የሶስት ታሪኮች ግማድ “ያየ አለ?”

Wednesday, 24 August 2016 14:03

 

የፊልሙ ርዕስ -  “ያየ አለ?”

ዳይሬክተሮች - ማቲያስ ባዩና ታዲዮስ አስረስ

ደራሲ - ማቲያስ ባዩ

ፕሮዳክሽን - የህዝብ አለም ፊልም ፕሮዳክሽን

ሲኒማቶግራፊ - አዲስ ጋዲሳና ታዲስ አስረስ

ኤዲተር - አዲስ ረገሳ

ተዋንያን - ሚካኤል ታምሩ፣ መለስ ወልዱ፣ ህይወት አራጌ፣ ትዕግስት ጥላሁን፣ ሙሉዓለም ጌታቸው፣ ማቲያስ ባዩ፣ ዮናስ አሰፋ እና ሌሎችም

“ያየ አለ?” ፊልም የበቀል ጥማትን፣ የወላጅ ስስትንና የፍቅር ጥምረትን፣ የታሪኩና ማንነት ምስጢርን ድንገቴ በማይመስሉ የሴራ ጥልፍልፎሽ የሚተርክ ፊልም ነው። ፊልሙ የኮሜዲ ድራማ ዘውግ ይኑረው እንጂ በየግላቸው ሊተርኩ የሚችሉ ሶስት ታሪኮችን በአንድ ላይ ገምዶ በማቅረቡ የተመልካችን ቀልብ መሳብ ችሏል። ፊልሙ በፒክሰል ስቱዲዮ ተዘጋጅቶ በየህዝብ አለም ፊልም ፕሮዳክሽን የቀረበ ሲሆን፤ ባሳለፍነው ወር ተመርቆ ለዕይታ ቀርቧል።

በፊልሙ ውስጥ የፊልም ችሎታቸውን ለህዝብ ለማድረስ የገንዘብ አቅም ያነሳቸውን ወጣቶች ጭንቀት እያየን ሳለ፤ ገንዘብ የማግኛ ዘዴ ይከሰታል። የስምንት ዓመት ህፃን ልጅ ከትምህርት ቤቷ ተሰርቃ መጥፋቷን በቲቪ ሲነገር ይሰማሉ። የህጻኗ ወላጆች ሞልቶ የተረፋቸው ሃብታሞች ስለሆኑም ልጃቸውን ላገኘላቸው ሰው 300 ሺህ ብር በወረታ መልክ ለመስጠት ተዘጋጅተዋል። ወጣቶቹ ለፊልም ስራ ማሟያ እንደሆናቸው የሚፈልጉት ብር ደግሞ 200ሺህ ብር ነበር። በአጋጣሚ  ደግሞ በህፃኗ ት/ቤት የምረቃ ፕሮግራም ላይ ከፊልም ሰሪዎቹ አንዱ የሆነው ወጣትኢዮብ (ሙሉዓለም ጌታቸው) በካሜራ ስራ ተገኝቶ ነበር። ህፃኗ ከመሰወሯ በፊትም ፍንጭ መስጠት የሚችሉ ፎቶዎችን አንስቷል። እናም ልጅቷን ከጠፋችበት ለማግኘትና የ300ሺህ ብሩን ወረታ የራሳቸው ለማድረግ የማይሆኑትን ሲሆኑ ማየት ወይጉድ እያሰኘ ያስቃል። ገፀ ባህሪያቱ በፊልም ውስጥ ሌላ ፊልም ይሰራሉ። እንደሊስትሮ፣ እንደቆራሌው፣ እንደልዋጭና እንደለማኝ ሆነው የጠፋችውን ህፃን ዱካ ይሰልላሉ።

“ያየ አለ?” ሌላም የሚያፋልገን ጉዳይ አለው። ወንድማማቾቹ ከአባታቸው የወረሱትና በታሪክም እንደሰሙት የቀዳማዊ ሃይለስላሴ የጣት ቀለበት እጃቸው ገብቷል። ታላቅ ወንድም (ሚካኤል ታምሬ) ቀለበቱን ለውጪ ዜጋ ለመሸጥ ያስማማል። ታናሽ በበኩሉ ቀለበቱ ታሪካችንና የማንነታችን ማሳያ ነውና መሸጥ የለበትም ሲል ይሞግታል። በዚህ መካከል “ቅርስን መሸጥ ሀገር እንደመሸጥ ይቆጠራል” የሚለው ታናሽ ወንድም ከወንድሙ ነጥቆ የወሰደውን ቀለበት ህፃኗን የሚፈልጉት ወጣቶች እጅ ሳይታሰብ ይገባል። እናም አሳዳጆቹ (ህጻኗን ፈላጊዎቹ) በራሳቸው ሳያውቁት ተሳዳጆች ሲሆኑ እንመለከታለን።

በሌላም በኩል ከዓመታት በፊት የቤት ሠራተኛውን የደፈረው አባወራ፤ አሁን ላይ ልጁ የተሰረቀችበት አባት (መለስ ወልዱ) “የወጋ ቢረሳም የተወጋ አይረሳም” ይሉት ተረት ገጥሞት ቤተሰቡ ሲታመስ እናያለን። ያኔ የደፈራት ሴት እልፍነሽ (ህይወት አራጌ) ከዓመታት በኋላ ቂም ቋጥራ ለበቀል ስታሳድደው ፊልሙ ያሳያል።

በ“ያየ አለ?” ፊልም ውስጥ አንዱ የበቀሉን ጥም ለማርካት በዳዩን “ያየ አለ?” እያለ ይፈልጋል፤ ። ሌላውም ህልሙን ያሳካ ዘንድ “ያየ አለ?” እያለ፤ ገንዘብ ይፈልጋል፤  አንዱም ገንዘብ ፍለጋ ታሪክና ቅርስን ለመሸጥ ይውተረተራል። ልጁ የጠፋበት ወላጅም ወረታውን አስቀምጦ ልጄን “ያየ አለ?” ሲል ይማጸናል።

ከቋንቋ አጠቃቀሙ አንጻር ገፀ- ባህሪያቱን የሚመጥንና ቀልድ የሚያጭሩ ቃላትን ይጠቀማል። በተለይም ገፀ-ባህሪያቱ ራሳቸውን ሲለወጡና ያለማንነታቸው ያልሆኑትን ለመምሰል በሚያደረጉት ጥረት መካከል የእነርሱ ያልሆነን አነጋጋሪ መሞከራቸው ሌላው ሳቅ ፈጣሪ ነው ማለት ይቻላል።

ተዋንያኑ ስምና ዝና ያላቸው እንዲሁም ወጣቶች ቢሆኑም፤ ሚዛናቸውን ጠብቀውና ተዋህደው የሰሩት አይነት ፊልም ነውም ማለት ይቻላል። የፊልምን ዋንኛ ተግባር ነገሮችን በድርጊት ለማሳየት ዳይሬክተሩም ቢሆን መልካም የሚባል ጥረት አድርጓል።

የ“ያየ አለ?” ፊልም ትልቁ ድክመት ድንገታዊነትና ኢ-ተዓማኒ የሆኑ ከስተቶችን ደጋግሞ ማሳየቱ ነው። በጥቂቱም ቢሆን ምክንያታዊነት ይጎለዋል። አሻንጉሊት ፍለጋ አንድ ቀን መንገድ ላይ ከተዋወቀችው ቤት የተገኘችው ገፀ-ባህሪይ ምሳሌ መሆን ይችላል። በአንጻሩ ደግሞ ወጥ የባህርይ ፅናት ጉድለት የሚታይበትም ቦታ አለ። ለምሳሌ ህጻን ልጁ የጠፋችበት አባት፤ “ለልጄ ስል ማንኛውንም ነገር አደርጋለሁ” ሲል በቁጭትና በጭንቀት የሚታየው አባት መልሶ ደግሞ ገንዘብ ለማውጣት የሚያሳየውን ስስት ስንመለከት በገፀ-ባህሪይው አወቃቀር ላይ ጥያቄ እንድናነሳ እንገደዳለን። በሌላ በኩል ለበቀል የተዘጋጀችው ሴት ወ/ሮ እልፍነሽ (ህይወት አራጌ) በዚህ ደረጃ ፊላጭ -ቆራጭና ጨካኝ የሆነችው በመደፈሯ ብቻ ነው፤ ወይስ ሌላ ኃይል አላት ተብሎ በግልጽ አለመታየቱ ተመልካችን ግር የሚያሰኝ ነው።

በተረፈ ግን ፊልሙ ባነሳው ታሪክ፣ በቋንቋ አጠቃቀሙ፣ በአተዋወንና ዝግጅቱ መልካም የሚባል ነው። በኢዲቲንግ፣ በብርሃንና በድምጽ አጠቃቀሙ ላይ ያለውን ልቀት እንዳለ ሆኖ ማለቴ ነው። ከ“ያየ አለ?” ፊልም ጋር መልካም የመዝናኛ ሳምንት ይሁንላችሁ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
16220 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 947 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us