላለህ እንጂ ትግራይ አካባቢ የታዩ ሶስት የሚደርሱ ፊልሞችን ሰርቻለሁ። ለድራማ የጀመረ ድምፅ ነው፤ ብዙ ልጆች ድምጽህ ጥሩ ነው ሲሉኝ ወደሙዚቃው መጣሁ። እንደውም ስጀምር አካባቢ በአማርኛ ዘፈኖች ነው የተነሳሁት።

ሰንደቅ፡- በነጠላ ዜማ ደረጃ ከሰራሃቸው ስራዎች ይህ አልበም በምን ይለያል? በድጋሚ የተካተቱ ስራዎችስ አሉ?

ፀጋልዑል ፡- ከነጠላ ዜማዎቼ ውስጥ በዚህ አልበም የተካተተ የለም። በዚህ አልበም ውስጥ ያሉት ስራዎች ስለሀገር፣ ስለስደት፣ ስለፀፀት፣ ስለሰርግና ፍቅር ያተኮሩ፤ በዘመናዊና በባህላዊ ዜማዎች የተቃኙ ዘፈኖች የተካተቱበት ነው። በግጥምም ሆነ በዜማ አንድ ደረጃ ከፍ ያሉ ናቸው ማለት እችላለሁ። “ማንታ ፀሐይ” አልበምን ለማዘጋጀት ስነሳ በትግርኛ ዘፈኖች ስራው የሚታወቀው ልጅ በላይ ሃየሎም በቅንብሩ አለ፤ ከአብርሃም ገ/መድህን አንስቶ ለበርካታ ድምፃዊያን በማቀናበር የሚታወቅ ልጅ ነው። ለኔም ወደአምስት ዘፈኖችን አቀናብሮልኛል። ከእሱ ሌላ ቢኒያም መስፍን (ቢኒ ገና) እና ዘመን አለምሰገድን ጨምሮ በርካታ ወጣት ባለሙያዎች ተሳትፈው አልበሜን አሳምረውታል። በግጥምም በትግርኛ ስራዎች አካባቢ የሚታወቀው ዳዊት ሰለሞን እና ምስግና አረጋይ አሪፍ- አሪፍ ስራዎችን ሰጥተውኛል። ሌሎቹም አብረውን ሰርተዋል።

ሰንደቅ፡- የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋች እንደመሆንህ በአልበሙ ውስጥ ያለህ ተሳትፎ በምን ደረጃ ይገለፃል?

ፀጋልዑል ፡- እኔ ጥሩ የኦርጋን ችሎታ አለኝ። ነገር ግን የትኩረት መበታተን እንዳይኖርና ስራዬን እንዳይሻማብኝ ለራሴ ከዚህ አልበም ውስጥ “ተመንየያ” የተሰኘውን ዘፈን ብቻ ነው ያቀናበርኩት። ከዚህ ሌላ ግን በአስራ ሁለት ዘፈኖቼ ውስጥ የዘጠኙን ዜማ የሰራሁት እኔ ነኝ። ሁለት ዘፈኖችን ደግሞ በግጥም ተሳትፌያለሁ።

ሰንደቅ፡- ከህይወትህ ጋር በተያያዘ የሰራኸው ዘፈን የትኛው ነው?

ፀጋልዑል ፡- በቀጥታ ከህይወቴ ጋር በተያያዘ የዘፈንኩት ዘፈን የለም። ነገር ግን በአልበሙ ውስጥ ካሉት ስራዎች መካከል “ዘከረኪብቖዳማይ” የሚለውን “ትራክ” ለአባቴ ማስታወሻ እንዲሆን አድርጌያለሁ።

ሰንደቅ፡- ይህን የመጀመሪያ አልበም ስትሰራ ፈተና የሆነብህ ምንድነው?

ፀጋልዑል ፡- እውነቱን ለመናገር አልበም ስራ ማለት ትልቅ ፕሮጀክት ነው። ብዙ ጥረህ ትንሽ የምታገኝበት ነው። እኔ ይህን አልበም ለመስራት በ2000 ዓ.ም አካባቢ ነው የጀመርኩት፤ ባይገርምህ ይህ አልበም ከ40 ዘፈኖች መካከል የተመረጠ ስብስብ ነው።

ሰንደቅ፡- በክለብ ደረጃ የት -የት ትሰራለህ?

ፀጋልዑል ፡- በምሽት ክበብ ደረጃ “ኢትዮ- ሚሊኒየም” እና “ኸርበት” የሚባሉ ሁለት ቤቶች ቦሌ አካባቢ ሰርቻለሁ። አሁን ደግሞ “ፍሪደም ሀውስ” የሚባል 22 አካባቢ እየሰራሁ ነው።

ሰንደቅ፡- ከመሳሪያ ተጫዋችነት ወደድምፃዊነት ስትመጣ መነሻህ የነበረው ማነው?

ፀጋልዑል ፡- እኔ በክለብ ውስጥ የቴዎድሮስ ታደሰን ጨምሮ የተለያዩ አርቲስቶችን ስራ እሞክር ነበር። ነገር ግን እንድብዙዎቹ የትግርኛ ዘፋኖች ኪሮስ አለማየሁ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሮብኛል ብዬ አስባለሁ። አሁንም ድረስ የኪሮስን ስራ ባገኘሁት አጋጣሚ እጫወታለሁ። ኪሮስ አሁን ድረስ ስራዎቹን በቲቪ ስመለከት ይገርመኛል። የስሜት ዘፋኝ ነው። ቃሉ፣ ድምፁና ስሜቱ በጣም የተጣመረለት አይነት አርቲስት ነው። ሌላው አብርሃም ገ/መድህንንም እንዲሁ አደንቀዋለሁ ይህን አልበም ስሰራ ብዙ ስራዎችንም አግዞኛል። በዚህ አጋጣሚ አመሰግነዋለሁ።

ሰንደቅ፡- የመጀመሪያ ስራህን ከስቱዲዮ ውጪ በሬዲዮ ጣቢያዎች ስትሰማው ምን ተሰማህ?

ፀጋልዑል ፡- የተለየ ስሜት ነው የሚሰማህ፤ እንደውም የሆነ ተአምር የሰራህ ያህል ሁሉ ሊሰማህ ይችላል። የመጀመሪያ ነጠላ ዜማዬን ሰርቼ በሬዲዮም በቲቪም ስመጣ፤ ይሄን ያህል ሰርቻለሁ እንዴ?ብዬ ሁሉ ራሴን ጠይቄያለሁ።

ሰንደቅ፡- የሰራኽው የትግርኛ አልበም ነው። ስራህ በመላው አገሪቱ እንዲደመጥ፤ “ሙዚቃ የአለም ቋንቋ ነው” በሚያስብል ደረጃ ሰርቼዋለሁ ብለህ ታምናለህ?

ፀጋልዑል ፡- ዋናው ነገር አሁን ያልከው ነው። “ሙዚቃ የአለም ቋንቋ ነው” ሙዚቃው ከተወደደ ማንም ሰው ይሰማዋል ብዬ አምናለሁ። ለዛም ነው ጊዜ ወስጄ የሰራሁት።

ሰንደቅ፡- አልበሙን ስትሰራ ለዜማው ነው ወይስ ለግጥሙ ትኩረት የሰጠኸው?

ፀጋልዑል ፡- እኔ በብዛት ትኩረት የሚደረገው ዜማው ላይ ነው። ነገር ግን ዜማም ብቻውን ዋጋ አይኖውም። በአንድ ወቅት አንድ የሙዚቃ መምህር ምን ብሎ አስተምሯል መሰለህ? “ዜማ አጫፋሪ ነው፤ ለግጥም አድርሶህ ይጠፋል” ይህ ማለት ዜማውን ወደህው ሙዚቃውን በደንብ ስትደጋግመው ግጥሙን ማጣጣም ትጀምራለህ፣ አሪፍ ግጥም ካገኘህ ዜማው ቢጠፋ እንኳን ግጥሙን በውስጥህ ለብዙ ጊዜ ታቆየዋለህ የሚል እምነት አለኝ።

ሰንደቅ፡- ድምጻዊ ነህ፤ በምንድነው የምትዝናናው?

ፀጋልዑል፡- በፊልም እዝናናለሁ፤ በየቀኑ ፊልም ማየት ያዝናናኛል። ከዚያ ውጪ መጽሐፍትንም ማንበብ እወዳለሁ። በሁለቱ ነው የምዝናናው።

ሰንደቅ፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ፤ ምናልባት በአልበም ስራ ውስጥ ላገዙህ ሰዎች ምስጋና ማቅረብ ከፈለግህ ዕድሉን ልስጥህ?

ፀጋልዑል ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ። የማመሰግናቸው ሰዎች ብዙ ናቸው። አንድ አልበም ያለውን ውጣ ውረድ እንድቋቋም ያገዙኝን ሰዎች በሙሉ በዚህ አጋጣሚ አመሰግናለሁ (አልበሜ ላይም በስም ጠቅሻቸዋለሁ) በተረፈ ግን ከመቀሌ ህዝብ ጋር አልበሙን ለመመረቅ በአሸንዳ በዓል የሙዚቃ ኮንሰርት አዘጋጅተን እንገናኛለን በልልኝ።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
10461 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us