“በኢትዮጵያ ውስጥ ዋነኛው ችግር ፊልም ዕውቀት እንደሚያስፈልገው አለማወቅ ነው”

Wednesday, 20 July 2016 14:04

 

አቶ ዕቁባይ በርኽ

የዶን ፊልም ፕሮዳክሽን ካምፓኒ ሥራ አስኪያጅ

 

አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጠው የፊልም ፕሮዳክሽን የትምህርት ዘርፍ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሰርተው ከተመረቁት ተማሪዎች መካከል አቶ ዕቁባይ በርኽ አንዱ ናቸው። ባለፉት ሃያ ዓመታት በኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብ ሥራዎች እና እድገቶች ላይ አሻራቸውን ካስቀመጡት ባለሞያዎች መካከል ተጠቃሽ ከመሆናቸውም በላይ፤ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በየሳምንቱ እሁድ ዕለት ይተላለፍ የነበረውን “ገመና” የቴሌቪዥን ድራማን ፕሮዲውስ ማድረጋቸው ከተመልካቹ ከፍተኛ ተቀባይነት ያስገኘላቸው ስራ ነው።

አቶ ዕቁባይ የሜጋ ኪነ-ጥበባት ማዕከል ዋና ሥራ አስኪያጅ በነበሩ ወቅትም፣ በሕዝብ ዘንድ አይረሴ የሆነውን የ“አንቲገን” ቴአትርን ለሕዝብ ተዳራሽ እንዲሆን አድርገዋል። በመጽሐፍ በኩልም “ቆንጆዎቹ” እንዲሁም በስነ-ግጥም የዮሐንስ እና የደበበ ሰይፉ ግጥሞች በመጽሐፍ መልክ እንዲቀርቡ ከፍተኛ ድርሻ ነበራቸው።

በአሁኑ ወቅት የዶን ፊልም ፕሮዳክሽን የተሰኘ ካምፓኒ በማቋቋምና በስራ አስኪያጅነትም እየመሩ ይገኛሉ። አቶ እቁባይ በርኽ በፊልም ፕሮዳክሽን የማስተርስ ዲግሪያቸውን ባገኙበት ዕለት፤ ልጃቸው ምህረት ዕቁባይም ከዚያው ዩኒቨርሲቲ ከሕግ ትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ዲግሪዋን በማዕረግ አግኝታለች። ከአቶ ዕቁባይ ጋር በተመረቁበት ትምህርትና በስራዎቻቸው ዙሪያ ተከታዩን ቆይታ አድርገናል።

ሰንደቅ፡- በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፊልም ፕሮዳክሽን ትምህርት ይዘቱ ምን ላይ ያተኮረ ነው?

አቶ ዕቁባይ፡-አጠቃላይ ይዘቱ ፊልም በማምረት ላይ የሚቀመጥ ነው። በፊልም ማምረት ሂደት ውስጥ አስፈላጊ ግብዓቶች ናቸው የሚባሉትን ተምረናል። ለምሳሌ ከሚካተቱት መካከል፣ ሲኒማቶግራፊ፣ የፊልም ስክሪብት አፃፃፍ፣ የካሜራ ቋንቋ፣ የመብራት ቴክኒኮች፣ የአርት ዳሬክቲንግ ሥራዎች እና ሌሎች ከፊልም ፕሮዳክሽን ጋር ተያያዥነት ያላቸው ኮርሶችን ወስደናል። አጋዥ ኮርሶችም ለምሳሌ የምርምር ሜቴዶሎጂ፣ የአእምሮ ጥበቃ እንዲሁም አጫጭር የተግባር ሥራዎችን ሰርተናል። በተጨማሪም፤ ከካናዳ፣ ከብራዚል፣ ከፈረንሳይ እና ከእንግሊዝ በርካታ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች እውቀታቸውን አካፍለውናል። ስለኮምፖዚሽን ስንማር ስዕል ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ መምህራን እውቀት አጋርተውናል። ስዕል፣ ፎቶግራፍና ፊልም በጣም ተያያዥነት ያላቸው ነገሮች ናቸው። በአጠቃላይ ፊልም ማምረት ምን እንደሆነ ተምረን ወጥተናል።

ሰንደቅ፡- ባለፉት ሃያ ዓመታት በኪነ-ጥበቡ ዘርፍ በኃላፊነትም የተለያዩ ሥራዎችን በማዘጋጀት አልፈዋል። ከዚህ አንፃር አሁን በተማሩት የሁለተኛ ዲግሪ ምን አዲስ ግብዓት የሚሆን ነገር አገኙበት?

አቶ ዕቁባይ፡- በመጀመሪያ ለሀገራችን አዲስ የትምህርት ዘርፍ በመሆኑ ይህንን የሚያቋቁመው አካል የራሱ የሆነ ግብ ይኖረዋል። አንድ ነገር ሲቋቋም ለማቋቋም የሚያስፈልገው የገንዘብ አቅም ብቻ ሳይሆን መሰረታዊ የሆኑ ዕውቀቶችም ያስፈልጉታል። ከፖሊሲ አውጪው እስከ ባለሙያው ድረስ ያለው የእውቀት መሰረት ማለት ነው። በዚህ መካከል የተወሰነ የዕውቀት ክፍተት ሊኖር ይችላል። ሙሉ ዕውቀትም ይዞ ቢጀመር የተወሰኑ ክፍተቶችም አይጠፉም።

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እኔ ልምድ ካላቸውም እውቀት ካዳበሩ ሰዎች ጋር አብሬ ሰርቻለሁ። የሺዋዚንገር ፊልሞችን ዳይሬክት ካደረገ ባለሙያም ጋር ሰርቻለሁ። ይህም በመሆኑ አንዳንዶቹ ለምን ትማራለህ ሲሉም ጠይቀውኛል። የተማርኩት ግን በሁለት ምክንያቶች ነው። አንደኛው፣ በቀጥታ ስክሪፕት ፅፌ ካሜራ ይዤ የተሳተፉኩበት ሥራ የለም። ስለዚህም በቀጥታ ተሳታፊ በመሆን መስራት ስለምፈልግ ነው። ሁለተኛው፣ በተለምዶ ከማውቃቸው የፊልም ቋንቋዎች ከፍ ባለ ደረጃ ፕሮፌሽናል የፊልም ቋንቋዎችን ማወቅ አስፈላጊ ነው የሚል እምነት ስላለኝ ነው። በርግጥም መማር ከፍተኛ የሆነ የአቅም ልዩነት ይፈጥራል። ለምሳሌ አንድ የካሜራ ሹት (ቀረፃ) ለማድረግ የሚስችል እውቀት አግኝተናል። ይህም ሲባል አንድ ሹት ለመውሰድ የምትመርጥባቸው ብዙ ሁኔታዎች መኖራቸውን አውቀናል። ከዚህ በፊት ፕሮዲውሰር በመሆን ነበር አብዛኛውን ጊዜ የሰራሁት። አሁን ላይ ዳይሬክተር ለመሆን፣ ስክሪፕት ፀሐፊ ለመሆን እንዲሁም የፊልም ኮምፖዚሽን እና አጠቃላይ የአርት ዳይሬክተር ለመሆን እድል አግኝተናል። በተጨማሪም ከዓለም አቀፍ የፊልም ባለሙያዎች ጋር ሊያግባባን የሚችል የፊልም ሙያዊ ቋንቋ አውቀናል። በልምድ ያገኘናቸውን በባለሙያ አይን ተመልሰን እንድናያቸው አስችሎናል። የሚነበቡ መጽሐፎች፣ የሚጎበኙ ድረገፆች፣ ፕሮዳክሽን ኩባንያዎች የት እንደሚገኙ ለማወቅ ችለናል።

ሰንደቅ፡- ከፊልም ታሪኮች አመጣጥ እና መነሻዎች ምን አይነት ግንዛቤ ወስዳችኋል?

አቶ ዕቁባይ፡- ትምህርት ስንጀምር ስለፊልም ታሪኮች አስቤ አላውቅም። የፊልም ታሪኮችን ስንማር ግን ፊልም እንዴት ተጀመረ? ቴክኖሎጂው እንዴት እያደገ መጣ? ገበያው እንዴት ነው? ሥርጭቱስ ምን ይመስላል? የፊልም ኤዲቲንግ እንዴት ተጀመረ? የት ሀገር ተጀመረ? ምን ችግሮች ገጥመዋቸው ነበር? የፊልም ፊሎሶፊዎች (ፍልስፍናዎች) እንዴት ናቸው? የሆሊውድ ፊልሞች፣ የሩሲያ ፊልሞች፤ የፈረንሳይ ፊልሞች፤ የኢትዮጵያ ፊልሞች እንዴት ናቸው? እነዚህን መሰረታዊ ዕውቀቶች ስታገኝ ስለፊልም ያለህ እውቀት ሙሉ ይሆናል።

ሰንደቅ፡- በኢትዮጵያ ፊልሞች ውስጥ በብዛት የሚታየው ችግር አንድ ግለሰብ፣ ፕሮዲውሰር፣ ስክሪፕት ፀሐፊ፣ ዳይሬክተር፣ አክተር፣ ኤዲተር አንዳንዴም የካሜራ ባለሙያ የሚሆንበት አሰራር ነው። እነዚህን አይነት ችግሮች ከመቅረፍ አንፃር ምን የምታበረክቱት አስተዋፅዖ ይኖራል?

አቶ ዕቁባይ፡- በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ግለሰብ ፕሮዲውሰር፣ ስክሪፕት ፀሐፊ፣ ዳይሬክተር፣ አክተር፣ ኤዲተር ለምን ሆነ የሚለው አይደለም መሰረታዊ ችግሩ። አሁን ያለው አካሄድ እንደውም በአብዛኛው ሥራዎች በተወሰኑ ሰዎች የሚሰራበት ሁኔታዎች ናቸው ያሉት። በኢትዮጵያ ውስጥ ዋነኛው ችግር ፊልም እውቀት እንደሚያስፈልገው አለማወቅ ነው። አንዳንዴ አንድ የሰርግ ፕሮግራም የቀረጸ ግለሰብ ፊልም ሲያዘጋጅ ታገኘዋለህ። ፊልም በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ኢንዱስትሪ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። በእኛም ሀገር ውስጥ በእውቀት እና በእውቀት ላይ ብቻ የተመሰረተ የፊልም ኢንዱስትሪ እንዲኖር መስራት ይጠበቅብናል። አውቀን ወደ ኢንዱስትሪው መቀላቀል ያለብን።

ከፈጣሪ የተሰጠኝ ስጦታ ነው ወይም እንቶኔ እጣፈንታዬ መሆኑን ነግሮኛል ማለት ብቻውን አዋጪ አይደለም። ከፈጣሪም የተሰጠ ሆነ በሰዎች የተነገረ ስጦታም ቢሆን ወደ ትምህርት ገበታ መግባት አስፈላጊ ነው። ወደ ምርምር መግባትም በጣም አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ “ገመና” የቴሌቪዥን ድራማ በምናዘጋጅነት ጊዜ የገጠመን ችግር የተለያዩ ዳይሬክተሮች ይመጣሉ የተለያዩ ነገሮችን ይሰነዝራሉ። በዚህ በመቸገሬ ስለፊልም ዳይሬክቲንግ የሚያስተምር መጸሐፍ በማስመጣት ወደ ንባብ ውስጥ ገባሁ። በተለምዶ የሚነገረን የዳይሬክቲንግ ስራዎች በመጽሐፎች ከሰፈረው ፈጽሞ የተለየ ነው። የፊልም እውቀቶችን ማወቅ መሰረታዊ መሆኑን ግንዛቤ ያገኘሁት በዚያን ጊዜ ነበር። አሁን ደግሞ ስንማረው የበለጠ አስፈላጊ መሆኑን ተረድቻለሁ። ስለዚሀም በእውቀት እና በእውቀት ብቻ የሚመራ የፊልም ኢንዱስትሪ መገንባት እንዳለብን ግንዛቤ መወሰድ አለበት።

ሰንደቅ፡- የፊልም ፕሮዳክሽን ውጤታማ የሚሆነው እንዴት ነው?

አቶ ዕቁባይ፡- የአንድ ፊልም ፕሮዳክሽን ውጤታማነት የሚወሰነው በሚዋቀረው ክሩ (የፊልሙ አባላት) ነው። ይህም ሲባል፣ ምርጥ ሲኒማቶግራፈር፣ ስክሪፕት ፀሐፊ፣ አርት ዳይሬክተር፣ ካሜራ ማን፣ ካስቲንግ ዳይሬክተር፣ ሙዚቃ አዘጋጅ በክሩ ውስጥ ማካተት ከተቻለ ተመጋጋቢ እና ተደማሪ የፊልም እውቀት ማግኘት ስለሚያስችል ከጅምሩ የፊልም ፕሮዳክሽኑ ውጤታማ ይሆናል። ከዚህ ውጪ በአንድ ግለሰብ ወይም በሁለት ሶስት ሰዎች የሚዘጋጁ ፕሮዳክሽኖች ብዙውን ጊዜ ውጤታማ አይሆኑም። በነገራችን ላይ አንድ ሰው ምርጥ ዳይሬክተር ነው የሚባለው፣ ምርጥ ባለሙያዎችን መለየትና ማዋቀር ሲችል እንዲሁም ባለሙያዎቹ ለስራ እንዲነሳሱ ማነቃቃትና መምራት የሚያስችል እውቀት ሲኖረው ነው።

ሰንደቅ፡- በኢትዮጵያ ውስጥ ከመድረክ ቴአትሮች እስከ ፊልሞች ድረስ ተመሳሳይ ግለሰቦች በተለያዩ ገጸባህሪዎች የሚቀርቡበት ተደጋጋሚ አሰራር ይስተዋላል። ሙያው በተወሰኑ ሰዎች በሞኖፖል የተያዘ ነው። በእውቀት ላይ የተመሰረተ ኢንዱስትሪ መገንባት አለበት ከተባለ፣ አንዱ እውቀት መሆን ያለበት ለፊልም ትወና ብቃት ያላቸውን ወጣቶች መለየት ነው። በዚህ ላይ የእናንት አስተዋፅዖ ምን ሊሆን ይችላል?

አቶ ዕቁባይ፡- አንዱ የፊልም ኢንዱስትሪ ውጤታማነት መመዘኛው የትወና ብቃት ያላቸውን ወጣቶች አስሶ ማግኘት ነው። “ክሩ ዴቬሎፕመንት” ላይ ሲሰራ ነባሮች ምን ይሰጡናል? ወጣቶች እነማን አሉ? የሚለውን መመለስ ያስፈልጋል። ክህሎቶች ማሰስና ማግኘት በጣም ጠቃሚ ሥራ ነው። እዚህ ላይ ግን መታወቅ ያለበት ወጣቶችን ማብቃት ወይም ክህሎታቸውን ማሰስ ሲባል በተለምዶ አባባል የቀረበ አቀራረብ አይደለም። የፊልም ፕሮዳክሽን አንዱ የሥራ ክፍል ስለሆነ ነው። ውጤታማ ለመሆን ከፈለግን ምርጥ ባለሞያዎችን ማግኘት የግድ ነው።

በትወናው አለም ስኬታማ የሆኑ አክተሮች እንዲሁም ዳሬክተሮች አብዛኛዎቹ በዲግሪ ወይም በማስተርስ የተመረቁ አይደሉም። ሆኖም በተዘረጋላቸው መሰረተ ልማት ከፍተኛ ባለሞያዎች ለመሆን በቅተዋል። ምክንያቱም መሰረተ ልማቶቹ የሚመሩት በባለሙያዎች በመሆናቸው ነው። ስለዚህም ኢንዱስትሪው የወጣቶችን ክህሎቶች አስሶ የሚያገኝ ብቻ ሳይሆን የሚያበቃም መሆኑ መቻል አለበት። እኛም በተማርነው ትምህርት በመታገዝ ወጣቶችን ወደ ኢንዱስትሪው ለማምጣት ማገዝ እንችላለን።

ሰንደቅ፡- የፊልም ኢንዱስትሪው የወደፊት ተስፋ እንዴት ይገልፁታል?

አቶ ዕቁባይ፡- የፊልም ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ገንዘብ አፍስሰህበት ከፍተኛ ገንዘብ የምታገኝበት መሆኑን ተምረናል። ለምሳሌ ለአንድ ኮርስ ማሟያ የጥናት ፅሁፍ ሰርቼ ነበር። ለጥናት የመረጥኩት ፊልም ርዕስ “The Sound of Music” የሚለውን ነበር። ማን ሰራው? እንዴት ሰራው? ምን ያህል ገንዘብ ፈጀ? ምን ያህል ገንዘብ አስገባ? የሚለውን ተመልክቼው ነበር። ፊልሙ በጣም ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘ ነው። ፊልሙ የተሰራው ኦስትሪያ ውስጥ ሳልስበርግ በሚባል ከተማ ነው። በዚህ ከተማ ውስጥ የሚኖረው የህዝብ ብዛት 130ሺ ናቸው። ፊልሙ የተቀረጸበትን ከተማቸውን ለመጎብኘት በዓመት የሚመጣው የሰው ብዛት ግን 450ሺ ነው። ስለዚህም ይህ ፊልም የወጣበትን ወጪ ሸፍኖ፣ ከፍተኛ ገቢ ተገኝቶበት እንደሀገርም ከፍተኛ የቱሪስቶች መዳረሻ ለመሆን የበቃ እና በየአመቱ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ ሥፍራ ለመሆን በቅቷል። ሥፍራው ላይ ጎብኝዎች ሲደርሱ የሚቀበሏቸው “The Sound of Music” የሚባሉ አውቶብሶች አሉ። ወደሥፍራው አውቶብሶቹ ሲንቀሳቀሱ ከየትኛውም ዓለም የመጣ ቱሪስት “The Sound of Music” የሚለውን ዘፈን እየዘፈነ ይጓዛል። ድንበርና ባሕልን የተሻገረ ፊልም ነው።

ስለዚህም ፊልም ምን ያህል ሃይል እንዳለው አውቀናል። ፊልም የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ የሚያግዝበት መንገድ ብዙ መሆኑን ተረድተናል። ሌሎች ሀገር የደረሱበት ለመድረስ ብዙ መስራት እንዳለብን አውቀናል። ሆኖም ግን የፊልም ኢንዱስትሪው ተስፋው እንደተሟጠጠ አድርገን የወደፊቱን የምንናገርለት ሳይሆን ገና ያልሰራንበት ብዙ ዕድሎች ያሉት “ሴክተር” መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።

ሰንደቅ፡- የኢትዮጵያ ፊልም ለማደግ ተስፋ አለው እያሉ ነው። ተጨማሪ ማሳያዎች ምንድን ናቸው?

አቶ ዕቁባይ፡- በተለያዩ ሲኒማ ቤቶች የኢትዮጵያ ፊልሞች ከፍተኛ ተመልካች እንዳላቸው መመልከት ይቻላል። ይህ በራሱ አሁን ካለው የተሻለ ሥራዎች ቢቀርቡ ተመልካቹን ለማግኘት ያለው እድል ከፍተኛ መሆኑ ያሳያል። በርግጥ በተመልካች ሰልፎች ብቻ ለውጥ ይመጣል ብሎም መጠበቅ አይቻልም።

የፊልም ኢንዱስትሪውን መንግስት ሊመራው ይገባል። የፊልም ፖሊሲ መውጣት አለበት። የፊልም ፕሮዳክሽን ትምህርት መንግስት መክፈቱ የሚያስመሰግ ነው። እውቅናም የሚሰጠው ተግባር ነው። ተጠናክሮም መቀጠል አለበት። ሌላው መነሳት ያለበት ስለማንዴላ ፊልም በአዲስ አበባ ውስጥ ለሚካሄድ ቀረፃ 5 ሚሊዮን ዶላር ተመድቦ ነበር። ከዚህ ውስጥ 1 ሚሊዮን ዶላር እንኳን መጠቀም አልተቻለም። ምክንያቱ ደግሞ ቀረፃውን ለማከናወን የሚያስፈልጉ መሣሪያዎች በኪራይ መልክ እንኳን በአዲስ አበባ ውስጥ ማግኘት ባለመቻሉ ነው። ለፕሮፌሽናል ፊልም የሚሆኑ መሣሪያዎች የሉም። ምክንያቱም ደግሞ በመሣሪያዎቹ ላይ የሚጣለው ግብር በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ነው። በዓለም ላይ ለፊልም ስራ ተመራጭ አየር ካላቸው ጥቂት ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን ከግምት ወስዶ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል።

ሰንደቅ፡- መንግስት ማበረታቻ ከማይሰጣቸው ዘርፎች አንዱ የፊልም ኢንዱስትሪው ነው። በዚህ ላይ ምን አስተያየት አልዎት?

አቶ ዕቁባይ፡- ከላይ ላስረዳህ የፈለኩት አሁን ስላነሳኽው ጉዳይ ነው። በጣም በሚገርም መልኩ በዓለም ላይ ፊልም የተሰራበትን አንድ ሥፍራ ለመመልከት ከሚመጡ ጎብኝዎች ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ የሚያገኙ ሀገሮች አሉ። ስለዚህም በፊልም ኢንቨስትመንት ላይ ማበረታቻዎች መደረግ አለባቸው። የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት እና የዓለም አቀፉ አእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት በጋራ ያጠኑት ጥናት እንደሚያሳየው ከአመታዊ ገቢ 4 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆነው ከአእምሮ ንብረት ጥበቃ የተገኘ ነው። መጠነኛ የፖሊሲ ለውጥ ቢደረግ ከፍተኛ ገቢ ሊያመጣ እንደሚችል አመላካች ነው።

ሰንደቅ፡- በቅርቡ ለእይታ የበቃው ቃና የቴሌቪዥን ጣቢያ በኢትዮጵያ ፊልሞች ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተፅዕኖ ይኖር ይሆን?

አቶ ዕቁባይ፡- በርግጥ ተፅዕኖ ይኖረዋል። ተጠያቂ ማድረግ ግን አንችልም። ምክንያቱም እኛ ባልሰራነው የቤት ስራ ክፍተት የመጣ በመሆኑ ነው። በግሎባላይዜሽን ዘመን ውስጥ ስለምንገኝ ብንፈልግ እንኳን ልናስቀረው አንችልም። በፖሊሲም ልናግደው አንችልም። ቃናን ማስቀረት ካለብን በጠንካራ ስራዎች ተወዳድረን ማስቀረት ብቻ ነው። ከግለሰቦች ጋር ሳይሆን በሀገር ደረጃ ነው ብቁ ሆነን መወዳደር ያለብን። አንዳንዴም አንዳንድ ነገሮች እንደፋሽን ይወሰዳሉ። በጊዜ ሒደት ግን እየከሰሙ የሚመጡበት ሁኔታዎች አሉ።

በአሜሪካ ውስጥ የፊልም ኢንዱስትሪው እያደገ ሲመጣ መከራከሪያ የነበረው የቴአትር እድገት እያሽቆለቆለ ነው የሚል ነበር። ሆኖም ግን በጣም ጥሩ የሆነ ቴአትር ሲሰራ ደግሞ ሕዝቡ ፊቱን ወደ ቲያትር ይመልስ ነበር። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ቴአትር ቤቶች ሲመሰረቱ የአዲስ አበባ ሕዝብ ብዛት ከ500ሺ አይበልጥም ነበር። አሁን ደግሞ እነዚህን ቴአትር ቤቶች ይዘን የአዲስ አበባ ሕዝብ ብዛት ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጋ ሆኗል። መጠየቅ ካለብን የሕዝቡ ብዛት ሲጨምር ቴአትር ቤቶቹ በሰው መጨናነቅ ነበረባቸው። የሆነው ግን ሌላ ነው። አንድ ቴአትር ተሰርቶ አምስት አመት ከመድረክ ሳይወርድ ይቀመጣል። ከመድረክ የወረዱ ተመልሰው ወደ መድረክ ይመጣሉ። ተመልካች አዳዲስ ስራዎች ይፈልጋል። ስለዚህም ያልሰራናቸው የቤት ስራዎች ናቸው ለሌሎች በር የከፈቱት። በሚዲያዎች ላይ ተመልካች ወደ ቴአትር ቤቶች እንዲመጣ ምን አይነት ስትራቴጂ እንንደፍ? ጥሩ ስክሪፕቶች እንዴት እናዘጋጅ? የሚሉ የውይይት አጀንዳዎችም ሲቀርቡ አላየንም። እገሌ መጣ ሳይሆን ውስጣችን መፈተሽ አለብን። ሰነፍ መንግስት ነው የሚደፈረው። ሰነፍ ኢንዱስትሪ ነው የሚደፈረው። ባለሙያውና መንግስት እጅ እና ጓንት ሆነው ከሰሩ የማይለወጥ ነገር የለም፣ ይለወጣል።¾

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
15015 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 128 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us