ቀይና ነጭ ሽብር የወለደው፤ “የነገን አልወልድም”

Thursday, 14 July 2016 15:47

 

የፊልሙ ርዕስ - “የነገን አልወልድም”

ዳይሬክተር - አብርሃም ገዛኸኝ

ፀሐፊ - ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ)

ፕሮዳክሽን - ፎርሞድ መልቲሚዲያ ፕሮዳክሽን

መብራት - ደረጀ ወ/ማሪያም፣ ዳንኤል ባዩ፣ ሚሊየን ካሳሁን

ድምፅ - ብሩክ አየለ

ገፅ ቅብ - ፅጌረዳ ወንድምአገኝ

ሙዚቃ - ታደለ ፈለቀ

ቪዥዋል ኢፌክት - ናሆም ግርማ

ተዋንያን - ብርሃኑ ድጋፌ፣ ተስፋዬ ይማም፣ ህይወት ግርማ፣ በሃብቱ ፈቃዱ፣ ዲና ወንደሰን፤ ሔኖክ መኩሪያ እና ሌሎችም

 

የመፅሐፍት ታሪክን ወደፊልም በመቀየር ስሙን የተከለው ዳይሬክተር አብርሃም ገዛኸኝ እነሆ ከአዳም ረታ የ“ሎሚ ሽታ” ፊልሙ በመቀጠል የታዋቂውን የስፖርት ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) መፅሐፍ “ኢህአፓ እና ስፖርት”ን መነሻ አድርጎ “የነገን አልወልድም” የተሰኘ ጭፍግ ኮሜዲ ዘውግ ያለውን ፊልም ይዞልን ቀርቧል። በአገራችን የሲኒማ ታሪክ ከመፅሐፍት የወጡ ፊልሞችን ስናስታውስ “ቃል ኪዳን” (ጌታቸው ደባልቄ)፣ “ግርዶሽ” (ሲሳይ ንጉሱ)፣ “የትሮይ ፈረስ” (አሳምነው ቢረጋ) ይጠቀሳሉ።

አሁን ወደዛሬው ትኩረታችን እንመለስ፤ ምንም እንኳን ፊልሙ ለዕይታ ከበቃ ወራት ቢቆጠሩም የሲኒማ ቤት ቆይታው ግን በርካታ የፊልም ባለሙያዎች ከመነሻው እንደገመቱት/ እንደጠበቁት ሳይሆን ቀርቷል። ብዙ መቆየትና ብዙ መታየት የሚችል ፊልም ነበርና “የነገን አልወልድም” ፊልም በአሁኑ ወቅት ዘወትር ሐሙስ በኢትዮጵያ ሲኒማ እየታየ ይገኛል። ፊልምን ከንግግር ይልቅ በድርጊት ማሳየት ከሚችሉ ጥቂት የሀገራችን ወጣት ዳይሬክተሮች መካከል ስሙ እየገነነ የወጣው አብርሃም ገዛኸኝ በዚህም ስራው በተለየ መልኩ ካሜራውና አይናችን በአበጀዲው ትዕይንቶች ላይ እንዲናበቡ ብዙ መልፋቱ ያስታውቃል።

 

 

አዬ አንተ ጊዜ፣ የእግዜር ታናሽ ወንድም

የዛሬን ማርልኝ፣ የነገን አልወልድም።

ስላስባለው የአገራችን የአንድ ወቅት ክስተት ውበት ባለው መልኩ አስመልክቶናል። . . . በእግር ኳስ አሰልጣኝነቱ የሚታወቀው አዱኛ (ብርሃኑ ድጋፌ) ከፖለቲካ ሸሽቶ የወቅቱን ወጣቶች በስፖርት ለመግራት በሚያደርገው መታተር ውስጥ ከአብዮቱ ግራና ቀኝ በተሰለፉ ወጣቶች ሳቢያ ሲናወጥ እናያለን፡ “ደህና ጊዜ እስኪመጣ ስፖርቱን ተወት ብታደርገው” የምትለው እርጉዝ ባለቤቱ ሌንሳ (ዲና ወንደሰን) “ካልደረስኩባቸው አይደርሱብኝም” በሚል አቋሙ የፀናው አዱኛ ያላሰበው ነገር ይገጥመዋል።

“ለአስራሁለት አናርኪስት 36 ጥይት እንዴት ታባክናላችሁ? አብዮቱ ብክነት አይፈልግም” የሚለው የአካባቢው ሊቀመንበርና ወታደር ጓድ አስታጥቄ (ተስፋዬ ይማም) የወቅቱን የወጣቶች ህይወት ዋጋ እና የጥይት ዋጋ በንፅፅር የሚያሳየን ይሆናል።

በሌላ በኩል ተፈላጊው የኢህአፓ አባልና ጎበዙ ተጫዋች እስክንድር (በሀብቱ ፈቃዱ) ለርሱ የመጣው ዳፋ ከእህቱ አልፎ ለቡድኑና ለጓደኞቹ የቅጣት ምክንያት ሲሆን ፊልሙ ያሳየናል። ወንድሟ ያለበትን አድራሻ እንደማታወቅ የምትናገረው የእስክንድር እህት ቴሬዛ (ህይወት ግርማ) ባሏን ፊቷ ሲገደል ከማየቷም ባሻገር በእስር ቤት የድብደባ ቆይታዋም እንዲያስወርዳትና የበለጠ ስቃይ ሲገጥማት ማየቱ የወቅቱን ስቃይና እንግልት ለማጽናት ተጠቅሞበታል።

“የነገን አልወልድም” ፊልም የአገራችንን የአንድ ነበልባል ወቅት ታሪክ ተንተርሶ የወጣቶችን ስሜትና ይናፍቁት የነበረውን የተሻለ ጊዜ በቀይና ነጭ ብርሃን (ቀለም) የሚተርክ ፊልም ነው። በሰራተኞቹ፣ በጓደኛሞች፣ በአከራዮችና በመሀል ሰፋሪዎች መካከል የነበረውን አለመተማመንና ጥርጣሬ በጉልህ አሳይቶናል።

ፊልሙ በተለየ መልኩ በጥቁርና ነጭ ምስል መቅረቡ፣ በተለይም የቀይ እና የነጭ ቀለም ብቻ ደምቆ በጉልህ እንዲታይ መደረጉ የሁለቱን ፖለቲካዊ ጎራዎች ለማጉላት ያለመ ይመስላል። . . . ከዚህም በላይ የወቅቱ ትናንሽ ባለስልጣናት የነበራቸውን ትላልቅ ጉልበት ፊልሙ ደጋግሞ ያሳያል።

“የነገን አልወልድም” ፊልምን ጭፍግ ኮሜዲ ከሚያስብሉት የታሪኩ ፍሰቶች መካከል ጥቂቶችን ለመጥቀስ ያህል እነሆ። ከላይ ለመጠቆም እንደሞከርኩት ከሰው ልጅ ህይወት በላይ አንዲት ጥይት ምን ያህል ዋጋ እንደነበራት መስማት መራር ስላቅ ነው። በሌላም በኩል ዘመኑ የደረሰበትን የፎቶ ቴክኖሎጂ ሲያስታውሰን፣ ለመታወቂያ የሚሆን ፎቶ ለመነሳት ከአሰልጣኙ ጋር ወደፎቶ ቤት የሄደው እስክንድር አስቸኳይ ብሎ የተነሳው ፎቶ “በሶስት ቀን ውስጥ በአስቸኳይ አደርስልሃለሁ” መባሉን ስንሰማ መቼም የዛሬ ሰው በወቅቱ ላይ መሳቁ አይቀርም። በሌላም በኩል የኑሮ ውድነትን ለማሳየት “በስሙኒ” ላይ የሚወርደውን የምሬት ውርጅብኝ በፊልሙ ውስጥ ማየት በራሱ ወይ ጊዜ የሚያሰኝ ነው።

“ዘጠኝ ሞት መጣ ቢሉት አንዱን ግባ በለው” እያለ ከጓደኞቹ ጋር ሲፎክር የምናየው አዱኛ፤ በአብዮቱ ጠባቂዎች የሚያመሽበት መጠጥ ቤት ድረስ ተፈልጎ ሲገኝ የሚያሳየው መርበትበት ምንም እንኳን የተጋነነ ቢመስልም ሳቅ የሚያጭር ነበር ማለት ይቻላል። ተጨማሪ አስቂኝ ትዕይንት ሊባል የሚችለው እስረኛ ተጫዋቾች ፈርመው በወታደርና በሲቪል ለባሾች እየተጠበቁ ወደሜዳ መግባታቸው ነው።

በአራት ምዕራፎች ተከፋፍሎ የቀረበው “የነገን አልወልድም” ፊልም በስተመጨረሻም ጥቆማ (ትንቢት) በሚመስል መልኩ የቀይ ሽብር አፋፋሚዎቹ በቡድን ተከፍለው በኳስ መልክ ያሳየናል። “የመቻል ቡድን” እና “አብሪ ኮከብ ቡድን” በሚያደርጉት ጨዋታ በስተመጨረሻ የወቅቱን የአብዮት ግለት የት እንደደረሰ ማሳያ ነበር። እናም ወቅቱ “መሐል ሰፋሪ መሆን በሁለት ጥይት እንደሚያስመታ" ከማስታወሱም በተጨማሪ የጭካኔውን መጠንና የስርዓት አልበኝነቱን መንደር በጉልህ አሳይቷል። በተረፈ ፊልሙ የታሪኩን መቼት ጠብቆ ዘንድሮን አስረስቶ ድሮን ቁልጭ የሚያደርግ ከመሆኑም ባሻገር የተዋንያኑ አተዋወንና አልባሳት ለተመልካች አንዳችም የማይጎረብጥ ነው ማለት ይቻላል።

ዳይሬክተሩ አብርሃም ገዛኸኝ መሰል ትርጉም ያላቸው የመፅሐፍት ታሪኮችን በሲኒማው በኩል እየደጋገመ ያሳየን ዘንድ ምኞታችን ነው። ምክንያቱም ይህ የእርሱ መለያ (ብራንድ) እየሆነ የመጣ የፊልም ቴክኒኩ ሆኗልና። አሁን ላይ በሀገራችን ብዙ ትኩረት ያልተሰጠው ይህ ፊልም በአምስት ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫሎች ላይ ተቀባይነት አግኝቶ ለውድድር እንደቀረበም ሰምተናል። መልካም የመዝናኛ ሳምንት!!!

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
549 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us