የተረሱትን የእኒያ ልጆች ትንሳኤ የሚተርከው “የትንሳዔ” ታሪክ

Wednesday, 10 August 2016 13:39

 

በይርጋ አበበ

የመጽሀፉ ርዕስ   “ከኒያ ልጆች ጋር”

ጸሀፊ፦            ፋሲካ መለሰ

የመጽሀፉ ዘውግ፦   እውነተኛ ታሪክን የያዘ ቃለ ምልልስ

የህትመት ጊዜ    ሚያዝያ 2008

አታሚ          ፋር ኢስት ትሬዲንግ

አከፋፋይ፡-        ክብሩ መፅሐፍ መደብር

ዋጋ            90 ብር ከ99 ሳንቲም

አቶ ክፍሉ ታደሰ የተባሉ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) መስራች “ያ ትውልድ” ሲሉ በሶስት ቅጽ የተከፈለ ዳጎስ ያለ መጽሀፍ አዘጋጅተው በኢህአፓ ዙሪያ ለአንባቢያን አቀረቡ። አቶ ክፍሉ በቅጽ በከፋፈሏቸው የያ ትውልድ መጽሀፍት ውስጥ በብዛት የቀድሞውን መንግስት አስከፊነትና ጨካኝነት በስፋት ያስዳሰሱ ሲሆን አያይዘውም የኢህአፓ አባላት በነበሩት የዚያ ትውልድ አባላት የዓላማ ጽናት ዙሪያ ጽፈዋል።

መነሻውን ባህር ዳር አድርጎ አዲስ አበባ ለማረፍ እየበረረ የነበረውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነ አውሮፕላን ከጓደኞቻቸው ጋር ጠልፈው አልጄሪያ እንዲያርፍ ያደረጉትን የብርሀነ መስቀል ረዳን የህይወት ታሪክ የያዘው “የሱፍ አበባ” የተሰኘው መጽሃፍም ስለ ኢህአፓ የሚያተኩር ሌላ ድልብ መጽሀፍ ነው። የእነዚህ ሁለት መጽሃፎች ጸሀፊያን በፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ በመሆኑ ለኢህአፓ የታገሉ እና ያታገሉት የላይኞቹ ብቻ ናቸው እንዴ? ወይስ የታችኞቹ አመራሮችና ተራ አባሎቻቸውንስ የሚያስታውሳቸው የለም ወይ? የሚሉ ሀሳቦች በተደጋጋሚ ሲነሱ ቆይተዋል።

ራሳቸውን አስተማሪ እንደሆኑ ገልጸው መጽሃፋቸውን የጀመሩት አቶ ፋሲካ መለሰ ከላይ የተነሳው መጠይቅ አሳስቧቸው ሳይሆን አይቀርም፤ አንድ የስራ ባልደረባቸውን ታሪክ ከሰሙ በኋላ “የዚህ ሰው ታሪክ በሰነድ መልክ ቢሰነድ እኮ ለዚህ ዘመን ትውልድ ትምህርት ለዚያ ዘመን ትውልድ ደግሞ ታሪክ ሊሆን ይችላል” በማለት መነሳታቸውን ይገልጻሉ። አስተማሪው ግን ሳያስቡት ስለ ወዳጃቸው ትንሳዔ (መጽሀፉ በቃለ ምልልስ መልክ የተዘጋጀ ሲሆን ይህ ቃለ ምልልስ የሚካሄድለት ሰው ስም ትንሳዔ ይባላል) ብቻ ሳይሆን በወቅቱ ስለነበረው የእሱ (የትንሳዔ) ባልንጀሮች ውጣ ውረድና የዓላማ ጽናትም ማስነበብ ጀምረዋል።

 

 

“ከኒያ ልጆች ጋር” ከቋንቋ አጠቃቀም አኳያ

መምህር ፋሲካ መለሰ ከኒያ ልጆች ጋር ሲሉ ከባለታሪኩ ትንሳዔ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ከረጅም ጊዜ ድካምና ውጣ ውረድ (ቃለ ምልልሱን ለማድረግ ስድስት ወራት ታሪኩን በማቀናጀት ተጨማሪ ስድስት ወራት እንደወሰደባቸው ገልጸዋል) በኋላ ማሳተማቸውን በመጽሃፋቸው መግቢያ ላይ አስፍረዋል። ይህን ያህል ድካምና ረጅም ጊዜ የወሰደውን መጽሃፍ ከተለያዩ ምልከታዎች (አንጓዎች) ለመመልከት ስንነሳ በመጀመሪያ ልንመለከት የወደድነው የቋንቋ ለዛውን ይሆናል።

 

የታሪኩ ባለቤት ትንሳዔ (እሱ ግን ታሪኩ የእሱ ዘመን ትውልዶች በሙሉ እንደሆነ ይናገራል) ቃለ ምልልስ ለሚያደርግለት የሙያ አጋሩ ሲናገር የቋንቋ ችሎታ እንዳለው ያሳብቃል። ለምሳሌ በመጽሀፉ ገጽ 4 ላይ “….በዚያ ጭው ባለ በርሃ ጨረቃ ፍንትው ብላ መውጣት ሲገባት አልፎ አልፎ ሰማዩ ላይ የሚንሳፈፍ የጉም ባዘቶ ይሸፍናት ነበር” ሲል የሚገልጽበትን ቦታ እንገኛለን።ተራኪውትንሳዔ ይህን የሚናገረው ወደ ጅቡቲ ለመሰደድ በበርሃ ከሶማሊያዊያን ግመል ነጂ ኮንትሮባንድ ነጋዴዎች ጋር በድቅድቅ ጨለማ ሲጓዙ የነበረበትን ሁኔታ ሲያስረዳ ነው። በሌላ ቦታ ደግሞ ስለ ወላጆቹ በተለይም ስለአባቱ ባህሪይ ሲገልጽ አባቱ በአንድ ስራ እና በአንድ ቤት ተረጋግተው መኖር የማይወዱ መሆናቸውን ይናገራል። ይህን ያደመጡት አቶ ፋሲካ ታዲያ ስራቸው ምንድን ነበር? ብለው ሲጠይቁት “………….ሙያው የተለያየ ነበር። የተግባረ ዕድ ሙያ ስለተማረ በኤሌክትሪክ፣ በስልክ፣ በመኪና ጥገና እና በቧንቧ ስራ በሚገባ የተካነ ነበር። ……ከአብዮቱ በፊት በእርሻ መስክ ኢንቨስተር ሆነ። አብዮት ሲመጣ ጋሻ መሬቱን፣ ትራክተሩንና መጋዘኑን በሙሉ ተወረሰ። የወቅቱ ሀብታሞች በንዴት አንጀታቸው እያረረ ሲሞቱ እሱ እቴ!! ወይ ፍንክች የአባ ቢላ ልጅ!! አባቴ አራት ነገር ይጠላ ነበር። ፍርሃት፣ ውሸት፣ ሌብነት እና ድህነት። ስለ አባቴ ይሄው ይበቃሃል። ነብስህን ይማረው ጀግናው አባቴ!” ይላል በገጽ 13 እና 14 ላይ።

 

 

ተረብ አዋቂው ትንሳዔ በዚህ ብቻ ሳያበቃ እናቱን በተመለከተ በርካታ መግለጫዎችን ከተናገረ በኋላ በልጅነቱ እናቱ ልጆቻቸውን በስነ ስርዓት እንዲያድጉ ያወጧቸው የነበሩ መተዳደሪያ ደንቦችን ሲገልጽም አንባቢ መጽሀፉን ፈገግ እያለ እንዲያነብ ይጋብዛል። ለምሳሌ በገጽ 16 ላይ “…….. የእናቴ የተከለከሉ ህጎች ብዙ ነበሩ። ስስት፣ ሰው ሲበላ ማፍጠጥ፣ መቀላወጥ፣ በሁለት ጉንጭ መብላት፣ ከመጠን በላይ መጉረስ፣ …. ለትልቅ ሰው አለመነሳት (ወንበር አለመልቀቅ ለማለት የፈለገ ይመስላል)፣ በአንድ እጅ ሰው መጨበጥ…… አቤት የህጓ ብዛት!!!! ነብስሽን በገነት እናቴ ውዴ።” ይላል።

 

 

በእናቱ እና በአባቱ ብቻ ፈገግ ብለን እንዳናልፍ የፈለገ የሚመስለው ትንሳዔ ግን መኮንን የሚባል የቀድሞ የፓርቲ አጋሩ እና በኋላ እጁን ለደርግ የሰጠ ወዳጁ “….. በ1969 ዓ.ም መስከረም ደርግ ኢህአፓን ለማጥፋት ያቀደውን በመገናኛ ብዙሃን በይፋ ማወጁን አስታወስኩት። ቢሆንም ቢሆንም እያለ ውይይታችንን ወደ ዜሮ በማውረድ አታካች ሲያደርግብኝ ከረመ። ከዛሬ ጀምሮ በዚህ ርዕስ ዙሪያ እንዳታናግረኝ ብዬ እስከምናገር ድረስ ትዕግስቴን ተፈታተነው። የልብ ካውያ” ሲል ይናገራል። ጨዋታ አዋቂ መሆኑን በቃለ ምልልሱ ላይ የሚያስታውቀው ባለታሪኩ የኢህአፓ አባል ሆኖ ለተወሰኑ ዓመታት በወጣት ክንፍ እና በዋናው አባል ውስጥ ካሳለፈ በኋላ አንድ ቀን በደርግ የደህንነት አባላት እጅ መግባቱን ይገልጻል። ታዲያ በዚህ ጊዜም ቢሆን የታዘበውን ሲናገር አንባቢን ፈገግ በሚያሰኙ ውብ ቃላት ነው። ለአብነት ያህልም በደርግ ጽ/ቤት ገብቶ እግሩን እና እጁን ወደ ኋላ ታስሮ ሲገረፍ (በተለምዶ ወፌ ላላ አገራረፍ ይባላል) የተሰማውን የህመም ስቃይ ሲገልጽ አንባቢ የስቃዩ ግዝፈት እንዳይታየው አድርጎ ነው። “…….ያለማጋነን ከአንድ ሰዓት በላይ እንደተገረፍኩ እገምታለሁ። ሆኖም ሙሉ ቀን ነበር የመሰለኝ። … ወደመጨረሻው አካባቢ እግሬ ከሌላው አካሌ የተለያየ ያህል ግርፋቱ አልሰማህ አለኝ። ጊዜ መሄዱን አቁሟል እዚያው ተወልጄ እዚያው ያደግሁ መሰለኝ። …….. ገራፊው የአናርኪስት እና የድመት ነብስ አይወጣም ያለ መሰለኝ። ጊዜው ለምን እንደማይሄድ ገረመኝ። እግሬን በጭራሽ አይሰማኝም። አካሌ ላይ መኖሩንም ተጠራጥሬያለሁ። ያ ደንደሳም ገራፊ ቆርጦ የወሰደው ነው የመሰለኝ።” ሲል ይገልጻል በገጽ 221 እና 222።

 

 

ጨካኝ መሆናቸውን አምርሮ የገለጻቸው የደርግ ጽ/ቤት ገራፊዎች እና የምርመራ ሰዎች ፊት ቀርቦም ቢሆን በእነሱ ላይ ሲቀልድ ይታያል ባለታሪኩ ትንሳዔ። የሰው ልጅ ጭካኔ የመጨረሻው ደረጃ አመላካች እንደሆነ በገለጸው አስር አለቃ መሰለ በሚባል መርማሪ ፊት ቀርቦም “ይልቅ እናቴ በጭንቀት እንዳትሞት ስልክ ደውለህ ንገርልኝ” ብሎ እንደጠየቀው ይገልጻል። በእውነቱ ከሆነ በዚያ ሰዓት እና በዚያ ሁኔታ እናቴ እንዳትጨነቅ ስልክ ደውለህ ያለሁበትን ንገርልኝ ብሎ መጠየቅ ከማሳቅም በላይ ያስገርማል። መርማሪውም ቢሆን በዚህ ንግግሩ ከሶስት ደቂቃ በላይ ስራውን ትቶ እንደሳቀ ባለታሪኩ ይናገራል። የባለታሪኩ ጨዋታ አዋቂነት እና የቋንቋ ለዛ በዚህ ብቻ የሚያበቃ አይደለም። መጽሀፉ ሙሉ በሙሉ በሚያስብል ደረጃ በምሬትና ስላቅ (በትራጃይ ኮሜዲ) የተሞላ ነው ማለት ይቻላል። እኛ ግን እዚሁ ላይ እናቁምና ወደ ሌላው መመልከቻ አንጓ እናምራ።

 

 

“ከኒያ ልጆች ጋር” ያን ዘመን ሲያስታውስ

መጽሀፉ ከአንድ ሰው ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ በመሆኑ ባለታሪኩ ያለፈበትን ዘመን እያስታወሰ መናገሩ የሚጠበቅ ነው። በዚህም መሰረት “ከኒያ ልጆች ጋር” ባለታሪኩ በኖረበት ዘመን የነበረውን የገበያ ዋጋ፣ የትምህርት ደረጃ፣ የፖለቲካ ሁኔታ እና የአዲስ አበባን መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ሁሉ ያስታውሳል።

ለአብነት ያህልም በአምስት ሳንቲም ሁለት ጥምዝ ዳቦዎች ይሸጥ እንደነበር በመጽሀፉ ገጽ 12 ላይ አስቀምጧል። የትምህርት ሁኔታውን ሲገልጽ ደግሞ በእናቱ የትምህርት ደረጃ አስታኮ ነው። እንዲህ ይላል በገጽ 14 ላይ “…. እናቴ እንደብዙ የኢትዮጵያ እናቶች ነች። ሆኖም ፊደል ቆጥራለች እስከ ስድስትኛ ክፍል። ይህ እንግዲህ በእሷ ዘመን ምሁር ያደርጋታል ማለት ነው። በመንግስት መስሪያ ቤት ታይፒስት ነበረች።”  ይላል። በዚህ ገለጻው የባለታሪኩ እናት ወጣት በነበሩበት ወቅት የነበረውን የትምህርት ደረጃ እና የስራ እድል አመላካች ሆኖ አግኝንተነዋል። እሱ ራሱም ቢሆን ገና የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ሆኖ ከእሱ ያነሱ ተማሪዎችን ለማስተማር የበቃበትን ሁነት አስታውሷል።

 

 

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በቮልስ ዋገን ተጭነው ከስልጣን ሲወርዱ በዓይኑ በብረቱ መመልከቱን የሚገልጸው ባለ ታሪኩ ትንሳዔ በቦታው ተገኝቶ የነበረው ህዝብ ንጉሱን “ሌባ ሌባ “ እያለ ሲሰድባቸውም ሰምቷል። እሱ ግን በንጉሱ ላይ የስንፍና ቃል (ስድብ) ማውጣት አለመፈለጉን ሲገልጽ በገጽ 36 ላይ“… ጃንሆይን እንደ ተራ ሰው ሽማግሌ ምናምን የምትላቸው አይደሉም። ኢትዮጵያን በዘመኑ በነበረው እድገት እንድትጓዝ ያደረጉ፣ ትምህርት ያስፋፉ፣ ሀገራችንን በዓለም ስምና ክብር እንዲኖራት ያደረጉ ናቸው” በማለት ነበር የገለጸው። ሆኖም ንጉሱ ስልጣናቸው ላይ ሙጭጭ ማለታቸውንና የህዝቡን ንቃተ ህሊና ማየት ባለመቻላቸው እሳቸውም ሆኑ አገሪቱ ዋጋ እንዲከፍሉ ማድረጋቸውን ሳይናገር ማለፍ አልፈለገም።

 

 

የቦታዎችን እና የመንገዶችን መለዋወጥ የገለጸበትማ እጅግ ብዙ ነው። በአጭሩ አዲስ አበባ አሁን ያላትን ገጽታም ሆነ ያላትን ስፋት ከማግኘቷ በፊት ምን አይነት ከተማ እንደነበረች በውብ ቃላት አጅቦ አስቀምጦታል። ይህን ለአንባቢያን በመተው ወደ ሌላው አንጓ እንሸጋገራለን።

 

የፖለቲካ ቅኝት “ከኒያ ልጆች ጋር”

መጽሀፉ ሙሉ በሙሉ የ60ዎቹን ፖለቲካ የሚዳስስ ነው። የደርግን አምባገነንነት እና ጭካኔ፣ የኢህአፓን ወጣቶች የዓላማ ጽናት፣ የእድገት በህብረት የእውቀትና የስራ ዘመቻ፣ የደርግን የምርመራ እና የታራሚዎች አያያዝ፣ ኢህአፓ የፓርቲ አባላቱን እንዴት እንደሚመለምልና እንደሚያሰለጥን፣ እንዲሁም በኢህአፓ አባላት ላይ ስለተፈጠረው አንጃ በስፋት የሚዳስስ መጽሀፍ ነው። በተለይ በፓርቲው የተፈጠረውን አንጃነትና መከፋፈል “የስላሴዎች እርግማን” ሲል ከፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም በተዋሰው ሀረግ ይገልጸዋል።

 

 

የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለ በሽመልስ ሀብቴ ትምህርት ቤት ፖለቲካ እንደጀመረ የሚናገረው ባለታሪኩ በእድገት በህብረት የእውቀትና የስራ ዘመቻ ወቅት የፖለቲካ እውቀቱ እየበሰለ መሄዱንም ያስታውሳል። ከአምስት ጓደኞች ጋር በመሆንም ሀጎስ በሚባል ወጣት አስተባባሪነት የኢህአፓን ርዕዮተ ዓለም እና የፖለቲካ ትምህርት ለወራት ካጠና በኋላም የኢህአፓ አባል እንዲሆን በአስተማሪው ሀጎስ አማካኝነት እንደተነገረው ገልጾ በዚያው ዕለት የፓርቲው አባል እንደሆነ ይገልጻል።

 

 

የደርግ የደህንነት ሰዎች ከያዙት በኋላ ወደ ደርግ ጽ/ቤት ለምርመራ ሲወስዱት የሶስት ጓዶቹን ማንነት የሚገልጽ የኮድ (የሚስጥር ምልክት) እና ሌሎች ሰነዶችን ይዞ ነበር። በዚህ ጊዜ ታዲያ የሚስጢር ምልክቶቹን የያዘውን ወረቀት ከደህንነት አባሎቹ እጅ እንዳይገባ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረጉን የሚገልጸው ባለታሪኩ ከብዙ ጥረት በኋላ ወረቀቱን ከአፉ አስገብቶ እንደዋጠው ይናገራል። በገጽ 218 ላይ ሂደቱን ሲገልጽም “… የምንፈራፈር በመምሰልም በአፍጢሜ እንደተደፋሁ ኮዶቹን ከስር በመግፋት አወጣኋቸውና አፌ ውስጥ ከተትኳቸው። ሳላላምጥም ዋጥኳቸው። እንዴት እንደጣፈጡኝ ልነግርህ አልችልም። እዛው እወደቅሁበት እኔን ጥለህ ልታመልጥ ነበር ተነስ እያለ አፋኜ ረገጠኝ። ደሜ እየተንዠረገገ ባንገቴ ላይ ሲወርድ ተሰማኝ። ሶስት ነብሳትን ያደነ ደም ሰለሆነ የደሜ መፍሰስ ውስጤን በደስታ ሞላው እንጂ የህመም ስሜት አልተሰማኝም” በማለት ከእሱ መደብደብና መረገጥ ይልቅ የጓዶቹን ማንነት ባለማጋለጡ እርካታ ሲሰማው ያሳየናል። በዚህም የዓላማ ጽናቱን ይገልጽልናል።

 

 

ዘመን እንደ ቂጣ ተገለባባጭ ነው እንዲሉ በደርግ ጽ/ቤት ነግሰው የነበሩት መርማሪዎች “ደርግ እብድ ውሻ ነው መጀመሪያ አካባቢውን፣ ቀጥሎ ጎረቤቱን ከዚያም ራሱን ይበላል” ብሎ የገለጸው የደርግ መንግስት በራሱ አባላት ላይም ጨክኖባቸው የምርምራ ማዕከል አመራሮቹን አስሯቸው ስለነበር በወህኒ ቤት እንዳገኛቸው ባለታሪኩ ያወሳል። በተለይ መሰለ የተባለው ደንዳና ልብ ያለው አስገራፊ መርማሪ ሁሉ ነገሩ ተቀይሮ እንዳልነበረ ሆኖ በእስር ቤት ሲያገኘው መገረሙን ሳይደብቅ ገልጿል ትንሳዔ በመጽሀፉ ገጽ 378 ላይ። የመርማሪውን መታሰር ጨምሮ ሌሎች የደርግ አባላትና አመራሮች መታሰራቸውን የማይደግፈው ትንሳዔ “…ሰዎቹ 20 ዓመት ታስረው ከሚፈቱ ይልቅ ለህዝብ በቀጥታ በሚተላለፍ የቴሌቪዥን ስርጭት ያጠፉትን ጥፋት በሙሉ አምነው ቢናዘዙና 20 ቀናትን ብቻ ታስረው ቢፈቱ ይሻላል ባይ ነኝ። …. የይቅርታ ልብ ሊኖረን ይገባል። ይህ ከሌለን ግን ተተኪው ትውልድ ከእኛ የሚማረው የለም…” ሲል ይገልጻል። 

 

 

“ከኒያ ልጆች ጋር” መፅሐፍ ውስጥ የተገኙ ድክመቶች

መጽሀፉ ከላይ በተቆነጸለው መልኩ መልካም ጎኑ የተጠቀሰ ቢሆንም ችግር የሌለበት ነው ማለት ግን አይደለም። በዝግጅት ወቅት መስተካከል የሚገባቸው በርካታ ችግሮችን እንደያዘ የታተመ መጽሀፍ ነው ማለት ይቻላል። “ልጅን ሲወዱ ከእነ ……” እንዲሉ ከኒያ ልጆች ጋር መጽሀፍም አንባቢያን ሲገዙት ከእነ በርካታ ድክመቶቹ ነው ማለት ነው። እነዚህ ችግሮች ደግሞ የተፈጠሩት እንደበርካታዎቹ የአገራችን መጽሀፍት የአርትኦት ባለሙያ እንዲመለከተው ባለመደረጉ ነው። የቃላት ግድፈቱ እንዳለ ሆኖ ከአንድ በላይ የሆኑት የአማርኛ ሆሄያት የትኛው ሆሄ የትኛው ቃል ላይ መግባት እንዳለበት እንኳን የተረዱ አይመስሉም የመጽሀፉ አዘጋጅ።

 

 

ሌላው የመጽሀፉ አዘጋጅና ባለታሪኩ ካላቸው ቀረቤታ የተነሳ ቃለ ምልልሱን ሲያካሂዱ ከመደበኛ ቃለ ምልልስ ወጣ ባለመልኩ በወሬ መልክ የተዘጋጀ መሆኑ አንባቢን ግራ የሚያጋቡ ጥያቄዎች ይበዛሉ። በአንፃሩ ደግሞ እውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑ የትንሳኤ አባት ስም ቢገለፅ መልካም ነበር፡፡ ከዚህ ሌላ የመጽሀፉ የፊትና የኋላ ሽፋን (ከቨር ዲዛይን) ዓይነ ግቡ አለመሆን እና ርዕሱም ቢሆን አወዛጋቢ መሆኑ ሌላው የተመለከትኳቸው ችግሮች ናቸው። ቀጣዩ ዕትም ሲወጣ እነዚህን ስህተቶች አርሞ ቢወጣ መልካም ነው እላለሁ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
492 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us