ግለቱ ያልቀዘቀዘው “የብዕር ስም”

Thursday, 01 December 2016 15:14

 

በአሸናፊ ደምሴ

የቴአትሩ ርዕስ፡                 “የብዕር ስም”

ድርሰትና ዝግጅት፡          አለማየሁ ታደሰ

ቴአትሩ የሚታይበት ቦታ፡    ብሔራዊ ቴአትር

ፕሮዳክሽን፡               ጄ.አዲ. አርት ፕሮሞሽንና ቴአትር ኢንተርፕራይዝ

ተዋንያን፡                አለማየሁ ታደሰ፣ ፍቃዱ ከበደ፣ ማርታ ጌታቸው፣ ይገረም ደጀኔ (አስቴር)፣ ቅድስት ገ/ስላሴ እና አዳነች ወ/ገብርኤል።

 

የተደበቀ ማንነት፣ ያልተገራ ስብዕናና ጫፍ የረገጠ ራስ ወዳድነት በአንድ ወገን፤ በሌላ ወገን ደግሞ ብርታት፣ ፅናትና እንደአለት በቀላሉ የማይፈርስ መልካም ስብዕና በየፊናቸው የሚቧቀሱበትና በሚሳለቁበት የመድረክ ትግል ነው - ከአምስት ዓመታት ላላነሰ ጊዜ እየታየ በተመልካች ዘንድ ግለቱ ያልቀዘቀዘው “የብዕር ስም” ቴአትር።

በአዲስ አበባ ባህልና ቴአትር፣ በሀገር ፍቅር ቴአትር እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አዳራሾች ለመድረክ የበቃው “የብዕር ስም” ቴአትር ዘንድሮ አምስተኛ ዓመቱን ይዟል። ከራሳቸውም ሆነ ከባልደረቦቻቸው ጋር የማይገጥሙና የማይጣጣሙ ገፀ-ባህሪያትን የሚያስተዋውቀን ይህ ቴአትር የሳታየር ኮሜዲነት ዘውግ ያለው ነው።… ትምህርትንና ማንበብን ከኮሌጅ እንደወጣ እርግፍ አድርጐ የተወው “የተስፋ ጋዜጣ” የአስተዳደር ክፍል ኃላፊው ተፈሪ (ዓለማየሁ ታደሰ) ጋዜጣ ማንበብ የማይወድ የጋዜጠኞች ባልደረባ ሆኖ መሳሉ በራሱ የስላቁ መጀመሪያ ነው። እርሱም ቢሆን “ድሮ ባነበብኩት ቅጠሩኝ ይኸው አለሁ” ሲል ይሳለቃል። … ሲቀጥል ከስራው ይልቅ በሱሱ የከሰረው፤ የቤቱ ጣጣ መስሪያ ቤቱ ድረስ የሚከተለው አድርባዩ የጋዜጣው “ዓምድ አዘጋጅ” ነሲቡ (ፍቃዱ ከበደ) የእርሱ ያልሆነ ስራ በስሙ ስለተጠራ ብቻ የማያሳየው መመፃደቅ ከልኩ ሲያልፍ የተመልካችን የሣቅ በር ይበረግዳል።

ጋዜጣዋን ተገን አድርገው የራሳቸውን ጥቅም የሚያሳድዱት ተፈሪና ነሲቡ፤ ከራሳቸው የተጣሉና ጥቅመኞች ሆነዋል። የዝና ፍለጋ እና የሙስና መንገዳቸው ሁሉ የቢሮክራሲውን ጣጣ ፍንትው አድርጐ የሚያሳይ ነው። ከአንድ የድሮ ሆቴል ባለቤት (አቶ ሰማን) ጋር በገቡት “የእከክልኝ ልከክልህ” አካሄድ መሠረት ከዘመኑ ወደኋላ የቀረን ሆቴል በጋዜጣው ላይ “የከተማችን አነጋጋሪ ሆቴል” በሚል ርዕስ ስር ያለ ስሙ ስም ተለጥፎለት ሊወጣ የነበረው ስራ የሰዎቹን የህሊና ድህነት የሚያሳይ ነበር።

በዚህ የጋዜጠኞቹ ቢሮ ውስጥ በትጋታቸው የሚጠቀሱት ደግሞ “የዓምድ አዘጋጇ” ትርሲት (ቅድስት ገ/ስላሴ) በታታሪነቷና በቀናነቷ ምክንያት ለእርሷ የሚገባውን ዕድገት በስሙ የፃፈችለት ነሲቡ ሲያገኘው፤ “የበሬውን ዋጋ ወሰደው ፈረሱ፣ ከኋላ ተነስቶ ቀድሞ በመድረሱ” እንድንል ያስገድደናል።

መስሪያ ቤቱ ያወጣውን የክፍት ስራ ቦታ ለማግኘት ከተወዳደሩት መካከል በብቃቷም ሆነ በትምህርት ማስረጃዋ ተሽላ የተገኘችው መቅደስ (ማርታ ጌታቸው) የሴትነቷን ኬላ እንድታስደፍር ስትጠየቅ መመልከት የቢሮ ውስጥ ቢሮክራሲ ምን ያህል የተወሳሰበ እንደሆነ እንመለከትበታለን።

“የብዕር ስም” ቴአትርን በስላቅ እንድንመለከተው ከሚያደርገን ነገር መካከል፣ በቴአትሩ ውስጥ የተሳሉት ሴት ገፀ-ባህሪያት በሙሉ (የዓምድ አዘጋጇ ትርሲት፣ የተቋሙ ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ፋና እና ተወዳዳሪዋ መቅደስ) በስራቸው ታታሪዎች፤ በችሎታቸው ብቁዎችና ቅኖች ቢሆኑም ያልዘሩትን የሚያጭዱት ግን ወንዶቹ መሆናቸው ነው። ምናልባትም ከዋና አዘጋጁ ከሞገስ (ይገረም ደጀኔ) በቀር ማለት ይቻላል። በትርሲት የተፃፈው እና በነሲቡ ስም የወጣው ጽሁፍ ተወዳጅ ሲሆን፤ አድናቆትና ወቀሳው ቦታውን ይስታል። ለጋዜጣዋ በብዕር ስም የምትፅፈው ሴት በበኩሏ ስሟ በእጅጉ የሚታወቅና የምትደነቅ ቢሆንም፤ በሴትነቷ ምክንያት የሚገባትን ቦታ ባለማግኘቷ ትግልና ፈተናውን በሣቅ ታጅበን እንድንመለከት እንገደዳለን።

በጄ. አዲ. አርት ፕሮሞሽን እና ቴአትር ኢንተርፕራይዝ አማካኝነት ከአምስት ዓመታት በፊት ለመድረክ የበቃው “የብዕር ስም” በታሪኩ፣ በቃለ ተውኔቱ፣ በትወናውና በዝግጅቱ መዋደድ ምክንያት አሁንም ድረስ ሳይቀዘቅዝ ከተመልካቹ ስሜት ጋር ስለመጓዝ የቴአትሩ ፕሮዲዩሰርና ተዋናይት አዳነች ወ/ገብርኤል ትናገራለች። “ቴአትሩ ሊያስተላልፍ የፈለገውን መልዕክት በሚያዝናና መልኩ ማቅረብ መቻላችን በተመልካች ዘንድ እንዲወደድ አድርጐታል” ባይ ነች። “የመጣንበት ዘመን በማኅበረሰባችን ውስጥ ሴትን ወደታች ያወረደ ነው” የምትለው አርቲስት አዳነች፤ ይህንንም በግልፅ አሳይቶ ሴቶች በብቃታቸው ማሸነፍ እንደሚችሉ ቀለል ባለ መንገድ ቴአትሩ ማሳየት ችሏል ስትል ትናገራለች።

በዘመናችን ለዕይታ የሚበቁ ቴአትሮች ከሳምንታት ብሎም ከወራት የዘለለ ዕድሜ ሳይኖራቸው መቅረቱ እንደ ክፉ ዕድል የሚጠቀስ ሆኖ “የብዕር ስም” የሄደበትን መንገድ ተከትለው ብዙ የሚቆዩ ቴአትሮችን እንዴት ማግኘት ይቻላል? በሚል ላነሳነው ጥያቄ፤ አርቲስት አዳነች የሚከተለውን ሀሳብ ትሰጣለች፣ “የመጀመሪያው ነገር የፕሮሞሽን ጉዳይ ነው። ተመልካች ቴአትሩን አይቶትና ወዶት ከአዳራሽ ሲወጣ ለሌሎች ወዳጆቹም ይናገራል/ይጋብዛል። በሌላ በኩል ደግሞ ቴአትርን ለማስተዋወቅ የ30 ሰከንድ ማስታወቂያ እስከ ዘጠኝ ሺህ ብር እንከፍላለን። የአዳራሽ ኪራይ አለ። ሳምንታዊ የፕሮዳክሽን ወጪው እንዳለ ነው። ይሄ ሁሉ ሆኖ አርቲስቱ በፍቅርና በፅናት ካልሰራ በስተቀር ክፍያው አዋጭ ሆኖ የሚሰራ ቴአትር ያለ አለመሰለኝም። ስለዚህ ተዋንያኑ መስዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጀ መሆን አለባቸው።” በተረፈ ግን የአርት ቤተሰቡ ሁሉ መተጋገዝ አለበት ስትል ትጠቁማለች።

በቴአትሩ ውስጥ ያሉት ተዋንያን (አዳነች ወ/ገብርኤል፣ ማርታ ጌታቸው እና አለማየሁ ታደሰ) ቤተሰባዊ ትስስር መመስረታቸው ለብርታታቸውና ለቴአትሩ መወደድ አስተዋፅኦ ይኖረው ይሆን ወይ? በሚል ላነሳነው ጥያቄ፣ “አይመስለኝም፤ ይሄንን ተመልካቹ ሊፈርድ ይችላል። አንድ ጐበዝ ተዋናይ የትኛውንም ስራ ቢሰጠው አሳምሮ መስራት ይችላል። እኛም ባንሆን ሌሎች ይሰሩታል። ትውና ችሎታ ነው። የትም ማንም ችሎታው ያለው ይሰራዋል” በማለት ቤተሰባዊውን ትስስር የፈጠረው/የጨመረው ነገር አለመኖሩን ታስረዳለች።

“የብዕር ስም” በሀገር ፍቅር፣ በማዘጋጃ ቤት እና በብሔራዊ ቴአትር ቆይተው የተፈራረቁ ተዋንያን ነበሩበት። ለመጥቀስ ያህልም አበበ ተምትም፣ ተሻለ ወርቁ እና ባዩሽ አለማየሁ ቴአትሩ በሀገር ፍቅር አዳራሽ ሲሰራ ይተውኑበት ነበር።

ለሁለት ሰዓት ተኩል በመድረኩ የሚቆየው “የብዕር ስም” በአራት ትዕይንቶች ተከፋፍሎ ቀርቧል። ድርሰትና ዝግጅቱ የአለማየሁ ታደሰ ነው። በመድረኩ ላይ ያሉት ዕቃዎች ሁሉ ትወናውን በሚገባ የሚያግዙ ሆነው ቀርበዋል። በተለይም ትርሲት ከፍታ የተወችውን ሚሪንዳ፤ ድንገት ተፈሪ አንስቶ ሲጠጣው የሚፈጥርበት ትንታ “የሰው ሃቅ-ሲያንቅ” የሚያሳይ መልዕክት ነበረው።

ከስራቸው ውጪ ትኩረት የሌላቸው ወ/ሮ ፋና (አዳነሽ ወ/ገብርኤል) እና የጋዜጣዋ ዋና አዘጋጅ ሞገስ (ይገረም ደጀኔ) በመስሪያ ቤቱ አላጋጭ ባልደረቦች አፍ-ሲዘለዘሉ ማየት የቴአትሩ ስላቅ አንዱ አካል ነው ማለት ይቻላል።

በመጨረሻም የተደበቀው “የብዕር ስም” ይፋ ወጥቶ፤ ሙሰኞችና አጭበርባሪዎች ተጋልጠው፤ እውነትና ዕውቀት ነፃ ሲያወጡ የምናይበት አስደሳችና ግለቱ ሳይቀዘቅዝ የሚጠናቀቅ ቴአትር ይሆናል።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
407 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us