የ4 ኪሎ ማስታወሻ “ሀ እና ለ”

Thursday, 07 July 2016 14:51

 

የፊልሙ ርዕስ፡                “ሀ እና ለ”

ዳይሬክተር፡              ተሻለ ወርቁ

ደራሲ፡                      አይናዲስ በላይ

ፕሮዲዩሰር፡             የአምላክ ስራ ፕሮዳክሽን

ኤዲተንግ፡              ግሩም ፋንቱ (ቪኪ)

ኤክስኪዩቲቭ ፕሮዲዩሰር፡   አለማየሁ ቁምላቸው

ተዋንያን፡              መኮንን ላዕከ፣ ፍቃዱ ከበደ፣ ካሳሁን ፍሰሃ (ማንዴላ)፣ አዲስዓለም ጌታነህ፣ ህፃን ኢዮብ ዳዊት፣ ሉሊት ገረመው፣ ህይወት አራጌ እና ሌሎችም።

“ኪስህ ውስጥ ዳይመንድ ይዘህ ወርቅ ፍለጋ አትዙር” ይላል የፊልሙ ይዘት፤ መተሳሰብና ፍቅር፣ ይቅርባይነትና አደራ፣ ማንነትና ማህበረሰባዊነት፣ ለየቅል የሆነ ኑሮ፣ ድሮና ዘንድሮ ጭምር በገሃድ የሚታዩበት ፊልም ነው - በአይናዲስ በላይ ተፅፎ፤ በተሻለ ወርቁ የተዘጋጀው “ሀ እና ለ”

በቪኪ ፊልም ፕሮዳክሽን ተዘጋጅቶ በየአምላክ ስራ ፊልም ፕሮዳክሽን የቀረበው ይህ ፊልም ከዚህ ቀደም በሰራቸው “የባል ጋብቻ” እና “የህዝብ ነኝ” በተሰኙት ፊልሞች በሚታውቀው ተሻለ ወርቁ አዘጋጅነት የተሰራ ነው። የፊልሙ ደራሲ ደግሞ ከዚህ ቀደም “ባንቺ የመጣ” ፊልምን እንካችሁ ያለን አይናዲስ በላይ የድርሰት አቅሙን አሳይቶናል።

አራት ኪሎን መቼቱ አድርጎ የተሰራው “ሀ እና ለ” ፊልም በአንድ ቤት ውስጥ በደባልነት የሚኖሩ ወጣቶችን የግጭት፣ የቁጭትና የፍቅር ታሪክ ከማህበራዊነት ጋር በጥምረት የሚያሳይ ነው።

“ቤት ይፈርሳል ሰው ግን መቼም ቢሆን ይታወሳል” የሚል አቋም ያላቸው ጋሽ ደረጀ (መኮንን ላዕከ) በተለይም የአራት ኪሎ ነገር ቀላል እንዳልሆነ ሲጠቅሱ “የአራት ኪሎ አድባር ቀላል አይደለም” ይሉናል። በታሪኩ ውስጥም የእሳቸውና የጎረቤቶቻቸው ኑሮና ብልሃት ስላቅና ትችት የወዝ ያህል በየመሐሉ የሳቅ ፋታ ይሰጣል።

ገና ከፊልሙ ጅማሬ በከተማችን ያሉና የሀገር ታሪክ ምልክቶች የሆኑ ሀውልቶችን የሚያሳየው “ሀ እና ለ” ፊልም፤ አራት ኪሎ ደርሶ ፓርላማ ላይ ይቆማል። እናም የሁለቱ ደባሎችን ታሪክ ከግጭቱ ተነስቶ ያስተዋውቀናል።

ማን እንደሆነ የማታወቀው ሀብታም የኮሌጅ ትምህርቷን ክፍያ እና ወጪ የሚሸፍንላት ሔለን (አዲስአለም ጌታነህ) በሚታወቀው ሰው ፍቅርና ናፍቆት ትዋልላለች። በሌላ በኩል ደግሞ ዕጣ -ፈንታ ከወላጆቻቸው በወረሱት የቤት ቁጥር 119 ሀ እና ለ ውስጥ በደባልነት የሚያኖራቸው ወጣቶች በነፃነት ፍለጋና በአትቆጣጠረኝም ሰበብ ግጭታቸው ያይላል።

ከ16 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ የኖረውን ሱዳናዊ (ፍቃዱ ከበደ) ጨምሮ የአካባቢው ሰው ወጣቶቹን ለማስታረቅ የሚያደርገው ጥረት በራሱ የፊልሙ ታሪክ “ወዝ” ነው ማለት ይቻላል። የደባሏ “የት ገባሽ የትወጣሽ?” ቁጥጥር የበዛበት ሄለን በአቡሽ (ካሳሁን ፍሰሃ) የተፈቀረች በመሰላት ጊዜ በጎረምሳ ልታስቀናው ትሞክራለች። ይባስ ብሎም በደባልነት የሚኖሩበት ቤት ድረስ በኮሌጅ የምታውቀውን ጎረምሳ ይዛ ትመጣለች። ነገር ግን ደባል ሱስን እንጂ “ደባልነትን” ፈፅሞ የሚያውቀው ይህ ሰው በቅናት ተነሳስቶ አቡሽን አስደብድቦ እጁ ይሰበራል።

ይህ እንግዲህ የፊልሙን የታሪክ አቅጣጫ የሚቀይር ክስተት ይሆናል። አቡሽ (ካሳሁን ፍሰሃ) እጁ በመሰበሩ ምክንያት የአካባቢው ሰው ባዋጣለት ገንዘብ ወጌሻ ጋር ሄዶ ይታሻል። ዳሩ ግን በእድሜ የገፉት ወጌሻ ስብራቱን የተሻለ እንዲታከም በሚል የልጅ ልጃቸውንና የሶስተኛ አመት የስነ- ማህበረሰብ (ሶሾዮሎጂ) ተማሪዋን አስከትለው በቤቱ ይመጣሉ። ወጣቷ ከወጌሻነት አልፋ የጥሩ ወዳጅነት መስመር መግባቷን የተመለከተችው የአቡሽ ደባል ሔለን በተራዋ ቅናት ያንገበግባታል።

እርሱ ልበሰፊና የአካባቢው ሰው እንደሚጠራው ሆደ ቡቡ ነው። እናም በቤቱ ግድግዳ ላይ፣ “ስላደረክልኝ ሁሉ አመሰግንሃለሁ” እና “እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን” የሚል የቅዱስ መፅሐፍ ጥቅሶችን ስናነብ፤ በአንፃሩ በሔለን በኩል ያለው የግድግዳ ላይ የተለጠፈው ጥቅስ የሚከተለው ነው።

“በሲጋራ ማጨስ ብዙ ገንዘብ ያልቃል

መቃጠል ያማረው ደባል ይቀመጣል”

የቅናት ፈረስ የሚጋልባት ሄለን የወጣቷን ወጌሻ የሊሊን (ሉሊት ገረመው) ወደቤታቸው መመላለስ ለማስቀረት ከኮሌጅ ወዳጇ ጋር የወጠኑትን ሰይጣናዊ ሴራ እርሷን ማስገደል ይሆናል። “የቆጡን አውርድ ብላ የብብቷን ጣለች” እንዲሉ ለወጌሻዋ የተላከው ነፍሰ-ገዳይ ሰባራ ደባሏን ወግቶት ይሰወራል።

አብሮ ለመኖር በቂ ምክንያቱ ፍቅር ብቻ ነው የሚለው “ሀ እና ለ” ፊልም፤ በገፀ-ባህሪያቱ ህይወትና ስሜት ውስጥ ኑሯቸውን፣ ሃሳባቸውን፣ ምኞታቸውን፣ ፀፀታቸውንና ይቅርታቸውን በታሪክ ፍሰቱ ቅደም ተከተል ውስጥ ያሳየናል። እናም ከቤቷ የተቀመጠውን አልማዝ ማየት የተሳናት ወጣት፤ ወርቅ ፍለጋ ወደ ውጪ ስትማትር የሚያጋጥማትን ክስተት እነሆ ይለናል።

በፊልሙ ውስጥ ምናልባትም እንደህፀፅ ሊነሳ የሚችል ሁለት ክስተቶች አሉ። አንደኛው በሩሩህነቱና በታጋሽነቱ፤ በመልካምነቱና በሴት አክባሪነቱ የሚታወቀው አቡሽ (ካሳሁን ፍሰሃ) ድንገት በአጋጣሚ ሊሊ (ሉሊት ገረመው) “ሔለንን የሴት ልጅ ብዬ ሰድቤያታለሁ” በማለቷ ብቻ ሁላችንም የሴት ልጅ ነን በሚል ስሜታዊነት፤ በእኩለሌሊት ከቤቱ ማባረሩ ምክንያታዊነት ይጎድለዋል። ሴትን እወዳለሁ እያሉ፤ ሴትን አከብራለሁ እያሉ፤ ሴትን ለአደጋ መዳረግ አያስኬድም። ነገር ግን ከገዳይዋ ለማስመለጥ ታስቦ ከሆነም ሌላ መንገድ ያሻል ባይ ነኝ።

ሁለተኛው በታሪኩ አሳማኝ ያልሆነ ክስተት የገንዘቡ ምንጭ አለመታወቁ ነው። በድህነት አብሯት የሚኖረው ሰው ምን እንደሚሰራ ሳይታወቅ፤ የገቢ ምንጩ ሳይነገረን ከትምህርት ክፍያ አልፎ የሚተርፍ ወጪ እስከመሸፈን መድረሱ የታሪኩን ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ይሆናል። 

በተረፈ ግን “ሀ እና ለ” ፊልም ታሪካችንን፣ ዘመናችንን፣ ኑሯችንን፣ ቀልድና ቁምነገራችንን ሁሉ በድሮና ዘንድሮ ባለታሪኮች ኑሮ ውስጥ የሚያስመለክተን አዝናኝ የፍቅር ታሪክ ነው ማለት ይቻላል። ከዚህም ባለፈ በብዙ የአገራችን ፊልሞች እና የቴሌቭዥን ድራማዎች ከምናያቸው የተቀናጣ ኑሮ ላይ ትኩረት ከሚሰጡ ትዕይንቶች በተቃራኒው ሆኖ  ነው ያገኘሁት። “ሀ እና ለ” ፊልም የብዙሃኑን ኢትዮጵያዊያን ኑሮ የሚወክል ፊልም ነው ማለት ይቻላል። የመልካም የመዝናኛ ሳምንት ይሁንላችሁ!!!  

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15024 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 130 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us