ኢትዮጵያውያኑ የፊልም ተዋንያን “የአፍሪካ ኦስካር”ን መድረክ

Wednesday, 31 August 2016 12:17

 

በ2011 (እ.ኤ.አ) ስራውን የጀመረውና “ናፋካ” በሚል ስያሜው የሚታወቀው የአፍሪካውያን አስካር ዘንድሮ ኢትዮጵያውያንን ለሽልማት አብቅቷል። በሆሊውድ እና በአፍሪካውያን የፊልም ባለሙያዎች አማካኝነት የተመሰረተው ይህ የሽልማት ድርጅት፤ በአስደናቂ ስራቸውና ችሎታቸው የሚመሰክርላቸውን የአፍሪካ የፊልም ባለሙያዎች በአለም አደባባይ ለማስተዋወቅ የሚተጋ ነው።

ዘንድሮ በህዳር 10 ቀን 2016 (እ.ኤ.አ) በአሜሪካ ካሊፎርኒያ በአሌክስ ቴአትር ኦፍ ሎሳንጀለስ በሚከናወነው ደማቅ ስነስርዓት ላይ አርቲስት ግሩም ኤርሚያስ በምርጥ ተዋናይነት የህዝብ ምርጫ አሸናፊ ሲሆን፤ አርቲስት ሩታ መንግስተአብ ደግሞ በህዝብ ምርጫ (Peoples choice Award winners) በሚለው ዘርፍ አሸናፊዎች የሚያደርጋቸውን የላቀ ድምጽ አግኝተዋል። ከሁለቱ አሸናፊ ባለሙያዎች በተጨማሪም ከሀገራችን ተወዳድረው የዕውቅና ሽልማትን ከሚያገኙ ባለሙያዎች መካከል በቅርቡ ለሲኒማ በበቃው “ሰባ ዘጠኝ” ፊልም የሚታወቀው ወጣቱ ዳይሬክተር ተካበ ታዲዮስ፤ ብስራት ጌታቸው በምርጥ ሲኒማቶግራፊ፤ ተስፋዬ ወንድማገኝ በምርጥ ቪዥዋል አርትና ሜካፕ፤ ብሩክ ታምሩ በምርጥ ፕሮዳክሽን ሲሆኑ በስብዓዊ ድጋፍ ዘርፍም መሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት የዕውቅና ተሸላሚዎች እንደሚሆኑ የኢትዮጵያውያኑን ስራ ለአወዳዳሪዎቹ በማቅረብ በትብብር የሰራው በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው የቆንጆ ፕሮሞሽን ባለቤትና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ማርቆስ ሁሉቃ ተናግረዋል።

የተገኘውን ውጤትና የአሸናፊዎቹን ሽኝት በሚመለከት ባሳለፈው አርብ ነሐሴ 20 ቀን 2008 ዓ.ም በአዜማን ሆቴል በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ውጤቱ ለበርካታ የአገራችን የፊልም ባለሙያዎች ማነቃቂያ እንደሚሆን ተነግሯል። ከአስራ አምስት የአፍሪካ ሀገራት በቀረቡ ዕጩዎች መካከል በተካሄደው የህዝብ ምርጫ  (people’s Choice award winners) መሠረት አብላጫውን ድምጽ ያገኙት ተዋናይ ግሩም ኤርሚያስና ተዋናይት ሩታ መንግስተአብ የተገኘው ውጤት ሙሉ ለሙሉ የተመልካቾቻችን ነው ሲሉም ተደምጠዋል።

ውጤቱን ከ “ናፍካ” ድረ-ገፅ በየዕለቱ ይከታተሉት እንደነበር የገለፁት አሸናፊዎች ስለአሸናፊነታቸው ላቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት መልስ የሚከተለውን ነበር። “ለአፍሪካ ኦስካር መታጨቱ በራሱ ለኔ እንደአሸናፊነት የምቆጥረው ነበር” የምትለው ተዋናይት ሩታ መንግስተአብ፤ በአጠቃላይ ውጤቱ በሰፊ ድምፅ በማሸነፏ ከጎኗ ለነበሩትና ለኢትዮጵያ ህዝብ በጠቅላላ ምስጋናዋን አቅርባለች። ተዋናይ ግሩም ኤርሚያስ በበኩሉ በንግግሩ መሀል እንዲህ ይላል። “ፊልም እኛን ብቻ ሳይሆን አገራችንንም የምናስተዋውቅበት ትልቁ መሳሪያ ነው። አሜሪካዎች በሶስት ነገሮች ሃያልነታቸውን ያስመሰክራሉ። የመጀመሪያው ዋይት- ሀውስ ነው። ቀጥሎ የሚጠቀሰው የጦር ጥበብ መቀመሚያው ፔንታጎን ሲሆን፤ ሶስተኛው ደግሞ የፊልም ግዛታቸው ሆሊውድ ነው” ብሏል።

“ስኬት የሚጀምረው ሰው የተፈጠረበትን ምክንያት ሲያውቅ ነው የሚለው ግሩም፤ ለእርሱ “የአፍሪካን ኦስካር” የተሰኘውን ሽልማት በህዝብ ድምጽ አሸናፊ ሆኖ ማግኘቱ ሳይሆን ትወናን ጀምሮ በሚሰራቸው ስራዎች ውስጥ አቅሙን ማሳየት መቻሉ የስኬቴ መጀመሪያ ነው ይለዋል። በቀጣይም ከሀገር አልፈው አለምአቀፍ ፊልሞችን የመስራት አጋጣሚ እንደሚኖር የተናገሩት ተዋንያኑ፤ የአፍሪካውን ኦስካር “ናፍካ” መድረክ ተከትሎ ከበርካታ አለምአቀፍ ባለሙያዎች ጋር መገናኘት በራሱ የሚፈጥረው ዕድል ብዙ እንደሆነ ያስረዳሉ።

በዚህ ደረጃ አገራችን ኢትዮጵያ ተሳትፋና ባለሙያዎቿም ተሸላሚ ሆነው የማየት ከፍተኛ ጉጉት እንደነበረው የሚናገረው የቆንጆ ፕሮሞሽን ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ማርቆስ ሁሉቃ ውጤቱ አስደሳች እንደሆነ ይናገራል። ወደዚህ የፊልም ሽልማት በመምጣትም ከሚያስፈልገው መስፈርት መካከል ዋነኛው ሁሉም ዕጩዎች በሀገራቸው የፊልም ሽልማት ያገኙ መሆን እንደነበረባቸው ያስታውሳል። ይህም በመሆኑ ግሩም ኤርሚያስ ከስምንት ጊዜ በላይ ተሸላሚ ሲሆን፤ ሩታ መንግስተአብ ደግሞ ከሶስት ጊዜ በላይ ተሸላሚ መሆኗ ለዕጩነት እንዳስቀረባቸው ተናግሯል።

እነዚህን “የአፍሪካ ኦስካር” ተሸላሚዎች በምስጋናና በመልካም ምኞት ለመሸኘትም ጳጉሜ 3 ቀን 2008 ዓ.ም በኤዜማን ሆቴል ልዩ ዝግጅት መሰናዳቱን የቆንጆ ፕሮሞሽን እና የግሪን ኤቨንትስ የስራ ኃላፊዎች ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ዲፕሎማቶች፣ የፊልም ፕሮዲዩሰሮች፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትርና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች በርካታ አርቲስቶችና  ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በዕለቱ ይገኛሉም ተብሏል። በዚሁም ለአሸናፊዎቹ የአሜሪካ ቆይታ ወጪን ለመደገፍና ለመመሰጋገን የተሰናዳ ስለመሆኑ ወ/ት ራሄል ይፍሩ የግሪን ፕሮፌሽናል ኢርቪስ ኦቨንት ማኔጀር ተናግራለች።

ዕጩ ተሸላሚዎቹ በአሌክስ ቴአትር ኦፍ ሎስአንጀለስ መድረክ ስለሚጠብቃቸው ሽልማትና ስለሚያደርጉት ንግግር የሚሰጡት አስተያየት “በአለባበስም ሆነ በንግግራቸው ፍሬ ሀሳብ ውስጥ ኢትዮጵያዊነትን ከአፍሪካዊነት ጋር አጉልተው የማሳየት ፍላጎት አለን” ብለዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
16251 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1039 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us