የጣይቱ- “የጥበብ መዓዛ”

Wednesday, 03 August 2016 14:22

“ጣይቱ የባህልና የትምህርት ማዕከል” በያዝነው ወር ለ4ኛ ጊዜ ያዘጋጀው “የጥበብ መዓዛ” የተሰኘ የስነ-ፅሁፍ ምሽትን በአክሱም ሆቴል አካሂዷል። ይህ ዓመታዊ የሥነ-ፅሁፍ ድግስ ለአዳዲስ ፀሐፊያን መበራከትና ከነባሮቹም ልምድ የመለዋወጥን አላማ ያነገበ ሲሆን፤ የዚህ መድረክ ደጋፊ በዋሽንግተን የሚገኘው “ጣይቱ የባህልና የትምህርት ማዕከል” እንደሆነ ከአስተባባሪዎቹ አንዱ የሆነው ገጣሚ ሰለሞን ሞገስ ይናገራል።

በያዝነው ወር መጀመሪያ በተካሄደው አመታዊ የሥነ-ፅሁፍ ድግስ ላይ ግጥም፣ መነባነብ፣ ዲስኩር እና ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል። በዕለቱ በመድረኩ ከተገኙት ገጣሚያን መካከል ሄኖክ ስጦታው፣ አደም ሁሴን፣ በላይ በቀለ ወያ፣ ወሰንሰገድ ገ/ኪዳን፣ ሰለሞን ሞገስ፣ ያለው ተክሉ፣ የምስራች ግርማ እና ሰይፉ ወርቁ ይጠቀሳሉ። በምሽቱ ከቀረቡት የስነ-ፅሁፍ ዝግጅቶች በተጨማሪ በመጋቢ ሃዲስ እጩ ዶ/ር ሮዳስ ታደሰ አማካኝነት ስለስነ-ከዋክብትና የህዋ ጥናት በቀደምት ኢትዮጵያውያን ስለተደረጉ ትጋቶች ዘርዘር ያለ መረጃን ለታዳሚው አቅርበዋል። እንዲሁም “ሁሉም በአገር ነው” የተሰኘ ዲስኩር በንግድ ስራ ባለሙያውና በአነቃቂ ንግግሮቹ በሚታውቀው ሽመልስ ታደሰ አማካኝነት ታዳሚውን ያበረታና ያዝናና ዲስኩር ተሰምቷል።

በዕለቱ ገጣሚ ሰለሞን ሞገስ ከራሱ የግጥም ስራዎች ይልቅ ከገጣሚ አለምፀሐይ ወዳጆ “የማታ እንጀራ” የግጥም መድብል እና ከሻምበል ክፍሌ አቦቸር “አንድ ቀን” የተሰኘ የግጥም መድብል መካከል የሚከተሉትን ስራዎች አቅርቧል። በቅድሚያ ከሻምበል ክፍሌ አቦቸር መድብል የወሰደውን በቅንጭቡ እነሆ፤

የሚታየኝ- ላይታያቸው

የሚሰማኝን - ላይሰሙ

የቸገረኝ - ላይቸግራቸው

የቸገራቸው - ላይቸግረኝ

ቅዠታቸው - ላያቃዠኝ

ምሬታቸው - ላይበግረኝ

ምናለ አቦ ቢተውኝ

በኢትዮጵያ አንድነት ውስጥ የተገለፀን ልዩነት በምሬት የሚያትት ግጥም ነው።

ገጣሚ ሰለሞን ሞገስ ከአለምፀሐይ ወዳጆ “የማታ እንጀራ” የግጥም መድብል ውስጥ ካቀረባቸው ግጥሞች መካከል የመጽሐፉ ርዕስ የሆነው የቀረበ ሲሆን፤ ገጣሚዋ በስንኞቿ እንዲህ ትላለች።

የማታ እንጀራ ስጠኝ

የጠዋት አታስመርጠኝ

ዘግይተህ በኋላ አስጊጠኝ

ማታ በክብሬ ደብቀኝ

ከሰው በር አንተው አርቀኝ።

የምትለዋ የግጥሙ ገፀ-ባህሪይ ስጋቷንና ምኞቹን ለአምላኳ የፀሎት ያህል የምታነበንብበት ገፅ ነው። የግጥሙ የመጨረሻ ስንኞችም እንዲህ ይላሉ።

አንገቴ እንዲል ቀና

የወዳጅ ደጃፍ ሳልጠና

“ዘራፍ” እንዳልኩኝ ይብቃልኝ

ሲጨልም መንገድ አቅናልኝ

አደራ ጌታዬ አደራ

አትንሳኝ የማታ እንጀራ!

ገጣሚ በላይ በቀለ ወያ “እንቅልፍና ሴት” ከተሰኘ የግጥም መድብሉ ደግሞ፣ የሚከተለውን እነሆ በረከት ብሏል።

ካጣሁሽ ለሁዋላ. . .

“ወንዝ ውስጥ ገብተህ ሙት”

የሚል መካሪ ሀሳብ ውስጤ ተከሰተ

የምሞትበትን ወንዝ እየፈለኩኝ

መካሪ ሀሳቤ ውሃ ጠምቶት ሞተ።

በውሃችን ላይና በወንዞቻችን መድረቅ ላይ እንዲህ በመሪር ምጸት የተሳለቀው ገጣሚ በላይ በቀለ ወያ በዚያው ግጥም ስር እንዲህ ሲል ያዝናናናል።

ካጣሁሽ በኋላ. . .

በሞቴ ልረሳሽ ኖሬ እንዳልከፋ

ይገለኛል ብዬ

ኮረንቲ ብጨብጥ - ወዲያው መብራት ጠፋ።

እስካሁን አልመጣም እንደጠፋ ቀረ

እንዴት ጨለማ መሞት ይችለዋል ብርሃን ያፈቀረ?

ብቻ ምን አለፋሽ

ይገለኛል ብዬ የሞከርኩት ሁሉ አልሆነም አለሜ

እስከሚሆን ድረስ በአንድ ኪሎ አቅሜ

ኩንታል ትዝታሽን አለሁ ተሸክሜ።

ሌላኛው ገጣሚ አደም ሁሴን በቅርቡ ለንባብ ከበቃው “እሳት ያልገባው ሐረግ” መድብሉ ውስጥ “ዳግም ፍጥረት ቢኖር” የተሰኘ ግጥሙን እንካችሁ ብሏል።

ካልጋገሩት ቆርሰው

ካልጠመቁት ቀድተው

ካልዘሩት ከሚያጭዱ ከትውልድ በሽታ

ከጉንጭ አልፋ ወሬ ሁካታ ጫጫታ

ከምቀኞች ሽሽት ቤቴ በድር ታጥሮ

ካልቀረስ መመኘት ዳግመኛ ተፈጥሮ

የሰው አይን ካላየው ከተረሳ ቦታ

ምነው ባደረገኝ ሸረሪትን ላፍታ።

ምሽቱን ወዝ ባላቸው ግጥሞቻቸው ካደመቁት ገጣሚያን መካከል ሌላኛው ገጣሚ ሔኖክ ስጦታው ነው።

“መፍትሄ መዶሻ”

“መፍትሄ ተበጀ ለችግር

ሌላ መንስኤ ተቀመረ

የዓለም አሰስ ገሰስ

ዕለት ከዕለት እየናረ

የችግሩ መፍትሄ መላ

አያሌ ችግር ፈጠረ።”

አልኩ. .  .

እኚህ  ሁሉ መዶሻዎች ለመፍትሄ የታገሉ

ያነጹትን አፈረሱ ግንባታ ላይ እንደዋሉ

“ችግር ተቀርፏል” ሲሉ

መቸገሩ ካልቀረ፤

ህያውነቱ ከፀና መልኩን እየቀየረ

መፍትሄን ነው ማስቀረት እስከዛሬ የት ነበረ?!

ልክ እንደዚህ ማለት፡-

(መፍትሄ ነው ችግር ልክ እንደመዶሻ

ይገነባል ሲሉት ይሆናል ማፍረሻ)

 በፕሮግራሙ ላይ ከተገኙት ሙዚቃ ተጫዋቾች መካከል በክራር መድረኩን ያደመቀው ታምሩ ንጉሴ እንደሚከተለው ዋዘኛ ቅኔ ተቀኝቷል።

“ ብጨርሰው ኖሮ ቅኔውን ተምሬ

ከዘረፉት እኩል እሆን ነበር ዛሬ”

***      ****        *****

ከባለቤቴ ጋር ሁልጊዜ አታካራ

እንጀራ አልጋገረች ወጥም አልተሰራ

ቤቴን አፈረሱት ዛራና ቻንድራ።

በአሜሪካን ሀገር ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ የሚኖሩት ዕውቋ የኪነጥበብ ባለሙያ አለምፀሐይ ወዳጆ እና ወዳጆቿ የሚደግፉት ይህ “ጣይቱ የባህልና የትምህርት ማዕከል” ከሀገራችንም አልፎ የአፍሪካን ባህል፣ ስነ ጽሁፍና ቴአትር ለማስተዋወቅና መድረክ ለመፍጠር አላማ ይዞ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ገጣሚ ሰለሞን ሞገስ ይናገራል። ፕሮግራሙ እዚህ በሚካሄድበት በተመሳሳይ ቀንና ጊዜ እዚያም (አሜሪካ - ዋሽንግተን ዲሲ) በተመሳሳይ ርዕስ የሥነ-ፅኁፍ መድረክ እንደሚሰናዳ ለማወቅ ችለናል።

“ጣይቱ የባህልና የትምህርት ማዕከል” መሰል የሥነ-ፅሁፍ ምሽቶችን ከማገዝና ከማሰናዳት በተጨማሪም የአልበም፣ የሙዚቃ፣ የመፅሀፍት ምርቃቶች እንዲካሄዱ የሥዕል አውደ-ርዕይዎች እንዲሰናዳም ይሰራል ተብለናል።

ይህ አመታዊ የሥነ-ፅሁፍ ፕሮግራም በበርካቶች ዘንድ ትኩረትን ያገኘ ቢሆንም ከአመታዊነት ወደ ወርሃዊነት አልያም ብዙ ያልራቀ ጊዜ ውስጥ ተደጋግሞ ማዘጋት ቢችል መልካም እንደሆነ የፕሮግራሙ ታዳሚያንና ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡ የሥነ-ፅሁፍ ሰዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።  

ይምረጡ
(9 ሰዎች መርጠዋል)
16553 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1049 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us