“የኛ” ልጆች “የማይወራውን እናውራ” ይሉናል

Wednesday, 22 June 2016 11:53

እነሆ የ“የኛ” ሳምንታዊ የሬድዮ ድራማና ቶክ ሾው 7ኛ ምዕራፉን ጀመረ። እስካሁን የመጣባቸውን ሂደቶች ተንተርሶ ያስገኛቸውን ውጤቶች በመዘርዘር የጀመረው ይህ 7ኛ ምዕራፍ ፕሮግራሙ ትኩረቱን በማህበረሰባችን ዘንድ ደፍረን የማናወራቸውን ጉዳዮች ያነሳል ያሉት የፕሮግራሙ ክሬቲቭ ዳይሬክተር ወ/ሮ አይዳ አሸናፊ ናቸው። አክለውም ይህ ምዕራፍ በተለየ መልኩ የወር አበባ እና “የሹገር ዳዲዎች” ጉዳይ በሀገራችን ወጣቶች ሴቶች ዘንድ እንዴት እንደሚታዩና እንዴት እንደሚታለፉ እናሳይበታለን ብለዋል። “የማይወራውን እናወራ! በተሰኘው በዚህ አዲስ ምዕራፍ የማይወራ ነገር የለም ተብሏል።

የእስካሁን ሂደቱን በገለልተኛ ወገን እስጠንቼ አቅርቤያለሁ የሚለው የ“የኛ” ቡድን፤ በውጤቱም የፕሮግራሙ መደበኛ አድማጮች ያለዕድሜ ጋብቻና ፆታዊ ጥቃትን የመቋቋም አቅማቸው የተሻለ ነው ይላል። እንደጥናቱ ውጤት በአዲስ አበባና በአማራ ክልል ከፕሮግራሙ መደበኛ አድማጮች መካከል 60 በመቶ ያህሉ ፕሮግራሙ አስተማሪ ነው ሲሉ፤ 50 በመቶ ያህሉ ደግሞ አዝናኝ እንደሆነ ገልጸዋል።

ዕድሜያቸው ከ10 ዓመት በላይ ያሉ ታዳጊዎች የፕሮግራሙ ተቀዳሚ ኢላማዎች ናቸው የሚለው ጥናቱ፤ ፕሮግራሙ መደበኛ አድማጮች ቁጥርም 1 ሚሊዮን እንደደረስ ተገልጿል።

በድራማው ውስጥ ያሉት አምስቱ መሪ ገፀ ባህሪያት የኢትዮጵያ ወጣት ሴቶች ለገሃዱ አለም የሚገጥማቸውን ውጣ ውረድ በጠንካራ ጓደኝነትና አስተሳሰብ ሲያልፉት ያሳዩናል። እናም ለዚህ ምዕራፍ ከተዘጋጀው ሙዚቃ የአንዱን ስንኝ ስንመዝ እንደህ ይሉናል፤

“ከበሰለ አእምሮ ወርቅ አልማዝ ይወጣል፣

ጥንቱንም ጥበብ ሴትን ልጅ ያስጌጣል።

የ“የኛ” ሰባተኛ ምዕራፍ መጀመርን ምክንያት አድርገን ባለፈው ማክሰኞ (ሰኔ 7 ቀን 2008 ዓ.ም) በቪላቨርዴ ከተገኙት የድራማው አውራዎች ጋር አጠር ያለ ቆይታን አድርገን ነበር። በፕሮግራሙ ሂደትና ውጤት ደስተኛ መሆናቸውን የሚናገሩት ጠረፍ ካሳሁን (ሜላት)፣ ራሄል ጌቱ (ለምለም)፤ ዘቢባ ግርማ( እሙዬ) እና ለምለም ሃ/ሚካኤል (ሚሚ) የሳራን ገፀ-ባህሪይ የምትጫወተው እየሩሳሌም ቀለመወርቅ በግል ችግር ምክንያት በቦታው ያልተገኘች መሆኑን ማስታወቅ እንወዳለን።

ይህ በመደበኛ አድማጩ የመጣው ለውጥ በራሳቸው  በ“የኛ”ዎችስ እንዴት ይታያል ለሚለው ጥያቄ ጠረፍ ካሳሁን (ሜላት) ስትመልስ፤ “ከዚህ በፊት ስለአንዲት ሴት ጥቃት ከውጪ ሆነን ነበር የምንሰማው ሰምተንም ዝም ነበር የምንለው፤ አሁን ግን የነዚህ የተጠቁ ሴቶችን ችግርና ብሶት ለብዙ ሰው ማድረስ ችለናል። በግልፅ መነጋገርንና መመካከርን አሳይተናል። የግድ በቀጥታ እኛ ላይ ችግሩ ባይደርስም ከችግር መውጫ መንገዱን ማሳየታችን በራሱ ለእኛ እንደአንድ ለውጥ ነው” ትላለች።

በቀጣይ ምዕራፍ ከሚነሱት ጉዳዮች መካከል አንዱ ስለሆነው “የሹገር ዳዲ” ጉዳይ ጠረፍ ካሳሁን (ሜላት) ስትናገር “ብዙ ሴቶች ከዕድሜያቸው በላይ የሆነን ሰው በመገናኘት ከችግር ለመውጣት ሲያስቡ የሚገጥማቸውን ችግር እናሳያለን። አማራጮችንም በድራማው ውስጥ ለወጣት ሴቶች እንጠቁማለን። በድራማችን ውስጥ በጓደኛ መታለል ምክንያት “ሹገር ዳዲዎች” በሴት እህቶቻችን ላይ የሚደርሱትን ጫናና ስነልቦናዊ ቀውስ ከእነመፍትሄው እናሳያለን ብለናል” ስትልም ትገልፃለች።

በዚህ ሰባተኛ ምዕራፍ ላይ ከሚነሱት አንኳር ጉዳዮች ሌላኛው “የወር አበባ ነው” የምትለው ራሄል ጉቱ (ለምለም) ናት። “የወር አበባ የተፈጥሮ ፀጋም ግዴታም ነው የምትለው ራሄል፤ ነገር ግን በተለይ በገጠሪቱ አካባቢ ያሉ ወጣት ሴቶች እንደመቆሸሽ እያዩት ይቸገራሉ፤ በተለይ እንደመጀመሪያ የስሜት መረበሽ ያሳያሉ” ስትል ምን መደረግ እንዳለበት በድራማችን የተሻለ  ግንዛቤን እንፈጥራለን ትላለች።     

ወጣቶቹ የ“የኛ” ተከታታይ የሬዲዮ ድራማ ተዋንያንና ድምፃዊያን ባሳላፉዋቸው ምዕራፎች ውስጥ ስለአጋጠማቸው ተግዳሮቶችም ተጠይቀው ነበር። “እስካሁን የገጠመን ችግር የለም። ምክንያቱም ስራውን ስንጀምረው እንዳንቸገር በተሟላ ሁኔታ ውስጥ እንድናልፍ ተደርገን ነው። ይህን የምትለው ዘቢባ ግርማ (እሙዬ) ናት። ሁላችንም በሙዚቃን በሬዲዮ ድራማ ሰልጠነን እንድንቀርብ ተደርገናል የምትለው ጠረፍ ካሳሁን (ሜላት)፤ ስራውን አወቀነውና ገብቶን ነው የምንሰራው ትላለች። ይሁን እንጂ አድማጮች እንዲያውቁልን የምንፈልገው ነገር አለ ባይም ነች፤ “እኛ የምንሰራው ተፅፈው የተሰጡንን ገፀ ባህሪያት ነው። ከእኛ (ከተዋንያኑ) ጋር ምንም የሚያመሳስላቸው ነገር የለም። ውጪ ስንወጣ የራሳችንን ህይወት ነው የምንኖረው። አንዳንዴ መንገድ ላይ እንደራስህ ስትኖር ያዩህና ከድራማው ጋር የሚምታታባቸው ሰዎች ይገጥሙናል። ገፀ ባህሪያቶችን የተቀረፁት ለታዳጊዎች እንዲሆኑ ተደርገው ነው። ነገር ግን እኛ ከዚያም ዕድሜ ከፍ እንላለን” ስትል፤ በገፀ ባህሪያቶቹና በተዋንያኑ መካከል ያለውን ግልጽ ልዩነት ታዳሚው እንዲረዳቸው ታሳስባለች።

በስራ ሂደት በርካታ ጥሩ ትምህርቶችን አግኝተናል የምትው ደግሞ ለምለም ሃ/ሚካኤል (ሚሚ) ናት። እንደሷ አገላለፅ፤ ከታዋቂ የአገራችን ተዋንያን ጋር መስራት መቻላቸው የትወናን ጥበብ የማግኘት እድል አለ ባይ ናት። በትወናው ሂደት ስሜት ውስጥ መግባትና ያም ስሜት ቤት ድረስ ተከትሎ መሄዱ አልፎ አልፎ የሚያጋጥማት የተለየ ክስተት መሆኑን ታስታውሳለች።

ከማይረሱት ገጠመኛቸው መካከል በሰሜኑ የአገራችን ክፍል (እንጅባራ) ለወጣቶች የሚሆን የሙዚቃ (ኮንሰርት) ለማሳየት በሄድንበት ጊዜ የገጠመን የተለየ ነው የምትለው ጠረፍ ካሳሁን (ሜላት) ተመልካቹ በሬዲዮ የሚያውቁትና “ቀበጧን” ሜላትን ከመጥላቱ የተነሳ “በድንጋይ እንበላት” እስከማለት ደርሶ ነበር ስትል ገጠመኟን ታስታውሳለች።

በስተመጨረሻም ታዳጊ ወጣቶችን በማስተማርና በማዝናናት የመጠመዳቸውን ያህል እነርሱ በምን እንደሚዝናኑ ላነሳንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ቀዳሚዋ ጠረፍ ካሳሁን (ሜላት) “ቀልድ በጣም ያዝናናኛል፤ በመንገድ ላይም ይሁን ከማላውቀው ሰው ጋር አሪፍ ቀልድ ከሰማሁ በጣም ነው የምዝናናው” ባይናት። አከል አድርጋም፤ ሙዚቃና ዳንስም እንደሚያዝናናት አልሸሸገችም።

በድራማው ውስጥ የጎዳና ተዳዳሪ ገፀ-ባህሪውን የተላበሰችው ሚሚ (ለምለም ሃ/ሚካኤል) በሙዚቃና በፊልም በእጅጉ እንደምትዝናና ተናግራለች። የእርሷ ተመሳሳይ የሆነችው ለምለም (ራሄል ጌቱ) በበኩሏ ፊልም ማየትም ሆነ መስራት እንደሚያስደስታት ይሰመርልኝ ስትል ተደምጣለች። በአንጻሩ ደግሞ እሙዬ (ዘቢባ ግርማ) እንደመዝናኛ ከጓደኞቹና ከቤተሰቦቼ ጋር የማሳልፈው ጊዜ እኔን ያዝናናኛል ባይ ናት።

በስተመጨረሻም “የኛ”ዎች የሚከተለውን መልዕክት ለአድናቂዎቻቸው ያሰተላልፋሉ። “የኛ እናንተ ነው፤ እናንተም የኛናችሁ እንወዳችኋለን። ፃፉልን ደውሉልን፤ ሃሳባችሁን እንፈልገዋለን” ብለዋችኋል። የ“የኛ” ድራማን ቶክሾው ፕሮግራም በሸገር ኤፍ ኤም፤ በባህር ዳር፣ በደሴና በደብረብርሃን ኤፍ ኤሞች፤ እንዲሁም በአማራ ኤፍ ኤም ራዲዮ ሥርጭቶች አየር ላይ የሚውል ሲሆን፤ በቅርቡም በፋና ኤፍ ኤም ለአድማጭ መድረስ እንደሚጀምር የፕሮግራሙ መሪዎች አስታውቀዋል። መልካም የመዝናኛና የመረጃ ሳምንት እንዲሆን ተመኝተናል። 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
14868 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us