“ስራዬ መዝናኛዬም ጭምር ነው”

Wednesday, 12 March 2014 12:16

አርቲስት ጀንበር አሰፋ

ከአስር ዓመታት በላይ በተለያዩ የቴአትር መድረኮች የትወና ብቃቷን አሳይታለች። በርካቶችም በቴአትሮቿ፣ በፊልሞቿ፣ በሬዲዮና በቴሌቭዥን ድራማዎቿ ጠንቅቀው ያውቋታል። ላጤ፣ የስልጣን ማደጎ፣ ጥቋቁር ፀሐዮች፤ እና ጓደኛሞቹ በመሳሰሉ በርካታ ተውኔቶች ላይ በብቃት ተውናለች። በተለይ ደግሞ ከቲቪ ስራዎቿ “ገመና” ድራማ አሁን ድስ የምትታወስበት ሲሆን ቀደም ብሎ ከሰራቻቸው ውስጥም ቢሆን ቅብብል፣ አቋራጭና ማን ገደላት የሚጠቀሱላት ስራዎቿ ናቸው። የዛሬዋ እንግዳችን ከትወና ባሻገር በቅርቡ የፊልምና የቴአትር ደራሲነቷንም አሳይታናለች። ከአርቲስት ጀንበር አሰፋ ጋር ያደረግነውን አጭር ቆይታ እነሆ፤

ሰንደቅ፡- ጀንበርምን ያህል ስራዎችን እንደሰራሽ ብታስታውሺን?

ጀንበር፡- በጣም ይገርማል እንዲህ ድንገት ስጠየቅ የማስታውሰው ጥቂቱን ነው። ፅፌ እና ተዘጋጅቼ ቢሆን አውቀው ነበር። በአጠቃላይ ግን በሬዲዮ፣ በቲቪና በመድረክ በርካታ ስራዎችን ሰርቻለሁ ማለት ይቀለኛል።

ሰንደቅ፡- ከትወናው መልስ መፃፍ ጀምረሽ በርካታ ስራዎችን ሰርተሻል። ከጽሁፍ ጋር ያለሽ ነገር እንዴት ነው?

ጀንበር፡- ለፅሁፍ ቅርብ ነኝ ብዬ አስባለሁ። ከዚህ ቀደምም ቢሆን በተለያዩ ሬዲዮ ጣቢያዎች የተላለፉ ተከታታይ ድራማዎችን ፅፌያለሁ። አሁንም ተሰርተው የስርጭት ጊዜያቸውን የሚጠብቁ ድራማዎች አሉኝ። ከዛ በተረፈ በአዲስ አበባ መስተዳድር ቲቪ በኩልም ድራማዎችን ፅፌ አሳይቻለሁ። ጥሩ ምላሽም ነበረው።

ሰንደቅ፡- በቅርቡ “ምዕራፍ አራት” የተሰኘ ተውኔትሽን ለተመልካች ልታደርሺ እንደሆነ ሰምቻለሁ። በቴአትሩ ላይ ያንቺ ድርሻ ምን ድረስ ነው?

ጀንበር፡- “ምዕራፍ አራት” ቴአትር ለመድረክ የበኩር ስራዬ ነው። በዚህ ቴአትር ውስጥ የኔ ድርሻ ድርሰትና ፕሮዲዩሰርነት ነው። በጀንበር ቴአትር ፕሮዳክሽን ማለት ነው። ወደትወናው አልገባሁበትም። ምክንያቱም የፕሮዳክሽን ስራው በጣም ብዙ ውጣ ውረድ አለው። ቴአትር መድረክ ላይ የምትተውን ከሆነ በሙሉ ልብህ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ። በመሆኑም ሀሳቤ ተከፋፍሎ ብተውን ውጤታማ አያደርገኝም ብዬ ስላሰብኩ በትወናው አልተሳተፍኩም። በነገራችን ላይ ይህ ቴአትር ሁለት እኔነቴን የፃፍኩበት ነው። ይህ ማለት እናቴና አባቴ የማይገናኝ ባህሪይ ያላቸው ናቸው። አባቴ ዘመናዊ ሰው ነው። እናቴ ደግሞ የፊውዳል ባህሪይ ያላት ናት። እናም እናቴ ብቻዋን ብታሳድገኝ እና አባቴ ብቻውን ቢያሳድገኝ ሊኖረኝ የሚችለውን ሁለት የተለያዩ ባህሪይ ነው በተውኔት ለማሳየት የሞከርኩት።

ሰንደቅ፡- አንቺ በጣም የምትታወቂው በትወናሽ ነውና በፅሁፍ ከዚህ በኋላ እንጠብቅሽ ማለት ነው?

ጀንበር፡- ለነገሩ ለመድረክና ለፊልም ስራው ትንሽ ልዘግይ እንጂ ከዚህም በፊት ቢሆን እንደነገርኩህ በሬዲዮና በቲቪ በኩል ስራዎቼ ተላልፈዋል። “ምዕራፍ አራት” የበኩር የቴአትር ፅሁፌ ነው። በቅርቡ ደግሞ የበኩር የፊልም ስራዬ “የልጃችን እናት” በሚል ርዕስ በያዝነው ወር መጨረሻ አካባቢ እንደእግዚያብሔር ፈቃድ ተመርቆ ለዕይታ ይበቃል።

ሰንደቅ፡- በፅሑፍሽ (በስራዎችሽ) ማስተላለፍ የምትፈልገውን ነገር ማድረስ እችላለሁ ብለሽ ታስቢያለሽ?

ጀንበር፡- ከሰራሁዋቸው የሬዲዮና የቲቪ ድራማዎቼ ውስጥ ሁሉ ልናገረው የምፈልገውን ማህበራዊ ጉዳይ በሚገባ አስተላልፌያለሁ ብዬ አምናለሁ። አሁን ደግሞ “ምዕራፍ አራት” በተሰኘው ቴአትር በኩል ሁለት የማይጣጣሙ ባህሪያትን አጣምሬ ለማሳየት ሞክሬያለሁ። በአስተዳደግም በባህሪም የማይገናኙ ኋደኛሞችን ህይወት ነው በቴአትሩ ያሳየሁት። በርካታ ፊልሞችን ቴአትሮችን በመስራት ያካበትኩትን ልምድ ተጠቅሜ የሰራኋቸው ስራዎች ናቸው። ለህዝብ የሚደርሱት እንግዲህ ምላሹን ተመልካቹ ይሰጠኛል ብዬ እጠብቃለሁ።

ሰንደቅ፡- ፊልሞች በብዛት እየተሰሩ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ቴአትር ይዘሽ መጥተሻል። ገቢያውን ስትገመግሚው አዋጭ ነው ማለት ይቻላል?

ጀንበር፡- መፃፍ ስጀምር መጀመሪያ የሬዲዮ ድራማዎችን ነበር። ቀጥዬ የቲቪ አጫጭር ስራዎችን ፅፌያለሁ። አሁን ደግሞ ደረጃዬን ከፍ አድርጌ የፃፍኩት የሚመስለኝ የመድረክ ተውኔት ነው። ባይገርምህ እንደአጋጣሚ ሆኖ በወሩ መጨረሻ ለዕይታ ከሚበቃው ፊልሜ ጋር ተገጣጠመ እንጂ ይህ ቴአትር ተሰርቶ ካለቀ አንድ ዓመት ሆኖታል። የዘገየ ነው በቴአትር ቤቶች ወረፋ ምክንያት ነው። እንደምታውቀው በአሁኑ ሰዓት ያሉን ቴአትር ቤቶች ሁለት ናቸው። ብሔራዊ እና ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤቶች። ሌሎቹ በእድሳትና በመንገድ ስራው ምክንያት ስራቸውን አቁመዋል። ስለዚህ የግድ ወረፋ መጠበቅ ስለነበረብን ቆይተናል። በዚህ አመት ውስጥ ቁጭ ከምል ብዬ ፊልሜን ሰራሁ። የሚገርመው ነገር ሁለቱም በአንድ ወር ውስጥ ተመርቀው ለተመልካች ሊደርሱ ነው ማለት ነው። አዋጭነቱን በተመለከተ ለጠየከኝ ጥያቄ እውነቱን ለመናገር ከስድስት ወር በኋላ እርግጠኛ ሆኜ ልመልስልህ እችላለሁ። ብዙ ነገሮች ሰምቻለሁ ነገር ግን ከምሰማው ይልቅ በራሴ አይቼው ምስክርነቴን ብሰጥ የተሻለ ይመስለኛል።

ሰንደቅ፡- ባልሳሳት በትወናው አለም ከ10 ዓመት በላይ ቆይተሻል። ስራ የጀመርሽው በፅሁፍ ነው ወይስ በትወና?

ጀንበር፡- የሚገርምህ ነገር የመጀመሪያ የመድረክ ስራዬን የጀመርኩት ልጅ እያለሁ በቤተክርስቲያን ውስጥ ነው። የአስር ወይም የዘጠኝ ዓመት ልጅ እያለሁ ነው፤ ደግሞ የተጫወትኩት ገፀ-ባህሪይ ስራዬ የክርስቶስ ደቀመዝሙር ሆኜ ነው። ቴአትርን የጀመርኩት ወንድ ገፀ-ባህሪይ በመጫወት ነው ማለት ይቻላል (ሳቅ) ታሪኩ የመፅሀፍ ቅዱስ ታሪክ ነው።

ሰንደቅ፡- በስራ አጋጣሚ ከነማን ጋር ሰርተሻል? በኢትዮጵያስ የት የት ተዘዋውረሻል?

ጀንበር፡- የሚገርምህ ነገር እኔ በጣም እድለኛ ነኝ። ከብዙ ሰዎች ጋር ሰርቻለሁ። በርካታ የኢትዮጵያ ክልሎችን አይቻለሁኝ። ለምሳሌ ከጋሽ መላኩ ጋር ሰርቻለሁ፤ ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ እና ኢሳያስ ግዛው ያቋቋሙት አንድነት የቴአትር ክበብ ነበርን በዛ ቡድን ውስጥ “ጥቋቁር ፀሃዮች”ን ይዘን የተለያዩ አካባቢዎችን ዞረን አሳይተናል። አንድ ነገር አምናለሁ ኢትዮጵያን እየተከፈለኝ ጎብኝቻለሁ ማለት እችላለሁ። ከሽመልስ አበራ (ጆሮ) ጋርም “የስልጣን ማደጎ” የተሰኘ ቴአትር ይዘን ዞረናል። ከጥላሁን ጉግሳ ጋር ደግሞ “ላጤ” ቴአትርን ይዘን ብዙ ከተሞች ዞረናል።

ሰንደቅ፡- የክፍለ ሀገሩ ተመልካች አቀባበል እንዴት ይገለፃል?

ጀንበር፡- በጣም ነው የሚገርምህ፤ የተለየ ፍቅር ነው የሚሰጥህ። በተለይ በቲቪ ድራማዎችና በማስታወቂያዎች የሚያያቸውን ሰዎች እዛ በአካል ሲያቸው አንዳንድ ጊዜ ሳስበው ከሚገባው በላይ መሆን የሚችል ህዝብ ነው ብዬ እንድናገር ያስደፍረኛል። አክብሮታቸውና ፍቅራቸውን ስታይ እኛ ትወናን የምንሰራወው ለእንጀራችን ብለን ሁላ አይመስላቸውም። ትወና ለኛ እንጀራችን ነው እነርሱ ግን ለእነሱ ስንል የምነሰራ እስኪመሰላቸው ነው ለእኛ የሚሰጡን አክብሮትና ፍቅር።

ሰንደቅ፡- የማትረሺው የአድናቂዎችሽ አጋጣሚ የቱ ነው?

ጀንበር፡- እኔ በጣም በሙቀት ውስጥ ነው ያለሁት (ሳቅ). . . ሙቀት እወዳለሁ። ከምንም በላይ ሰው ምንም ባያረግልህም ፈገግ ያለ ፊት ማየት መታደል ነው። አንዳንድ ጊዜ ከባለቤቴ ጋር ስንሄድ ምን ያጋጥመኛል መሰለህ ግጥም አድርገው ይዘውኝ፣ ስመውኝ፣ አዋርተውኝ ሁሉ ሲሄዱ ባለቤቴ ዝም ብሎ ቆሞ ይታዘባል። ይሄ በጣም ነው የሚያስቀኝ። ዞር ብለው ሲያዩት ይደነግጡና “በጣም ስለምንወዳት ነው” ይሉታል። “እኔም ባለቤቷ ነኝ” ብሎ እርሱም ይተዋወቃቸዋል (ሳቅ) . . . ባይገርምህ እኔ የሰው መውደድ አለኝ ። “ገመና 1” ላይ ያለችውን ገፀባህሪይ ያህል ክፉ ሆኜ ሰርቼ አላውቅም ነበር ግን በርሱም ቢሆን ብዙ ሰዎች ይወዱኛል።

ሰንደቅ፡- ጀንበር ተዋናይ ወይም ፀሃፊ ብቻ ነው መሆን የምትችይው የሚል ምርጫ ሊቀርብልሽ የቱን ትመርጫለሽ?

ጀንበር፡- ሁለቱንም እወዳቸዋለሁ። ነገር ግን አንዱን ምረጪ ብባል ወደመፃፉ የማዘነብል ይመስለኛል። ነገር ግን አንዱን ብቻ እንድመርጥ ከተገደድኩና ምርጫ አጥቼ እንጂ ትወናንም ቢሆን እንደምወደው አትርሳ (ሳቅ)

ሰንደቅ፡- እሺ ከሬዲዮ፣ ከቲቪ፣ ከፊልምና ከቴአትር ስራ አንዱን ብቻ ምረጪ ብትባይስ?

ጀንበር፡- በዚህ ላይ ያለጥርጥር የመድረክ ተውኔትን እመርጣለሁ። ምክንያቱም መድረክ የነፍስ ስራ ነው። ከተመልካቹ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝተህ ነው ደስታውንም ብስጭቱንም፣ ሳቁንም ለቅሶውንም ሆነ ጭብጨባውን ፊት ለፊት ነው የምታገኘው ስለዚህ ለኔ ቴአትር ይመረጣል።

ሰንደቅ፡- በሀገራችን ባሉ ፕሮፌሽናል መድረኮች ላይ ሁሉ ተውነሻል። ወደፊትስ ከነማን ጋር ብትሰሪ ትወጃለሽ?

ጀንበር፡- ቅጥር ባለመሆኔ ሁሉንም ቴአትር ቤቶች ዛሬ ሰርቼባቸዋለሁ። እንደዛውም ከማደንቃቸው ባለሙያዎች ጋር ሁሉ ሰርቻለሁ። ከሽመልስ አበራ (ጆሮ) ጋር፣ ከአለማየሁ ታደሰ ጋር፤ ከጀማነሽ ሰለሞን ጋር፤ ከነጋሽ ጀንበሬ በላይ ጋር፤ ከሰብለ ተፈራ ጋር ተውኛለሁ፤ ከጥላሁን ጉግሳ ጋር ሰርቻለሁ፤ ከሳምሶን ታደሰ (ቤቢ) ጋር ሁሉ ተውኛለሁ. . . አስበው አሉ ከሚባሉ ተዋንያን ጋር ከሞላ ጎደል ተውኛለሁ። ለወደፊቱ ግን በጣም የምመኘው ምን እንደሆነ ታውቃለህ፤ ጌትነት እንየሁ አዘጋጄ ሆኖ አብሬው ብሰራ በጣም ነው ደስ የሚለኝ። የሆነ አጋጣሚ ተፈጥሮ አብረን ብንሰራ በጣም የምፈልገው ምኞቴ ነው።

ሰንደቅ፡- እስካሁን ከሰራሻቸው ስራዎች ውስጥ የማትረሻት ገፀ-ባህሪይ ካለች እስቲ ንገሪኝ፤ ወደፊትስ የተለየ ልትሞክሪያት የምትፈልጊያት ገፀ-ባህሪይ አለች?

ጀንበር፡- መቼም የማልረሳቸው በጣት የሚቆጠሩ ገፀ-ባህሪያቶች አሉ። ከነዚያም ውስጥ ለምሳሌ “የስልጣን ማደጎ” ፍታሌ፤ ላይ እንደገና ደግሞ “አብሮ አደግ” ቴአትር ላይ ያላቸው የማህሌት ገፀ-ባህሪይ በህይወቴ ሙሉ አልረሳቸውም። ሁለቱ በጣም ፈታኝ ገፀ-ባህሪያት ናቸው። በዚህ ላይ አብረውኝ ይሰሩ የነበሩት ሰዎች ትላልቆች ስለነበሩ አልረሳቸውም። ለወደፊትም ቢሆን አዲስና ፈታኝ ገፀ-ባህሪይ ብሰራ እመርጣለሁ።

ሰንደቅ፡- በትወና ብዙ ሰርተሻል፤ በፅሁፍም እንዲሁ በፊልምና በቴአትር ሳይቀር ብቅ ብቅ እያልሽ ነው። በቀጣይስ ምን እንጠብቅ?

ጀንበር፡- እንደ እግዚያብሔር ፈቃድ የተለያዩ ስራዎችን ለመስራት አስባለሁ። በፅሁፉም በትውናውም ማለት ነው። በነገራችን ላይ በቅርቡ የዓለም ፀሀይ በቀለ “ወንድ አይገባም” የተሰኘ ተውኔት ላይ ወደመድረክ ተመልሼ እተውናለሁ።

ሰንደቅ፡- ጀንበር በስራዎቿ ሰዎችን ታዝናናለች፤ አንቺ በምን ትዝናኛለሽ?

ጀንበር፡- እኔም ራሴ የምዝናናው ፊልምና ቴአትርን በማየት ነው። ያለንን ጊዜ አብቃቅቼም ቢሆን አዳዲስ ስራዎችን አያለሁ፤ ስራዬ መዝናኛዬም ጭምር ነው ማለት ይቻላል።

ሰንደቅ፡- በመጨረሻ ልታመሰግኚው የምትፈልጊው ሰው ካለ እድሉን ልስጥሽ?

ጀንበር፡- “ምዕራፍ አራት” እንደመጀመሪያ ስራዬ ሳይሆን ተመልካች የሚወደው እንደሚሆን ተስፋ አለኝ። ጓደኞቼና ባለሙያዎች አይተው ሃሳባቸውን የሰጡበት ስራ ነው፤ ለዚህም አመሰግናለሁ። ስራው ተጠናቆ ላለፈው አንድ አመት አብረውኝ ለቆዩት የቴአትሩ ተዋንያኑ በሙሉ ከልብ አመሰግናለሁ። በተለይ ለአዘጋጅ ቅድስት ገ/ስላሴ ምስጋናዬ ላቅ ያለ ነው። በተለይ በተለይ ደግሞ በመጨረሻዋ ሰዓት ያገኘኋት የልጅነት ጓደኛዬ ቀለመወርቅ በቀለ ትባላለች ፕሮዳክሽን ማኔጀር ሆና አግዛኛለች እሷንም በጣም አመሰግናለሁ። በተረፈ ግን ተመልካቹ አይቶት በቅንነት የተሞላ ግልፅ አስተያየቱን እንደሚሰጠኝ እጠብቃለሁ። እናንተንም በዚሁ አጋጣሚ አመሰግናለሁ። እግዜር ይስጥልኝ

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
9407 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us