የ“እያዩ ፈንገስ” ስንብት በብሔራዊ ቴአትር

Wednesday, 27 July 2016 13:56

 

የማንም ቆራጭ መጥረቢያ ቢስል

እዬዬ አልልም እንጨት ይመስል

ይሻለን ነበር ላይነት ቢያዳርሱን

ይሻለን ነበር ላመል ቢያቃምሱን

የዘለልነው ላንጀት የቀለብነው ፈርሱን።

                (እያዩ ፈንገስ)

የሀገር ቤት የሁለት ዓመት የመድረክ ቆይታውን አጠናቆ በደማቅ የምስጋና ምሽት “እያዩ ፈንገስ” ስንብቱን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አድርጓል። ባሳለፍነው ሰኞ ሐምሌ 11 ቀን 2008 ዓ.ም በደመቀው በዚህ አዳራሽ በርካታ ታዳሚያን ሞልተው ተርፈው ነበር። አንጋፋው ድምጻዊ ፀሀዬ ዮሃንስ “ኢትዮጵያን” በሚያደምቁ፤ ከድሮ እስከ ዘንድሮ ያቀነቀናቸው ስራዎቹን በቅላፃ ባንድ ታጅቦ ከታዳሚው ጋር በስሜት ሲጫወት አምሽቷል።

ይህ ሁሉ የሆነው “እያዩ ፈንገስ” ቴአትር የሁለት አመት የመድረክ ቆይታውን በተመለከተ አብረውት ለነበሩት አጋሮቹና ለተመልካቾቹ ያለውን ክብርና ምስጋና ለመግለፅ በተሰናዳው ምሽት ነው። ይህም ብቻ አይደለም ቴአትሩ በውል ላልተገለፀ ጊዜ በተለያዩ የአለማችን ከተሞች በሚገኙ መድረኮች ላይ ለተመልካች ሊቀርብ መሆኑን አዘጋጆቹ ተናግረዋል። እናም ምሽቱ “እያዩ ፈንገስ” ቴአትር ለሀገር ቤት ቆይተው ምስጋናና ስንብት ነው ሊባል ይችላል።

በደራሲ በረከት በላይነህ ተፅፎ በፕሮዲዩሰሩ አበባው መላኩ ተደግፎ፣ በተዋናይ ግሩም ዘነበ ተዘጋጅቶ ለተመልካች የቀረበው “እያዩ ፈንገስ” በዕለቱ በተለየ መልኩ ለመድረኩ በሚመጥን ደረጃ አዳዲስ ታሪኮችን ይዞ ቀርቧል።

“ተመልካቹን የማክበሪያ ብቸኛ ምክንያታችን ነው” በሚል ፅኑ ፍላጎት በከፍተኛ ጥረት ተዋናይና ዳይሬክተሩ ግሩም ዘነበ በአስራ አምስት ቀናት ውስጥ አጥንቶ አዲስ ስራውን እነሆ ብሏል። ያም ሆኖ “እያዩ ፈንገስ” አሁንም በስላቅ ትዝብቱን ይናገራል። አንድ ሰዓት ከሩብ በሆነ ጊዜ የተሰራው ይህ ቴአትር እንደቀድሞ ሁሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሰንኮፎቻችን ላይ በምሬት ይሳለቃል።

የ“እያዩ ፈንገስ” የቀድሞ አጫዋች (በመድረክ ሳይታዩ ግን ጎልተው የምናውቃቸው ስውሩ ገፀ-ባህሪይ) ጋሽ ቆፍጣናው ነበሩ። አሁን ላይ ደግሞ ጋሽ ድንቁ እና ወፍራሙ ዳምጤ “የቀልድ ማገዶዎች” ሆነው የቀረቡ ሲሆን የቀድሞዋን “ህያብ” ስንዘነጋ በዚህኛው ውስጥ በሁለተኛው ትዕይንት ታሪኳን የምናጣጥምላት “ቱቱዬ” ትገኝበታለች።

በዘመናችን ያለውን ግራ መጋባት የሚተቸው እያዩ “ግራ መጋባታችን ልክ የለውም” ይለናል። በግራ መጋባታችን ላይ ሲሳለቅም፣ “ሰው ቤንዚል ለመግዛት መኪናውን እየሰጠ ነው” ሲል ይሳለቃል። ሌላም የአንዳንዱን ሰው የተገላቢጦሽ ታሪክ ይነግረናል። “በቅዠቱ ያጠረውን አጥር ግቢዬ ነው እያለ፤ ዘበኞቹን ጭምር ሲጠብቅ የሚያድር” ሰቀቀናም አለ ባይ ነው።

የሰው ስራሽና የተፈጥሮን ጥፋት እንዲሁም ስደትን በተመለከተ የጎርፍና የመኪና አደጋውን መጠን ሲገልፅም፣ “አይቆጠሩም እንጂ ወንዝና መኪናው ስንቱን ይበላዋል መሰለህ” ይለናል። መማር ፊደልና ክፍል መቁጠር ብቻ አይደለም ትንሽም ቢሆን ሰብዓዊነትና ሞራል ያስፈልገናል የሚለው እያዩ፣ “መማር ከፊደልም በላይ ነው” ባይ ነው።

በተለይ የዘመናችንን (የሀገራችንን) ፖለቲካ በቆሰቆሰበት ሀሳቡ መሀል፤ መደማመጥ እንደራቀንና የሚወራውና የሚሰማው ለየቅል እየሆነብን እንደተቸገርን ሲጠቁመን፣ “ለዚህች ሀገር ችግር መፍትሄው ጆሮ ነው። ከሰማህ ትድናለህም ታድናለህም። አለበለዚያ ግን ዋ!” ሲል ያስጠነቅቀናል። በህግ ስም እርስ -በርስ መተረማመስም እንደማይገባን ሲጠቁም፣ “ሰው ከህግም በላይ ነው” ይለናል።

የዘመናችን ፖለቲከኞች የመናገር መብትን ብቻ ቢሰጡን ምን ዋጋ አለው? የሚለው እያዩ ፈንገስ፤ “የመናገር መብት ብቻ ሳይሆን የመደመጥ መብትም ሊኖረን ይገባል” ሲል ድምጹን ጮክ አድርጎ ስለምስኪኖች ይሟገታል። . . . እናም በሰው ላይ፤ በወንበር ላይ፤ በስልጣ ላይ ለተንፈራጠጡ ሁሉ እንዲህ ይላል” የረገጥኩት ነው ያቆመኝ ብለህ ላለመውደቅህ የረገጥከውን አመስግን”

“ለበላው ሁሉ ስቆም ስነሳ

ለየገበታው አንጀቴ ሳሳ”

የሚለው እያዩ ዘመኑ የሚፈልገው አለማንጋጠጥን ነው ይላል። “ባንጋጠጥክ ቁጥር ሰማይ ነኝ የማይልህ የለም” ሲል ይሳለቃ። ህጋችን ከሰውነታችን በታች ነው የሚለው ተሳላቂው ገፀ-ባህሪይ “ህጋችን ስም እየቀየረ የሚቀጣ” ከሆነ ምን ዋጋ አለው ሲል ይጠይቃል።

በችግራችን ላይ በሚሳለቀው እያዩ ፈንገስ የአንዱ ሞት ለሌላው ህይወት ግብር ያበላል የሚል ይመስላል። እናም የአንዱን ምስኪን ሰፈር እንደምሳሌ ሰው ሲሞት እንዲህ ነው ይለናል። “እዚህ ሰፈር ሰው ሲሞት ሞተ አይባልም። የሶስት ቀን ራት ዘጋ እንጂ” ሲል ለተመልካቹ ሳቅ ያቀብላል።

በሁለት ትእይንቶች መካከል የትወና ብቃቱን እንደቀድሞው ሁሉ ያሳየን ግሩም ዘነበ፤ የቀድሞዋን የእርሱን አዛኝ ህያብን እያስታወሰ ስለጠንካራዋና ታታሪዋ ማስቲካ ሻጭ “ቱቱዬ” ይተርክልናል። ሁሉም ሰው የሚናገረው ታሪክና አቤት የሚለው ብሶት አለው የሚለን” እያዩ ፈንገስ” በትዕይንቱ ሁለት መጀመሪያ ላይ እንዲህ ይቀኛል፤

“ባሳላፊ ቋንቋ ታፍኖ ካልቀረ

ሁሉም በየቋንቋው ተናግሮ ነበረ።

“ላለመርዳት ባዶ ኪስህን ሰበብ ስታደርግ” ሲል የሚሞግተው እያዩ፤ “አንተ ባዶ ኪሴን ነኝ ስትል ኪስ የሌለው ሱሪ የሚናፍቀው ወገንህ ላይ እየተሳለቅህ ነው” ይለናል። የአንድ ሰው ዋጋ ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ ሲያስታውሰንም፣ “በዚህች ሀገር የሃይል ጉልበት ውስጥ ግለሰብ ራሱን ረስቷል” ባይ ነው። እናም በስላቀ መካከል እንዲህ ይላል፣ “የዚህች ሀገር የችግር ስፋትም ሆነ የግለሰብ እጅ እርዝመት ልኬቱ ጠፍቷል” እያዩ ፈንገስ።

ባልተመጣጠነ ማህበራዊ ደረጃ፣ ፖለቲካዊ ደረጃና ኢኮኖሚያዊ ደረጃ ላይ ሆነህ እንዴት ዝም ትላለህ የሚለን እያዩ፤ “ሙሉ ርሃብና ሙሉ ጥጋብ ጎረቤት ሲሆኑ እያየህ ዝም አትበል” ባይ ነው። እናም ማህበራዊ ፍትህና የሞራል መራቆት ምን ያህል እያስተዛዘበን እንደሆነ ያሳየን “እያዩ ፈንገስ”፤ በደራሲው በረከት በላይነህ ድንቅ ቅኔ ይዘጋዋል።

በታምር ጠፍቷል የፍቅር መላው

አንዱ ሲታከም ይድናል ሌላው

ይህ የ“እያዩ ፈንገስ” ስንብት ከብሔራዊ ቴአትር ነው። መልካም የመዝናኛ ሳምንት።

 

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
531 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us