“ሽልማቱን እጠብቀው ነበር”

Wednesday, 19 March 2014 13:47

ለምለም ደምሴ

በጉማ ፊልም አዋርድ በሜካፕ አራት ዘርፍ አሸናፊ

 

ለመጀመሪያ ጊዜ ዘንድሮ በተካሄደው “የጉማ ፊልም አዋርድ” ላይ በሜካፕ አርት ዘርፍ ባሳየችው ብቃት ተሸላሚ ሆናለች። ሽልማቱን ለየት የሚያደርገው በዘርፉ በእጩነት ከቀረቡት አምስት ፊልሞች መካከል ሁለቱ ማለትም “ሎሚሽታ” እና “የመጨረሻዋ ቀሚስ” እርሷ የሰራቻቸው መሆናቸው ነው። የዛሬዋ እንግዳችን የሜካፕ አርትና የአልባሳት ዲዛይነር ባለሙያዋ ለምለም ደምሴ ናት፤ መልካም ቆይታ

ሰንደቅ፡- ወደሜካፕ አርት ሙያ እንዴት መጣሽ በሚለው ጥያቄ ብንጀምርስ?

ለምለም፡- በመጀመሪያ አንድ የሜካፕ አርቲስት መሰረታዊ የሆነ የስዕል ችሎታ ሊኖረው ይገባል። ይህን ስልህ ግን ሰዓሊ ሁሉ ሜካፕ አርቲስት መሆን ይችላል ማለቴ አይደለም። የሜካፕ አርቲስት ስራ በተለያዩ የሰውነት አካሎች ላይ “ስፔሻል ኢፌክት” ወይም በውበት ላይ ተመስርቶ ሊሰራ ይችላል። በተረፈ ግን የሜካፕ አርት ስራ ከስዕል ስራ ማቴሪያሎቹ ይለያሉ። የራሱ የሆኑ ምርቶች፣ ቅባቶችና ቀለሞች ይኖሩታል። ያገኛቸውን ኬሚካሎችን ወይም ፓውደሮች (ዱቄት) በምን መልኩ አደባልቆ ለምን አላማ መጠቀም እንዳለበት ሊያውቅ ይገባል። ስለዚህ እኔ ወደሜካፕ አርት የመጣሁት ስዕልን መሰረት አድርጌ ነው ማለት እችላለሁ።

ሰንደቅ፡- የስዕል ችሎታሽንስ እንዴት አዳበርሽ?

ለምለም፡- ስዕል ከልጅነቴ ጀምሮ አብሮኝ ያደገ ነው። ትዝ የሚለኝ ተማሪ እያለሁ ደብተሮቼ ላይ ከመሞነጫጨር ባሻገር የእረፍት ጊዜዬን የማሳልፈው “ብላክ ቦርድ” ላይ የተለያዩ ስዕሎችን በመሳል እንደነበር ነው።

በጣም ትዝ የሚለኝ የ5ኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ ሙሉ “ብላክ ቦርድ” ላይ አንድ ስዕል ስዬ ነበር። ያኔ ተማሪዎቹም አስተማሪዎቼም ነበር የተደነቁብኝ። በተረፈ ግን የስዕል ችሎታው ውስጤ አለ ብዬ ማመን የጀመርኩት 9ኛ ክፍል ከደረስኩ በኋላ ነው። አንድ የህንድ መምህር ነበረን። ፊዚክስ አስተማሪያችን ነው። በእረፍት ሰዓት በብላክ ቦርዱ ላይ ምስሉን ሳልኩት። ጭንቅላቱ ላይ ይጠመጥም ነበር። ስዕሉ መምህራችንን ቁጭ ነበር። መምህራችን ሲገባ ተመለከተው። ተማሪ አንዴ ወደስእሉ አንዴ ወደመምህራችን ያያል። ማን እንደሳለው አልታወቀም ነበር። መጨረሻ ላይ ግን እንዴት እንዳወቀ አላውቅም “ለምለም” ብሎ እኔን ጠራኝ። አንዴ ውጪ አናግሪኝ ብሎ ከክፍል ወጣሁ። በጣም ተደንቆ ነበር። ለምንድነው ትምህርት ቤት ውስጥ ለአንዳንድ ፕሮግራሞች የማትስይው አለኝ። መታየት አልፈልግም ነበር እምቢ! አልኩት። በተረፈ ግን በቤቴ ለራሴ እንደምስል የሚያውቁ የእናቴ ጓደኞች ውጪ ሀገር ደርሰው ሲመለሱ የተለያዩ የስእል ዕቃዎችን ይዘውልኝ ይመጡ እንደነበር አስታውሳለሁ። የስዕል ችሎታዬን ያዳበርኩት በቤቴ ውስጥ ነው ማለት እችላለሁ።

ሰንደቅ፡- ወደሜካፕ አርቱ የመጣሽበት አጋጣሚ ምን ይመስላል?

ለምለም፡- ከሀይስኩል ትምህርቴ በኋላ በኬኒያ “ግራፊክስ አርት ስኩል” የመማር አጋጣሚውን አግኝቼ እማር ነበር። ከትምህርቴ ውጪ ግን በሰዎች የፊት ገጽታ እና በቀለሞች ላይ ትኩረት አድርጌ በግሌ አንዳንድ ሥራዎችን እሰራ ነበር። ወደፊልሙ የአርት ሜካፕ ስራ የመጣሁት ግን በመጀመሪያ የ”ሎሚሽታ” ፊልም ዳይሬክተር ከሆነው አብርሃም ገዛኸኝ ጋር እንተዋወቅ ነበር። ያኔ እነሱ “ሚዜዎቹ” የተሰኘ ፊልም እየሰሩ ነበር። በፊልም ዙሪያ አውርተን አንድ የሙዚቃ ክሊፕ መስራት እንደምፈልግ ነገርኩት። ከዚያ አንድ የሙዚቃ ክሊፕን በአልባሳት ዲዛይኒግ እና በሜካፕ አርት አብረን ሰራን። በስራዬ በጣም ደስተኛ ነበር። ከዚያም የሎሚ ሽታን ለመስራት አስቦ አብሬው እንድሰራ ጋበዘኝ። በዚያን ጊዜ እኔ “የመጨረሻዋ ቀሚስ” የተሰኘ ፊልም ላይ እየሰራሁ ነበር። ስራዬን ወዶት ስለነበር እስከጨርስ እንደሚጠብቀኝ ነግሮኝ አብረን ሰራነው።

ሰንደቅ፡- በ“ሎሚሽታ” እና በ“የመጨረሻዋ ቀሚስ” ፊልሞች በሜካፕ አርት ዘርፍ እጩ ሆነሸ በሎሚ ሽታ ፊልም ሽልማት አግኝተሽበታል፤ ስኬቱ እንዴት መጣ?

ለምለም፡- ቅድም እንዳልኩህ አንድ ሜካፕ አርቲስት ወደስራው ከመግባቱ በፊት የፊልሙን ፅሁፍ በደንብ ማንበብ አለበት። ይህም ገፀ-ባህሪያቱን በደንብ እንዲያውቅ ይረዳዋል። በፊልም ውስጥ የተፃፈው ገፀ ባህሪ የ40 ዓመት ሰው ሆኖ የሚሰራው ተዋናይ ደግሞ የ20 ዓመት ወጣት ቢሆን። ያን ወጣት ወደ 40 ዓመቱ ሰው ማምጣት የሜካፕ ባለሙያው ስራ ነው። በሁለቱም ፊልሞች ውስጥ የሰራሁዋቸውን ገፀ ባህሪያት አንብቤና አውቄያቸው ነው የሰራሁት ማለት እችላለሁ። ለዚያም ነው ስኬታማ የሆንኩት።

ሰንደቅ፡- ምናልባት በተለይ ለሜካፕ አርት ስራ አመቺ ናቸው ብለን ልንመርጣቸው የሚያስችሉ የፊልም ፅሁፎች ይኖራሉ?

ለምለም፡- ለሜካፕ አርት ስራ ወሳኙ ነገር የፊልሙ ታሪክ ነው። ታሪኩ አሪፍ ከሆነ የኔም ስራ ሊታይ ይችላል። ለየት ያሉ የፊልም ሀሳቦች ለሜካፕ ባለሙያዎች አቅም ማሳያ ይሆናሉ። ለምሳሌ የወጪዎቹን ፊልሞች ውሰድ። ሆረርና አስፈሪ አይነት ፊልሞችን ሲሰሩ የሚጠቀሙት የሜካፕና የቪዥዋል አርት ጥበብ የተለየ ነው። የእጅና የአንገት መቆረጥ፤ የአይን መጥፋት ሁሉ በሜካፕ አርት ስራ ጎልተው የሚወጡ ናቸው። ነገር ግን የቀን ተቀን የከተማ ህይወት ብቻውን የጎላ የሜካፕ አርት ስራን ጥረት ላያሳይ ይችላል። ስለዚህ የድሮ ታሪኮች፤ የነገስታት ታሪኮች፤ መስራት ቢቻል ለሜካፕ አርት ስራ ተመራጭ ፊልሞች ናቸው። የተለዩ እና ወጣ ያሉ ታሪኮችን አሁንም ድረስ ማየትና መስራትን እናፍቃሁ።

ሰንደቅ፡- በሀገራችን ሁኔታ ለሜካፕ አርት ባለሙያዎች ተግዳሮቹ ምንድነው?

ለምለም፡- ዋናው ነገር የፊልም ፅሁፍ ነው። የተለየ አቅምህን ማሳየት የምትችልበት ታሪክ የለም ማለት ይቻላል። ምክንያቱም የውበት ስራ ከሆነ ማንኛውም የውበት ሳሎን ውስጥ ሊሰራ ይችላል። በአሁኑ ጊዜ እንደውም ሴቱ ሁሉ ራሱን የሜካፕ ዕቃ በቦርሳው ይዞ፤ ራሱን የሚያስተካክልበት ደረጃ ደርሷል። ስለዚህ የባለሙያውን የፈጠራ አቅም ማሳየት የሚችሉ የተለዩ ታሪኮች እጥረት ዋናው ፈተናችን ይመስለኛል። ለምሳሌ ወደኋላ መለስ ብለን የኢህአፓ ጊዜ ታሪክ ቢሰራ አስበው፤ የአሁኖቹን ተዋንያን የዛን ጊዜ ገፀ-ባሪይ ለማላበስ የምታሳየው ጥበብ ወሳኝ ይሆን ነበር። ለየት ያለ ፈጠራ የማይታይ ከሆነ የፊልም ኢንዱስትሪው በራሱ ብዙ ሊያድግ የሚችል አይደለም። የውጪዎቹን ስንመለከት እኮ የድሮ ታሪኮችን ሰርተው፤ የፈጠራ ታሪኮችን ሰርተው አሁን ደግሞ ከሌላ አለም የመጡ ፍጡሮችን አስመስለው መስራት ሁሉ ጀምረዋል። የዚህ አይነት ፈጠራ ነው ለሜካፕ አርት ስራ መታየት ዋናው ነው።

ሰንደቅ፡- የጉማ ፊልም ሸልማትን በማሸነፍሽ ምን ተሰማሽ?

ለምለም፡- እውነቱን ለመናገር ሽልማቱን በሜካፕ አርት ዘርፍ እጠብቀው ነበር። ምክንያቱም ጥሩ ስራ እንደሰራሁ መተማመኑ ነበረኝ። ነገር ግን በኔ ሽልማት ውስጥ ሌሎችንም አይቻለሁ። ለምሳሌ ተስፋዬ ወ/አገኝ፣ አቡ፣ ተሚማ አለች፤ ዳጊ አለ አሁን ደግሞ አንድ ታዳጊ ልጅ እየመጣ ነው። ጥሩ ጥሩ ስራዎችን የሚሰሩና የለፉ ልጆች አሉ። ይህ ዘርፍ እውቅና አግኝቶ ለሽልማት መብቃቱ በራሱ አሪፍ ጅምር ነው። ለሌሎቹም ባለሙያዎች መነቃቃትን ይፈጥራል። ሁሌ እናስብ የነበረው ፕሮዲዩሰሮች ለዘርፉ ትኩርትና ክብር ለሰጡት እንደሚገባ ነበር። በጉማ ፊልም አዋርድ ሁሉም የፊልም ሙያ እንዲታይ በማድረጋቸው ሊመሰገኑ ይገባል። ፊልም የደረሰው፣ የዳይሬክተሩና የተዋንያኑ ውጤት ብቻ አይደለም። ከኋላ ያልታዩ ብዙ ዋጋ ከፋዮች አሉበት።

ሰንደቅ፡- ሽልማቱ ምን ጨመረልሽ?

ለምለም፡- ሽልማቱ ለኔ ልዩ ነው። የበለጠ መስራት እንዳለብኝ ኃላፊነት ጨምሮብኛል። ለኔ ትልቅ ታሪክ ነው። ስራዬ የሚቀጥል ሆኖ ሳለ ገና ከመነሻዬ እንደዚህ እውቅና ሰጥቶ መሸለም የበለጠ እንድተጋ አድርጎኛል። በባለሙያ መካከል ውድድር እንዲኖርም ያደርጋል። ለየት ያለ ፈጠራ ለማምጣት እንድንተጋ ያደርገናል ብዬ አምናለሁ። ይህ ሁሉ የሽልማቱ አስተዋፅኦም ጭምር ነው። በመጀመሪያው የሽልማቱ ፕሮግራም ላይ በዘርፉ ይህን ሽልማት በማግኘቴ በጣም እድለኛ ነኝ።

ሰንደቅ፡- የተሳሳተ የሜካፕ ድብልቅ ተጠቅመሽ ስህተት የፈጠርሽበት ጊዜ ይኖራል?

ለምለም፡- የለም። በርግጥ ሙያው ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚፈልግ ነው። የማላውቀውን ማቴሪያል ስለማልጠቀም መጥፎ ነገር ገጥሞኝ አያውቅም። ነገር ግን አንዳንዴ የካራክተር ሜካፕ ስንጠቀም በተለይ ሴት ተዋንያን ፈተና ነው የሚሆኑብን። ለምን? ፊታችን ይበላሽ ይሆን ብለው ይፈራሉ። ሜካፑ ፊታቸውን ሲለውጣቸው የሚረብሻቸው ተዋንያን አጋጥመውኛል። ያደጉት ሀገሮች ላይ ማንኛውም ታዋቂ አክተር ቢሆን ለሜካፕ ባለሙያው ታዛዥ ነው። ለምን በስራው ይተማመናልና። ነገር ግን አንድ ነገር መታወቅ ያለበት ነገር የፊት ሜካፕ አርትን መሰራት ያለበት ዕውቀቱ ያለው ሰው መሆን አለበት።

ሰንደቅ፡- ለምለምን ምን ያዝናናታል?

ለምለም፡- በምፈጥራቸው ስራዎቼ አዝናናለሁ፤ በስዕል ስራ እዝናናለሁ፤ በምፅፋቸው የፈጠራ ስራዎቼ እዝናናለሁ። በተረፈ ግን መፅሀፎችን በማንበብና ድረ-ገፆችን በመጎብኘት ዘና የምል ሰው ነኝ።

ሰንደቅ፡- በቀጣይ ምን ለመስራት አስበሻል?

   ለምለም፡- የራሴን የፈጠራ ድርሰት እያዘጋጀሁ ነው። ምናልባትም በተሻለ መልኩ የሜካፕ አርት ሙያ መግለፅ የሚያስችለኝ ታሪክ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፤ እሱን እየፃፍኩ ነው። በተረፈ ግን የመጡ ፊልሞች አሉ፤ እነሱንም እየሰራሁ ነው። ወደፊትም ብዙ እሰራለሁ ብዬ አስባለሁ። በዚህ አጋጣሚ ግን የጉማ ፊልም አዋርድ አዘጋጆችንና ለዚህም እንድበቃ እድሉን ለሰጠን አብርሃም ገዛኸኝ ምስጋናን ሳላቀርብ ማለፍ አልፈልግም።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
11511 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us