የ2008 የዓመቱ በጎ ሰዎች ሲታወሱ

Wednesday, 07 September 2016 13:50

“በጎ ሰዎችን በመሸለምና ዕውቅና በመስጠት ሌሎች በጎ ሰዎችን እናፍራ” በሚል መርህ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ከፀኑ የዕውቅና መድረኮች መካከል አንዱ የሆነው “የበጎ ሰው” ሽልማት ዕድሜውን ቆጥሮ አራተኛው ላይ ደርሷል። ክብር ለሚገባቸው ምስጉን ሰዎች ዕውቅናን በመስጠትና በአደባባይ በመሸለም 4ኛ ዓመቱን የያዘው የዘንድሮው የበጎ ሰው የሽልማት ፕሮግራም በአስራ አንድ ዘርፎች ተከፋፍሎ የተካሄደ ነው።

ባሳለፍነው ቅዳሜ ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም በባታ ኮምፕሌክስ አቤል ሲኒማ አዳራሽ በተካሄደው ደማቅ ፕሮግራም ላይ በአስራ አንድ ዘርፎች የታጩና የተመሰገኑ ሰዎቸ ሁሉ ሽልማታቸውንና የምስክር ወረቀታቸውን አግኝተዋል።

በመድረኩ በስተመጨረሻ በልዩ ተሸላሚነት የቀረቡትና በድምጻዊ ጸሐዬ ዮሐንስ ለቤተሰባቸው ሽልማቱ የተበረከተላቸው የፊደል አባት የሆኑት ቀኝ አዝማች ተስፋ ገ/ስላሴ ናቸው። “እውቀት ይስፋ፤ ድንቁርና ይጥፋ፤ ይህ ነው የኢትዮጵያ ተስፋ” በሚለው የፀና ቃላቸው የሚታወቁት እኚህ ታላቅ ሰው በአርበኝነት፤ በደራሲነትና በአሳታሚነት ለሀገራችን ታላቅ ውለታ የዋሉ ጀግና እንደሆኑም በመድረኩ ተወስቷል። በዕለቱ ሽልማቱን ያበረከተው ድምጻዊ ፀሐዬ ዮሃንስ በአይረሴ ዜማው፡-

ማንበብና መጻፍ፣ ዋናው ቁምነገር

በህይወቴ ሁሉ እመኘው ነበር።

ሲል ታዳሚውን አነቃቅቷል። እነሆ እኛም የዓመቱን መጠናቀቅ አስምልክተን በመድረኩ ተሸላሚ የሆኑ ታላላቅ ኢትዮጵያውያን በጥቂቱ እናስታውሳለን።

·        በመምህርነት ዘርፍ ተሸላሚ

በዚህ ዘርፍ የቀረቡት እጩዎች መ/ር አውራሪስ ተገኝ፣ ተ/ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው እና ዶ/ር መረራ ጉዲና ሲሆኑ፤ በዳኞች ምርጫ ተሸላሚ የሆኑት መ/ር አውራሪስ ተገኝ ሆነዋል። መምህር አውራሪስ ከ18 ዓመት በላይ በመምህርነት ከማገልገላቸውም ባሻገር ባስተማሩባቸው አካባቢዎች በሚገኙ የገበሬ ልጆች የዕውቀት ወጋገን እንዲደርሳቸው በእጅጉ ለፍተዋል። “የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትን ለሁሉም ማዳረስ” በሚል መርህ በእርሳቸው በጎ ተፅዕኖ ከ15 ሺህ በላይ ህጻናትን ከመሃይምነት ነፃ አውጥተዋል። በተለያዩ ቦታዎች ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ አድርገዋል። በዚህም የፍሬ ውጤታቸው የሆኑ ተማሪዎች ከሀገር ቤት እስከ ውጪ ሀገር ድረስ በከፍተኛ ማዕረግ እንዲመረቁ አስችለዋል ተብሎላቸዋል።

·        በንግድ ስራ ፈጠራ ዘርፍ ተሸላሚ

በዚህም ዘርፍ አቶ ብዙአየሁ ታደሰ፣ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ እና አቶ ሳሙኤል ታፈሰ በእጩነት የቀረቡ ሲሆን ተሸላሚ የሆኑት፤ ከትንሽ ተነስተው ትልቅ ደረጃ በመድረስና ለወገኖቻቸው ባበረከቱት መልካም ተግባር ምስጉን ናቸው የተባሉት አቶ ሳሙኤል ታፈሰ ናቸው። በአሁኑ ሰዓት ከ6ሺህ 200 በላይ ሠራተኞችን የሚያስተናግደው የሰን ሻይን ኮንስትራክሽን የግል ማህበር ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ሲሆኑ፤ በዋናነት በኮንስትራክሽን ኢንቨስትመንት ላይ ተሰማርተዋል። አስቸጋሪ መንገዶችን በመገንባት፣ በነቀምት፣ በአክሱም፣ በደብረብርሃንና በጉራጌ ዞን ት/ቤቶችን በመገንባትና ተማሪዎችን የኪስ ገንዘብ በመስጠት ጭምር እንዲማሩ በማበረታታት ላደረጉት አስተዋጽዖ በዳኞች ምርጫ የዓመቱ በጎሰው ተብለው ተሸልመዋል።

·        በማህበራዊ ሳይንስ ጥናት ዘርፍ ተሸላሚ

ለማህበረሰባቸው ፋይዳ ያለው ጥናት አቅርበዋል ከተባሉ በርካታ የአገራችን ምሁራን መካከል ለመጨረሻው ዕጩነት የቀረቡት ፕሮፌሰር ባየ ይማም፣ ዶ/ር አንዳርጋቸው ጥሩነህ እና ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ናቸው። በዚህም ዘርፍ በአለም አቀፍ ደረጃ የግዕዝ መዛግብት ጥናት ሊቅ የሚባሉት ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌን ተሸላሚ አድርጓል። ፕሮፌሰሩ የኢትዮጵያ ጥንታዊ የብራና ጽሁፎች በማጥናት፣ የካታሎግ ስራን በመስራትና በጉዳዩ ዙሪያ የሚያጠኑ ተመራማሪዎችን በማማከር ይታወቃሉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ-ፅሑፍ ክፍለ ትምህርት በተባባሪ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ የአማርኛ ሰዋሰው፣ የአማርኛ ስነ-ፅሁፍ ፣ የግእዝ ሰዋሰው፣ የግዕዝ ሥነ-ፅሁፍ፣ የአረብኛ ሰዋሰውና የሴም ቋንቋዎችን ሰዋሰው አስተምረዋል። በአሁኑ ወቅት በአሜሪካን ሀገር ይገኛሉ።

·        በሳይንስ ዘርፍ ተሸላሚ

በሳይንስ ዘርፍ በዕጩነት የቀረቡት ልሂቃን ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ፣ ዶ/ር ወንዱ ዓለማየሁ እና ሎሬት ዶ/ር መላኩ ወረደ ናቸው። በዘርፉ በዳኞች ምርጫ ተሸላሚ የሆኑት ሎሬት ዶ/ር መላኩ ወረደ ሲሆኑ፤ በተለይም ባደረጉት ጥናትና ምርምር “አረማም” ለተሰኘው ምርት አስተጓጓይ በሽታ መፍትሄ በማግኘታቸው ይታወቃሉ። ሎሬት ዶ/ር መላኩ ወረደ በዓለም በሚገኙ 4ሺህ የስንዴ ዝርያዎችን የፕሮቲን ይዘት በማጥናት አራቱ በጣም ምርታማ የሆኑትን ለይተው፤ ሶስቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል። የዛሬውን የብዝሃ ይህወት ኢንስቲትዩትና የኢትዮጵያ ዕፅዋት ጀነቲክ ሀብት ኢትዮጵያን በጠቅላላ ዞረው በማሳሰብ ተቋሙን መስርተው አቋቁመዋል። በገበሬው ዕውቀት ቦታ በመስጠት የሚታወቁት ሎሬት ዶ/ር መላኩ ወረደ፤ ከ20 የበለቱ ጥናቶችን በዓለም አቀፍ ጆናሎና መፅሔቶች አሳትመዋል።

·        በቅርስና ባህል ዘርፍ ተሸላሚ

በዚህ ዘርፍ እጩ ሆነው የቀረቡት የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም፣ አቶ ካህሳይ ገ/እግዚያብሄር እና ኢ/ር ታደለ ብጡል ክብረት ናቸው። በዳኞች ምርጫ ተሸላሚ የሆኑት ኢ/ር ታደለ ብጡል ክብረት ሲሆኑ፤ የተለያዩ ባህላዊና ትውፊታዊ ቅርሶችን ከተለያዩ ክፍላተ ዓለማት በራሳቸው ወጪ በመግዛትና በመሰብሰብ ይታወቃሉ። የሰበሰቧቸውን ቅርሶችንም በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ልዩ ልዩ ሙዚየሞች በመለገስ ታሪካዊ አስተዋፅኦም አድርገዋል። የአክሱም ሀውልት ከሮም ወደሀገሩ እንዲመለስም ከአስመላሽ ኮሚቴው ጋር በመሆን ከ17 ዓመታት በላይ ታግለዋል። በአክሱም ሀውልት መመለስ ጋር ተያይዞ “ኢትዮጵየዊ ፅናት” የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም እና 640 ገፆች ያሉት መፅሐፍም እንዳሳተሙ ከታሪካቸው ተቀንጭቦ ተወስቷል።

·        በመንግስታዊ የሥራ ዘርፍ ተሸላሚ

በዚህ ዘርፍ የመጨረሻዎቹ እጩዎች ሆነው የተመሰረጡት ኢ/ር ዘውዴ ተክሉ፣ አቶ ስንታየሁ ዘለቀ እና ዶ/ር ተወልደብርሃን ገ/እግዚአብሔር ናቸው። በዳኞች ምርጫ ተሸላሚ ሆነው የተመረጡት ዶ/ር ተወልደብርሃን ገ/እግዚያብሔር ሲሆኑ፤ ከመምህርታቸው ባሻገር በዓለም አቀፍ መድረክ አፍሪካን ወክለው ለብዝሃ ሕይወትና በአካባቢ ጥበቃ መስክ ያበረከቱት አስተዋፅኦ ይጠቀሳል። በዘርፉም ከ30 በላይ የጥናት ፅሁፎችን በማሳተም ሀገርና ህዝብ የሚጠቅሙ ተግባራትን ፈፅመዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃም የተለያዩ የክብር ሽልማቶችን ያገኙ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ እ.ኤ.አ. በ2006 ዓ.ም በተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የአካባቢ ጥበቃ ሽልማት “የምድር ሻምፒዮን” ተብለው ተሸልመዋል።

·        በስፖርት ዘርፍ ተሸላሚ

ለአገራችን ስፖርት በጎ አስተዋፅኦ አበርክተዋል ከተባሉ በርካታ ባለውለታዎች መካከል የመጨረሻ እጩዎች ሆነው የቀረቡት አቶ ጌቱ በቀለ፣ አቶ ጋቶች ፓኖም እና ዶ/ር ይልማ በርታ ናቸው። በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውስጥ ስውር አሻራቸውን ማሳረፍ ከቻሉና ደምቀው ካልወቱ ሙያተኞች መካል የሚጠቀሱት ዶ/ር ይልማ በርታ የዘርፉ ተሸላሚ ሆነዋል። “በኮስትሬ ስኬት የተደበቁ ምርጥ አሰልጣኝ” የሚሰኙት ዶ/ር ይልማ በርታ፤ በስፖርቱ ዘርፍ ከፍተኛ የትምህርት ደረጃና ልምድ ያላቸው ከመሆናቸውም ባሻገር ጀግናው አትሌት ሃይሌ ገ/ስላሴን ጨምሮ በ5 እና በ10ሺህ የሩጫ ዘርፍ በርካታ ጀግኖችን ከአማተርነት አንስተው ለዓለም አደባባይና ለድል ያበቁ ሰው መሆናቸውን ተወስቷል።

·        በኪነጥበብ (ድርሰት) ዘርፍ ተሸላሚ

በኪነጥበብ በተለይም በድርሰቱ ዘርፍ የጎላ አሻራቸውን ካሳረፉ አቅም ያላቸው ፀሐፍት መካከል ወ/ሮ ፀሐይ መላኩ፣ አቶ አስፋው ዳምጤ እና አቶ አውግቸው ተረፈ በመጨረሻ ዕጩነት ቀርበዋል። በዚህም ዘርፍ ለበርካታ ዓመታት በብዕር ስማቸው ጭምር በመፃፍ በመተርጎምና አርታኢ በመሆን የሰሩትን ደራሲ አውግቸው ተረፈ (ህሩይ ሚናስን) ተሸላሚ አድርጓል። ደራሲ አውግቸው ተረፈ፤ አሮጌ መፅሀፍትን ከመሸጥ ጀምሮ አጫጭር ልቦለዶችን ኢ-ልቦለዶችንና የትርጉም ስራዎችን ከመጻፋቸው በተጨማሪ የህፃናት ተረቶችንና መዝገበ ቃላትን አዘጋጅተው አቅርበዋል። በህትመት ብርሃን ካገኙ ስራዎቻቸው መካከል “ወይ አዲስ አበባ”፣ “እብዱ” እና “የፕሮፌሰሩ ልጆች” የፈጠራ ስራዎቻቸው ሲሆኑ፤ ከትርጉም ስራዎቻቸው ደግሞ “ምስኪኗ ከበርቴ”፣ “ያንገቴ ጌጡ”፣ “ፅኑ ፍቅር” እና “ምስጢራዊቷ ሴት” ይገኙበታል። ከኢ-ልቦድ ስራዎቻቸው መካከል በቅርቡ በህትመት የበቃውና በባለቤቶላ የተፃፈው “የትውልድ ዕልቂት” ይገኝበታል።

·        በሚዲያና ጋዜጠኝነት ዘርፍ ተሸላሚ

በሚዲያና ጋዜጠኝነት ዘርፍ የመጨረሻዎቹ ዕጩዎች ሆነወ የቀረቡት ጋዜጠኛ መንሱር አብዱል ቀኒ፣ ጋዜጠኛ ደረጃ ሃይሌ እና ጋዜጠኛና ደራሲ አጥናፍ ሰገድ ይልማ ናቸው። በዘርፉ በርካታ ዓመታትን በመስራትና መፅሐፍትንም በማሳተም የሚታወቁት አቶ አጥናፍ ሰገድ ይልማ በዳኞች ምርጫ ተሸላሚ ሆነዋል። በኢትዮጵያ የዘመናዊ ጋዜጠኝነት ላይ ሙያውን ካስተዋወቁና ተፅዕኖ መፍጠር ከቻሉ ጥቂት ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ጋዜጠኛ አጥናፍ ሰገድ ይልማ መሆናቸውን በዕለቱ ተናግሯል። በ“ዛሬይቱ ኢትዮጵያ” በ“አዲስ ዘመን” እና በ“ድምፅ” ጋዜጦች ላይ ኮርኳሪ የሆኑ መጣጥፎችን በመጻፍና ማህበራዊ ሂስ በማቅረብ ይታወቃሉ። ልምዳቸውን ለማካፈል የማይሰስቱ፣ የወጣት ደራሲያንን ስራዎች ማረም የሚተባበሩ፣ በየመድረኩ የአንጋፋ ጋዜጠኞችንና ደራሲያንን ታሪኮች በመዘከር የሚያብራሩ፣ በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በልዩ -ልዩ ኮሚቴዎች የሚያገለግሉ አንጋፋ ደራሲና ጋዜጠኛ መሆናቸውም በመድረኩ ተገልጿል።

·        በበጎ አድራጎት ዘርፍ ተሸላሚ

በሚያስገርም መልኩ ሶስቱም የመጨረሻ ዕጩዎች ሴቶች በሆኑበት በዚህ ዘርፍ ወ/ሮ ፀሐይ ሮቺሊ፣ ወ/ሮ ዘውዲቱ መሸሻ እና ዶ/ር ቦጋለች ገብሬ ስማቸው በዕጩነት ተዘርዝሯል። በዚህም ዘርፍ በተለይ ሴቶችን በማስተማርና ማህበረሰባዊ ለውጥን በማምጣት ረገድ በርካታ ስራዎችን ለሰሩት ለዶ/ር ቦጋለች ገብሬ ሽልማቱ ተብርክቷል። ዶ/ር ቦጋለች ገብሬ፤ ሴቶችን በመለወጥ በተለይም እንደግርዛት፣ ጠለፋና፣ የሴቶች የቤት ውስጥ ጥቃትን ለመግታት እንዲረዳ ከእህታቸው ጋር በመተባበር ባቋቋሙት ኬ.ኤም.ጂ በጎ አድራጎት ተቋም በደቡብና በኦሮሚያ ክልሎች 26 ወረዳዎች ውስጥ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ። በቀጥታ ከ481 ሺህ በላይ፤ በተዘዋዋሪ ደግሞ ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን መድረስ መቻላቸው ተነግሯል። ላበረከቱት መልካም ተፅዕኖም የዓመቱ በጎ ሰው ተብለው ተሸልመዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
598 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us