“አባ-ጃንቦ” እና “ባቢሎን በሳሎን” የደመቁበት ምሽት

Wednesday, 17 August 2016 12:25

በኢትዮጵያ የመድረክና የሬድዮ ድራማ ታሪክ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠሩት ስራዎችና ባለሙያዎቻቸው የእውቅናና የምስጋና የሽልማት ፕሮግራም በድምቀት ተከናውኗል። ይህ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ቴአትር ባለሙያዎች ማህበር አማካይነት ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰናዳ መሆኑንም የማህበሩ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አርቲስት ካሌብ ዋለልኝ፤ ከትናንት በስቲያ (ነሐሴ 9 ቀን 2008 ዓ.ም) በአፍሮዳይት ኢንተርናሽናል ሆቴል የመክፈቻ ስነ-ሥርዓት ላይ ባደረገው ንግግር አስታውቋል።

በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ረጅም ዓመታትን በመድረክ እና በሬዲዮ ተከታታይ ድራማነት ያሳለፉት ስራዎች “ባቢሎን በሳሎን” እና “አባጃንቦ” የሬድዮ ድራማ ናቸው። የዕውቅናና የምስጋና ሽልማት በተሰጠበት ምሽት ለበርካታ ባለሙያዎች የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በሶስት የተለያዩ ዘርፎች የተሰጠው ሽልማቱ፤ በድራማው ውስጥ ከፍተኛ ተሳትፎ በማድረግ ቢያንስ ከስራዎቹ ጋር ከግማሽ ጊዜ በላይ የቆዩ በሚለው ዘርፍ “አባ-ጃንቦ” በተሰኘው ተከታታይ በሬድዮ ድራማ ውስጥ በትወና የተሳተፉት ዳዲ ቱፋ፣ ድማ ደዩ፣ ሽለመ ከቤ፣ ደበሌ ጋረደው፣ አበበች አደማ፣ ዳርቲ አበራ፣ ደራርቱ ካቦ የዕውቅና ሽልማቱን አግኝተዋል።

“ባቢሎን በሳሎን” ቴአትር ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ ያደረጉ ባለሙያዎች በሚለው ዘርፍ የዕውቅና ሽልማቱን ያገኙት አርቲስት ፍቃዱ ከበደ፣ ራሄል ተሾመ፣ ዳንኤል ተገኝ፣ ሽልማት አግኝተዋል። ለረጅም ዓመታት ከቴአትሩ ጋር በመቆየት አለማየሁ ታደሰ፣ ህንፀተ ታደሰ፣ ሉሌ አሻጋሪ፣ እንድሪስ አህመድ፣ ስናፍቅሽ ተስፋዬና እመቤት ወልደገብርኤል ከባቢሎን በሳሎን” ተሸላሚ ሲሆኑ፤ ከ“አባ -ጃንቦ” ተከታታይ የሬድዮ ድራማ ደግሞ ደራሲው ሰብስቤ አበበ፣ የሺ ረጋሳ፣ ኢሳያስ አህመድ እና ታምራት ከበደ እስካሁን ድረስ ባላቸው ተሳትፎ ተሸላሚ ሆነዋል።

ከ30 ዓመት በላይ የሆነው የኢትዮጵያ ቴአትር ባለሙያዎች ማህበር ፕሮግራሙን ለማዘጋጀት የተነሳበትን ምክንያት አርቲስት ካሌብ ዋለልኝ ሲያስረዳ፣ “ለትውልድ መልካም ስራ የሰሩና አርአያ መሆን የሚችሉ ባለሙያዎቻችን እንደጀግኖቻችን ስናከብራቸው ራሳችንንም እናከብራን። በዚህም የተዘነጉትንና ለረጅም ጊዜ በመድረክና በሬድዮ ድራማ ላይ የተሳተፉትን ሰዎች በዚህ መሰል ፕሮግራም ዕውቅና መስጠት ይገባል” ብሏል።

አዲስ አበባን ከአፍሪካ ህብረት ማረፊያነቷ ባሻገር የኪነ-ጥበብ መዲና ለማድረግ እየሰራሁ ነው የሚለው ማህበሩ፤ በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ላይ ወሰን ተሻጋሪ የትወና ጥበባት ፌስቲቫልን ማሰናዳቱም በትውስታ ተነስቷል።

አርቲስት ሽመልስ አበራ (ጆሮ) እና አርቲስት አዜብ ወርቁ በተዋዛ መልኩ በመሩት በዚህ የዕውቅናና የምስጋና ሽልማት መድረክ ላይ “ባቢሎን በሳሎን” በተሰኘው ቴአትር ላይ አርቲስት ሃ/ማርያም ሰይፉ የጥናት ፅሁፉን ሲያቀርብ፤ በኦሮምኛ ቋንቋ ከ18 ዓመታት ላላነሰ ጊዜ ሲተላለፍ የነበረውን “አባ-ጃንቦ” የተሰኘውን ድራማ በተመለከተ ደግሞ ጋዜጠኛና ደራሲ ዝናሽ ኦላኒ አጠር ያለ የጥናት ፅሁፍ አቅርባለች።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ በድምሩ ለአስራ ሶስት አመታት ለተመልካች የቀረበው “ባቢሎን በሳሎን” ቴአትርን በሚመለከት ጥናታቸውን ያቀረቡት አርቲስት ሃ/ማሪያም የቴአትሩን ባለሙያዎች በሙሉ በማመስገን ጀምረዋል። ከግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መጋቢት 1994 ዓ.ም ታይቶ የነበረው “ባቢሎን በሳሎን” ከሁለት ዓመት በኋላ በድጋሚ ግንቦት 1 ቀን 2000 ዓ.ም ወደመድረክ ከተመለሰ ጀምሮ እስካሁን ለተመልካች በመታየት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ለበርካታ አመታት የቆየው “ባቢሎን በሳሎን” በአንድ ዓመት ውስጥ 45 መድረኮችን አግኝቷል ያሉት ጥናት አቅራቢው፤ ቴአትሩ አሁን ድረስ በመድረክ ሲቆይ፤ ሌሎች 34 ቴአትሮች ግን ወደመድረክ ወጥተው ከመድረክ ወርደዋልም ተብሏል። በአንድ መድረክ የተመለከተው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተመልካች 1ሺህ 416 ሲሆን፤ አነስተኛ ሆኖ የተመዘገበው ደግሞ 180 ነበር። በአሁኑ ሰዓት ቴአትሩ በአዘቦት ቀን ቢታይም በሰንበት ከሚታዩት ቴአትሮች ያልተናነሰ ተመልካች አለው ሲሉም ጥናት አቅራቢው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

በእንግሊዝ ሀገር ለረጅም ዓመታት በመታየት 60ኛ አመቱን ያከበረው “The Mousetrap” ሲሆን የአጋታ ክርስቲ ድርሰት ነው። ይህ ቴአትር 60 አመታት በመድረክ ሲቆይ 25ሺህ 889 መድረኮችን ያገኘ ሲሆን፤ ከ400 ያላነሱ ተዋንያንም ተፈራርቀውበታል ሲሉ ጥናት አቅራቢው ተናግረዋል። አክለውም “ባቢሎን በሳሎን” በአፍሪካ ታሪክ ረጅም ጊዜ የታየ ቴአትር ነው ያሉ ሲሆን፤ ለንፅፅርም በግብፅ የታየ አንድ ቴአትር ቆይታ ለአራት አመት ነው ያሉት አጥኚው፣ በናይጄሪያ፣ በኬኒያና በታንዛኒያ ከአንድ ዓመት እስከ ቀናት ብቻ የሚቆዩ ቴአትሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በአገራችንም ሆነ በአፍሪካ ተከታታይ የሬዲዮ ድራማ ታሪክ ግንባር ቀደም ነው የተባለለት በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በኦሮምኛ ቋንቋ ላለፉት 18 ዓመታት በመደመጥ ላይ የሚገኘው “አባ -ጃንቦ” ነው።ድራማው የኦሮሞ ህዝብን ባህል፣ ታሪክና ትውፊት በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል ያለችው ጥናት አቅራቢዋ ጋዜጠኛና ደራሲ ዝናሽ አላኒ፤ ድራማው ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ በህዝብ ዘንድ ተወዳጅ እንደሆነ በመደመጥ ላይ ነው ብላለች።

“አባ ጃንቦ” የኮሜዲ ዘውግ ያለው የሬዲዮ ተከታታይ ድራማ ይሁን እንጂ፤ በርካታ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችንም ይዳስሳል ተብሏል። ድራማው ተወዳጅና ተደማጭ ያደረገው ወቅታዊነቱ ነው የምትለው ጥናት አቅራቢዋ፤ ሰሞነኛ ጉዳዮችን በአዝናኝና አስተማሪ መልኩ ያቀርባል ስትል አፅንኦት ሰጥታበታለች።

ድራማው የሬዲዮ ድራማ ገፀ-ባህሪያት አሳሳልን በሚገባ አሟልቶ የተሰራ መሆኑን የጠቆመችው ዝናሽ፤ በርካታ ጠንካራ ጎኖች እንዳሉትም አንስታለች። በቅርቡም በቲቪ የመስራት ዕቅድ መኖሩ የተገለፀ ሲሆን፤ በታዳሚው ለምን በተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉሞ አይቀርብም በሚል ለተነሳው ጥያቄ የተሰጠው መልስ ብዙዎችን የሚያስደንቅ ነበር።

“አባ ጃንቦ” ተከታታይ የሬዲዮ ድራማ ላለፉት 18 ዓመታት ሲደመጥ ደራሲውና መሪ ተዋናዩ ሰብስቤ አበበን ጨምሮ ባለሙያዎቹ ሁሉ ምንም አይነት ክፍያ አለማግኘታቸው በአዳራሹ የታደመውን ሰው ሁሉ አስደንግጧል። ጥናት አቅራቢዋ ዝናሽም ለማጠቃለያዋ፣ “አባ ጃንቦ” ከድራማነቱማ ባሻገር ቅርሳችን ነው” ስትል የድራማውን አቅም አጉልታ አሳይታለች።

በምሽቱ የክብር እንግዳ በመሆን ሸልማቶቹን ለባለሙያዎቹ ያበረከቱት ተ/ፕሮፌሰር አቦነ አሻግሬ፣ አርቲስት ፋንቱ ማንዶዬ፣ አርቲስት ዲማ አበራና አርቲስት ተክሌ ደስታ ናቸው። በልዩ ተሸላሚነትም በሁሉም መድረኮች “ባቢሎን በሳሎን” ቴአትር ላይ በመተወን አቻ ያልተገኘላት ሉሌ አሻጋሪ ተሸላሚ ሆናለች። የቴአትሩ ደራሲ ውድነህ ክፍሌ እና አዘጋጁ ተስፋዬ ገ/ሃናም እንዲሁ ተሸላሚዎች ሲሆኑ፤ ከ “አባጃንቦ” ተከታታይ የሬዲዮ ድራማ ደግሞ ደራሲና አዘጋጁ ሰብስቤ አበበ ተሸላሚ ሆኗል።

በምሽቱ መድረኩን አግኝተው ንግግር ያደረጉት የድራማውና የቴአትሩ ደራሲያን ተመሳሳይ ስሜቶችንና መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ ሰምተናል። ደራሲ ውድነህ ክፍሌ ብሔራዊ ቴአትር ያልሰጠኝን ዕውቅናና ሽልማት የዚህ ፕሮግራም አዘጋጆች ስለሰጡኝ ከልቤ አመሰግናለሁ ያለ ሲሆን፤ የአባጀንቦ ድራማ ጸሐፊና አዘጋጁ ጋዜጠኛ ሰብስቤ አበበ በበኩሉ፤ ይህን የምስጋናና የዕውቅና ሽልማት መስጠት የነበረበት ሬዲዮ ጣቢያው እንደነበር በትዝብት ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ቴአትር ባለሙያዎች ማህበር ይህን መሰል የምስጋናና የዕውቅና ሽልማት በቀጣይም አመታዊ አድርጎ ለመስራት ማቀዱን የሰማን ሲሆን፤ ኪነ-ጥበቡን መደገፍ የሚፈልጉ ተቋማትም ሆኑ ግለሰቦች ከጎናቸው እንዲሆኑ ጠይቀዋል።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
16359 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 820 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us