“ጥሞና” - በባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያ የቀረበ አዲስ ጣዕም

Wednesday, 29 June 2016 12:15

ኢትዮጵያ የራሴ ናቸው የምትላቸውን የሙዚቃ መሳሪያዎች ብቻ በመጠቀም ባልተለመደ መልኩ በሙሉ ባንድ የተሰራ በሙዚቃ ቅንብር የያዘ አልበም በቅርቡ ለገበያ ቀርቧል። በምሳብ የባህላዊ ሙዚቃ ቡድን የቀረበው ይህ አዲስ አልበም “ጥሞና” የተሰኘ ራስ ተሰጥቶታል። አልበሙን ያዘጋጁት ወጣትና ልምድ ያላቸው የሙዚቃ ባለሙያዎች በጥምረት ሲሆን፤ አልበሙ ባሳለፍነው ሰኔ 6 ቀን 2008 ዓ.ም ጥሪ የተደረገላቸው በርካታ እንግዶች በተገኙበት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ በድምቀት ተመርቋል።

“ጥሞና” በሙዚቃ መሳሪያ የተሰራ ቅንብር ሲሆን፤ አልበሙን የቀረፀውና ሚክሲንጉን የሰራው ዘሪሁን ሳ/ማሪያም ነው። በአልበሙ ላይ የተሳተፉት ባለሙያዎች ጣሰው ወንድም (በዋሽንት)፣ ሔኖክ አለሙ (በከበሮ)፣ ዳዊት ልሳነወርቅ እና ሀዲስ አለማየሁ (በመሰንቆ)፣ ቢኒያም ዳኛቸው እና ታምሩ ንጉሴ (በድርድር ክራርእና በክራር) እንዲሁም ቶፊቅ አባ ሲመል እና ይገረም ጉልላት (በቤዝ ክራር) ሙዚቃውን ቀምረውታል። የባንዱ አባላት በአጠቃላይ ስድስት ተወዛዋዦችንና ሶስት ድምጻዊያንን ጨምሮ ከአስራ ሰባት በላይ ናቸው።

አብዛኞቹ የባንዱ አባላት ገና ድሮ “በሰርከስ ኢትዮጵያ” ውስጥ ሳሉ እንደሚተዋወቁ የሚናገረው የሞሰብ ባንድ አስተባባሪና ዋሽንት ተጫዋቹ ጣሰው ወንድም ነው። ነገር ግን በጊዜ ሂደት በግላቸው ጥሩ ሙዚቃን ለመስራት በማሰብና ነጻነቱንም በመሻት ባንዱን እንደመሰረቱት ያስታውሳል። በግል ተሰባስበው በመስራት ካደመቋቸው መድረኮች መካከል የመጽሐፍት ምርቃቶች፤ በሙዚቃ የሚቀርቡ የግጥም ምሽቶች (ፖየቲክ ጃዝ) በተለየ መልኩ  ከሰሯቸው ዝግጅቶች መካከል ደግሞ 118ኛውን የአድዋ ድል በጣይቱ ሆቴል፤ እንዲሁም 120ኛውን የአድዋ ድል በዓል በሙሉ ድምቀት በሸበሌ ሆቴል ማዘጋታቸው ይጠቀሳል።

“አላማችን ብለን የተነሳነው የእኛን መሰል የባህል መሳሪያ ተጫዋቾች ለማነቃቃትና አድማጩም አዲስ ዜማን በተለየ በባህላዊ መሳሪያዎች የተቀነባበረን ሙዚቃ በሙሉ አልበም ደረጃ እንዲገኝ ከማድረግ አንጻር ነበር፤ ያም ተሳክቶልናል ብዬ አምናለሁ” የሚለው ደግሞ በባንዱ ውስጥ በመሰንቆ ተጫዋችነትና በመምህርነትም እየሰራ የሚገኘው ሀዲስ አለማየሁ ነው።

“የተሻለ ነገር ለመስራት ባቋቋምነው ባንድ ውስጥ የሀገራችንን ሙዚቃ ለማስተዋወቅ እየሰራን ነው” የሚለው ሌላኛው የሞሰብ ባንድ አባልና ክራር ተጫዋቹ ቢኒያም ወርቁ ነው። ይህ ሃሳብ ሁሉም የባንዱ አባላት የሚስማሙበት ይመስላል።

ወጣቶቹ በትምህርትም ሆነ በድንገት የሙዚቃን አለም የተቀላቀሉ ናቸው። ለምሳሌ ሀዲስ አለማየሁ ከኮተቤ የመምህራን ኮሌጅ በሙዚቃ ዲፕሎማውን ያገኘ ወጣት ባለሙያ ነው። ወደባንዱ ከመቀላቀሉ በፊትም ለሁለት አመታት ሙዚቃን በተለያዩ ት/ቤቶች በማስተማር ቆይቷል። በአንጻሩ ቢኒያም ወርቁ የነገ ተስፋ ሰርከስ ውስጥ ሙዚቃን ጀምሮ በሂደት የበቃ ባለሙያ እንደሆነ ይናገራል። ከክፍለሀገር ወደአዲስ አበባ በመምጣት የሙዚቃ ስራውን ያዳበረው የባንዱ አስተባባሪ ጣሰው ወንድም በበኩሉ በሰርከስ -ኢትዮጵያ እና በብሔራዊ ቴአትር በዋሽንት ተጫዋችነት መስራቱንም ይናገራል። “አሁን ላይ ከሞሰብ ባህላዊ ባንድ ውጪ ከታዋቂው የሙዚቃ ባለሙያ (የክቡር ዶክተር) ሙላቱ አስታጥቄ እና ጆርጋ መስፍንን ከመሳሰሉ ባለሙያዎች ጋር በአፍሪካ ጃዝ መንደር ሙዚቃን እየሰራሁ እገኛለሁ ይላል።

ለእነርሱ የመጀመሪያ የሆነውና “አዲስ ጣዕም” ይዟል የተባለለትን “ጥሞና” የተሰኘ በባህላዊ መሳሪያ ብቻ የተቀነባበረ የሙዚቃ ስራ ለመስራት የነበረውን ሂደትና ውጣውረድ በሚመለከት ባለሙያዎቹ እንዲህ ይላሉ።

“ከሁለት ዓመት ያላነሰ ጊዜን ወስደን በጥሞና የሰራነው አልበም ነው” የሚለው የሞሰብ ባንድ አስተባባሪው፣ “በሙዚቃም ጥሞና መኖሩ ለማስታወስ ጭምር ነው የአልበማችንን መጠሪያ “ጥሞና” ያልነው” ይላል። በአልበሙ ውስጥ የተካተቱት አስሩም ሙዚቃዎች የተመረጡት ታሪክና ምክንያት ያላቸው እንደሆኑም ያስረዳሉ።

አልበሙን ለአድማጭ ለማድረስ ፕሮዲዩስ ያደረጉት ባንዱ አባላት ራሳቸው መሆናቸውን የገለፁ ሲሆን፤ የአልበም ሽያጩ የወደቀበት ሰዓት ቢሆንም በድፍረት መደመጥ አለበት በሚል መንፈስ ሰርተው ማቅረባቸውንም ያሰምሩበታል። የአልበሙ አሳታሚና አከፋፋይ ቮካል ሪከርድስ ቢሆንም፤ እነርሱም አድማጭ ዘንድ እንዲደርስ የበኩላቸውን እየለፉ እንደሆነ ይናገራሉ።

ሙዚቃዎቹን ከመምረጡ ጀምሮ ከረጅም ልምምድ ጊዜ በኋላ ወደስቱዲዮ መግባቱ በራሱ አድካሚ ሂደት እንደነበረው የሚገልጸው ደግሞ ሀዲስ አለማየሁን  ሃሳብ ለማጠናከር፤ “እንደመጀመሪያ አልበም ብዙ መስዋዕት አስከፍሎናል” ሲል አፅንኦት ይሰጥበታል። ያም ሆኖ ቢኒያም እንዲህ ይላል፤ “በመጨረሻ አልበሙ ተሰምቶ ከአድማጩ ባገኘነው ምላሽ ግን ሁላችንም ደስተኞች ነን ሲልም ልፋታቸው መና አለመቅረቱን ያስታውሳል።

አልበሙን ሰርቶ ለአድማጭ ማድረስ በራሱ ትልቅ ምዕራፍ እንደሆነ የሚስማሙት የባንዱ አባላት፤ በስተመጨረሻ የተገኘው ምላሽም አመርቂ ነው ባይ ናቸው። “ከአድማጭ ያገኘነው ምላሽ እንደጠበቅነው ስላልነበረ በጣም ያስደነግጣል፤ ድንጋጤው ግን ከደስታ የመነጨ ነው” የሚለው ጣሰው ወንድም፤ ስራውን በሚገባ አድምጠው ምስጋና የቸሯቸው ሰዎች እንዳሉ ሁሉ ለተማሪዎቻቸው የሚያስደምጡ መምህራንና የግጥም ሀሳብ መነሻ የሆኑላቸው ገጣሚያን መኖራቸውን ጭምር ለምስክርነት ጠቅሳል።

በተለይ በብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ የነበረውን የተመልካች ምላሽ በፍፁም አንረሳውም የሚሉት የሙዚቃ ባለሙያዎቹ፤ በዕለቱ መታወስም መመስገንም የነበረባቸውን ባለሙያዎች ማንሳታችን ትልቅ ዝግጅት እንዲሆን አድርጎታል ይላሉ። በዕለቱ በመድረኩ ከታወሱት አንጋፋ የሙዚቃ ባለሙያዎች እና ባለውለታዎች መካከል አርቲስት ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ጋሽ ታደሰ እጅጉ፣ ክቡር ዶ/ር ሙላቱ አስታጥቄን እና ተወዛዋዡ መላኩ በላይን ለመሳሰሉ ባለሙያዎች በይፋ በህዝብ ፊት ክብርና አድናቆትን አበርክተዋል።

“ሙዚቃ የማይዳሰስ ጥልቅና ውስጣዊ ፊልም ነው” ሲል ስለሙዚቃ ያለውን መረዳት የሚገልጸው የሙዚቃ ባንዱ የክራር ተጫዋች ቢኒያም ነው። አክሎም፤ “ሙዚቃ ከፍ ሲልም ሰውና ፈጣሪን የሚያገናኝ ጥበብ ነው” ሲል ይገልፀዋል።

“ሙዚቃ በእኔ አንደበት መገለፅ የሚችል አይመስለኝም” የሚለው የመሰንቆ ተጫዋቹና የሙዚቃ መምህሩ ሀዲስ አለማየሁ፤ ሙዚቃ ለኔ ገና ተተርጉሞ ያላለቀ ነው” ባይነው። ነገር ግን ከሙዚቃ መሳሪያዎች ሁሉ “መሰንቆን” ስጫወት የሚሰማኝ ስሜት “ይሄ ሰው አብዷል” የሚያስብለኝ ነው ሲል፤ ሙዚቃ በመንፈስ ለውጥ ላይ ያለውን አቅም ይገልፃል። በእዚህ አጋጣሚ መነሳት ያለበት ሌላው ሃሳብ የሙዚቃ ህክምናን ይመለከታል። ለመሆኑ ስራዎቻችሁን ከህክምና አንጻር አገልግሎ ላይ ለማዋል ምን ሰርታችኋል? በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “በርካታ የሥነ አእምሮና የሥነ ልቦና አዋቂዎች እንደሚስማሙበት ሙዚቃ ሰውን የማረጋጋትና መንፈስን የማደስ ኃይል አለው። በቀጣይም በተለይ ከአእምሮ ህመም ጋር በተያያዘ ህክምና ላይ ያሉ ወገኖቻችንን ለማገዝ በተለያዩ ሆስፒታሎች በመገኘት ስራዎቻችንን የማቅረብ እቅድ አለን” ይላሉ።

“ሙዚቃ የሚስብ አቅምን፤ የስሜት ፈውስን፤ መረጋጋትንና የፈጠረ ኃይልን የሚሰጠን ጥበብ ነው ብዬ አምናለሁ” የሚለው ደግሞ የሞሰብ ባንዱ አስተባባሪና የዋሽንት ተጫዋቹ ጣሰው ወንድም ነው።

በሀገራችን ተደጋግሞ የሚሰማው የሙዚቃ መሳሪያ ቅንብር የትዝታ ስራዎች ብቻ ስለመሆናቸው የሚናገሩት የሞሰብ ባንድ አባላት፣ በአዲስ አልበማችን ግን ከታሪካዊው ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስ ጀምሮ የ“ፍቅር እስከ መቃብሩ” አበጀ በለውን (ገፀ -ባህሪይ) የሚያስታውሱ ስራዎችን ሰርተናል ይላሉ። አቡነ ጴጥሮስን ለማስታወስ መንፈሳዊ ይዘት ያለውን “ዘለሰኛ” ዜማ ያካተቱ ሲሆን፤ በ“ፍቅር እስከ መቃብር” ውስጥ ያለውን ጀግና ገፀ-ባህሪይ አበጀ በለውን ለማስታወስ ደግሞ “እንደው ዘራፌዋ” የተሰኘውን ወኔ ቀስቃሽ የጀግና ስልት አካተን አቅርበናል፤ ከዚህም ባሻገር “እረኛው በተሰኘው ዜማ ውስጥ የከብቶች ድምጽ እንዲገባ መደረጉ አድማጭን የሚያግዝ ይመስለናል ይላሉ። ይህን አልበም የሚያደምጥ ሰው የዜማውን ርዕስ ባየ ጊዜ ስሜት እንዲሰጠው ተደርጎ የተሰራ ቅንብር እንደሆነም ያትታሉ።

በሙዚቃ መሳሪያ ለተቀናበሩ ስራዎች አድማጩ ጆሮ ገና ነው ብዬ አስባለሁ” የሚለው ሀዲስ አለማየሁ፤ ያም ቢሆን ግን አድማጮቹን ማስለመድ የባለሙያው ድርሻ ነው ይላል። የዚህ ባንድ አላማም የኢትዮጵያን ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያና ባህል ለማስተዋወቅ የሚታትር ነው ይሉናል።

በሀገራችን ያሉን ባህላዊ መሳሪያዎች በመጠቀም በቁጥር አናሳ የሆኑትን የሙዚቃ መሳሪያ ቅንብሮች ከፍ ለማድረግ አድማጩ ጋር መድረስ ዋነኛ አላማችን ነው የሚሉት አባላቱ፤ ስራዎቹ ሲበራከቱ አድማጭ መጨመሩ አይቀርም የሚል ተሰፋ አላቸው።

የሙዚቃ ቡድኑ አባላት ሙዚቃን በማድመጥ፣ በዋና፣ በማንበብና የተለያዩ ሙዚቃዎችን መጫወት በተለይ እንደሚዝናኑ ይናገራሉ”. . . በቀጣይ የሙዚቃ ዝግጅቶችን ከመስራት ባለፈ፤ ወጣቶችን የሙዚቃ መሳሪያ ለማስተማር እየሰሩ ሲሆን፤ ይህ እንቅስቃሴያቸውን በኢንተርኔት /ኦንላይን ስርጭት የታገዘ ተግባራዊ ስልጠና እንሰጣለን ብለዋል። ይህንንም ስልጠና በመላው አለም ያሉ መማር የሚፈልጉ ኢትዮጵያን ማግኘት እንደሚችሉም አስረድተዋል።

የባህላዊ ሙዚቃ ባንዱ ስያሜ ለምን “ሞሰብ” ተባለ ለሚለው ጥያቄ ሲመለሱ፤ ሞሰብ ኢትዮጵያዊ ገበታ ነው፤ ቤተሰባዊነትን፣ ፍቅርንና አንድነትን የሚገልፅ በመሆኑና አሰራሩም “አርቲስቲክ” ስለሆነ ለመጠሪያነት እንደመረጡት ይናገራሉ። ኢትዮጵያዊ (ሀገራዊ) ለዛ ያላቸውን በባህላዊ ሙዚቃ የተቀናበሩ ስራዎች እነሆ በረከት ያለው “ሞሰብ ባህላዊ የሙዚቃ ቡድን በቀጣይም በርካታ የሙዚቃ ድግሶችና አልበሞችን የመስራት ህልም ያላቸው እንደሆነ ከባለሙያዎቹ ጋር በነበረን ቆይታ ተረድተናል። በመጨረሻም በሙዚቃ ህይወታቸውም ሆነ በአልበም ስራቸው ሂደት ያገዟቸውን የደገፏቸውን ሰዎች ሁሉ በእጅጉ አመስግነዋል። እኛም አዲስ ሙዚቃዊ ጣዕምን ከ“ጥሞና” አልበም ታገኙ ዘንድ ስራዎቻቸውን ጋብዘናል። መልካም የመዝናኛ ሳምንት።   

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
566 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us