“አፄ ኃይለስላሴም ጎበዝ ሰዓሊ ነበሩ”

Wednesday, 14 December 2016 13:46

 

አርቲስት ለማ ጉያ

 

ቀደምትና አንጋፋ የአፍሪካ መሪዎችን፤ ከጀግኖች ምስል፤ ከማህበራዊ መስተጋብርና ተፈጥሮ ጋር አዋህዶ ለተመልካች የሚያሳይ የስዕል አውደ ርዕይ ባሳለፍነው ሰኞ ታህሳስ 3 ቀን 2009 ዓ.ም በኦሮሞ ባህል ማዕከል ግቢ ውስጥ በሚገኘው የ “አርት ትሬኒንግ ሴንተር” በድምቀት ተከፍቷል። “የአፍሪካ ህብረት መስራች አባቶች” የተሰኘ ስያሜ የተሰጠው ይህን የስዕል አውደ-ርዕይ በክብር እንግድነት ተገኝተው የከፈቱት የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ፕሬዝዳንት ዶክተር ዲላሚኒ ዙማ ናቸው። ከእርሳቸውም በተጨማሪ የቀድሞው የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ፣ የኦሮሚያ ክልል ም/ፕሬዝዳንት አቶ በከር ሻሌ፣ በኢትዮጵያ የሩሲያ ፌዴሬሽን አምባሳደር ዋና ፀሐፊ ሚካኤል እስቲንኮቭ እና የብሔራዊ ሙዚየም ኪሮግራፈር አቶ ግርማ ቡልቲን ጨምሮ የበርካታ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በስፍራው ተገኝተዋል።

የአውደ-ርዕይው ትኩረትና ዋነኛ ማጠንጠኛ ቀደምት የአፍሪካ ህብረት መስራች መሪዎች መሆናቸውን የሚናገሩት የስዕሎቹ ባለቤት አርቲስት ለማ ጉያ፤ “አፍሪካን ከባርነት ጨለማ ነፃ ያወጡ አባቶች በመሆናቸው በታሪክ ሊታወሱ ይገባል” ይላሉ። በዚህ የስዕል አውደ-ርዕይ ላይ በቀዳሚነት የአፍሪካ ህብረት እንዲመሰረት የስምምነት ፊርማቸውን ያኖሩ የ32 አገራት መሪዎች ምስል በተወጠረ ቆዳ ላይ ተሰርቶ ለተመልካች እይታ ይፋ ሆኗል።

“በአፍሪካ ህብረት መስራች አባቶች” የስዕል አውደ-ርዕይ ላይ የሰላሳ ሁለቱን የአፍሪካ መሪዎች ምስል ጨምሮ፤ የእንግሊዛውያኑን ነገስታት የንግስት ቪክቶሪያ እና የንግስት ኤልሳቤጥ ምስል፤ የጀግናው ጄነራል ታደሰ ብሩም ምስል እንዲሁም በጉልህ ይታያል። ከስፖርቱ ዓለም ደግሞ የጀግኖቹን አትሌቶች ሻለቃ ኃይሌ ገ/ስላሴ፣ የደራርቱ ቱሉ እና ምሩጽ ይፍጠርን ምስሎች ተመልክተናል። ከዚያም ባለፈ የዕውቁን ሳይንቲስት አልበርት አንስታይን የፈጠራና የፀፀትን ስሜቱ የሚያንፀባርቅ አንድ ስራ በጉልህ ይታያል። በተጨማሪም በርካታ የተፈጥሮና የማህበራዊ ተግባራትን የሚዳስሱ የስዕል ስራዎች ጨምሮ ከ50 በላይ ስራዎች በአውደ ርዕይው ላይ ለዕይታ ቀርበዋል።

በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ (በጋምቢያ ምርጫና ውጤቱ ምክንያት የተፈጠረውን ግጭት አስምልክቶ) ዘግይተው የደረሱት የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዲላምኒ ዙማ ባሰሙት ንግግር፤ አፍሪካ በ2063 (እ.ኤ.አ) ዜጎች በየትኛውም የኪነጥበብ ዘርፍ የተሻለ እንዲሰሩ ሁኔታዎችን ምቹ እንደምታደርግ ገልጸው፤ የአርቲስቱን ስራዎች አድንቀዋል። በአፍሪካ ህብረት ስምም ለአርቲስት ለማ ጉያ ጋላሪ ማስፋፊያ የሚውል የ40 ሺህ ዶላር ድጋፍ አድርገዋል። በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱም ላይ የኢትዮጵያውያንን የብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ ጭፈራ የሚያሳይ ስዕል ተበርክቶላቸዋል።

የቀድሞው የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በበኩላቸው፤ ለአርቲስት ለማ ጉያ ስራዎች ያላቸው ክብርና አድናቆት ገልፀው፤ ከእርሳቸው በፊት ስለ አርቲስቱ የተባለው ሁሉ እንደሚገልፃቸው ለታዳሚው ተናግረዋል። ለአስራ አምስት ቀናት ለዕይታ ከፍት ሆኖ ይቆያል የተባለለት ይህ የስዕል አውደ-ርዕይ፤ ቀደምት የአፍሪካ አንድነት መስራች መሪዎችን ምስል ሲያሳይ በተለየ መልኩ የአፄ ኃይለስላሴን፣ የፕሬዝዳንት ኩዋሚ ኑኩማንና የፕሬዝዳንት ጆሞ ኬኒያታን ምስሎች በጥቁር መደብ ላይ በነጭ የደመቁ አድርጎ ያሳያል። ይህ የተለየ ትርጉም ይኖረው ይሆን ስንል የጠየቅናቸው አርቲስት ለማ ጉያ የሚከተለውን ይመልሳሉ፣ “እነዚህ መሪዎች አፍሪካን በጨለማ ዘመኗ አግኝተው ወደብርሃን ያመጧት ናቸው። በሙሉ ስዕሎቹ እንደተመለከታችሁት በጥቁርና ነጭቀለም የተሰሩ ናቸው። ይህም አፍሪካዊነትንና ዘመኑን እንድናስታውስ ይረዳናል። ከሁሉም ግን ኃይለስላሴ አፍሪካን ከባርነት ነፃ ለማውጣት፣ በተለይም የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ለማቋቋም ከጭለማ ወደብርሃን አምጥተዋል” የሚሉት አርቲስት ለማ ጉያ፣ ስለቀዳማዊ ኃይለስላሴ ተናግረው የሚጠግቡ አይመስሉም።

“ለአፍሪካ እንደኃይለስላሴ የሰራ ሰው የለም” የሚሉት አርቲስት ለማ፤ አውሮፕላን እንዲገነባ እና ስነ-ጥበብም እንዲከበር ያደረጉ መሪ ስለመሆናቸው ምሳሌ እየጠቀሱ ያስረዳሉ። “እኔንም ለዚህ ደረጃ ያበቃኝ የእርሳቸው ትምህርት ነው” የሚሉት አርቲስት ለማ፤ “ለአፍሪካ ትልቁን የነፃነት መሠረት ጥለዋል ብዬ አምናለሁ” ባይ ናቸው።

በኪነ-ጥበቡ ዘርፍ፣ በተለይም ለስዕል ስራ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የነበራቸው ትኩረትና እገዛ እንዴት ይገለፃል? ያልናቸው አርቲስት ለማ ጉያ ሲመልሱ፤ “ራሳቸው አፄ ኃይለስላሴ ጎበዝ ሰዓሊ ነበሩ። ስዕልን እንደሳቸው የሚወድ ማንም የለም” ሲሉ ህያው ምስክርነታቸውን ይናገራሉ።. . . በዘመናቸው ሃያ ሺህ ብር እና መሬት በመስጠት የስዕል ማዕከል እንዲከፍቱ አድርገዋቸው እንደነበር የሚያስታውሱት አርቲስቱ፤ ወታደራዊው ደርግ ግን ድንገት መጥቶ ወርሶት ቀረ ሲሉ በሀዘን ስሜት ተውጠው ያስረዳሉ።

“አሁን ላይ አፍሪካ የግዛት ነፃነቷን አግኝታች፤ ከዚህ በኋላ ግን የጠፈር (ህዋ) ምርምር ላይ ማተኮር እንደሚገባት በስራዎቼ አመላክቻለሁ” የሚሉት አርቲስት ለማ ጉያ፤ “ዘመኑ ከጉልበት ጦርነት ወደአእምሯዊ ጦርነት (አዳዲስ የምርምር ውጤት) የምንሸጋገርበት ነው” ይላሉ።

ከ1952 ዓ.ም ጀምሮ በስዕል ስራቸው አንቱ የተሰኙት አርቲስት ለማ ጉያ፤ በርካታ አገራዊና አለምአቀፋዊ ስራዎችን ሰርተዋል። በቢሾፍቱ (1960)፣ በብሔራዊ ቴአትር (1977)፣ በአስመራ (1958 እና 1960)፣ በአፍሪካ ሕብረት (2000) በኦሮሞ ባህል ማዕከል (2015) እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ በናይጄሪያ፣ በኬኒያ፣ በደቡብ አፍሪካና በተባበሩት መንግስታት ዋና መገኛ ኒዮርክ ስራዎቻቸውን ለእይታ አብቅተው አድናቆትን ያገኙ ባለሙያ ናቸው። በወጣትነት ዘመናቸውም “ስዕልን ያለአስተማሪ” ማስተማር የሚያስችል መፅሐፍ ለመጀመሪያ ጊዜ አሳትመው ያቀረቡ ሰው ናቸው። በአሁኑ ወቅት ቢሾፍቱ በሚገኘው የመኖሪያ ግቢያቸው ውስጥ የስዕል ስራዎቻቸውን ለተመልካች ክፍት ያደረጉ ባለሙያም ናቸው። ከትናት በስቲያ በኦሮሞ ባህል ማዕከል የተከፈተው የስዕል አውደ-ርዕይም ለቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ቀደምት የአፍሪካ አንድነት መስራቾችንና የጀግኖችን ምስል ለአሁኑ ትውልድ እያሳየ ይቆያል ተብሏል።

 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
16198 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1074 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us