“77” የዘመን አሻራ

Wednesday, 15 June 2016 12:20

      የመፅሐፉ ርዕስ - “77” (በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ)

ደራሲ        - ተወልደ ሲሳይ

የገፅ ብዛት    - 363

ዋጋ          - 75 ብር

የህትመት ዘመን - 2007 ዓ.ም

ይህ የግለሰቦች ታሪክ ብቻ አይደለም፤ የአንድ ወቅት የአገራችንም አስከፊ ታሪክ ማሳያ ጭምር እንጂ። 1977 ዓ.ም የተከሰተውን ከፍተኛ የድርቅ አደጋ ተንተርሶ የተከሰተውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እያጣቀሰ የወቅቱን ፖለቲካዊ ትኩሳት ተንተርሶ የሚተርክ መጽሐፍ ነው። በደራሲ ተወልደ ሲሳይ የተፃፈው “77” የተሰኘውና የእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተው ረጅም ልቦለድ መፅሐፍ፤ መፅሐፉ የታሪክና የዘመን አሻራ የታተመበት ነው ማለት ይቻላል።

ለገፀ-ባህሪያት ህይወት መመሰቃቀል ዋነኛው ምክንያት በወቅቱ የተከሰተው ርሃብ ያስከተለው አደጋ እንደሆነ የሚጠቁመው ደራሲው፤ የወቅቱን የርሃብ ጣር አስመልክቶ “ኧረ የሞት ያለህ” ያስብል እንደነበር በገፅ÷ 352 ላይ ይተርክልናል። መጽሐፍ የህይወትን ውጣ ውረድ፤ ነጭና ጥቁርነት፤ የደስታና የሃዘን፣ የተስፋና የትካዜ መንገዶች ሁሉ በተምሳሌታዊ ቋንቋው ያሳየናል። ይህንን የሚገልጽበት መንገድ እንዲህ ይነበባል፤ “ከደቂቃዎች በኋላ ተመልሶ ቢወጣ ግን ሌጣውን ሳር እንጂ ጤዛውን አላገኘውም። ግልፅ ባይሆንለትም ላልበሰለው አምሮው አንዳች ትርጉም አጫረበት” (ገፅ ÷ 157) ሲል የህይወት አጋጣሚ በደቂቃዎች ውስጥ የሚለዋወጥ መሆኑን ይነግረናል።

 የልጅነት ፍፁም ፍቅር፤ መከራና ችግር፤ ማግኘትና ማጣት፤ አላማና ፅናትን ሁሉ ደራርቦ አስከፊውን ዘመን ምስል በሚከስት መልኩ የሚተርክልን “77” የተሰኘው ልቦለድ፤ ገና ርዕሱን ለተመለከተው ሰው ክፉውን ጊዜ የሚያስታውስ ይመስላል። መጽሐፉ የወቅቱን ማህበራዊ ትስስር፤ ፖለቲካዊ ውጥንቅጥና ስደት፤ ሰፈራና ተከትሎ የመጣውን ሂደት በሙሉ ከልጅነት እስከ ዕውቀት በሳላቸው ገፀ-ባህሪይ አማካኝነት ለማሳየት ይታትራል። መፅሐፉ የአደራን ሸክም፤ የቃል ኪዳንን ክቡርነት፤ የህይወትን ፈተናና የዕጣ ፈንታን ጉዳይ ከአንዱ ጫፍ ወደሌላኛው እየጎተተ የሚተርክ ነው።

ከገፀ- ባህሪያ አንጻር

የልቦለዱ የታሪክ መስታወት ሁለት ገፀ-ባህሪያትን ተከትሎ ይዘወራል። ዮሐንስ መኮንን እና ስምሃል አብርሃም ይሰኛሉ። እነዚህ ሁለት ገፀባህሪያት እትብታቸው ከተቀበረበት ከአድዋ አጠገብ ካላችው ዓዲዕሽር የገጠር መንደር ተነስቶ እስከ ለንደን ይደርሳል። ያንን የመከራ ጊዜ ተከትሎ የደረሰውን ማህበራዊና ቤተሰባዊ ቀውስ ተከትሎ የልጅነት ፍቅራቸውን ሳያጣጥሙ የተለያየት ሁለቱ ገፀ ባህሪያት፤ በራሳቸው ጥረትና ጥንካሬ ህይወታቸውን ሲለወጡ እንመለከታለን። በሰውነት ድካማቸው ውስጥ ተስፋቸው፣ ፍቅራቸው፣ ናፍቆታቸውና ጽናታቸው በጉልህ የሚታይ አብይ -ገፀ ባህሪያት ናቸው። ከእነዚህ ዋነኛ ገፀባህሪያት በተጨማሪ መጥተው የሚጠፉ፤ የታሪኩ ገባሮች ሆነው ሊጠቀሱ ይችላሉ። በሁሉም ውስጥ ግን ፍቅርን፣ ጥላቻን፣ ቂምን፣ ተስፋንና ሰብዓዊነትን እንድናይ ተደርገናል።

ከታሪክ አንጻር

“77” መቼቱን ጠብቆ የወቅቱን ከሞላ ጎደል ማሳየት የሚችል ታሪክ አለው። ድርቁ ያስከተለው የርሃብ ደረጃ፤ እሱን ተከትሎ የመጣው የሰፈራ አማራጭ፤ የደርግ መንግስት የዘመቻ ትግልና የህወሃት የምልመላ ስልትን ሁሉ ይተርካል። በወቅቱ የነበረውን ክስተት እና የባለታሪኮቹን ሁኔታ ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ “ጃ ያስተሰርያል” በሚለው ዘፈኑ የተጠቀመውን ግጥም ያስታውሰናል። “ከጉልበታቸው በላይ የሚታየው በመንገድ ብዛት የፈረጠመው የእግራቸው ጡንቻ ሲኮማተር ተመልካችን ያሰፈራል። ከፍ ሲል ደግሞ የlበሱት ብዙ ቦታ የተጣፈው ቁምጣ የትኛው የመጀመሪያና የትኛው ደግሞ እንደተጣፈ መለየት አይቻልም” ይለናል (ገፅ ÷ 5). . . ከሀገር ውስጥ ሰፈራ እስከ ለንደን ስደት ታሪኩ ይተርካል። በዚህም ውስጥ ገፀ-ባህሪያቱ የሚያልፏቸውን መሰናክሎች ምስል ከሳች በሆነ አፃፃፍ ያሳየናል።

ከቋንቋ አጠቃቀም አንጻር

ታሪኩ ለአንባቢ በሚደርስ ቋንቋ ተፅፎ ቀርቧል። ገላጭና ምስል ከሳች በሆነ መንገድ የሚተርክልን የመፅሐፉ ደራሲ “ሁሉን አወቅ” አተራረክ ስልትን የተከተለ በመሆኑ የትም ቦታ ቢገኝ ግድ አይለንም። በመፅሐፉ ውስጥ እንደታሪኩ ፍሰት የትግርኛ ተፅዕኖ፣ የኦሮምኛ ተፅዕኖና የእንግሊዝኛ ተፅዕኖ በጥቂቱም ቢሆን ከቋንቋ አጠቃቀም አንጻር ታይቶበታል። ይህ ምናልባት ገፀ-ባህሪያቱ አካባቢያቸውን የሚወክሉበት ነው ሊባል ይችላል። “77” ልቦለድ የቋንቋ አጠቃቀሙ በረጅም አረፍተነገር እና አንቀፆች አሉት” ምናልባትም በአፃፃፍ ስልቱ ውስጥ እንደድክመት የሚገልፅ ይሆናል። በመፅሐፉ ውስጥ የደራሲውን የቋንቋ አጠቃቀም ሊያሳዩ ከሚችሉ አገላለፆች መካከል ግን የሚከለተውን መጠቆም ይገባል። “ሌሊት ዝናብ ዘንቦ ስለነበር መሬቱ ጨቅይቷል። ጭቃው ሲያንሸራትት ከድንግሉ መሬት ተንጦ የወጣ ቅቤ እንጂ በዝናብ የራስ አፈር አይመስልም።” (ገፅ ÷149). . .

­­

በመፅሐፉ ውስጥ ሊሻሻሉ የሚገባቸው ጉዳዮች

“77” በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ ልቦለድ እንደመሆኑ መጠን ወቅቱንና ማህበራዊ መስተጋብሩን ከውስን ባለታሪኮች ላይ ተመሰርቶ አሳይቶናል። ይህ ማለት ግን በመጽሐፉ ውስጥ የተተቀሱት ገፀ-ባህሪያት ጥቂት ናቸው ማለት አይደለም። በታሪክ አጋጣሚ ይሁን ሆን ተብሎ በርካታ ገፀ ባህሪያት ከመምጣታቸው የተነሳ አንባቢን ያደናግራሉ። በመሆኑም አስፈላጊነታቸው የጎላ ያልጎነ ገጸ-ባህሪያትን መቀነስ ቢቻል መልካም ነው።

በሁለተኛ ደረጃ እንደእንከን የሚገለፀው ከላይ የተጠቀሰው የቋንቋ አደራደሩ በረጃጅም አረፍተነገሮችና አንቀጾች የተዋቀረ መሆኑ ነው። ሊገለፅ የተፈለገው ታሪክ ወይም ጉዳይ በተቻለ መጠን አጥሮ ቢቀርብ መልካም ይሆናል። አልያ ግን አንባቢን የሚያሰለችና የርዕሰ ጉዳይ መደራረብን ይፈጥራል።

በሶስተኛ ደረጃ መነሳት ያለበት የመፅሐፉ ችግር ትረካው በምዕራፎች የተከፋፈለ ሆኖ ታሪክ አለመቀየጡ ነው። የአንዱን ቤተሰብ ታሪክ ጀምሮ እስካልጨረሰ ድረስ ወደሌላው የማይመለስ መሆኑ ችግር ሆኗል። በመሆኑም በተመሳሳይ ወቅት የሚሄዱ ታሪኮችን እያጠላለፈ እና መልክ እየሰጠ ቢያቀርብልን መልካም ነው። አንድም አንባቢን የቀድሞውን ታሪክ እንዳይረሱ፤ አንድም እንደልብ ማንጠልጠያ ቴክኒክ ለመጠቀም ይረዳል። በተረፈ ግን “77” የተሰኘው በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተው ይህ መፅሐፍ፤ በደረቁ የሚነገር ታሪክን ማንበብ ለማይፈልጉ አንባቢያን አማራጭ ከመሆኑም ባሻገር በሀገራችን ታሪክ ውስጥ የነበረውን የክፉ ዘመን አሻራ ማሳየት ችሏል። ፀሐፊው ሊመሰገን ይገባል።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
6172 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us